ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቀደምቶቹ አምስት ምርጫዎች ለየት ያለና ሕዝቡ በምርጫ ሒደት እምነት እንዲያገኝ የሚያስችለው እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ እንዲሁም መንግሥት በተደጋጋሚ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡ ይኼ ምርጫ በመንግሥት ትኩረት እንደተሰጠው ከሚያሳዩ ጉዳዮች አንዱ የተመደበለት በጀት መጠን ሲሆን፣ በአገሪቱ የምርጫ ታሪክ ከፍተኛ የሆነው 2.5 ቢሊዮን ብር ለምርጫ ዝግጅት በፓርላማ ፀድቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫው በአንድ ዓመት እንዲራዘም ከተደረገ በኋላ፣ ቦርዱ ለፓርላማ የ1.1 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ይኼ ከመንግሥት የቀረበለት በጀት ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የምርጫ ድጋፍ አማካይነት ደግሞ፣ በዓይነት የሚደረግ 1.8 ቢሊዮን ብር ገደማ ተመድቧል፡፡ ሆኖም ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲከወን ቀን የተቆረጠለት ምርጫ በርካታ መሰናክሎች የተጋረጡበት ሲሆን፣ በተወሰኑ ሁኔታዎች ደግሞ ውዝግቦች የታዩበት ነው፡፡ የተወሰኑት ውዝግቦች ቦርዱ የሕግና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የቆዩ ናቸው፡፡ የምርጫ ዝግጅት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ተቋማዊ ትዕግሥቱንና ጥንካሬውን የፈተሹ በርካታ ተግዳሮቶችን አስተናግዷል፡፡ ብሩክ አብዱ ከቦርዱ ተቋማዊ ዓላማና ከምርጫ ዝግጅቶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችና ተግዳሮቶች የተዳሰሱበትን ቆይታ ከብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ጋር አድርጓል፡፡ በቆይታውም ኢትዮጵያ ስላለችበት የፀጥታ ችግር፣ ቦርዱ ከመንግሥት ይደርስበታል ስለሚባለው ተፅዕኖ፣ ቦርዱ ለብልፅግና ፓርቲ ያደላል ተብሎ ስለሚቀርብበት ክስ፣ እንዲሁም ምርጫን ለማከናወን ቦርዱ ስለሚገኝበት ተቋማዊ ብቃት፣ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ተዳስሰዋል፡፡ በቃለ መጠይቁ ወቅት የሰዓት እጥረት ስለነበረ የመጨረሻዎቹ ሁለት ጥያቄዎች በኢሜል መመለሳቸውንና ተከታይ ጥያቄ ማቅረብ እንዳልተቻለ ለአንባቢያን እናስታውቃለን፡፡
ሪፖርተር፡– ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ካለፉት አምስት ምርጫዎች ለየት እንደሚል፣ ሕዝቡም በምርጫ ያለውን እምነት መልሶ የሚያገኝበት ለማድረግ እንደሚሠራ እርስዎ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎችም ይህንን ሲናገሩ ነበር፡፡ ነገር ግን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና በእናንተም የማኅበራዊ የትስስር ገጾች አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች፣ ዋነኛ ተፎካካሪ ሊሆኑ የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በእስር እያሉ፣ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች የሰዎችን ሕይወት እየቀጠፉ፣ ይህንን ግብ ማሳካት እንደማይቻልና እንዲያውም ምርጫ ማድረግ መታሰብ የለበትም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ በእናንተ ግምገማ እነዚህ የተባሉትን ጉዳዮችን ጨምሮ፣ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ለምርጫው ያስቀመጣችሁትን ግብ ለማሳካት የሚያስችል ድባብ አለ ብላችሁ ታምናላችሁ?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- ይህንን ግብ ምናልባትም የሚገዳደሩ ተግዳሮቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ የመለዋወጥ ነገር ያሳያሉ፡፡ የምርጫ ዝግጀት ማድረግ ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት የጊዜ ሰሌዳ (ካላንደር) አውጥተን ምርጫውን ልናደርግ በምንዘጋጅበት ወቅት፣ በዚህ ምርጫ ሒደት ‹‹እሳተፋለሁ››፣ ‹‹አልሳትፍም›› ብሎ የሚያመነታ ፓርቲ ብዙ አላየንም ነበር፡፡ ሌሎች ጉዳዮች ነበሩ የምንመለከታቸው፡፡ ያው የፀጥታ ጉዳይ በተወሰነ ደረጃ ያኔም ተግዳሮት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ አንድና ሁለት ፓርቲዎች በምርጫው አንሳተፍም ብለዋል፡፡ ቢሳተፉ በጣም ጥሩ ነው፣ ተሳትፎውን ምሉዕ ያደርገዋል ብለን እናስባለን፡፡ እኛም እነሱ እንዲሳተፉ ለማበረታታትና በሒደቱ ውስጥ እንድናገኛቸው ብዙ ጥረት አድርገናል፣ ግን አልተሳካም፡፡ ያ ማለት ግን አማራጮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው 47 ፓርቲዎች በተለያየ ቦታ፣ ክልል፣ የምርጫ ክልል ብዙ ዕጩዎችን አስመዝግበዋል፡፡ ዋና ዋና ተፎካካሪ የሚባሉት በሙሉ በሒደቱ ውስጥ የሉም የሚለው ድምዳሜ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ሁሉም በዚህም በዚያም፣ በግራም በቀኝም የምናውቃቸው በሒደቱ ውስጥ ቢሳተፉ እንዳልኩት የተሟላ ተሳትፎ አለን ማለት እንችላለን፡፡ ግን አሁንም ቢሆን የፓርቲዎች ተሳትፎ አለ፡፡ አሁንም ቢሆን በየቦታው ያለው መራጭ ሕዝብ አማራጭ አለው፡፡ ደግሞም ተስፋ የማደርገው አንዳንዶቹ ፓርቲዎች ብዙ ዕጩዎችን ያቀረቡ ፓርቲዎች ጭምር ለየአካባቢው፣ በክልሎችም ብናየው በፌዴራልም ደረጃ የሚያስቧቸውን ሐሳቦችና አማራጮች ገና ተናግረው አላየናቸውም፡፡ ስለዚህ ገና ከአሁኑ ምን አማራጭ አለ ዓይነት ድምዳሜ ትክክለኛ አካሄድ አይመስለኝም፡፡ እኛ የዕጩዎችን ብዛት ስንመለከት በሁሉም ክልሎች ተወዳዳሪዎች፣ ተፎካካሪዎች ቀርበዋል፣ ፓርቲዎች ቀርበዋል፣ የግል ተወዳዳሪዎች ቀርበዋል፣ ያንን ዓይቶ ሕዝቡ እዚህም እዚያም የሚፈልገውን አማራጮችን የሚመርጥበት ዕድል ኖሮታል፣ ይኖረዋልም ብለን እናምናለን፡፡
ስለዚህ እንዳልኩት ሐሳቦቹ ሲገለጹና በመገናኛ ብዙኃን ሲወጡ፣ እንዲሁም ክርክር ሲኖራቸው ሰው የሚፈልገውን ለማወቅ የተሻለ ዕድልና አማራጭ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አኳያ አሁንም ከዚህ ቀደም እንደ ቦርድ ያስቀመጥነው የተለየ፣ አሳታፊና አማራጭ ያለው ምርጫና ሕዝቡም ደግሞ የምር መምረጥ ትርጉም አለው ብሎ እንዲያምን በፊት ከነበረበት አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ የሚያደርግ ምርጫ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን እንኳን እኛ አገር ሌላም አገር በየደረጃው ነው መሻሻሎች የሚታዩት፡፡ ስለሆነም ውዥንብር አሊያም ግራ መጋባት ዓይነት ስሜት አይኖረንም፡፡ ሁሉንም እንደ ተቋም የምንፈልጋቸውን ለውጦች በዚህኛው ዙር አሳክተን እንጨርሳን የሚል እምነት የለንም፡፡ ምክንያቱም አንዳንዶቹ ነገሮች የመሳካታቸው ሁኔታ በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎችም ተዋንያን (በመንግሥትም፣ መንግሥታዊ ባልሆኑም) ላይ የሚመረኮዝ ስለሆነ፡፡ ነገር ግን ከተነሳንበት የምርጫ ማሻሻያ ከጀመርንበት (ሕግ ከመቀየር) ከዚያን ጊዜ የተረከብነውን የተቋም ታሪክ እንደ መነሻ ተወስዶ ከተለካ፣ እስካሁን በሄድንበት ብዙ ልዩነት ፈጥረናል፡፡ ምክንያቱም ተቋማዊ ግንባታ ለሒደቱና ለውጤቱ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ መጨረሻው ብቻ ታይቶ ማን አሸነፈ? ማን አላሸነፈም? የሚለው ነገር ብቻ አይደለም የምርጫን ተዓማኒነትና የምርጫን ተቀባይነት የሚጨምረው፡፡
ሪፖርተር፡– ተፎካካሪዎች ሲባሉ ከምርጫ በፊት ቀንደኛ ተፎካካሪ እነማን ሊሆኑ እንደሚችሉ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ የሚታወቅ ነው፡፡ ከምርጫ በፊት ሊፎካከሩ የሚችሉ ጠንካራ ዕጩዎች ይታወቃሉና እነዚህን በስም ሳይቀር እያነሱ የሚጠይቁ ሰዎች አሉ፡፡ እነሱ የሉም ማለት በምርጫው ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ አይኖርም ከተባለ ከዚህ ጋር አይቃረንም?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- ይህ አባባል ጉድለት የሚኖረው ነገር ምንድነው? ራሱ ዋና ዋና ተፎካካሪዎች የታወቁበት የፖለቲካ ዓውድ ነው ያለን ብሎ ማሰብ ትክክለኛ አይመስለኝም፡፡ እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ የሕዝብ ድጋፍ አለኝ ብሎ ይናገራል፡፡ ይኼኛውን ሕዝብ የምወክለው እኔ ነኝ ብሎ ይገልጻል፡፡ ግን ያ በተወሰነ ደረጃ የሚረጋገጠውና አዎ እኔ ፊት ለፊት ነኝ፣ አሊያም ትልቅ ነኝ ለማለት ማረጋገጫ ይዞ መጣ የሚባለው አንድ ወገን ወይም መሪም ሊሆን ይችላል፣ ፓርቲም ሊሆን ይችላል፣ በተወሰነ ደረጃ በምርጫ ውድድር ተወዳድሮ፣ በክርክር ተሳትፎ፣ ሐሳቡን አሳይቶ የሕዝብን ድምፅ ሲያገኝ ነው፡፡ በአጠቃላይ እንደ ማኅበረሰብ በነበረን ትዝታ ይህኛው ፓርቲ እንደዚህ ነው ልንል እንችላለን፡፡ ነገር ግን ያንን ወስዶ በሕዝብ ድምፅ የመለካቱን ነገር አለመታደል ሆኖ በደንብ አድርገነው አናውቅም፡፡ በተወሰነ ደረጃም የተደረገበት ጊዜም አለ እንኳን ቢባል፣ እንደገና ወደ ኋላ የመመለስ ነገር እንጂ፣ በዚያው ላይ ያው ፓርቲ እየቀጠለ እዚህ ጋ ደርሷል ወይም አልደረሰም ለማለት አይቻልም፡፡ ገዥው ፓርቲ እንኳን ባለፈው ሁለት ዓመታት ሌላ ሆኗል፡፡ በተቃዋሚዎችም በኩል ብትመለከት በእርግጥ አንዳንድ ስሞች ለረዥም ጊዜ የቆዩ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በአዲስ መድረክ ላይ በአዲስ አደረጃጀት አዳዲስ ፊቶች ይዘው የመጡ አሉ፡፡ ድሮም የምናውቃቸውም እኮ ቢሆኑ ሒደቶችና የምንሠራበት ዓውድ ሲለዋወጥ ምን ያህል እንደተለወጡ፣ መሠረታቸው ምን ያህል እንደተለወጠ፣ ጨምሯል? ወይስ ቀንሷል? እነዚያ ነገሮች ሁሉ መታየት አለባቸው፡፡ አሥር ፓርቲዎች አይደሉም የሚሳተፉት አሁን 47 ፓርቲዎች ይሳተፋሉ፡፡ ይህ ትልቅ ቁጥር ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡– ከ107 ፓርቲዎች ነው 47 ፓርቲዎች የሚሳተፉት?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- ከ107ቱማ በሕጉ መሠረት ማሟላት የሚገባቸውን ነገር አሟሉ ስንላቸው ማሟላት ስላልቻሉ፣ ምርጫው ጋ ሳንደርስ የፓርቲዎቹ ቁጥር 53 ደረሰ፡፡ ስለዚህ ከ53ቱ 49 እንወዳደራለን ብለው ምልክት ወሰዱ፡፡ ከዚያ በኋላ 47 ብቻ ለውድድር ቀረቡ፡፡ ስለዚህ በመቶኛ ብትመለከተው ከ53 አንፃር ማለቴ ነው ያን ያህል ጉድለት የለውም፡፡ እናም ግማሾቹ የቅንጅት አካሎች ናቸውና እንደ ቅንጅት የሚወዳደሩ አሉ፡፡ ስለዚህ ያንን ብታሠላው በጣም አነስተኛ የሚባል ቁጥር ነው፡፡ ግን ያ ማለት ቢቀሩም ትርጉም የለውም ለማለት አይደለም፡፡ እንደ እሱ ማለት አልፈልግም፣ ትክክልም አይሆንም፡፡ ግን ተሳትፎው በጣም ትልቅ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ ተሳትፏቸው እነዚህ ተወዳዳሪዎች የፖለቲካውንም ደረጃ የተሻለ ለማድረግ፣ ውይይትንም ክርክሩንም ትርጉም የሚሰጥ፣ ዋጋ ያለው፣ ለመራጮችም የሚጠቅም፣ በተለይ ደግሞ ከጥላቻ ንግግር፣ ከግጭት የፀዳ ሆኖ ከሰው ፍላጎትና ችግር ጋር የሚገናኝ ፖለቲካ ማራመድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁንና በምርጫ ቀን የምንጠብቀው ነገር ይህንን ነው፡፡ እንደ ቦርድ ይህንን የማገዝ፣ መድረክ የመፍጠርና በቂ ዕድል ማግኘታቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ነው ያለብን፡፡ ስለዚህ ዋና ዋናዎቹ ቀርተዋል ወይም ዋናዎቹ ገብተዋል የሚለውና በእርግጠኝነት የሚሰጠው ድምዳሜ፣ ያልተፈተነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያለን አገር ከመሆናችንና ከተሳታፊዎችም ብዛት አንፃር ትክክለኛ ድምዳሜ አይመስለኝም፡፡
ሪፖርተር፡– ወደ ምርጫ ቦርድ ተቋማዊ ለውጥ (Reform) ስንመጣ፣ አንደኛው ምሰሶ ገለልተኝነቱን ማረጋገጥና የሚታመን ተቋም መሆን ነው፡፡፡ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብዛት ወደ ቦርዱ የሚሰነዘረው ወቀሳ ገለልተኛ ለመሆን እንኳን የሚያስችለው ሁኔታ የለውም የሚል ነው፡፡ ለፓርላማው ተጠሪና በጀቱንም የሚያፀድቀው ፓርላማ ቢሆንም፣ የአስፈጻሚው አካል ጠንካራ እጁን ያሳርፍበታል ይላሉ፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚያደርጉት በኮቪድ-19 ምክንያት ቦርዱ ምርጫውን ለማራዘም ሲሞክር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደገለጹት እርስዎ ላይ ጫና ለማድረግ መሞከራቸውን መናገራቸውን በመጥቀስ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እውነት ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ምርጫውን ፍትሐዊ፣ ገለልተኛና ነፃ አድርጎ ለማካሄድ የሚያስችል ብቃቱ አለው?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- እውነት ለመናገር አንዱ በጣም ብዙ መሻሻልና እመርታ አሳይተናል ብዬ የምገምተው አንዱ ነገር የተቋሙ ገለልተኝነት ነው፡፡ በእያንዳንዱ ጉዳይ መመርያዎች ስናወጣ ገዥው ፓርቲ እንደ ማንኛውም ፓርቲ መጥቶ ይከራከረናል፣ ሐሳቡን ይገልጻል፡፡ ሐሳቡም ተቀባይነት ያላገኘበት ብዙ ጊዜ አለ፡፡ ከዚያ በላይ ግን አልፎ እንደዚህ ማድረግ አለባችሁ፣ ካላደረጋችሁ ብሎ ከባድ ተፅዕኖ የምትለውን ነገር እኔ እስካሁን አላየሁም፡፡ ነገር ግን ምንድነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ብለህ የጠቀስከው ነገር እኔ በጣም ይገርመኛል፡፡ በዚህ የፖለቲካ ሒደት ውስጥ እንደ አቅሜ ብዙ ጊዜ ቆይቻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ የተወሰነ የፖለቲካ ባህሉንም፣ የተቋም ባህሉንም እዚህ ብቻ ሳይሆን ፍርድ ቤት በነበርኩበት ጊዜ አውቀዋለሁ፡፡ ተቋም ወደ ገለልተኝነትና ወደ ጥንካሬ መምጣት፣ ገለልተኝነቱንም ማስከበር የሚችለው እንዲሁ አንድ ቀን በአዋጅ ከዛሬ ጀምሮ ምርጫ ቦርድን ምንም ነገር እንዳትናገሩት፣ ወይም ለፍርድ ቤት ምንም እንዳትሉ ተብሎ የሚፈጸምበት ዓይነት ነገር አይደለም፡፡ ሁላችንም እዚህ ውስጥ ተለማማጆች ነን፡፡ የለመድናቸው አሠራሮች አሉ፡፡ ይህ ነገር እኮ እንደዚህ መሆን አለበት ብሎ ለምሳሌ ሥልጣን የሌለው አካል ገፋ ሊያደርግ ይሞክር ይሆናል፡፡ ደግሞ መነጋገር ሁሌም የሚቀር ነገር አይደለም፡፡ ገለልተኛ ተቋማትም ቢሆኑ ከሌሎቹ ተቋማትና ከአስፈጻሚው ጋር አብሮ የሚሠሯቸው ብዙ ነገሮች ስላሉ፣ መነጋገርንና መወያየትን ማስቀረት የምትችለው ነገር አይደለም፣ አስፈላጊም ነው፡፡ ግን በዚያ ውስጥ ከአቅሙ ወይም ከሥልጣኑ በላይ አልፎ ተፅዕኖ ለማሳደር ቢሞክር ወይም ስለሞከረ አለቀ ማለት አይደለም፡፡ ተቋሙ ደግሞ አንድ አካል ነው፡፡ በወዲህ በኩል ገለልተኝነቱን ሊያስጠብቅ የሚፈልገው፣ አይ ይኼ እኮ እኛ የምንወስነው ነው እየተባለ ሒደቱ ነው ወደ ጥንካሬና ወደ ገለልተኝነት የሚመራው እንጂ፣ በቃ ከዕለታት አንድ ቀን ሁላችንም ይህንን ተምረን አናገኝም ወይም ደግሞ ችለነው አናገኘውም፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ እዚህም እዚያም የሐሳብ ልዩነቶች ነበሩን፣ ወደ ፊትም ይኖሩናል፡፡ እንደ ተቋም አንድ ቀን ከገዥው ፓርቲ ጋር ላንስማማ እንችላለን፡፡ አንድ ቀን ደግሞ ከተቃዋሚው ጋር ላንስማማ እንችላለን፡፡ እስካሁን ባሳለፍነው እንዲህ ያለ ነገር ብዙ ጊዜ አጋጥሞናል፡፡
ለምሳሌ የሕግ ማሻሻያ ሲደረግ ብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከእኛ ጋር ብዙ ነገር ብለዋል፡፡ ግን ያው አቋማችንን ከሕግና ከዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር አያይዘን ሐሳባችንን ገልጸን አልፈነዋል፡፡ በገዥውም ፓርቲ እንደዚያው ነው፡፡ ገለልተኝነት ሁልጊዜ ከአንድ በኩል የሚመጣ አይደለም፡፡ ያው ገዥው ፓርቲ ጉልበት አለው ወይም አቅም አለው በሚል እናስበዋለን እንጂ፣ ያ ነገር ከሁሉም አንፃር ሊመጣ ይችላል፡፡ ከሕዝብ አስተያየትም ሊመጣ ይችላል፡፡ ከዚያ አንፃር እኛ በጣም ብዙ ብዙ ዕድገት አሳይተናል ማለት እችላለሁ፡፡ እናንተም ጋዜጠኞች ብታጣሯቸው የኮቪድ ጉዳይ የገለልተኝነታችን አንድ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በጣም ከባድና ትልቅ ልዩነት ነበረን፡፡ የፌዴራል መንግሥቱን የሚመራው ኃላፊ ነገሩ መቀጠል አለበት በሚልበት ጊዜ፣ ከዚያ በኋላ ይህ ተቋም ደግሞ ይህን ይህን ነጥብ ዓይቼ ምርጫውን ለጊዜው አግደዋለሁ ሲል እውነት ለመናገር ትልቁ ፈተናችን ነበር፡፡ ምክንያቱም በተወሰነ ደረጃ በሕግም በአስተሳሰብም እንደገና አስበውት ኃላፊዎቹ ካልተቀበሉት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ልንገባ እንደምንችል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋ እንደማያበቃ፣ ፓርላማም ሊሄድ እንደሚችል ገምተን ነበር፡፡ ግን ጥሩነቱ ጥናት አድርገን ነበር፡፡ እሱን አቅርበን አጋራናቸውና የእኛን ውሳኔና ሐሳብ እንግዲህ ከቅሬታ ጋር ይሁን ወይም ሙሉ በሙሉ ይሁን አላውቅም፣ የተቋሙን ሥልጣን አክብረው የቀጠልንበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በፓርላማም ደረጃ በአስፈጻሚም ደረጃ ማለት ነው፡፡ እንደማስበው ከዓመታት በኋላ እንደ ተቋም ታሪክ በጣም ጥሩ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡
ይህ ብቻ ደግሞ አይደለም ሌሎችም ያጋጠሙን ነገሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የፓርቲ አመዘጋገብን ሁኔታ ብንመለከት የአንዳንድ ፓርቲዎችን ምዝገባ አስፈጻሚው በደስታ የሚያየው እንዳልነበር ይታወቃል፡፡ በተለይ እነ ኦነግና ሌሎች፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች እኮ ሰላማዊ አይደሉም ብሎ በእኛ በኩል የውትወታ ሥራ (Lobby) የማድረግ ነገር አልተሞከረም አልልህም፣ ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን እኛ በቀጥታ ወረቀታችንን ዓይተን ሕገወጥ ናቸው ካላችሁ፣ ጠብመንጃ እያነሱ ነው ካላችሁ ማስረጃውን ስታመጡ ነው የምንሰርዘው ብለን ነው ያለፍነው፡፡ ማንም ሰው እኮ ዓይቶ የሚረዳው ነገር ነው፡፡ ቴሌቪዥን ላይ ሄደው የተለያዩ የአስፈጻሚው አካላት የሆኑ ሰዎች ይህ ፓርቲ ሕግ እየጣሰ ነው ይላሉ፡፡ እኛ ግን እርሱን በእርግጠኝነት ብናውቅ ኖሮ ሰርተፊኬቱን ይዞ እንዲቀጥል አናደርግም ነበር፡፡ ግን ማስረጃ የለንም፡፡ ማስረጃ አለኝ የሚለውም አካል ይኼውና ብሎ አቅርቦ አላሳየንም፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ፓርቲ የኃይል ተግባር ውስጥ ገብቶ እየሠራ እንደሆነ ካረጋገጥን መሰረዝ አለብን፡፡ ይህ አንዱ ግዴታችን ነው፡፡ ብዙ ነጥቦችን ማንሳት እችላለሁ፡፡ ከፍ ሲል እንደገለጽኩት የመመርያዎችን ይዘት በተመለከተ መነጋገር እንችላለን፡፡ በእኛ በራሳችን ኃላፊነት ውስጥ የሚወድቀውን ነገር በተመለከተ ባለን መረጃ፣ ባለን ሰነድ፣ ባለን ሕግ መሠረት ህሊናችን በሚመራንና ትክክል ነው በሚለን ነው እስካሁን እየመራን ያለነው፡፡ ከውጭ በሚደርስ ተፅዕኖ ወደዚህ ተቆለመምን ወደ እዚያ ሄድን የምንልበት ነገር የለም፡፡ እውነት ለመናገር ምናልባት ዛሬ ላናየው እንችላለን፡፡ ዛሬ ያለው ቦርድ ምን ያህል የዚህን ተቋም አሠራርና ተቋማዊ ታሪክ እንዴት ልዩነት እንደፈጠረበት ዛሬውኑ ላይታይ ይችላል፡፡ እኔ ግን የተወሰነውን ነገር አሳክተናል በሚል ምክንያት ዕርካታ ይሰማኛል፡፡
ሪፖርተር፡– በዚያኛው ወገን ደግሞ ቦርዱ ለብልፅግና ፓርቲ ያደላል የሚሉ ትችቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ በፖለቲካ ፓርቲ አመዘጋገብ ላይ በተለየ የሚያነሱ አሉ፡፡ ፓርቲው ከኢሕአዴግነት ከተቀየረ በኋላ ጉባዔ አላደረገም የሚሉ አሉ፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ የመተዳደሪያ ደንቡን በጉባዔ አላፀደቀም በሚል ምክንያት መመዝገብ የሌለበትን ፓርቲ መዝግቦ ነው እያወዳደረ ያለው የሚል ወቀሳ አለና ለዚህ ወቀሳ ምላሽዎ ምንድነው?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- ክስ አይኖርም አይባልም፡፡ ሁልጊዜ ነው የምትከሰሰው፡፡ ምክንያቱም እውነት ለመናገር በምርጫ ሥራ በጣም በከፍተኛ ደረጃ ፖለቲካዊ የሆነ ሁኔታ ነው የምናስተዳድረው፡፡ ፖለቲካ ደግሞ በጣም ተገለባባጭ ነው፡፡ በሦስትና በአራት ሳምንታት በተለይ በዚህ ዘመን ሰዎች አቋማቸውን ከዚህ ወደ እዚያ ሊቀይሩ ይችላሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነት በጣም ተለዋዋጭ ነገር ውስጥ ተለዋዋጭ ሐሳብ የሚያራምዱ ተዋንያን የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የምናስተዳድር ተቋም ነን፡፡ ስለዚህ የእኛ ኃላፊነት ከዚያ ወጀብና ከዚያ ተለዋዋጭ ሁኔታ ራሳችንን መጠበቅ ነው፡፡ ወደ እኛ የውሳኔ ሒደት ውስጥ ገብቶ እንዳያሰናክለን ማድረግ ነው እንጂ ከክስ ነፃ መሆን አንችልም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሰው እንደ ዕይታው ብዙ ነገር ሊመስለው ይችላል፡፡ ውሳኔያችንን፣ መነሻችንን፣ ሕጋዊነቱን፣ ፍትሐዊነቱንና ለማንም እያደላን እንዳልሆነ ለማሳየት እንሞክራለን፣ እናስረዳለን፡፡ ግን ከዚያም ደግሞ በተለያዩ ምክንያት የሚከስ አይጠፋም፣ እንቀጥላለን፡፡ ግን ቅድም እንዳልኩት በረዥም ጊዜ አንዳንድ የሠራናቸው ሥራዎች፣ የወሰንናቸው ውሳኔዎች እንደገና ተመልሰው ቢመረመሩና ቢጠኑ የምር መሀል ቦታ ሆነን ለግራም ለቀኝም ሳንል የምንሠራውን ነገር እንደሠራን ሰነዶቹም፣ ውሳኔዎቹም ያሳያሉ ብዬ ነው የማምነው፡፡ ነገር ግን በተለይ የፓርቲ ምዝገባን በተመለከተ ላነሳኸው ጥያቄ፣ ብልፅግና ሲቋቋም ያደረገው ጠቅላላ ጉባዔ፣ እንዲያውም አንድ ጠቅላላ ጉባዔ አይደለም ያደረገው፡፡ ስምንቱም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ አድርገዋል፡፡ ራሱ ሕጉ ውህደት ሲደረግ ወይም ቅንጅት ሲደረግ እኛን አረጋግጡ የሚለን ዋናው ነገር የፓርቲዎቹ አባላት ወደ ውህደቱ ወይም ወደ ቅንጅቱ ከመምጣታቸው በፊት፣ እነሱ የሚፈልጉት ነገር መደረጉን ማረጋገጥ ነው፡፡ ማንኛውንም ቅንጅትም፣ ውህደትም ብትመለከቱ ዝም ብሎ ላይ ያለው መሪ ተነስቶ ከእከሌ ፓርቲ ጋር እዋሀዳለሁ እንዳይል የአባላቱ ፍላጎት ተጠብቋል ወይ? ይህ የአባላቱ ድምፅ ነው ወይ? የሚለውን ነገር ነው ማረጋገጥ የሚኖርብን፡፡ ስለዚህ በእያንዳንዱ ጠቅላላ ጉባዔ ተረጋግጧል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው እንደ ብልፅግና ሆናችሁ እንደገና አንድ ጉባዔ ካላደረጋችሁ፣ የዛሬ ሳምንት ስምንት ጉባዔ አድርገው የአባላቶቻቸውን ፍላጎት አረጋግጠው፣ ውሳኔ አሰጥተው፣ ሰነዶችን አስቀርበው አረጋግጠው የተዋሀዱትን ፓርቲዎች እንደገና ደግሞ አንድ ላይ ሆናችሁ ጠቅላላ ጉባዔ ካላደረጋችሁ የምንልበት ምንም ሕጋዊ መሠረት የለንም፡፡
ሪፖርተር፡– ሕገ ደንቡን ግን አላፀደቁም፡፡ የተዋሀዱት ስምንቱ ፓርቲዎች የወሰኑት ለመዋሀድ ነው እንጂ፣ በምን ዓይነት ሕገ ደንብ እንደሚተዳደሩ አፅድቀው አይደለም ወደ ብልፅግና ፓርቲ የመጡት የሚባለውስ?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- ለምን እንደዚያ እንዳሰብክ አላውቅም፡፡ ከፓርቲ ጉዳዮች ሰነዶችን ጠይቆ ማየት ነው፡፡ የሚመጣው የውህዱ ፓርቲ የሚኖረውን የአመራር አባላት እንዴት እንደሚወስኑ፣ ቀጥሎ ጉባዔያቸውን ሲያደርጉ እንዴት እንደሚወስኑ፣ እነዚያ ሁሉ ነገሮች ለእያንዳንዱ ፓርቲ ቀርቦ የፀደቀበት ሰነድ አለ፡፡ ያንን ሳናይማ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሌላውን ነገር ትተኸው መሪዎቹ እንዴ ተመረጡ? የሚለው ነገር መጠየቅ አለበት፡፡ ግን መሪዎቹ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ወይም ፊት ለፊት የሚመጣውን ብቻ ሳይሆን፣ ማዕከላዊ ኮሚቴው እንዴት እንደተዋቀረ? ከድሮው እንዴት እንደሚለይ፣ ራሳቸውን ከሚያከስሙት ፓርቲዎች ስንት ሰው እንደሚመጣ ዝርዝር ሰነድ አለ፡፡ ያ ሰነድ ቀርቦና ፀድቆ በዚህ መሠረት ነው ማዕከላዊ ኮሚቴያቸውን ያቋቋሙት፣ አስፈጻሚያቸውን ያቋቋሙት፣ እንዲሁም ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበራቸውን የመረጡት፡፡ ደግሞ ለሽግግር ጊዜ ብለው ያቀረቡት ሰነድ አለ፣ እነሱ ያንንም ማድረግ ይችላሉ፡፡ ግን እንደ ማንኛውም ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ አሁን ማድረግ ነበረባቸው፡፡ ብዙዎች ፓርቲዎች የጎደሏቸውን ነገሮች ለማሟላት ማድረግ ነበረባቸው፡፡ ሆኖም ያው የምርጫ ዝግጅት በአንድ በኩል ስላለና ሁለቱንም አድርጉ ማለት ስለማንችል፣ ፓርቲዎቹም ራሳቸው ስለጠየቁን ከምርጫ በኋላ እንዲደረግ ፈቃድ ሰጥተናል፡፡ ለሁሉም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮን) ጨምሮ በእርግጥ እነሱ በምርጫው ስለማይሳተፉ መልሰን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ ኦፌኮ ግን በጽሑፍ ጠይቆናል፡፡ ምርጫው ውስጥ ለሚሳተፉ ሌላ ጠቅላላ ጉባዔውን ያራዘመው ብልፅግና በዚያ ውስጥ ተካቷል፡፡ ለብልፅግና ለማድላት ምን መነሻ አለን? እኔን በግሌ ብትጠይቀኝ ለአንድ ፓርቲ የማደላ ከሆነ ሄጄ እዚያው ፓርቲ እገባለሁ፡፡ ከዚህ በፊትም አድርጌው አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኛ ዓይነት ተቋም ውስጥ ሆኖ ለአንደኛው ፓርቲ ለማድላት የሚፈልግ ካለ፣ እውነት ለመናገር ፓርቲውንም ተቋሙንም ይጎዳዋል፡፡ ለጊዜው ያው ሰዎች ይመስላቸዋል እንጂ፣ የአንደኛውን አጀንዳ መግፋት ለጊዜው ልታዋጣ ትችላለች፡፡ ግን በረዥም ጊዜ አዋጭ ነገራችን ተቋማችን ነው፡፡ ለማንኛውም ለብልፅግናም፣ ለኢዜማም፣ ለአብንም ለሁሉም የሚጠቅም ነገር መሥራት እየተቻለ ለምንድነው አንዱን የሚጠቅም ነገር ለሁለት ዓመት ሠርተህ፣ ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ በሆነ አጋጣሚ ብልፅግና ሸርተት ቢል ደግሞ ተረኛው መጥቶ ለዚያኛው እያደላህ ብልፅግናን ይጎዳዋል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን ስንት ጊዜ ሞክረነው ምንም ያልጠቀመን ነገር ነው፡፡ ገለልተኛንን ማስጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ሥራ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ወደ መጪው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጀቶች እንግባ፡፡ በዋናነት ቦርዱ ገለልተኛ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ በተለያዩ ደረጃ ካሉ የመንግሥት አካላት ደግሞ ትብብር ያስፈልገዋል፡፡ በምርጫ ዝግጅቶች ሒደት ውስጥ የታየው ከፍተኛ ክፍተት የክልሎች አለመተባበር ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለት የዕጩዎች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ እንዲወጣ አስገድዷል፡፡ በ673 የምርጫ ክልሎች የገጠሙ በርካታ ውጣ ውረዶችን በማንሳት ወደ 50 ሺሕ ያህል የምርጫ ጣቢያዎች የሚመዘገቡ ዕጩዎች ጋ ሲመጣ ምን ያህል ፈታኝ ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ በርካታ አካላት አሉ፡፡ እነዚህን ፈተናዎች እንዴት ታዩአቸዋላችሁ? በብቃት ለመወጣት የሚያስችል አቅምስ አላችሁ?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- በዕጩዎች ምዝገባ ሒደት ወቅት ከምርጫ ቦርድ ጋር የመተባበር ግዴታን ከመወጣት አንፃር ክፍተቶች በደንብ ታይተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በሒደት እዚህም እዚያም መሻሻሎችን ዓይተናል፡፡ ያው ሒደቱ እየቀጠለ ሲመጣ ክልሎቹም ትኩረታቸውን ወደዚህ የመመለስ አዝማሚያ አለ፡፡ ለምሳሌ አሁን በ50 ሺሕ ቦታዎች ጣቢያዎች ለመክፈት ዝግጅት ስናደርግ፣ በ673 ቦታዎች በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የምርጫ አስፈጻሚዎች በሁለትና በሦስት ዙር የሚሠለጥኑባቸው ማዕከላት ማግኘት ነበረብን፡፡ ከዚህ አንፃር ትምህርት ሚኒስቴርን፣ የክልል ትምህርት ቢሮዎችን አነጋግረናል፡፡ ሆኖም ተግዳሮቱ ነበር፡፡ የአቅም ውስንነት በየቦታው ይስተዋላል፡፡ አሁን እነዚያን የማሠልጠኛ ቦታዎች ለማዘጋጀት በመጀመርያው ዙር ለዕጩዎች ምዝገባ በ20 ቦታዎች ነው ያሠለጠንነው፡፡ አሁን ግን በ673 ቦታዎች ነው የምናሠለጥነውና ምን ያህል ልዩነት እንዳለው መመልከት ትችላለህ፡፡ ግን አሁንም በተወሰኑ ቦታዎች ቦታ ያለ ማግኘትና የፀጥታ ችግሮች ያለባቸው ቦታዎችም አሉ፡፡ ከእነዚህ መንገራገጮች ውጪ በሌሎች ቦታዎች በየምርጫ ክልሎቻችን አቅራቢያ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን አግኝተን ሥልጠናው ተጀምሮ እየተከናወነ ነው፡፡ ችግር አለ ወይ? በደንብ አለ፡፡ ምርጫ ቦርድ ይችላል ወይ? ለሚለው ጥያቄ ምርጫ ቦርድ መቼም ቢሆን ይኼን በሚያህል አገር፣ አጠቃላይ ምርጫም ሆነ የአካባቢ ምርጫ የሚባሉትን ይህን ያህል የቆዳ ስፋት፣ የመሠረተ ልማት ችግርና የሕዝብ ብዛት ባለበት አገር ራሱን ችሎና የራሱን አቅም አደርጅቶ ከላይ እስከ ታች ወጥ ሆኖ፣ መኪናውንም ወይም የሥልጠና ቦታዎቹንም አደራጅቶ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ቢያደርግ ደግሞ ትክክለኛ አካሄድ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም አሁን ለምሳሌ ዛሬ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ብትጠይቀኝ ከመቶ በላይ የፓትሮል መኪናዎች ወደ ክልሎች ለመላክ እፈልጋለሁ፡፡ ግን ይህ የመጀመርያው የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁስ ስናመላልስ የሚያስፈልገን የመኪና ብዛት ነው፡፡
ከዚያ ደግሞ እንደገና ሌሎች በጣም ብዙ መኪናዎች ያስፈልጉናል፡፡ የምርጫው ቀን በሚደርስበት ቀን ደግሞ ከዚህ ከፍ ያለ ያስፈልገናል፡፡ ግን ከዚያ በኋላ ይህ ተቋም ምንድነው የሚያደርገው? ውጤቱን ይናገርና ሥራዎቹ ቀስ እያሉ ፍጥነታቸውና ስፋታቸው ይቀንሳል፡፡ ከምርጫው የተማርነው ምንድነው? ወደሚል የጠረጴዛና የጥናት ሥራ ነው የሚያመራው፡፡ ስለዚህ ይህን ያህል አቅም በዚህ መሥሪያ ቤት አከማችቶ ለአራት ወራት እየተጠቀሙበት፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ለሁለትና ለሦስት ዓመት ዝም ብሎ ያለ ሥራ ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ መኪናም ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ የትም አገር የሚሠራው እንደዚያ ነው፡፡ አሁን በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግሥት ደረጃ ያንን አውቆ ልክ ምርጫ ቦርዱ ሲዘጋጅ፣ እነሱም ዝግጅታቸውን መጀመር አለባቸው፡፡ ምናልባት ከዚህ ምርጫ የምናየው ነገር እሱ ይመስለኛል፡፡ አሊያም አስገዳጅ ሕግ ማውጣት ያስፈልግ ይሆናል፡፡ ምናልባት አስገዳጅ አደረጃጀት ማምጣት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የሕዝብና ቤት ቆጠራን ብትመለከት ራሱን የቻለ ኮሚሽን አለው፡፡ ያ ኮሚሽን እያንዳንዱን ክልል ይህን ያህል ዕቃ፣ መኪና፣ ገንዘብ አዋጣ እያለ የሚያስገድድበት ቋሚ አሠራር አለው፡፡ እኛ እንደ እነሱ ሙሉ በሙሉ በአስፈጻሚው ሥር ልንሆን አንችልም፡፡ ምክንያቱም ከዚያ ውጪ ሆነናል፡፡ ግን የተቋሙን ገለልተኝነት ችግር ላይ ሳይጥል፣ የሚያስፈልገውን ዕገዛና ትብብር የሚያደርግለት አደረጃጀት የግድ ያስፈልጋል እላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡– የፀጥታን ጉዳይ እርስዎም ጠቅሰውታል፡፡ በዋናነት ከፀጥታው ጋር በተገናኘ በበርካታ ቦታዎች ጉዳዩ ይነሳል፡፡ በቅርቡ እናንተም ይፋ እንዳደረጋችሁ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለይ መተከል አካባቢ ባለው የፀጥታ ችግር ዕጩዎች መመዝገብ እንዳልቻሉና ለመንቀሳቀስ አደገኛ እንደሆነባቸው ሲገልጹ ነበር፡፡ በመተከል ዞን ነዋሪዎች ተፈናቅለው ነው የሚገኙት፡፡ ግጭቶች እስካሁን እንደቀጠሉ ነው፣ ሕዝቡ እየተፈናቀለ ነውና እንዲህ ባለ ሁኔታ ምርጫ ማድረግ ይቻላል?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- ምርጫ በተወሰነ ደረጃ የፀጥታና የመረጋጋት ሁኔታ ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ እኛ መጀመርያውንም ይህንን ሒደት ስንጀምረው ደጋግመን እንደተናገርነው፣ አጠቃላይ በሆነ ምዘና የግጭት ወይም የፀጥታ ሁኔታን ለመረዳት መሞከር አይጠቅምም፡፡ አገሪቱ ሰላም የላትም ወይም ደግሞ ኦሮሚያ ሰላም የለም፣ ወይም ደግሞ አማራ ክልል የለም የሚለው ምዘና ምንም ስሜት አይሰጥም፡፡ ምክንያቱም ሁልጊዜም ትክክለኛ ምሥል አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ ግጭቶች በጣም አካባቢያዊ ሁኔታ አላቸው፣ የጊዜ ሁኔታ አላቸው፡፡ እነዚያ ግጭቶች ተለይተው ምርጫ ማድረግ የሚያስችሉ ቦታዎች ላይ ለጊዜው እያቆየንም ቢሆን ነው መቀጠል ያለብን፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ስላማዊ ሁኔታ አላቸው ብለን በአጠቃላይ ስለምንመለከት፡፡ ስለሆነም ከዚያ አንፃር የራሳችንን የግጭት መለየት (Mapping) ሥራ እየሠራንና መረጃዎች እየሰበሰብን ቆይተናል፡፡ ግን እኛ ሥራችን ምርጫ ማደራጀትና ማስፈጸም እንጂ፣ የሕግ ማስከበር ወይም የፀጥታ ሠራተኛ መሥሪያ ቤት አይደለንም፡፡ ከመንግሥት በኩል ከፌዴራልም ሆነ ከክልል በዚህ መንገድ የተተነተነ እስከ ታች የወረደ መረጃ እንዲመጣልንና የእኛ ውሳኔም፣ የሎጂስቲክስም፣ የእንቅስቃሴም ሥራ በዚያ መሠረት እንዲመራ ነበር የምንጠብቀው፡፡ ከዚያ አንፃር እውነት ለመናገር የምንፈልገውን ዓይነት ድጋፍ አላገኘንም፡፡ የፌዴራል ተቋማት በተወሰነ ደረጃ በመተባበርና ችግሮች ሲያጋጥሙም በማገዝ ረገድ የተሻሉ ናቸው፡፡ የዕጩዎች እስር በየቦታው አጋጥሞናል፡፡ ለሁሉም አካላት፣ ለሕግ አስፈጻሚዎችም በሌላ ኃላፊነት ላሉ የመንግሥት ኃላፊዎችም ነግረናል፡፡፡ ዕጩ ማሰር ምንም ተቀባይነት የለውም፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ ሲገድልና ሲዘርፍ እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር፡፡ ማስረጃ ካላቸው ሌላ ቀን መጠያየቅ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር እዚህም እዚያም ችግር አጋጥሞናል፡፡ ባያጋጥም ጥሩ ነበር፡፡
ነገር ግን ካጋጠመ በኋላ እንዳልኩህ በአብዛኛው ከፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ጋር፣ ከሕግ አስፈጻሚዎች ጋር በነበረን ትብብርና በምርጫ ደኅንነት ግብረ ኃይል ውስጥ በነበረን ሚና ችግሮቹ ቶሎ ቶሎ እንዲፈቱ በተለይ የታሰሩ ዕጩዎች እንዲፈቱ ለማድረግ ችለናል፡፡ ሌሎች አቤቱታዎች ግን አሁንም አሉ፡፡ እነሱንም ደግሞ እንዲሁ እያደራጀን በማስረጃ የተደገፉትን በየቦታው መፍትሔ እንዲሰጣቸው ለማድረግ እንሠራለን፣ እንሞክራለን፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች አያጋጥሙንም ብለን መጠበቅ አንችልም፡፡ ምክንያቱም ልምድ ቶሎ አይለቅም፡፡ በነገራችን ላይ ልምድ አይለቅም ስል ለገዥው ፓርቲ ብቻ አይደለም፡፡ ተቃዋሚዎችም በሒደት የለመዷቸው መጥፎ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ አቤቱታዎችን አጋኖ ማቅረብ፣ ያለ ማስረጃ ማቅረብ፣ አንድ ቦታ አንድ ነገር ሲሆን አንዱን ነገር አሥር ነው ማለት፣ እኛ ባጣራንባቸው ሥፍራዎች እንደዚያ ዓይነት ነገሮች ዓይተናል፡፡ ምክንያቱም የተቃውሞ ፖለቲካ ሁልጊዜ ከሚያጋጥም ችግር፣ ከመታሰር፣ ከመገረፍና ከመሰደድ ጋር የተያያዘ ስለነበር አሁንም ልክ አንድ ነገር ሲታይ እዚያው ላይ ጩኸት ማምጣትና ያን ጩኸት ከፍ ማድረግ ላይ ያተኩራሉ፡፡ ግማሹን እረዳቸዋለሁ፡፡ ለምንድነው? ከመደንገጥ አንፃር ይኼም ሁኔታ ያው ነው ብሎ ‹‹እባብ ያየ በልጥ በረየ›› እንደሚባለው በልጥ የመደንገጥ ነገር አለ፡፡ ግን ሆን ብሎም ደግሞ ነገሮችን ጮክ የማድረግ ነገር አለ፡፡
ሪፖርተር፡– የመተከልን የፀጥታ ሁኔታ ያነሳሁት ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ እንደሌለና እስከ ዛሬ የቀጠሉ ጥቃቶችና መፈናቀሎች መኖራቸው ስለሚነገር ነው፡፡ ከዚያ አንፃር ማድረግ እንችላለን ብላችሁ ታምናላችሁ?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- በተለይ መተከልን በተመለከተ ለመመለስ፣ ባለፈው ሳምንት እዚያ አካባቢ ያለውን ኮማንድ ፖስት የሚያስተባብሩት፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት ምን ያህል ሰው እንደተፈናቀለ፣ ምን ያህል ሰው ደግሞ ወደ ቄዬው እንደተመለሰ (ምክንያቱም ከዚያ አንፃር ብዙ ለውጦች ታይተዋል ስለተባለ)፣ የፀጥታው ሁኔታ ምን እንደሚመስል የተሟላ መረጃ ከፌዴራል ተቋማትም ጭምር የሚገኝ ስለሆነ አሰናድተውና አሟልተው እንዲልኩልን የፕሬዚዳንቱን ጽሕፈት ቤት ጠይቀን ነበር፣ አልመለሱም፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፣ ሌሎችም ተቋማት እንዲህ ያደርጋሉ፡፡ ወይ ሥራውን አይሠሩትም፣ ከሠሩት ደግሞ የእኛን ተቋም እንደ የውጭ አካል ይቆጥሩታል፡፡ ተቋሙ ከእነሱ ውጪ ነው፡፡ ነገር ግን መታገዝ ያለበት ነው፡፡ የማገዝ ግዴታም አለባቸው፡፡ ከዚያ አንፃር ያገኘነው ምላሽ በጣም የሚያረካ አይደለም፡፡ ውሳኔያችንንም አዘግይቶብናል፡፡ በተመሳሳይ ከፌዴራል መሥሪያ ቤቶችም የምንፈልጋቸው መረጃዎች እንደዚያው ተደራጅተው እየመጡ አይደለም፡፡ በተለይ የሕግ ማስከበርና የፀጥታን ሁኔታ በተመለከተ፡፡ ጥሩ ነገሩ ግን ምንድነው? የእኛ ራሳችን መዋቅር ወደ ታች በወረደ ቁጥር የተሻለ መረጃ ከራሳችን አስፈጻሚዎች እናገኛለን፡፡ የከሚሴውን የሰሞኑን ሁኔታ ብንመለከት ከመንግሥት የደረሰን መረጃ የለም፡፡ ግን የራሳችን አስፈጻሚዎች መረጃ ሰጥተውናል፡፡ ከእኛ ጋር እየተነጋገሩ ከቦታው ራሳቸውን እንዲያሸሹ፣ በጥበቃ ጥላ ውስጥ እንዲሆኑ፣ አንዳንድ ቦታ ደግሞ ጽሕፈት ቤቱንም ማስጠበቅ እንዲችሉ አድርገናል፡፡ ግን ጠቅለል አድርጊው ብትለኝ በፌዴራልም በክልልም ደረጃ የፀጥታን ሁኔታ በተመለከተ በጣም በሚጠቅም ሁኔታ አደራጅቶ የሚሰጠን ምላሽና መረጃ እስካሁን የለም፡፡ ያ መቀየር አለበት፡፡ ለተቋማቱም እየነገርናቸው ነው፡፡ ያንን ካላደረጉ ሒደቱ ለሚደርስበት የመዘግየት ወይም እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች የእነሱ ኃላፊነት ነው የሚሆነው፡፡
ሪፖርተር፡– ስለዚህ በዚህ ክፍተት የተነሳ ምርጫ ላይደረግባቸው የሚችሉ አካባቢዎች ሊኖሩ ይችላሉ ብለን መገመት እንችላለን?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- አሁን ልነግረህ የምችለው የመራጮችን ምዝገባ በተመለከተ ለመረዳት ስለሚቀል፣ መተከል ላይ ያለውን ሁኔታ መልሼ ላብራራ፡፡ አሁን መጀመርያ መወሰን ያለብን ነገር ምንድነው? ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው መብታቸው መገፈፍ ስለሌለበት የፀጥታው ሁኔታ ሳያግደው የመራጮች ምዝገባ እንዴት ነው ሊደረግ የሚችለው የሚለውን ነገር ማየት አለብን፡፡ ለምሳሌ ተፈናቅለው ያሉበት ቦታ መመዝገብ እንችላለን፣ አስፈላጊው መረጃና ዕገዛ ከመንግሥት ተቋማት እስከመጣ ድረስ፡፡ ለምሳሌ አንድ የመንግሥት አካል ከመተከል የተፈናቀሉ ሰዎች የት ነው የሚኖሩት? ስንት ናቸው? ተብሎ ሲጠየቅ ለምን እንደማይመልስ እኔ አይገባኝም፡፡ ይህ አሁን ብቻ አይደለም፡፡ በሌሎችም የተፈናቃይ ጣቢያዎች ያጋጠመን ነው፡፡ ያው በብዙ ትግል ዕቅዳችን ውስጥ አሁንም አለ፡፡ የተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ ጣቢያዎች በጋምቤላ፣ በሶማሌ፣ በኦሮሚያና በደቡብ አነስተኛ ቦታ ላይ አሉን፡፡ ተፈናቃዮችን እንመዘግባለን፣ እናስመርጣለን፡፡ ስለዚህ አሁንም የመተከል ነገር ስላላለቀ ነው እንጂ የማልነግርህ ወይ የተፈናቀሉበት ቦታ ሄደን እናስመርጣለን፣ ወይም ደግሞ መሻሻሎች በፍጥነት የሚከናወኑ ከሆነ የተወሰነ ጊዜ ገፋ አድርገንላቸው ለእነሱ ሌላ ዕቅድ ልናወጣ እንችላለን፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን መምረጥ አለባቸው፡፡ የማይሳተፉበት ሁኔታ መኖር የለበትም፡፡ ሌሎችም አካባቢዎች እንዲሁ፡፡
ሪፖርተር፡– በዘንድሮ ምርጫ አከራካሪ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የምርጫ ክልሎች አከላለል ነው፡፡ ምንም እንኳን እናንተ ካለፈው ምርጫ በኋላ የምርጫ ካርታ ለውጥ አላደረግንም ብላችሁ ብትናገሩም፣ የአፋርና የሶማሌ ክልሎች የምርጫ ካርታ እጀግ አወዛጋቢ ከመሆን አልፎ ተቃውሞዎችን እያስነሳ ነው ያለው፡፡ ይህ ችግር እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ለዚያ ደግሞ እያሰባችሁት ያላችሁት መፍትሔስ ምንድነው?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- ይኼ ክርክርና ችግር እንዲሁም የአደባባይ አተካሮ የመጣው በፍፁም ከምርጫ ቦርድ የምርጫ ክልል ካርታ፣ ወይም ደግሞ ከጣቢያዎች ዝርዝር ወይም አወሳሰን ጋር አይደለም፡፡ እነሱ የቆየ የአስተዳደር ድንበር ችግርና ጭቅጭቅ አላቸው፡፡ ይህን ሁሉም ሰው የሚያውቀው ነው፡፡ ወደኋላም ትንሽ ሄዶ ማየት ቢቻል አደባባይ ላይ የወጣም ነገር ስለሆነ፣ ያንን ችግር ለመፍታት የሁለቱ ክልል መንግሥታት መሪዎች ስምምነትም ፈጽመናል ብለው የጨረሱበት ጊዜ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በተለይ በሶማሌ ክልል አስተዳደር በኩል ያ ስምምነት እንዴት እንደሚተረጎም እናውቃለን፡፡ ክርክሩ ሌላ መሠረት ነው ያለው፣ ፖለቲካዊ ነው፡፡ ከአስተዳደር ወሰን ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከአካባቢው የቋንቋ ማንነት፣ ከጎሳ አደረጃጀት፣ ከብዙ ነገሮች ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ እኛ ቴክኒካዊ መሥሪያ ቤት ነን፡፡ ስለዚህ ቅድም እንዳልከው የምርጫ ክልሉን አሁን አናሻሽልም ምክንያቱም የሕዝብ ቆጠራ ውጤት የለንም፡፡ ስለዚህ ባለንበት እንቆያለን፣ እርሱ ላይ የሚነሱ ደስ የማይላቸው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የማያረካቸው ነገር፣ አሊያም ደግሞ ፍትሐዊ አይደለም የሚሉት ነገር እንዳለ እንረዳለን፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ጊዜ ማድረግ ስለማንችል ባለው እንቀጥላለን አልን፡፡ ስለዚህ ባለው ስንቀጥል በ2007 ዓ.ም. የነበሩትን የምርጫ ጣቢያዎች እንዳለ ይዘናቸው እንቀጥላለን፡፡ አንዱ ነገር ምንድነው ችግሩ? በአስተዳደር በኩል የምርጫ ጣቢያዎች በምናደራጅበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት የምርጫ ክልሎችን አደረጃጀት በምንወስንበት ጊዜ ልክ የከረመ የአስተዳደር ጭቅጭቃቸው ላይ ውሳኔ እየሰጠን ይመስላቸዋል፡፡ ይህ ግን ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም በክልሎች መካከል የድንበር ችግር ካለ፣ ክርክር ካለ፣ የማንነት ጥያቄ ካለ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዴት እንደሚሄድና ሌላ ተቋም እንዴት እንደሚወስነው የታወቀ ነው፡፡ ምርጫው ግን በራሱ ጊዜ ይሄድና ከዚያ በኋላ ለዚያ ምርጫ ሒደት ውስጥ ይቺኛዋ ቀበሌ እዚህ ጋር መረጠች ማለት ምንም ማለት አይደለም፡፡ ለአስተዳደር ወሰን ወይም ይህችኛዋ ጣቢያ እዚህ ጋ ነበረች ማለት ምንም አይደለም፡፡ ነገሩን እያቀለልኩት አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡– ነገር ግን እዚያ ቦታ ተወካይ አይኖራቸውም፡፡ አንዱ ክልል ከአንዱ ወደ አንዱ ሄዶ መረጠ ማለት ተወካይ አይኖርም፡፡ ለምሳሌ የሆነ ቦታ ላይ ያለ ሰው እዚህኛው ቦታ ላይ መረጠ ወይም እዚያኛው ቦታ ላይ መረጠ ልዩነት የለውም ሲባል፣ የእኔ ነው ብሎ የሚጠይቀው ክልል ደግሞ የእሱ የሆነ ተወካይ አይኖረውም?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- በነገራችን ላይ ስለአፋርና ሶማሌ ክልሎች ስናወራ እነዚህ ክርክር የሚደረግባቸው ቦታዎች፣ አንዳቸውም አንድ የምርጫ ክልል አይደሉም፡፡ ቀበሌዎች ናቸው፡፡ በድምሩ 30 የምርጫ ጣቢያዎች ናቸው፡፡ እዚህኛው የምርጫ ክልል ጋ፣ የዚያኛው የምርጫ ክልል ጋ ትንሽ ትንሽ አለው እንጂ፣ የምርጫ ክልሉን ውጤት ደግሞ በጣም በትልቁ የሚቀይሩም አይደሉም፡፡ ልዩነት ከፈጠረና ችግር አለብን ማለት ካለባቸው፣ እዚያ ያሉ መራጮች እዚህ ጋ መምረጥ ሲገባን እዚህ ጋ አደረጋችሁን ብሎ ብዙ ነገሮች ማንሳት ይችላል፡፡ ከእነሱ አይደለም እየመጣ ያለው፡፡ እየመጣ ያለው ከፖለቲከኞች ነው፡፡ እውነት ለመናገር እየመጣ ያለው ደግሞ ስለድንበሩና ስለመሬቱ ነው እንጂ፣ የመራጮች ድምፅ አቆጣጠር ላይ አይደለም ክርክሩ ያለው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ የምርጫ ሰላምን በተመለከተ ሊያውከን ስለሚችል የራሳችንን ዕርምጃ እንወስዳለን፡፡ ግን መረሳት የሌለበት ነገር ከዚህ ክርክር አሊያም አለመግባባት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ነገር ከዋናው ጉዳዩ ከምርጫ ጋር አይደለም፡፡ በብዙ ነገሮች ውስጥ ቆይቶ የፖለቲካዊ ውስብስብነት (Complexity) አለው፡፡ የድንበሩ ጉዳይ ለረዥም ጊዜ ሳይፈታ የቆየበት ሁኔታ፣ እንዲሁም የፀጥታ ሁኔታ አለው፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ልዩ ኃይል አደራጅተዋል፣ እስካሁን በልዩ ኃይል ይጠብቃሉ፡፡ ምናልበት ልዩ ኃይል ባይኖር ይፈታ ይሆን? አላውቅም፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ይህንን ነገር ትልቅ አስመስለው ለማሳየት የራሳቸው አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ልክ እኛ ጋ ሲመጣ በምርጫ ምክንያት ይመስላል፣ ግን አይደለም፡፡ መሆን የነበረበት የምርጫው ጉዳይ ለብቻው መታየት ነው ያለበት፡፡ የአስተዳደሩም ችግር እስካሁን መፈታት ነበረበት፡፡ ሲንከባለል ስለቆየ ነው ምርጫው ላይ ጥላውን የሚያጠላበት፡፡
ሪፖርተር፡– የዘንድሮን ምርጫ ለየት ከሚያደርጉ ጉዳዮች አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምርጫዎች ከአገራዊ ምርጫዎች ዘግይተው እንዲከናወኑ መወሰኑ ነው፡፡ ይኼ ለምን እንደሆነ እርስዎም ሆኑ የቦርዱ ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜያት ማብራሪያ ሰጥታችኋል፡፡ ይሁንና አንዱ የመራጮች ሥጋት ይኼ ውሳኔ የአካባቢዎቹ ነዋሪ ያሆኑ መራጮች ከሌላ ሥፍራ መጥተው ድምፅ እንዲሰጡ በር ይከፍታ የሚል ነው፡፡ ይኼ ሊሆን እንደሚችል እርስዎም በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫዎት ላይ አመላክተዋል፡፡ ሆኖም ይኼንን ለመከላከል የያዛችሁት መፍትሔ ምንድነው?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- በመጀመርያ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ያልኩትን በትክክል በማስቀመጥ ልጀምር፡፡ ይመስለኛል ልትል የፈለግከው ደግሞ ለመምረጥ የሚፈልግ ሰው በማንኛውም ጊዜ ይኖራል ያልኩትን ሐሳብ ነው። ልክ ነው የምርጫ ወንጀል ለመፈጸም የሚፈልግ ሰው ከዚህ በፊት በነበሩ ምርጫዎች፣ በመጪው ምርጫና ወደፊት በሚኖሩ ምርጫዎችም ይኖራል። የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ምርጫዎች በተመሳሳይ ቀን ቢደረጉም፣ አጭበርብሮ ለመሳተፍ የሚፈልግ ሰው ሁሌ መኖሩ አይቀርም። ስለዚህ ሰዎች አጭበርብረው በድጋሚ እንዳይመርጡ የሚደረጉበትን መንገድ ምንድነው የሚለውን ብናይ ጥሩ ነው። አንደኛ አንድ ሰው ድምፅ ለመስጠት ብቁ ለመሆን መመዝገብ አለበት፡፡ በምዝገባው ወቅት ነዋሪነቱን የሚያረጋግጥና ማንነቱን የሚያሳይ ሰነድ አሳይቶ ይመዘገባል፡፡ በምዝገባው ወቅት ቀሪና በራሪ (ለመራጩ የሚሰጥ) ያለው የድምፅ መስጫ ካርድ ይወስዳል፡፡ እያንዳንዱ መራጭ የራሱ ልዩ ቁጥር ያለው ሲሆን፣ ያ ቁጥር በምርጫ ጣቢያው ያለው ቀሪ ላይና መራጩ የሚወስደው ካርድም ላይ ይገኛል፡፡ የካርዱም ዓይነት ለማጭበርበርና አስመስሎ ለመሥራት የማያስችል ነው። በእኛም በኩል የተመዘገቡ መራጮች በየምርጫ ጣቢያው ይህንን መሥፈርት አሟልተዋል ወይ? የሚል የኦዲት ሥርዓት አለን። ከእኛ ወጣ ስትል ደሞ ፓርቲዎች በምርጫ ጣቢያው በወኪሎቻቸውና ዕጩዎችም በወኪሎቻቸው አማካይነት በመገኘት ሒደቱን መታዘብ ይችላሉ። ምርጫ ጣቢያውም ለአገር አቀፍ ታዛቢዎችና ለሚዲያዎች ክፍት ነው። ከዚህም በላይ የመራጮች ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ መዝገቡ ለሕዝብ ይፋ የሚሆንባቸው አሥር ቀናት አሉ። በዚህ ወቅት ጥርጣሬ አለኝ የሚል አካል እዚያው ቅሬታውን ማቅረብ ይችላል። ይህንን ሁሉ ሒደት አልፎ የምርጫ ቀን መራጩ/ጯ ራሳቸው ናቸው ወይ? የሚለውን አጣርተው ነው ድምፅ እንዲሰጥ የሚያደርጉት። እነዚህ ሁሉ መጠበቂያዎች ሒደቱን በተሻለ ሀቀኝነት እንዲከናወን የሚያደርጉ ናቸው። እንግዲህ ይህ ሆኖ እያለ በዚህ ሁሉ ሒደት ለማለፍ ብሎ አንድ ሰው ሁለት ማንነት ፈጥሬ ልሳተፍ ካለ ወንጀል ነው። ወንጀል ደግሞ በማንኛውም ምርጫ ወቅት ሊፈጠር የሚችል ነገር ነው። ሥጋት ያላቸው ፓርቲዎች ሒደቱን በሚገባ እንዲከታተሉና ወኪሎቻቸውን እንዲያሠማሩ እንፈልጋለን። እኛም በሥራችን የምርጫውን ትክክለኝነት የሚያዛባ ሥራ ሠርተን ከተገኘን ማሻሻያ እንድናደርግ፣ ተጠያቂም እንድንሆን እንፈልጋለን።
ሪፖርተር፡– ከምርጫው ጎን ለጎን በአምስት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ የሚደረግ ሕዝበ ውሳኔ አለ፡፡ ይሁንና ይኼንን ሕዝበ ውሳኔ በማስታከክ በአንዳንድ ዞኖች ብልፅግናን ካልመረጣችሁ ክልል አትሆኑም እያሉ የሚቀሰቅሱ ሰዎች እንዳሉ ጥቆማዎች አሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ቦርዱ ለሀብት ቁጠባ ሲል ሁለቱ ምርጫዎች በአንድ እንዲደረጉ መወሰኑ የፈጠረው ክፍተት አይደለም ይላሉ?
ወ/ሪት ብርቱካን፡- ይኼ ጥያቄ ምን ማለትህ መሰለህ? ሕዝቡ የሚፈልገውንና የሚሆነውን አያውቅም ማለትህ ነው አይደል? አሁን ያነሳኸው ጥያቄው እንኳን ምክንያትና ውጤት (Cause and Effect) ቀርቶ ትስስር (Correlation) የለውም። ድምፅ ሰጪዎች በአሉባልታና በመሳሰሉት ነገሮች ተታለው የሚፈልጉትን ሳይመርጡ ይቀራሉ ማለት ነው። ይኼ የመራጮችን ባህሪ በትክክል የሚወክል አይመስለኝም። መራጮች የሚፈልጉት ያውቃሉ፡፡ ሒደቱ በሥርዓት የሚከናወን ከሆነ ድምፃቸው በትክክል እንደሚቆጠር ካመኑ አንተ ያልካቸው ጥቆማዎች (ካሉ) በላይ ፍላጎታቸውን በምርጫ ያሳያሉ ብዬ ነው የማምነው። ለምሳሌ እገሌን ካልመረጣችሁ ፀሐይ መውጣት ታቆማለች ቢባል መራጮች ያምናሉ? (ሳቅ) ሕዝበ ውሳኔውና ምርጫው በተለያየ ጊዜ ቢደረግስ የፖለቲካ ኃይሎች የሕዝበ ውሳኔን ዓይነትና የፓለቲካውን ሁነት ተጠቅመው ድጋፍ ለማሰባሰብ መሞከራቸው ይቀራል? በአጭሩ የመራጮችን ባህሪ በአጠቃላይ ካልገመገምነው በስተቀር፣ ያልከው ክፍተትና ሥጋት የእኛ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም። (ብሩክ አብዱ – ሪፖርተር-28 March 2021)
Tesfa says
በሃበሻው ምድር እውነት ከጠፋች ዘመን አለፈ። ትላንት አሳሬና ገራፊ የነበረው ነፍሴ አውጪኝ ሲል ሌላው ከዚሁ አጥፊ ቡድን የክፋት ኮሮጆ ያመለጠው የዶ/ር አብይ የኦሮሞ ስብስብ ደግሞ ጊዜው የእኛ ነው ይሉናል። አታድርስ ነው። የውስልትና ፓለቲካ የድላ ቅብብሎሽ ይሉሃል ይሄ ነው። ልክ እንደ በፊቱም እንዲያውም በከፋ ሁኔታ ማለት ይቻላል ሰዎች እንደ አውሬ በራሳቸው ዜጋና በተላላኪዎች ተንኮል በየቀኑ እያለቁ ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ተገለውና ተጥለው የሚገኙ አስከሬኖች ስፍር ቁጥር የላቸውም። ችግሩ ገዳዪ ራሱ መርማሪ መሆኑ ነው። ዶ/ር አብይ ምላሱ ብቻ እንደ ቀረ ማንም ሰው በግልጽ ማየት ይችላል። ረጅም ንግግርና ዲስኩር ምንም የሰላምና የጸጥታ ፍትህ ለህዝባችን አላመጣም። ትላንትም ነፍሴ አውጭኝ ዛሬም ነፍሴ አውጭኝ፤ ያኔም ስደት፤ ዛሬም ስደት፡ ዛሬም ልመና ያኔም ምጽዋተኛ የቱ ላይ ነው የብልጽግናው ከፍታ?
እህቱን ለባእዳ የሚሸጥ፤ ለገንዘብ የነፍሰ ጡር ሆድ ቀዶ አማራ አይወለድም በዚህ ምድር ብሎ አውጥቶ በመጣል እናትን የሚያርድ የጅምላ አሳቢና የዘር ፓለቲከኛ ምንም ስሙን ቢቀይሩት፤ ነገርየውን ቅቤ ቢቀቡት የኦሮሞ ስብስቦች ሰውን ከማረድ አይመለሱም። አሁን በምድሪቱ ላይ የምናየው ይህን ነው። በወለጋ፤ በስሜን ሽዋ በሃረር ወዘተ ልክ እንደ ወያኔ የኦሮሞ ጠበንጃ አንጋቾች ሰውን ያሰቃያሉ፤ ይገላሉ፤ ያፈናቅላሉ። ዝምታው እስከ መቼ ነው? የሚታወቅ ነገር የለም። የሚያሳዝነው ግን ያው እንደ ተለመደው የአማራ ህዝብ ተጠሪዎች ነን የሚሉትም ቆፍጠን ብለው ህዝባችውን ከገዳዪች መታደግ አለመቻላቸው ነው። ችግሩ ውስብስብ ነው። ኦነጎች አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠው ነው ሰው የሚያጫርሱት። ኦነግ ሸኔ በቀጥታ ከእነርሱ ነው ትዕዛዝ የሚቀበለው። የገንዘብ ድጎማው ከውጭ ካሉ አክራሪ የኦሮሞ ተወላጆች፤ የአረብ ሃገራት፤ እንዲሁም በሃገር ውስጥ በሚስጢር በተገመደ ውጥንቅጥ የኦሮሞ አሰራር በመዋጮ የተሰበሰበ ነው። የሚገርመው ለዚህ ሰው አራጅ ቡድን ትጥቅና ስንቅ የሚያቀብሉትም በመከላከያው ውስጥ ያሉ የኦሮሞ ከፍተኛ መኮንኖችና የሲቪል ሰራተኞች ናቸው። ምድሪቱ አዙሪት ውስጥ ገብታለች። ሰው በሰውነቱ መፈረጅ ቀርቷል። ወንዝ በማያሻገር ቋንቋ ተከፋፍሎ ይቧቀሳል። የተከመረ የእህል ክምር አቃጥሎ ተራብኩ ይላል። ልቡ የሸፈተ ሌላውንም ያሸፈተ፤ ሃገርና ወገኑን የሸጠና የሚሸጥ ሰው እንደ ተባይ የበዛበት ምድር ሆኗል። የኦሮሞ የፓለቲካ ጡሩንበኞች ባያውቁት ነው እንጂ ኦሮሚያን መስርተው አንድ ቀን በሰላም አያድሩም። እርስ በእርሳቸው ነው የሚተራረድት። እብዶች የራሳቸውን ቤት አቃጥለው እሳት አደጋ ይጠራሉ። እየሆነ ያለው ይህ ነው። 60 ዓመት ሙሉ ፓለቲካ ሲያኝኩ የኖሩ የሃበሻ የዘርና የጎሳ ፓለቲከኞች ዛሬ ሰካራም የረገጠው ጣሳ መስለው እንኳን ክፋታቸው ከልባቸው አለ። የሙቶች ፓለቲካ እንደዚህ ነው። ሁሌ ንዝንዝ። ፍሬ የለሽ።
አሁን በአለም ሚዲያና በሃገር ቤት የኤርትራ ጦር የትግራይን ህዝብ በድሎ ገለ መሌ ሲሉ ግርም ይለኛል። ሃገሩ በሮኬት ስትደበደብ ዝም የሚል መንግስት አለ? ያ ሮኬት ኤርትራ ምድር ላይ ያደረሰውን ጉዳት ሰው ያውቃል? ግን የነጭ የአዞ እንባ አንቢዎችና ስመ የትግራይ ህዝብ ሰላም ፈላጊዎች ላንድ እሳት ለሌላው ነዳጅ እየሰጡ ሲያጫርሱን እልፍ ዘመን ተቆጥሯል። አሁንም የሚያደርጉት የተራዶ ድርጅት ስራም ሆነ ሌላው ለትግራይ ህዝብ ታስቦ ሳይሆን እየሰረቁ ያበሏቸው የነበሩትን ወያኔዎች አይዞአችሁ ለማለት ነው የሚንጋጉት። የትግራይ ህዝብ ያኔ ወያኔም እያለ እኮ የመከራ እህል እየተሰፈረለት የኖረ ህዝብ ነው። የሚጠጣው ውሃ አጥቶ ቀኑን ሙሉ ስልፍ ነበር እኮ የሚውለው። የነጻነት መለኪያው የአንዲት ሃገር ሰንደቅ በከፍታ ላይ መውለብለቡ ብቻ አይደለም። ህዝቦቿ እንዴት ይኖራሉ ብሎ መልስ ማግኘት አስፈላጊ ነው። ዛሬ እንደ ቅጠል የሚረግፉት የትግራይ ልጆች ማንን ከሞት ለማትረፍ ነው። እናስብልሃለን እየተባሉ የኖሩ ስለሆነ በራሳቸው ለማሰብ የነበራቸውን ችሎታ ተቀምተዋል። ለዚያ ነው እየገቡ የሚያልቁት እንጂ እኔ ጌታቸው ረዳንም ሆነ ደብረጽዪንን ካሉበት መገደል ያለባችው ጭራቆች ናቸው። ለእነርሱ ዘብ አይቆምም። የስንቶችን ህይወት አጥፍተዋል? ቤቱ ይቁጠረው።
ስለሆነም አሁን ምርጫ ተብሎ ሃተፍ ተፍ መባሉ ወሬ ነው። እየተካሰሱ/ድንበሬ አትምጣ/ክልሌ ውጣ/የሚሉ የቁም ሙታኖች ባሉበት ምድር ፍትሃዊ ምርጫ ይኖራል ብሎ ማመን ተንጋሎ መትፋት ነው። የምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባም ሆነ ሌላ ነገር እንዳያደርጉ የዘርና የክልል ፓለቲከኞች ተግተው ይሰራሉ። የታወቁት የቆመን በማፍረስ ነው። ትላንት የታሰረው ዛሬም እስር ቤት ከገባ፤ ትላንት የገደለውና ያሰረው ስሙን ቀይሮ በዘሩ ተሰልፎ የፓለቲካ አሳላፊ ከሆነ ለሃገርና ለወገን የሞቱትና የታሰሩት የት ይውደቁ? መልሱ የትም ነው። ያው እንደ ወያኔ የኦሮሞ ጠባቦችም ከተፈናጠጡበት የከፍታ ወንበር ላይ ወድቀው እስኪፈጠፈጡ ጠብቆ ማየት ነው። እስከዚያው ግድያው፤ እስሩ፤ ግርፋቱ፤ ማጭበርበሩ፤ የአፓርታይድ አገዛዙ፤ የአማራ ህዝብ ሰቆቃ ይቀጥላል። ይህ ትንቢት አይደለም። በምድሪቱ ላይ ያለ የዋይታና የእሪታ ጭኾት ነው። የዘር ፓለቲካ፤ የክልል ፓለቲካ ለሙታኖች። አንድ ሃገር አንድ ህዝብ። ሌላው ሁሉ የደንቆሮ ለቅሶ ነው። በቃኝ!