የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምን ጠየቁ ?
“አጠቃላይ የሀገራችን የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች በዋና ዋና አመላካቾች በምን ደረጃ ላይ ናቸው ?
በተለይ የኑሮ ውድነት እየከፋ ነው።
የዋጋ ንረትን ደግሞ ማረጋጋት አልተቻለም።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው ማህበረሰብ እና የመንግሥት ሰራተኛው መኖር አቅቶታል።
መኖር የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው።
ስለሆነም እንደ መንግሥት በቀጣይ አመታት እነዚህን ተግዳሮቶች ለመወጣትና የህዝቡን ጥያቄ ለመፍታት በምን ደረጃ ታቅዷል።” (አቶ አቤነዘር በቀለ – የተ/ም/ቤት አባል)
” … ማንኛውም መንግስታዊ አገልግሎት የሚገኘው በገንዘብ እና በእጅ መንሻ ሆኗል ” – የም/ቤት አባል
የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምን ጠየቁ ?
አቶ አብርሃም በርታ (የተ/ም/ቤት አባል) ፦ “ብዙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት እና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ባወጡት ሪፖርት ሙስና በሀገራችን ከአመት አመት እየጨመረ መምጣቱን ያሳያሉ።
ይህን ስር የሰደደ መንግሥታዊ ሌብነት ወይም ሙስና ለመዋጋት ብሔራዊ የጸረሙስና ኮሚቴ መቋቋሙን ብንሰማም አርቂ ስራ ሲሰራም ሆነ በሙስና ምክንያት ያንዣበበውን ሀገራዊ አደጋ ለመቀልበስ እርባና ያለው ስራ ሲሰራ አልታየም።
በአጠቃላይ መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት ይሄ ነው የሚባል መፍትሄ እየሰጠ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ቁርጠኝነቱም ላይ ጥያቄ ይነሳል።
ምክንያቱም የህዝብ እና የመንግስት ሀብት በዘረፉ ሙሰኛ ባለስልጣናት ላይ መቀጣጫ የሚሆን እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ተጨማሪ ሹመት እና የቦታ ዝውውር በመስጠት መንግስት ሙሰኞችን አብሮ አቅፎ ይኖራል ማለት ይቻላል።
ከዚህ የተነሳ ፦
➡ የመንግስት መዋቅር በሌቦች ተጠልፏል።
➡ ማንኛውም መንግስታዊ አገልግሎት የሚገኘው በገንዘብ እና በእጅ መንሻ ሆኗል።
➡ ዜጎች የዕለት ኑሯቸውን ለመግፋት በአደባባይ ገንዘብ እየተጠየቁ ነው።
➡ ከፍተኛ የሀገር ሀብት ከሀገር ወጥቶ እየሸሸ ነው።
➡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት እያባከኑ ነው።
➡ በኦዲት ሪፖርት መሰረት በየመ/ቤቱ ከፍተኛ የሆነ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ይታያል።
➡ መ/ቤቶች ገንዘብ ያለማስረጃ ወጪ በማድረግ ይጠቀማሉ ፣ ምንም ማስረጃ ሳያቀርቡ በወጪ ይመዘግባሉ፣ ከፋይናንስ መመሪያና ደንብ ውጭ የገንዘብ ክፍያ ይፈጸማል።
እንደሚታወቀው ብዙ ሀገራት ለችግሩ በሰጡት ትኩረት የማያወላውል እርምጃ ስለወሰዱ ችግሩን ማቃለል ችለዋል።
ለምሳሌ በቅርቡ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ለልምድ ልውውጥ የጎበኟቸው የእስያ ሀገራት እነ ሲንጋፖር ፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ ስንመለከት ለእድገታቸው ዋናው መሰረት በሙስና ላይ ያላቸው ቁርጠኝነት ነው።
በሀገራችን የሌብነት ችግር ለመቅረፍ አፋጣኝ እና አስተማሪ የሚሆን እርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር የጸረ ሙስና ህጋችንን አሻሽለን ቢሆን በሀገራችን አሁን የምናያቸው ፈተናዎች ተደምረው ሙስና የሀገራችንን ህልውና መፈተኑ አይቀርም።
ክቡር ጠ/ሚኒስትር በህዝቡ የሚቀርበው ተደጋጋሚ ቅሬታና የጄነራል ኦዲተር መ/ቤት በማስረጃ አስደግፎ ያቀረበልን ስር የሰደደ የሙስናን ችግር ለመቅረፍ መንግስትዎ ምን ያህል ቁርጠኛ ነው ?
በተደጋጋሚ እንደታዘብነው ቃል ከመግባት ባለፈ ምን ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ ታስቧል ?
ህዝቡስ ከመንግስትዎ ምን ይጠብቅ?”
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ እና የተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ አበባው ደሳለው ፦
” የመንግስት ኃላፊዎች በተለያየ ጊዜያት በተደጋጋሚ ስለ ሀገራዊ ምክክር እና ስለ ሽግግር ፍትህ ሲያነሱ ይደመጣል።
ነገር ግን ከሀገራዊ ምክክር እና ከሽግግር ፍትህ በፊት መቅደም ያለባቸው ነገሮች አሉ። ከነዚህ ውስጥ አንደኛውና ዋነኛው የእምነት ግንባታ ነው።
መንግስት በህዝብ ዘንድ እምነት አልገነባም ብለን እናስባለን። ይሄም የሚገናኘው ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር ነው።
ባለፉት 10 ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ሰበብ በማድረግ የመንግስት ኃይሎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል።
ከነዚህ ጥሰቶች ውስጥ የጅምላ ግድያ፣ በሰብዓዊ / ባልታጠቁ ዜጎች ላይ የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል። በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች።
ጥቂቱን ለመጥቀስ በመርዓዊ ፣ በጅጋ ፣ በደብረ ኤልያስ ፣ በፍትኖተ ሰላም፣ ደብረሲና አካባቢ ፣ ጎንደር እና ወሎም እንዲሁ ተፈጽሟል።
ይህንንም የተለያዩ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተቋማት የዘገቡት የአይን እማኞችም የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው።
ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጾታዊ ጥቃት፣ ድብደባ፣ ዘረፋ ፣ ንብረት ማውደም ፣ የሲቪል ተቋማት በጤና ፣ በትምህርት ተቋማት ላይ ውድመት እንደደረሰ በርካታ ምስክሮች ገልጸዋል።
ሌላው የሰብዓዊ መብት ችግር በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ምክንያት በርካታ ፖለቲከኞች የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ታስረዋል።
ከዚህ ባለፈ ጋዜጠኞች፣ አንቂዎች፣ አጠቃላይ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በተለይ በአማራ ክልል አማራዎች በጅምላ ለወራት በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ።
የምክር ቤት አባላትን ስናነሳ የምክር ቤት አባላችን አቶ ክርስቲያን ታደለ የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆኖ መንግስትን ከምዝበራ ያዳነ በሰላማዊ ትግልም በእጅጉ የሚያምን ሰው ነው አንድ አመት ለሚሞላ ጊዜ በእስር እየማቀቀ ያለው።
ሌሎችም በለውጡ ከእርሶ ጋር አብረው የሰሩ እንደ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ፣ ዶ/ር ካሳው ተሻገርና አቶ ታዬ ደንደአ ያሉም ለውጡ ስህተት ፈጽሟል በትክክለኛው ጎዳና እየሄደ አይደለም ብለው ስለሞገቱ ብቻ ለወራት ታስረዋል።
ከዚህ የከፋው ግን የት እንኳን እንደታሰረ የማይታወቅ አንድ የአብን አባላችን ነው ሀብታሙ በላይነህ ይባላል።
ሀብታሙ በላይነህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል ነው። እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ መምህር ነው። ላለፉት 4 ወራት የት እንደገባ አይታወቅም። ይህን ጉዳይ ቤተሰቡም እኔም ለተለያየ የመንግስት ኃላፊዎች አቤት ብለናል ምላሽ አላገኘንም። ዛሬ እርሶ ምላሽ ይሰጡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ እንማጸናለን።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ልክ እንዳበቃ ህጋዊ አሰራሩ ይቀጥላል ብለን እንገምት ነበር ነገር ግን አዋጁ አብቅቶ በኮማንድ ፖስቱ እየተዳደርን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።
የጅምላ እስር አሁንም አለ፣ ህገመንግስቱ በትክክል እየሰራ አይደለም። በደረቅ ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ብቻ መጠየቅ ሲገባቸው አሁንም በፖለቲካ አመለካከታቸው ዜጎች በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ።
ስለዚህ ህብረተሰቡ ስለ ሽግግር ፍትህና ስለ ሀገራዊ ምክክር መንግስት ሲያወራ ይመነው ? እምነት አልገነባንም።
በጅምላ የታሰሩ፣ የህሊና እስረኞች ቢፈቱ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መርምረው አጥፊዎች ተጠያቂ እዲሆኑ ቢደረግ ያኔ እምነት መገንባት ይቻላል።
መንግስት ምን እቅድ አለው እምነት ለመገንባት? የህሊና እስረኞችን ለመፍታት እና የጅምላ ግድያና ሌሎች ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማቆም ምን ወስኗል?”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኑሮ ውድነትን በተመለከተ ለተጠየቀው ጥያቄ ምን መለሱ?
” የኑሮ ውድነት የበርካታ ሀገራት ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በአንዳንድ ሀገራት ከ60 በመቶ በላይ የደረሰ የዋጋ ንረት እየተመዘገበ ነው፡፡
በኢትዮጵያም የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ መንግስት በርካታ ኢንሸቲቮችን ቀርጾ እየሰራ ነው፡፡
በተለይ የሌማት ትሩፋት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ይገኛል፡፡
ምርታማነትን ማሻሻልም ሌላኛው ስራ ነው፡፡
በዘንድሮው ዓመት ከዓለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ ያለው ምርት መሰብሰብ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም መንግስት 10 ቢሊዮን ብር ገቢ በመተው መሰረታዊ ሸቀጦችን ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ አድርጓል፡፡
ይህ ሁሉ የሚከናወነው የኑሮ ውድነቱ ዜጎቻችን ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለማቃለል ነው፡፡ በዚህም የዋጋ ንረቱን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 23 በመቶ ዝቀ ማድረግ ተችሏል፡፡ “
ስለ ኑሮ ውድነት …
” ልማትን የሚያፋጥን መንግስት እዛው ላይ እያለ የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር በጣም ፈታኝ ነው” – ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ስለ ኑሮ ውድነት ምን አሉ ?
” የኑሮ ውድነት ከምስራቅ እስከ ምዕራብ የሁሉ ዓለም ዋነኛ አጀንዳ ነው።
የኑሮ ውድነት የበርካታ ሀገራት ስብራት፣ ጭንቀት ፣ ውጥረት እንደሆነ መገንዘብ ይገባል። የተለየ ለኢትዮጵያ ብቻ የሆነ ችግር አይደለም።
በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሰሩ የፋይንናንስ ባለሞያዎችን ለማነጋገር ሞክረናል።
ችግሩን ምን ብናደርግ ነው የምንፈታው ? ብለን።
ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ልማትን የሚያፋጥን መንግስት እዛው ላይ እያለ የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር በጣም ፈታኝ ነው።
የኮሪደር ልማት ፣ ህዳሴ ግድብ ምናምን እያልን እዛው ላይ እያለ ኑሮ ውድነትን መቆጣጠር ያስቸግራል፤ ምክንያቱም በርከታ ሀብት ስለሚፈስ።
ኢንፍሌሽንን ለመቀነስ አንዱ መንገድ እየተፋጠነ ያለውን ልማት መግታት ነው ልማቱን ብንገታው በሌላ መንገድ ከኑሮ ውድነት ያላነሰ የስራ አጥነት ችግር ስላለ አንደኛውን ብንፈታው አንደኛው ቁስል መልሶ ጠልፎ ስለሚይዘን ይሄን ባላንስ አድርጎ ልማትም ሳናስቆም ስራ አጥነትንም ለመቀነስ እየሞከርን ኢንፍሌሽን መቀነስ ቀላል ጉዞ አልነበረም።
የብዙ አማካሪዎች ፣ የሞያተኞችም ምክር የነበረው ያለው መፍትሄ አንድ ብቻ ነው በፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ነው።
ይህን ለማድረግ ደግሞ ምርታማነትን ማሳደግ ነው። “
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ታሳሪዎች ምን አሉ?
“4 ኪሎ ተቀምጦ ‘ ጉዞ ወደ 4 ኪሎ’ ከሚሉ 4 ኪሎ ተቀምጠው ጉዞ ወደ ፓርላማ እያሉ በሰላም ቢታገሉ ችግር የለብኝም ” – ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ፦
” እስረኛ መፍታት ላይ እኛ እንታማለን ? ‘ እንዴት እስረኛ ትፈታለህ ? ‘ ተብለን ስንገመገም እና ስንወቀስ እንዳልነበረ።
ያልፈታነው ጉድ አለ እንዴ ? እስር ቤቱን በሩን ከፍተን ነው የለቀቅነው። በዚህ እንኳን አንታማም።
ከዚህ ፓርላማ የታሰሩት ወንድማችንን በተመለከተ (አቶ ክርስቲያንን ማለታቸው ነው) ሁሉም ተቃዋሚ የሚታሰር ከሆነ ጠያቂዬ (አቶ አበባውን ማለታቸው ነው) ለምን አልታሰሩም ?
ጠያቂዬ ተቀምጠው እየጠየቁ ነው እዚህ።
እርሶን የሚያስቀምጥ እሳቸውን የሚያሳስር ነገር ካለ ልዩነት አለ ማለት ነው። ልዩነቱን ግን እኔ ዳኛ አይደለሁም። ወንጀለኛ ናቸው ፣ ጥፋተኛ ናቸው ልል አልችልም። የፍትሕ ስርዓቱ አይቶ መርምሮ ፈትሾ ፍርድ ይስጥ።
የግል ምኞትህ ያሉኝ እንደሆነ እርሶም እርሳቸውም ከእርሶ ጎን ተቀምጠው ባያቸው ደስታውንም አልችለውም።
በሰላማዊ መንገድ 4 ኪሎ ተቀምጦ ‘ ጉዞ ወደ 4 ኪሎ’ ከሚሉ 4 ኪሎ ተቀምጠው ጉዞ ወደ ፓርላማ እያሉ በሰላም ቢታገሉ ችግር የለብኝም።
የግል ጥላቻ የለኝም። የግል መግፋትም የለብኝም።
ህግ ከፈታቸውና ከኛ መካከል ቢሆኑ ደስታውን አልችለውም። ነገር ግን ሁላችንም ማወቅ ያለብን ፦
– የፓርላማ አባል መሆን
– ጋዜጠኛ መሆን
– ሚኒስትር መሆን
– ማዕከላዊ ኮሚቴ መሆን ከወንጀል እና ከጥፋት አይታደገንም። አለማጥፋት ነው።
የኔ ዋስትና አለማጥፋት ነው። ካጠፋው እመጣለሁ ያለመከሰስ መብቴ ይነሳል እጠየቃለሁ።
እዚህ አካባቢ ላይ መቀመጥ ለማንኛውም ጥፋት ዋስትና አድርገው ፤ ዝም ብሎ መንገደኛ ይነሳና ዩትዩብ ከፍቶ ጋዜጠኛ ነኝ የሚለው እንደዛ ትክክል አይደለም።
ጋዜጠኛም ህግ አለው ፣ ወታደርም ቢሆን ህግ አለው መጠየቅ አለበት ፣ ሚኒስትርም ህግ አለው።
በዚህ አግባብ ማየት ካልቻልን ስራችንን ቆርጠን ጥለነው በኋላ የማንጠግነው ነገር ይፈጠራል። “
” የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና ወታደር ዜጎችን በጅምላ አይገድልም “ – ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ሀገር መከላከያ ሰራዊት በሺዎች የሚቆጠሩ አባላቱን በወታደራዊ ፍርድ ቤት ስርዓት እስር ቤት እንደሚገቡ ማድረጉን ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።
ዶ/ር ዐቢይ ፤ መከላከያ ከ ‘Code of conduct’ ውጭ በማይገባ መንገድ ኦፕሬሽን ሰርታችኋል በሚል በሺዎች የሚቆጠሩ አባላቱን እስር ቤት እንዳስገባ አሳውቀዋል።
የጅምላ ግድያን በተመለከተ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ ” የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና ወታደር ዜጎችን በጅምላ አይገድልም ” ሲሉ ተናግረዋል።
“በጅምላ ለማሸነፍ ይነሳና ሲሞት ነው በጅምላ ሞትኩኝ የሚለው እንጂ መንግሥት አይገድልም ” ሲሉ ገልጸዋል።
“ማንኛውም ስህተት በፈተጠረበት ደግሞ ኃላፊነት ወስደን እናርማለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንዴት አድርገን ህዝባችንን እንገድላለን ? ማነው እራሱን የሚገድለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ማለት ሁሉም ነው” ብለዋል።
ያም ቢሆን ግን ለተፈጠሩ ስህተቶች፣ በየቦታው ለሚያጋጥሙ ስህተቶች ግለሰብም ቢሆን ችግር ከፈጠረ ይጠየቃል ሲሉ ተናግረዋል።
መከላከያ ሰራዊቱ ስርዓት ያለው ቢሆንም በግለሰብ ደረጃ ችግር የፈጠረ ይጠየቃታል ሲሉ አክለዋል።
“መፈንቅለ መንግስት በጭራሽ አይሳካም ” – ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፥ በቅርቡ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ውይይቶች ሲደረጉ እንደነበር ተናገሩ።
ውይይት ሲያደርጉ የነበሩትም ‘ አባቶች ‘ ያሏቸውና በስም ያልጠሯቸው ግለሰቦች ናቸው።
” እኛ ወታደሮች ነን ተቋም የገነባነውም መፈንቅለ መንግስት እንዳይሳካ አድርገን ነው ” ያሉት ጠ/ሚስትሩ ፤ ” ኢትዮጵያ ውስጥ በጭራሽ አይሳካም በኃላ ዋጋ ትከፍሉበታላች ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ምን አሉ ?
“ለአባቶቼ ፤ ለታላላቅ ወንድሞቼ ምክር ቢጤ ልለግሳቸው።
በቅርቡ አንዳንድ ቦታ ላይ ‘ መፈንቅለ መንግስት እናካሂዳለን ‘ ብለው አንዳንድ አባቶቻችን ውይይት ያደርጋሉ።
መፈንቅለ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ አይሳካም። እኛ ወታደሮች ነን መፈንቅለ መንግስት እንዳይሳካ አድርገን ነው ተቋማት የሰራነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግስት አንዴ ተሳካ የዛሬ 50 ዓመት ከ50 ዓመት በኃላ ብዙ የሚረቡ እና የማይረቡ ሙከራዎች ነበሩ አልተሳኩም።
አሁን ጭራሽ አይሳካም። ጭራሽ።
ለወንድሞቼና ታላላቆቼ ምክር መስጠት የምፈልገው ጊዜ አታባክኑ ፣ የወዳጆቻችንን ሀገር ገንዘብም አታባክኑ፣ ገስት ሀውስም አታጣቡ አይሳካም !
በግጭት ፣ በጦርነት ፣ በሽፍታነት ፣ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ኢትዮጵያ ውስጥ መያዝ ማለት ብሎን እንደ ተበላበት ጥርስ ማለት ነው ፤ የሚሽከረከር እንጂ የማይሻገር።
በተደጋጋሚ እንዲህ አይነት ምክር ስንለግስ ቀለል አድርገው የሄዱ ሰዎች በኋላ ዋጋ ይከፍላሉ። “
” እኛ ለንግግር ዝግጁ ነን ! ” – ጠቅላይ ሚኒስትሩ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባሉ አቶ አበባው ደሳለው በተለይ አማራ ክልል የተለያዩ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መኖራቸውን በዝርዝር በመግለጽ ‘ ከምክክር እና ሽግግር ፍትሕ በፊት እምነት መገንባት ይቀድማል፤ መንግስት እምነት አልገነባም’ በማለት ላነሱት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተውበታል።
ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፥ “ህዝቡን ከእናተ በላይ እኛ እናውቀዋለን። ከእናተ በላይ እኛ እንመራዋለን። ከእናተ በላይ እኛ እናወያየዋለን” ሲሉ መልሰዋል።
” እኛ እንደ ድሮ መንግስታት የተደበቅን ሳይሆን ህዝቡ ውስጥ የምንውል ነን ” ብለው ” ህዝቡን እናውቀዋለን ” ሲሉ ተናግረዋል።
” ስለ ህዝብ ለኛ መንገር ሳይሆን ‘ እኛ አናምናችሁም ‘ ቢባል እኛ እና እናተ (አቶ አበባውን ማለታቸው ነው) እንደ ፓርቲ ለመተማመን ልንነጋገር እንችላለን ” ሲሉ ገልጸዋል።
” የአማራ ህዝብ ወይም የኦሮሞ ህዝብ መንገድ የሚሰራለትን ሰው ሳያምን በመንገድ ላይ ድንጋይ እየደረደረ የሚዘጋበትን ሰው እንዴት ያምናል ? ትምህርት ቤት የሚገነባለትን ሰው ሳያምን ልጆቹ ትህርት ቤት እንዳይሄዱ የሚከለክልበትን ሰው እንዴት ያምናል ? ምን ያክል ህዝቡን ብንንቀው ነው ? ” ሲሉ ጠይቀዋል።
” ግብርና ይሳለጥ፣ የበጋ ስንዴ ይብዛ ልመና ይቁም ብሎ የሚተጋውን ጠርጥሮ እንዴት ማዳበሪያ እንዳይንቀሳቀስ የሚያደናቅፈውን አርሶ አደሩ ሊያምን ይችላል ? ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ” እንደዚህ አንታለል። ህዝቡ ሰላም ይፈልጋል። ለውጥ ይፈልጋል። እድገት ይፈልጋል ” ብለዋል።
” ነገር ግን ጫካ የገቡትም ቢሆኑ ልጆቹ ስለሆኑ እንደውጭ ወራሪ ጠላት ‘ በቃ ጫርሷቸው ‘ ብሎ አሳልፎ አይሰጥም። የልጅ ነገር ነው። ይሄን መቀበል ያስፈልጋል ” ሲሉ ተናግረዋል።
” ኢትዮጵያውያን ከማንም ሀገር ጋር ብንዋጋ ፈተናው እንዳሁኑ አይደለም። እርስ በእርስ ትላንትም መከራ ነው ነገም መከራ ነው ” ሲሉ አክለዋል።
” አባት ልጁን ጠላ ማለት እንዲገደል ልጁን ይሰጣል ማለት አይደለም። ህዝቡ ተነጋገሩ የሚለን ለዛ ነው። እኛም ለንግግር ዝግጁ ነን ! ” ብለዋል።
” እምነትን ለመፍጠር ተገናኝቶ መነጋገር ነው ” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ ” በደብዳቤ አንተማመን ፤ በሚዲያ ፕሮፖጋንዳ አንተማመን ተገናኝቶ አላምንህም አምንሃለሁ እንዴት ? ዋሽተሃል ተሳስተሃል ብለን ተነጋግረን ጥፋት ካለም ደግሞ ይቅር ተባብለን ነው መተማመን የሚፈጠረው ” ብለዋል።
” እንነጋገር ያለው እኮ መነጋገርን ሲለምኑ ኖረው አሁን ተነጋገሩ ስንል መነጋገር አያስፈልግም ” ይላሉ ሲሉ ወቅሰዋል።
” በንግግርና ውይይት በምርጫ የተመረጠ መንግስት ብዙ የሚያገኘው ነገር የለም ፤ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠናል ሁለት ዓመት አለም ማንም አይነካብንም። ንግግርና ውይይት እድል የሚሰጠው በምርጫ ላላሸነፉና ሃሳቦች አሉን ህዝብ ሃሳባችንን ቢያደምጥ አውድ ቢፈጠር ሃሳባችን ሊገዛ ይችላል የሚሉ ሰዎች ናቸው የሚጠቀሙት እምቢ ባዮችም እነሱው ናቸው ” ብለዋል።
” እኛ ደመወዝ የማንከፍለው ፤ ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት ፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ ተቋም ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለናተው መተው ነው “ – ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ” የሰብዓዊ መብት አዋጅ ፣ ተቋም፣ አሰራር ይፈተሽ ” አሉ።
ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፥ ” ሰብዓዊ መብት ደስ የሚል ቋንቋ ነው – ለሰዎች የሚደረግ መብት ! በግርድፉ ሲታይ ደስ የሚል ቋንቋ ነው ግን ይሄ ቋንቋ ከዋናው የትርጉም ግንዱ ወጥቶ የፖለቲካ መጠቀሚያ እየሆነ ነው ” ብለዋል።
ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የሚታመሱት በዚህ (ሰብዓዊ መብት) ታርጋ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
” የሰብዓዊ መብት ስለ ሰው ልጆች ማሰብ፣ ማክበር ፣ የተሻለ ቤት፣ ጥሩ መማሪያ እንዲኖራቸው ፣ እንዲበሉ ማድረግ ጭምር ነው እንጂ ስለ ምግባቸው እና ስለ ቤታቸው ሳይጨነቁ በሚዲያ በዩትዩብ መናገር መብት ሊሆን አይችልም ” ብለዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ ” የተከበረው ምክር ቤት የሰብዓዊ መብት የሚባል አዋጅ፣ ተቋም፣ አሰራር መፈተሽ ያስፈልጋል ” ብለዋል።
” እኛ ደመወዝ የማንከፍለው ፤ ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት ፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለናተው መተው ነው ” ሲሉ ተናግረዋል።
” እኔ የሰብዓዊ መብት የሚባሉ ሃሳቦችና ተቋማት በየትም ቦታ ያሉ የማያቸው ልክ እንደመርፌ ነው ፤ መርፌ የራሱን ቀዳዳ መስፋት አይችልም። የራሳቸውን ድክመት ማየት አይችሉም። ይሄ ጥሩ አይደለም ሀገር ያፈርሳል ጥቅም የለውም፤ ተቋሞቻችንን ጸዳ ማድረግ አለብን ” ብለዋል።
የሰብዓዊ መብት ተቋማት ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከሌላ ሀገራትና ፍላጎቶች ነጻ መሆን አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ያሉት ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት ነጻ ቢሆኑም ከሌሎች ኃይሎች ነጻ አይደሉም ብለዋል።
ይህ ማለት ግን በሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የለም ማለት እንዳለሆነና ስህተቶችን መገምገም ኃላፊነትም መውሰድ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ መከላከያ እና ፌዴራል ፖሊስ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
የሀገር መከላከያ በወታደራዊ ፍርድ ቤት በሺዎች የሚቆጠሩ አባላቱን ከ code of conduct ውጭ ኦፕሬሽን ሰርተዋል በሚል ምክንያት እስር ቤት እንዳስገባ ጠቁመዋል።
የአብን አባሉ አቶ አበባው ደሳለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ጥያቄ ባለፉት 10 ወራት በአስቸኳይ አዋጅ ሰበብ በአማራ ክልል ፦
– የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደፈጸሙ፤
– በበርካታ የአማራ ከተሞች ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች በጅምላ እንደተገደሉ (ለምሳሌ ፦ በመርዓዊ ፣ በጅጋ ፣ በደብረ ኤልያስ ፣ በፍትኖተ ሰላም፣ ደብረሲና አካባቢ ፣ ጎንደር እና ወሎ)
– የጅምላ እስር አማራን መሰረት አድርጎ እንደሚፈጸም
– የምክር ቤት አባላት ሳይቀር በፖለቲካዊ አመለካከታቸው እስር ቤት እየማቀቁ እንዳለ
… ይህንን ጉዳይም የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት መዘገባቸውን አንስተው ነበር።
🟠 ” የመንግስት መዋቅር በሌቦች ተጠልፏል ፤ … ከፍተኛ የሀገር ሀብትም ከሀገር እየሸሸ ነው ” – የምክር ቤት አባል
🔵 ” የኢትዮጵያ መንግሥት መንግስታዊ ሌብነት አያካሂድም። ውሸት ነው! ” – ጠቅይላይ ሚኒስትሩ
ዛሬ በተወካዮች ምክር ቤት ከተነሳው ጉዳይ አንዱ የሙስናን የሚመለከት ነው።
የኢዜማ አባል የሆኑ የምክር ቤት አባል አቶ አብርሃም በርታ ፦
° ዓለም አቀፍ ሪፖርት ሙስና በኢትዮጵያ ከዓመት ዓመት እየባሰበት እንደሄደ እንዲያሳይ፤
° የመንግስት መዋቅር በሌቦች መጠለፉን፣
° ማንኛውም መንግስታዊ አገልግሎት የሚገኘው በገንዘብ እና በእጅ መንሻ መሆኑን
° ዜጎች የዕለት ኑሯቸውን ለመግፋት በአደባባይ ገንዘብ እየተጠየቁ መሆኑን
° ከፍተኛ የሀገር ሀብት ከሀገር ወጥቶ እየሸሸ መሆኑን አንስተዋል።
ሙስና የሰሩና የሰረቁ ባለስልጣናት ሲቀጡ ሳይሆን ቦታ ዝውውር እና ተጨማሪ ሹመት ሲሰጣቸው እንደሚታይም ገልጸዋል።
ሙስናን ለመከላከል ከቃል ባለፈ በተግባር ምን እርምጃ ለመውሰድ እንደታሰበ ጠይቀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ምላሽ ምን ነበር ?
– ሙስናን ለመታገል እየተሰራ ነው። አዲሱ የንብረት ማስመልስ አዋጅም ይህንን ሊያግዝ የሚችል ነው።
– እርምጃን በተመለከተ እናተው ያለ መከሰስ መብት አንስታችኃል፣ በሺህ የሚቆጠር ሰው ታስሯል፣ በርካታ ሃብት ተመልሷል። ግን በቂ አይደለም።
– የኢትዮጵያ መንግሥት 100 ፐርሰት ከፈለጋችሁ 1 ሚሊዮን ፐርሰት እርግጠኛ ሆኜ የማወራው መንግስታዊ ሌብነት አያካሂድም። ውሸት ነው !
– የፈለገ የዓለም ተቋም የፈለገ የዓለም ሳይንቲስት መርምሮ መንግስታዊ ሌብነት 1 ብር ሊያገኝብን አይችልም። እኛ የኢትዮጵያን ሃብት አናሸሽም። ለዚህ ነው ከተማችንን የምንሰራው።
– ያገኛትን ስሙኒ ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እያፈሰስን ነው።
– መንግስታዊ ሌብነት የለም። ይሄ ማለት ግለሰቦች፣ ስራ ላይ ያሉ ኃላፊዎች አይሰርቁም ማለት አይደለም።
– እስቲ የፓርላማ አባል የተጨበጠ ነገር ያቅርብና እርምጃ ካልወሰድን ጠይቁን፤ ጥቅል ንግግር ከሆነ መንግስት ይቸገራል።
– ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሙስና የትም የአፍሪካ ሀገር ውስጥ ካለው ሙስና አይወዳደርም። በብዛት የአፍሪካ ሀገራት የአንድ ፓርላማ አባል የሚበላው ደመወዝ እንዚህ ካላችሁት 10 ፣20 ፣30 ሰዎች ሊበልጥ ይችላል። አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች የአንድ ሳምንት ደመወዛቸው የኔን የአመት ደመወዝ ሊያክል ይችላል።
– ኢትዮጵያ ውስጥ ፓርላማው፣ አፈጻሚውም ፣በየደረጃ ያለው አመራር ህይወቱን ጎድቶ፣ ተቸግሮ ነው ሀገሩን የሚያገለግለው።
– በትናንሽ ገንዘብ ህዝባችሁን እያገለገላችሁ የናተን አይነት ስራ የሚሰሩ ሰዎች በጣም የገዘፈ ነገር እየወሰዱ እኩል መንግስታዊ እንትን ከተባለ ጥሩ አይመጣም።
– ሌብነት አለ ትክክል ነው ሌብነቱን አጋኖ ማሳየት ተገቢ አይደለም።
– የኛን ኑሮ የምናውቀው እኛ ነን የትኛው ሀገር ነው የኛን ሌብነት የሚያጠናልን ? የእኛ ኑሮ እኛ እናቅዋለን የነሱን ኑሮ ያውቁታል። (@tikvahethiopia)
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2017 በጀት አመት 971.2 ቢሊዮን ብር በጀት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
ከጸደቀው ገንዘብ ውስጥ ፦
➡️ 451,307,221,052 ለመደበኛ ወጪዎች
➡️ 283,199,335,412 ለካፒታል ወጪዎች
➡️ 222,694,109,445 ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ
➡️ 14,000,000,000 ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የተመደበ ነው፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply