
በጉጂ ዞን የአዶላ ሬዴ ወረዳ በሞተር ብስክሌት ሲጓጓዝ የነበረ 119 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ እጽ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አብዱልከሪም ሁሴን እንደገለጹት፤ አደንዛዥ እጹ በቁጥጥር ስር የዋለው ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም ጭለማን ተገን በማድረግ ወደ ነገሌ ከተማ ሲጓጓዝ በህብረተሰቡ ጥቆማ ተደርሶበት ነው፡፡
የሰሌዳ ቁጥር በሌለው ሞተር ብስክሌት ተጭኖ በገጠር ውስጥ ለውስጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረው አደንዛዥ እጹ አዳማ ዲባ በተባለ ገጠር ቀበሌ መቆጣጠር እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
የሞተር ብስክሌቱ አሽከርካሪ ለጊዜው ሞተሩንና አደንዛዥ እጹን ጥሎ ከአካባቢው ሸሽቶ ቢያመልጥም ለመያዝ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን አስረድተዋል።
የወረዳው ህዝብ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ላደረገው ትብብር ምስጋና ያቀረቡት ኢንስፔክተር አብዱልከሪም፤ ህገ ወጦችን ለመከላከል የህብረተሰቡ ትብብር እንዲቀጥልም አመልክተዋል።
ህገ ወጦች በዋና ዋና መንገድና በከተማ የሚያደርጉት የእንቅስቃሴ ስልት ሲነቃባቸው አሁን ደግሞ የገጠር መንገድን እንደ አማራጭ እየተጠቀሙ ነው ብለዋል አዛዡ፡፡
የወረዳው ፖሊስ ሀሰተኛ የብር ኖት፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያ እና አደንዛዥ እጽ ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ላይ እንደሚገኝም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
እንዲሁም በምዕራብ አርሲ ኤበን አርሲ ወረዳ ቡኮ ዎልዳ ቀበሌ ሦስት መኪና ጭነት ካናቢስ የተሰኘው አደንዛዥ እጽ መያዙን የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ዳኙ ዋሪቱ አስታወቁ።
አደንዛዥ እጹ ሊያዝ የቻለው በበርካታ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ በተደረገ ድንገተኛ አሰሳ እና የህብረተሰቡ ጥቆማ መሆኑ ተገልጿል።
እንዲህ አይነት ድርጊት በወረዳው ያልተለመደ እና አዲስ ነው ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው፥ ደርጊቱ የተሳተፉ አካላት ከዚህ መሰል ተግባር እንዲቆጠቡ እና ህብረተሰቡ የሚደረገው ጥቆማ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በ11 የአርሶ አደር ማሳ ውስጥ የተገኘው ከ 1 ነጥብ 5 ሄክታር ላይ የተሰበሰበ ሦስት መኪና ጭነት ነው በቁጥጥር ስር የዋለው። በሌሎች ሦስት ቀብሌዎች ውስጥ ጥርጣሬዎች እንዳሉም የኤበን አርሲ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ክብሬ ገመዲ ገልጸዋል።
እስካሁን በተደረገ ኦፕሬሽን 4 ተጠርጣሪ ግለሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፥ ሌሎች ተጠርጣሪዎችንም ለመያዝ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት ሀላፊ ዋና ሳጅን አቡ ተሺቴ ተናግረዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply