
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት ቡድን አባላት ሕንፃዎችን በገለልተኛ አካል እንዲተዳደር በወሰነው መሠረት፣ ሕንፃዎቹን ኮሜርሻል ኖሚኒስ ተረክቦ ሊያስተዳድር መሆኑ ተሰማ፡፡
በሰኔ 2013 ዓ.ም. አጋማሽ የሕወሓት ቡድን አባላት ንብረት የነበሩ ከ30 በላይ የንግድና የመኖሪያ ሕንፃዎች፣ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽሟል በሚል በተከናወነ የወንጀል ምርመራና የሀብት ጥናት መሠረት በገለልተኛ አካላት እንዲተዳደሩ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
እነዚህን ንብረቶች የማስተዳደር ጉዳይ አስመልክቶ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጋር ንግግር እያደረገ መሆኑን ለሪፖርተር የተናገሩት፣ የኮሜርሻል ኖሚኒስ የቢዝነስ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብረ ሕይወት ጌታሁን ናቸው፡፡
ንብረቶቹ የሕወሓት አመራሮችና ደጋፊዎች በተለያዩ መሠረተ ልማቶችና ሲቪል ተቋማት ላይ ላደረሱት ውድመትና ጉዳት ለማካካሻነት የሚውሉ በመሆናቸው፣ እንዲሁም የተጠርጣሪዎችን ንብረት የያዙ አካላት የሚፈጽሙትን ምዝበራ ለመከላከል ሲባል በተጠረጠሩበትና በተከሰሱበት ወንጀል ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ገለልተኛ አካል እንዲያስተዳድራቸው፣ ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት አቤቱታ በማቅረቡ መሆኑን መገለጹ አይዘነጋም፡፡
የሰው ኃይል በማቅረብና ንብረት በማስተዳደር ከ35 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በአብዘኛው በጥበቃና በፅዳት የሥራ ዕድል በመፍጠር የተሰማራው ኮሜርሻል ኖሚኒስ፣ እያከናወናቸው ባሉ ሥራዎችና እየገጠሙት ባሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ምክክር አድርጓል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ከ30 በላይ ቅርንጫፍ ቢሮ ያለው ተቋሙ ሕንፃዎችን ማስተዳደር ጨምሮ፣ የሰው ኃይል በማቅረብና በሌሎች በ13 የሥራ ዘርፎች ተሰማርቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
ከጥቂት ወራት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገ ጥናት ኮሜርሻል ኖሚኒስ በሥራ ላይ ላሰማራቸው ከ35 ሺሕ በላይ ሠራተኞች መንግሥት ያስቀመጠውን የ20/80 የደመወዝ ክፍያ አሠራር ተግባረዊ ባለማድረጉ ምክንያት፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ያደረገውን የማስተካከያ ዕርምጃ ለምክር ቤት እንዲያቀርብ መጠየቁ ይታወሳል፡፡
ተቋሙ አሁን ማሻሻያዎችን በማድረግ እየሄደበት ያለውን አሠራር ከሞላ ጎደል ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን በመጥቀስ፣ በሚቀጥለው ዓመት ለሠራተኞቹ የደመወዝ ማስተካከያ የማድረግ ዕቅድ እንዳለው አቶ ገብረ ሕይወት ተናግረዋል፡፡ (ሲሳይ ሳህሉ-ሪፖርተር)
(የአሸባሪው ህወሃት አባላት ቤት ፎቶዎች የተገኙት ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፌስቡክ ገጽ ነው)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply