
በሰሜን ኢትዮጵያ ከትህነግ (የትግራይ ነጻ አውጪ ግምባር) ጋር በተደረገው ጦርነት በተወሰነ መልኩ በጦር መሣሪያ በተለይ ግን በሰው ኃይል አብላጫውን ይዞ የነበረው ትህነግ ቢሆንም ጦርነቱ ለኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት እንደገና መጠናከር ብዙ ትምህርት ጥሎ ያለፈ ነበር። ከጦርነቱ በኋላ መከላከያ በሰው ኃይልም ሆነ በመሣሪያ በፍጥነት የሄደበት መንገድ ተጠቃሽ ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ስንገዛቸው የነበሩ የጦር መሣሪዎችን ማምረት ጀምረናል ማለታቸው የሚዘነጋ አይደለም። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነውም በየጊዜው በመከላከያ ሚኒስቴር ሥር በተለያዩ ክፍሎች ከተተኳሽ ጀምሮ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችና ተሸከርካሪዎች በአገር ውስጥ በልዩ ሁኔታ እየተመረቱ እንደሆነ የሚወጡ መረጃዎች በመጠቆማቸው ነው። ይህ በአየር ኃይል በኩል እየተደረገ ያለውን ፈጣን ለውጥ ሳይጨምር ነው።
አሁን ባለው አካሄድ ኢትዮጵያ በቅርቡ የሚሊታሪ ድሮኖችን እንደምታመርት ጠቋሚ መረጃዎች አሉ። በተለይ አገር በቀል ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ድሮን በማምረት ረገድ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ደቡብ አፍሪካና ኬኒያ ዋንኞቹ እንደሆኑ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ምንጮች ይናገራሉ። የምስራቅ አፍሪካ ቁንጮዎቹ ኢትዮጵያና ኬኒያ እንደሆኑ የጠቆመው መረጃው የሁለቱም አገራት ኢንጂኔሮች ከቱርክ ኢንጂኔሮች ጋር በመሆን ድሮኖቹን በአገር በቀል ቴክኖሎጂ እየቀየሩ እንደሆነ ጠቅሷል። ይህም በቅርቡ ኢትዮጵያም ሆነች ኬኒያ የቴክኖሎጂው ባለቤት እንደሚሆኑ ይጠበቃል። በኢትዮጵያ ምርት የአፍሪካን ገበያ መቆጣጠር በሚለው ስትራቴጂ ደግሞ ቴክኖሎጂው ሰፊውን የአፍሪካ ገበያ በራዳሩ ውስጥ የሚያስገባ እንደሚሆን ይገመታል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በተለይም አየር ኃይል ከስድስት ዓመት በፊት እንኳን በዚህ ደረጃ በቴክኖሎጂ የረቀቀ ምጥቀት ላይ ሊደርስ ይቅርና “ለኢትዮጵያ አየር ኃይል አያስፈልጋትም” በሚለው የትግነጉ መሪ መለስ ዜናዊ አገር አውዳሚ እሳቤ ግቢው ሳር በቅሎበትና የከብቶች ግጦሽ ቦታ ሆኖ ነበር። አየር ኃይሉ በተለይ ከግብፅና ግብፅ ከምትልካቸው የቀጣናው ጠብ ጫሪዎች የሚመጣውን ትንኮሳ በፍጥነት የመመከትና ድባቅ የመምታት ብቃቱን አስተማማኝ ደረጃ ላይ ከማድረስ አኳያ ከአፍሪካ ቀንድ ባለፈ የመካከለኛው ምስራቅና ካውኬዢያ (ምስራቅ አውሮጳና ምዕራብ ኤዢያን) የሚያካትተውን ጂኦፖለቲካ የቃኘ እንደሆነ ይስተዋላል። በዚህ የጂኦፖለቲካ ማዕቀፍ ውስጥ ዋነኛ ተጠቃሽ አገር ደግሞ አዘርባጃን ነች።
የቀድሞ ሶቪየት ኅብረት አካል የነበረችው አዘርባጃን አነስተኛና ብዙም ትኩረት የማይሰጣት አገር ብትሆንም አሁን ላይ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ አፍሪካ ቀንድ ባሉት አገራት ዘንድ የጂኦፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪ በመሆን እየታየች ነው። ከአዘርባጃን ደቡብ የምትገኘው ወሳኝ አጎራባች አገር ኢራን የዚህ መልከዓምድር “በጥባጭ” ተብላ የምትወነጀል ሲሆን በአካባቢው የኃይል አሰላለፍ የአዘርባጃን አስፈላጊነትም ከኢራን ጋር ካላት ጉርብትና የሚታይ ነው።
በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉ ቡድኖች በመካከለኛው ምስራቅ በተለይም በየመን፣ በሊባኖስ፣ በሶሪያ፣ በፍልስጤምና በኢራቅ የውክልና (proxy) ጥቃትና ውድመት ሲያደርሱ ከኢራን በስተሰሜን የምትገኘው አዘርባጃን በዚህ ልክ ሳትደፈር ከመቆየት ባለፈ እየበለፀገች ለመሆኗ ምክንያት ከእስራኤል ጋር የጠበቀ ግንኙነት በመመሥረቷ ነው። ይህ ወዳጅነት ሠላሳ ዓመታት ያስቆጠረና እስራኤልንም በብዙ መልኩ የጠቀመ ነው።
አዘርባጃን ከእስራኤል ጋር ያላት ግንኙነት ከኢራን በኩል በርካታ ቀጥተኛ ዛቻዎችና አንዳንዴም የውክልና ጥቃቶች እንዲደርስባት ያደረገ ነው። ከዚህም ሌላ፤ እስራኤልን ከማጥቃት አዘርባጃንን በቀጥታ ማጥቃት የተሻለ ነው የሚል ንግግር ከኢራን በኩል የተሰማበትም ሁኔታ አለ። ለምሳሌ የሐማስ መሪ የነበሩት ኢስማኤል ሐኒያ በተገደሉበት ጊዜ የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ እስራኤልን በቀጥታ ከማጥቃት አዘርባጃንን ዒላማ ማድረግ ይገባል ብለው ነበር።
በሌላ በኩል አዘርባጃንን በስተደቡብ ምዕራብ የምታዋስናትን አርሜኒያን በመጠቀም ኢራን አዘርባጃንን አጥቅታለች። ለምሳሌ አርሜኒያና አዘርባጃን ደም በተቃቡበት የናጎሮ ካራባህ የድንበር ጦርነት ኢራን ለአርሜኒያ ቀጥተኛ ድጋፍ በማድረግ አዘርባጃንን ያቆሰለ ተግባር ፈጽማለች። በዚህ ጦርነት አዘርባጃን በአሸናፊነት እንድትወጣ በማድረግ በኩል እስራኤል ከፍተኛውን ሚና ተጫውታለች።
አዘርባጃን ከሶቪየት ኅብረት ከወጣች በኋላ ነጻ አገር ሆና ስትቋቋም ወዲያው ዕውቅና ከሰጧት አገራት መካከል አንደኛዋ እስራኤል ነች። አዘርባጃን ከኢራን ጋር ለዘመናት ለቆየው የድንበር ግጭት መሢሕ ትሆነኛለች ብላ የተማመነችው በእስራኤል ሲሆን በዚያን ጊዜ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት የዚያን ጊዜውን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ይትዛቅ ራቢንን ከኢራን ታደጉን ብለው ላቀረቡት ጥያቄ ራቢን ቃል ገብተው ነበር፤ እስካሁንም ድረስ አዘርባጃን ከእስራኤልን የጸጥታና የደኅንነት ብቃትና ልምድ ተጠቃሚ ስትሆን ቆይታለች።
ነዳጅ አዘርባጃን ለእስራኤል በዋነኛነት የምታቀርበው የውለታ ማስጠበቂያ ሸቀጥ ሲሆን እስራኤል ደግሞ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት የጦር መሣሪያና የሚሊታሪ ቴክኖሎጂ ለአዘርባጃን ታቀርባለች። እስራኤል ወደ አገሯ ከምታስገባው ነዳጅ 55 በመቶው ከአዘርባጃን የሚመጣ ነው፤ አዘርባጃን ወደ አገሯ ከምታስገባው የጦር መሣሪያ 69 በመቶው ከእስራኤል የሚመጣ ነው። በናጎሮ ካራባህ ጦርነት አዘርባጃንን አሸናፊ እንድትሆን ያደረጋትን ድጋፍ ያደረገችው እስራኤል ሲሆን የቱርክ ድጋፍም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በዚያኛው ወገን አርሜኒያንን በጦር መሣሪያ ስትደግፍ የነበረችው ራሺያ ነበረች።
አርባጃን ካላት የጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታና ኃያላኑ የሚፋጠጡባት የፖለቲካ ዐውድማ ከመሆኗ አንጻር አሜሪካ ከአዘርባጃን ጋር ጠንካራ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት እንድትመሠርት በአሜሪካ የሚገኙ ይሁዲዎች ግፊት እያደረጉ ነው። በተለይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የእስራኤል ወዳጅ እንደመሆናቸው አሜሪካ ከአዘርባጃን ጋር በምትመሠርተው ግንኙነት ኢራንን ቀለበት ውስጥ ማስገባት ትችላለች፤ በአዘርባጃን በኩል በማዕከላዊ ኤዢያ አገራት ጠንካራ መልሕቅ መጣል የሚያስችል ይሆናል፤ በተለይ የማዕከላዊ ኤዢያ አገራት በማዕድናት የበለጸጉ በመሆናቸው አሜሪካንን በእጅጉ ተጠቃሚ ያደርጋታል የሚል ማሳመኛ የአሜሪካ ይሁዲዎች በማቅረብ እስራኤልን ለመጥቀም እየወተወቱ ይገኛሉ።
ኢራን በቀጥታ የማታገኛትን አዘርባጃንን በውክልና በኤርትራ በኩል ለማግኘት እየጣረች እንደሆነ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ኤርትራም ይህ ግንኙነቷ ዋጋ የሚያስከፍላት ከሆነ ለዘመናት የኢራን ወዳጅ በመሆኗ የምትከፍለው መስዋዕትነት እንደሆነ አድርጋ የወሰደችው ይመስላል።
ባለፈው ዓመት የኢራን ፕሬዚዳንት በመሆን ማሱድ ፔዜሽኪያን ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ መሐመድ ተገኝተው ነበር። በኤርትራ መገኘት የተደሰቱት አዲሱ የኢራን ፕሬዚዳንት ማሱድ “የኢራን እስላማዊ ሪፑብሊክ ያላትን ልምድ ለኤርትራ ለማስተላለፍና ብቃቷንም ለማጋራት ዝግጁ ነች” በማለት ነበር የገለጹት።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር ከመቼውም የበለጠ ግንኙነት እያደረገች ትገኛለች። የሁለቱ አገራት ግንኙነት የተጀመረው እኤአ በ1992 ዓም ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሁለቱ አገራት እጅግ የጠበቀ ወዳጅነት እንደመሠረቱ የተለያዩ ኩነቶች ያስረዳሉ።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን አስከትለው በአዘርባጃን ኢፊሴላዊ ጉብኝት አድርገዋል። በዋንኛነት የተጠቀሰው የዲጂታል ሥርዓትን ከአዘርባጃኑ ASAN፡ Azerbaijan Service and Assessment Network ለመማርና በኢትዮጵያ ለመተግበር ነው።
ባለፈው ኅዳር 5 (Nov 14, 2024) የኮፕ29 (COP29 የአካባቢ ጥበቃ ዓለምአቀፋዊ ስብሰባ) በአዘርባጃን ሲካሄድ በሥፍራው የተገኙት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከአዘርባጃኑ ፕሬዚዳንት ኢልሃም አሊዬቭ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደው ነበር። በውይይቱ የASAN አሠራር ወደ ኢትዮጵያ ስለማምጣት እንዲሁም በዓለምአቀፍ ድርጅቶች፣ በታዳሽ ኃይል፣ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ የተገለጸ ነበር። ከዚህ ውጪ ግን ውይይቱን ለየት ያደረገው ጉዳይ ወደ አቡ ዳቢ ይጓዙ የነበሩ ሦስት የአዘርባጃን መርከቦችን ኤርትራ ካገተች ከሰባት ቀን በኋላ መሆኑ ነው።
ከአንድ ወር በፊት የአዘርባጃኑ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያልቺን ራፊዬቭ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ሲሆን የጉብኝታቸውም ዋና ዓላማ የኢትዮ-አዘርባጃንን ሦስተኛውን የፖለቲካ ምክክር ከሚኒስትር ደኤታ ምስጋኑ አረጋ ጋር በመሆን ለመምራት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ራፊዬቭ ከሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ ከካቢኔ ሚኒስትሮች ጽ/ቤት ኃላፊዋ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ፣ ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት አካሂደዋል። እስካሁን በተደረጉት ውይይቶች ከአዘርባጃን በኩል የሚሰማው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን የጎላ የበላይነት ተጠቃሚ የመሆን ነው።
በያዝነው ዓመት (2017) ጥቅምት 28 (November 7, 2024) የካስፒያን የባሕር አገልግሎት የሚያሠራቸው ሦስት የአዘርባጃን መርከቦች (CMS Pehlеvan, CMS Igid, and CMS-3 vessels) የስዊዝ ካናልን አልፈው የአዘርባጃንን ሠንደቅ እያውለበለቡ ወደ አቡ ዳቢ (የተባበሩት አረብ ኤምሬት) ሊሄዱ ሲሉ ቀይ ባሕር ላይ በኤርትራ ቁጥጥር ሥር ውለዋል። መርከቦቹ ባጋጠማቸው የአየር መበላሸት ምክንያት ነበር ወደ ኤርትራ የባሕር ወሰን የገቡት ተብሎ ነው የተነገረው።
ከአዘርባጃን በኩል የወጣው ኦፊሴሊያዊ ሰነድ እንደሚያመለክተው መርከቦቹ የሚያልፉበት መንገድ አደገኛ የባሕር ዘራፊዎች (ፓይሬትስ) ያሉበት በመሆኑና መስመሩ ለደኅንነታቸው አደገኛ እንደሆነ ስለተነገራቸው ደኅንነታቸው የሚጠበቅበትን መስመር መምረጥ ግድ ሆኖባቸዋል። በዚህ ወቅት በኤርትራ የባሕር መስመር ሲያልፉ በተፈጠረ የአየር መዛባት መስመሩን ጥሰው እንዲገቡ ወደ መገደድ ሲደርሱ VHF-16 channel የተባለውን ዓለምአቀፍ የግንኙነት መንገድ በመጠቀም ወደ ኤርትራ ጥሪ ቢያስተላልፉም ምንም ምላሽ አላገኙም።

ይፋ የሆነው ሰነድ እንደሚያመለክተው ወደ ኤርትራ ወሰን መግባት የተገደዱት መርከቦች “ሐሙስ ጥቅምት 28 ወደ 10፡06 አካባቢ የኤርትራ ባሕር ኃይል 13°23′ North Latitude and 042°39′ East Longitude መገናኛ ላይ (ወደ አሰብ አካባቢ) ሦስቱንም መርከቦች በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል። ከኤርትራ የተሰጠው ምክንያት መርከቦቹ አቅጣጫቸውን ቀይረው በኤርትራ ባሕር ኃይል የተሰመረውን መስመር በማለፋቸው ነው” የሚል ነው። ባሕር ኃይል የተባለው ከመርከቦቹ ለቀረበለት ጥሪ ለምን ምላሽ እንዳልሰጠ ምንም ያለው ነገር የለም። በመርከቦቹ ውስጥ 18 የመርከቡ ሠራተኛ የአዘርባጃን ተወላጆች፣ 6 ደግሞ የሌላ አገራት ተወላጆች በድምሩ 24 ሰዎች እንዳሉ ሰነዱ ያብራራል።
የዛሬ 25 ዓመት ገደማ አዘርባጃን የናጎሮ ካራባህን ግዛት በተመለከተ ከአርሜኒያ ጋር ጦርነት በገጠመችበት ወቅት በስድስት ሳምንት (44 ቀናት) ጦርነቱ በአዘርባጃን ድል አድራጊነት እንዲጠናቀቅ ያደረገው ዋነኛው ነገር የወታደራዊ ድሮን ቴክኖሎጂ እንደሆነ ይነገራል። በወቅቱ አርሜኒያ ሩሲያ ሠራሽ ድሮኖች የተጠቀመች ሲሆን አዘርባጃን ግን ከእስራኤልና ከቱርክ ያገኘቻቸውን ድሮኖች በማጣመር ተጠቅማ የአየር የበላይነት ሊኖራት ችሏል። የአዘርባጃን ድሮኖች ዒላማ በመለየትና በማጥቃት፣ በመከታተል፣ በመግደል ወዘተ ልዩ ብቃት እንደነበራቸው የስትራቴጂክና የዓለምአቀፍ ጥናት ማዕከል ሰነድ ያብራራል።
ከእስራኤል በቢሊዮን የሚቆጠር የጦር መሣሪያና የሚሊታሪ ቴክኖሎጂ ድጋፍ የምታገኘው አዘርባጃን ባለፈው ዓመት አንድ ትልቅ የድሮን ማሠልጠኛና መጠገኛ ተቋም ከፍታለች። ቱርክ ሠራሽ Akinci drone ድሮኖ ጋር በተያያዘ የተሠራው ተቋም የአዘርባጃን ወታደራዊ ዓቅም እጅግ ከፍ የሚያደርግና ከድሮን ጋር በተያያዘ ከውጭ የምታስመጣውን በአገር ውስጥ ቴክኖሎጂ ለመለወጥ ታስቦ የተደረገ መሆኑ የወጡ ዘገባዎች ይጠቁማሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ እኤአ በ2028 የአዘርባጃን የመከላከያ በጀት 4 ቢሊዮን ዶላር (ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ) ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሜሪካ የሚገኙ ተጽዕኖ ፈጣሪ ይሁዲዎች ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ምክንያት በማድረግ አሜሪካ ከአዘርባጃን ጋር ግንኙነት ብትፈጥር በእጅጉ ትጠቀማለች እያሉ መወትወት ከጀመሩ ቆይተዋል። በተለይ አዘርባጃን ከእስራኤል ጋር የመሠረተችው የጠበቀ ግንኙነትና የእስራኤል “ምርጥ ወዳጆች” ከሚባሉ ሙስሊም አገራት መካከል አንዷ መሆኑ ለአሜሪካ መደላድሉ የተሠራ ነው ይላሉ። ስለዚህ ጥሩ ግንኙነት መጀመሪያ “በአብርሃም ስምምነት” አዘርባጃንም እንድትካተት በማድረግ እንደሆነ ይጠቁማሉ።
“የአብርሃም ስምምነት” (Abraham Accords) የሚባለው በአሜሪካ አደራዳሪነት እስራኤል ከአረብ አገራት ጋር ነገሮችን የማርገብና መሬት የማውረድ ስምምነት ነው። ይህም እኤአ በ2020 ዓም በኋይት ሐውስ እስራኤል ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ከባሕሬይን ጋር የተስማማችው ነው። በቀጣይ ሞሮኮና ሱዳን ሌሎች ፈራሚ አገራት ሆነዋል።
ይህንን እንደ መነሻ የሚጠቅሱት አሜሪካዊ ይሁዲዎች ይኸው የአብርሃም ስምምነት ለአዘርባጃን፣ ለካዛክስታን እና ለዑዝቤክስታን በተለይ ግን የእስራኤል ምርጥ ወዳጆች ለተባሉት ለሁለቱ አገራት መዘርጋት አለበት፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ተመልሰው ወደ መሪነት የመጡበትን ዕድል መጠቀም አለባቸው፤ ይህም ዞሮ ዞሮ የእስራኤል ወዳጅ አገራትን በመጠቀም አሜሪካንን በአካባቢው የበላይነት እንዲኖራት፣ ኢራንን በቅርብ ርቀት እንድትከታተል፣ አሜሪካንን በነዳጅና በሌሎች የኢኮኖሚ ጉዳዮች በብዙ እንድትጠቀም የሚያስችላት ነው የሚል መሟገቻ ሀሳብ ከሚያቀርቡት ቀዳሚው የመካከለኛው ምስራቅ ኤክስፐርት የሆኑት ጆሴፍ ኤፕስቲን ናቸው።
እንግዲህ ኤርትራ መርከብ አግታ እሰጥ አገባ ውስጥ የገባችው ከዚህች አገር አዘርባጃን ጋር ነው። ከኢትዮጵያ ጋር እጅግ የጠነከረ ወዳጅነት የመሠረተችው አዘርባጃን በእስራኤል በጥብቅ ከመደገፏ አንጻር የኢራን ወዳጅ የሆነችው ኤርትራ የያዘችው ዓቋም ዋጋ የሚያስከፍላት ሊሆን ይችላል።
በቅርቡ የእስራኤል ታዋቂ ጋዜጣ (ሐሬትዝ) ላይ ኤርትራ ከኢራን ጋር ገጥማ በእስራኤልና በአሜሪካ ጥቅም ላይ ያነጣጠረ ተግባር ላይ መሰማራቷን የሚገልጽ ትንታኔ ማተሙ አይዘነጋም። ከዚህም ባሻገር ኤርትራን ከሰላሳ ዓመት በላይ የተቆጣጠረው የኢሳያስ አፈወርቅ አገዛዝ የሽብር ቡድኖችን በውክልና በማሰለጥንና በማስታጠቅ ከነበረው የቀደሞ ታሪክ አንጻር አሁን የአዘርባጃንን መርከቦችና መርከበኞች ከነጭነታቸው ማገቱ ሸምቀቆውን እንደሚያጠብቅ ይገመታል።
ይህ አጋጣሚ በተደጋጋሚ በኢሳያስ አፈወርቅ ሤራና የውክልና ደባ ሰለባ ለሆነችው፣ ለዚህም ብዙ ዋጋ ስትከፍል ለኖረችውና ሕጋዊ ወደቧን ለተዘረፈችው ኢትዮጵያ እንደ ልዩ አጋጣሚ እየታየ ነው። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ “በአፍሪካ ቀንድ ሌላ ግጭት እንዳይከሰት ለማድረግ አሁን እርምጃ መውሰድ ይገባል” (To avoid another conflict in the Horn of Africa, now is the time to act) በሚል ርዕስ በአልጀዚራ ላይ በታተመው ሰፊ ጽሑፍ በኤርትራ ላይ እርምጃ የመውሰጃው ጊዜ አሁን ነው ሲሉ ለዓለም የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ፣ ለአሜሪካ፣ ለቻይናና ለአውሮጳ ኅብረት ያቀረቡት ጥሪ ከላይ የተባለውን የሚያጎላ ይሆናል።
ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ “ጦርነት ለኤርትራ የገቢ ምንጭ ነው” ባሉበት ሰፊ ማብራሪያቸው “ግጭት እዚህና እዚያ መፍጠር፣ አማጺያንን እና ገንጣዮችን መርዳት ወይም መንግሥታት ወደ ጦርነት እንዲገቡ፣ በቀጣናው መከፋፈል እንዲፈጠር ማድረግ የኤርትራ መንግሥት ለኅልውናው ሲል የሚፈጽመው ተግባር ሆኗል። … የምስራቅ አፍሪቃ ቀንድ ከታወከ መካከለኛው ምስራቅና መላው አውሮጳ የትርምሱ ዋንኛ ሰላባ ይሆናሉ። ስለዚህ ጫና ለማሳረፍ ጊዜው አሁን ነው” የሚል የዲፕሎማሲ ጫና ጥያቄ አቅርበዋል። እንደቀድሞ የኢሳያስን አገዛዝ ወደ ማዕቀብ ከርቸሌ እንዲመለስ የጠየቁበት አግባብ ዝም ብሎ የቀረበ ጥሪ እንዳልሆነም ጉዳዩን የሚከታተሉ ይገልጻሉ።
የታገቱት መርከቦች የአዘርባጃን ጉዳይ ብቻ ሳይሆኑ የእስራኤልም ናቸው። ኤርትራ ከኢራን ጋር ካላት የቀረበ ግንኙነት አንጻር በመርከቦቹ የተጫነውም ሆነ የኤርትራ ድርጊት እስራኤልን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚነካ ነው። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ካላት የሻከረ ግንኙንትም ይሁን ከኢራን ጋር ካላት ፍቅር በእነዚህ መርከቦች ላይ የምትወስደው ውሳኔ ግን ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል ይገመታል። መርከቦቹን ከመልቀቅ መዘግየቷም አንዱ ተጠቃሽ ይህ ይሆናል። መርከቦቹን በሰላም እንኳን ብትለቀቅ የፈጸመችው የባሕር ላይ ውንብድና ለአካባቢው የበለጠ የስጋት ምክንያት ያደርጋታል።
የቀጣናውንና ጂኦፖለቲካውን በጥሞና የቃኘ አካሄድ መከተል ይህ ክስተት ለኢትዮጵያ በርካታ በረከቶችን ይዞ እንዲመጣ የሚያስችል ነው። በአንድ በኩል ኤርትራ ወሳኝ የሆነውን የባብኤል መንደብ ሰርጥን በመቆጣጠር መቀጠል በቀጣናው የጦር ቤዝ ለመሠረቱ አገራት ሰላም የሚነሳ በመሆኑ ትኩረት እንዲሰጥበት ኃያላኑን የማሳሰብና ወደ ውሳኔ የማድረስ ሥራ ነው። ሌላው ኤርትራ ከኢራን ጋር ያላት ግንኙነት ከባሕር መንገዱ አልፎ ኢራን ጠላት የምትላቸውን አገራት በእጅ አዙር የምታጠቃበት መንገድ ከፋች መሆኑን በማሳወቅ፤ ሌላና ወሳኙ ደግሞ ሰርጡን እንደ ኤርትራ ዓይነት ግጭት ቀለቡ የሆነ አገር እንዲቆጣጠረው ከመፍቀድ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ኖሯት የሰርጡ ሚዛን አስተካካይ እንድትሆን ድጋፍ ለማሰባሰቢያ መጠቀም ነው። ከሁሉ የሚልቀውና ዘላቂ የሆነው ግን ከበረሃ ውንብድና ያለ ሕዝብ ይሁንታ ከሠላሳ ዓመት በላይ በሥልጣን የቆየውን የኢሳያስ አገዛዝ ዕረፍት እንዲወስድ በአገር ውስጥ ኢሳያስ ሲወገድ የሚከሰተውን ክፍተት ሊተካ የሚችል ኃይል ከማዘጋጀት ጀምሮ በሁሉም መስክ የማሳመን ዘመቻ ለማድረግ በር ከፋች በመሆኑ ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
ትላንት በየዓለማቱ እየዞሩ የኢትዮጵያን ስም ሲያጠፉ የነበሩት ሁሉም ባይሆኑ የሚበዙትን ሞት ወስዷቸዋል። አሁን ባለቀ ጊዜ ላይ ቆመው የሚያላዝኑትም ለመቃብር ቅርብ ናቸው። 30 ዓመት ሙሉ ወንድምና እህቱን ሲገድል ኑሮ ነጻነት አወጅኩ ካለ በህውላ እግሬ አውጭኝ እያለ ከፊትና ከህዋላ እየተተኮሰበት አዲሲቷን ኤርትራ እየጣለ ባህር ገብቶ የሰመጠው፤ በርሃ ገብቶ የቀረው፤ ተሳክቶለት እስራኤል ሳይቀር መጠጊያ ያደረገው ሁሉ አሁን ላይ ወይ ሃገር የሚልበት ጊዜ ላይ ደርሷል። ግን አፍሪቃ ለህዝቦቿ መልካም ሃገር አይደለችም። ኤርትራም አፍሪቃዊቱ ሰሜን ኮሪያ ተብላ የምትጠራው ያለ ምክንያት አይደለም።
አሁን ካዛርባጃን ጋር እሰጣ ገባ የገባው ሻቢያ ያላቻ ትግል እንደገጠመ ሊረዳ በቻለ ነበር። ግን ይህ አይሆንም። በለው፤ በይው፤ ያዘው፤ ጥለፈው እያለ የኖረ ትውልድ ሚዛናዊ ሆኖ አቅምና የአካባቢን ፓለቲካ መዝኖ ነገርን መፍታት አይችልም። የሱዳን ህዝብ መከራ በራሱ በሱዳን መሪዎችና በውጭ ሃይሎች ድጋፍ እየጋመና እየፈመ እንሆ እልፎችን ጨርሷል። ዓለም ስለ ፓለስቲኒያን መራብና መቸገር ሲጠበብ 40 ሚሊዪን ረሃብተኛ ስለ ፈሰሰባት ሱዳን ግን ግድ አይሰጠውም። ምዘናው የቆዳ ቀለም ነውና! ግን እኛ አይገባንም። ቢገባንም ወንድምና እህታችን የምናሰቃይ ለነጭ ተጎብዳጅና አደግዳጊ ሆነን እየታየን ነው። መቼ ይሆን የምንነቃው? መቼ ይሆን ጦርነት በቃ የምንለው። አሁን ማን ይሙት ሻቢያ እንደገና ጦርነት ለመግጠም ክተት ማለት ነበረበት? በጭራሽ! ለዚህ ነው ወያኔና ሻቢያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው የምንለው። ወያኔ 50 ዓመት የትግራይን ህዝብ ሲገድልና ሲያስገድል በስሙ ሲነግድበት ኑሮ ዛሬ ይለይለት ብሎ በትግራይ ምድር ላይ አርሚ 24 የሚባለው እናቶችና አባቶችን ተኩሶ እንዳቆሰለና ደማቸውን እንዳፈሰሰ መረጃዎች ያስረዳሉ። ይህ ነው ለትግራይ ህዝብ ማሰብ። እኔ ያልኩትን ካልሰማችሁ አፈር እመልስባቹሃለሁ አይነት አመራር! በዚህ ሁሉ ግን የፌደራል መንግስቱ ወያኔን ቸል ማለቱ ግራ ያጋባል። የወያኔ አመራሮች ተሰብስበው ዘብጥያ መውረድ ያለባቸውና አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ሆነው በለውና በይው የሚሉ ማንኛውም የተቃዋሚ ሃይሎችን ሁሉ በኢንተርፓል እየያዙ ለፍርድ ማቅረብ ነው። ግጭትና ጦርነት ለህዝባችን በምንም መንገድ አይጠቅምም።
ወደ ሻቢያ ስንመለስ በጉኑ ካሉት ጎረቤት ሃገሮች ጋር ያልተጋጨው የለም። ሁለት ወደቦችን ይዞ ቅጭ ያለው ይህ ህልፈተ ቢስ መንግስት ለኤርትራ ህዝብም ሆነ ለጎረቤት ሃገሮች አልጠቀመም አይጠቅምም። ሲጀመር እድሜ ለወያኔ ሃገር ቆርሶ ሰጠው እንጂ ዛሬ ላይ ወደብ ለማኞች ባልሆንም ነበር። ኢትዮጵያና ኤርትራ ከልብ ሰላም ፈጥረው ስንት አበረው የሚሰሩትና የሚያድጉበት ጉዳይ እያለ ዛሬም የምናላዝነው ይህኑ ነው። ኦማን ላይ የኤርትራው ተወካይ ይዘላብድ የነበረው ኢትዮጵያን የመክሰስና የመወንጀል ጉዳይ በቅርብ ምሳሌነት ይጠቀሳል። ልክ ነው ሻቢያ የወያኔ ግባተ መሬት ተመኝቶ ነበር ያ አልሆነም። በዚህና በሌላም ጉዳዬ ጠ/ሚ አብይና ፕ/ኢሳያስ ባይግባቡ በሚያግባባቸው ነገር ላይ በማተኮር የህዝባችን ሰቆቃ ለመለወጥ በሰሩ ነበር። ያ ቀርቶ አሁን ቀረርቶ ቀረሽ ዲስኩር በዚህም በዚያም ይሰማል። ይህ ደግሞ ዳግመኛ ውርደት ነው። ጦርነት የመንግስታት ውድቀት ዋዜማ ነው። ወዪ ለእናንተ!
ጠ/ሚ አብይ የወደብ ወይም የባህር በር መውጫ ጥያቄ ማቅረቡን እንደ እብደት ያዪ አሉ። እኔ ግን የጥያቄው መነሳት ህጋዊና የዛሬው ትውልድ ባያሳካው ቀጣዪ የሚያሳካው ሃሳብ ነው ባይ ነኝ። ስለዚህ በዚህም በዚያም ጠ/ሚሩን በዚህ ዙሪያ ላይ ጥላሸት ለመቀባት የተደረገው ሙከራ ሁሉ ፉርሽና ከእውነት የራቀ ነው። ለዚህ ነበር ፈረንጆች Give credit where credit is due የሚሉት። ግን የሚሰማ ጀሮ የሚያይ አይን እያለን ሥራና ተግባርን መዝነን ስንዴን ከንክርዳድ መለየት ሲኖርብን በጥላቻ ብቻ ተሞልቶ የሰውን በጎ ሃሳብና መልካም ስራ ማጣጣል ተገቢ አይደለም።
በዓለም ላይ 44 ሃገሮች ያለ ባህር በር ሲሆኑ ከእነዚህ ሃገሮች መካከል ደግሞ ሁለት Liechtenstein and Uzbekistan በእጥፍ የታጠሩ ናቸው። 120 ሚሊዪን ህዝብ የሚርመሰመስባት ኢትዮጵያ በህጋዊ መንገድ የባህር መውጫ ማግኘቷ አይቀሬ ነው። ጊዜ ሊፈጅ ይችል ይሆናል። ግን ይሆናል። ደግሞስ መሬቱ በአፋርና በአካባቢው እየተናደ አይደል እንዴ ምን አልባት ቀይ ባህር ሰመራ ይገባና ጀልባችን ይዘን እንሸራሸር ይሆናል።
ግራም ነፈሰ ቀኝ እንዲህ አለማችን ባጋደለችበት ጊዜ ኢትዮጵያና ኤርትራ በጠላትነት መፈላለጋቸው የጠላት መፈንጫና መጠቀሚያ ለመሆን እንጂ ለህዝባችን ኢምንት የሚተርፈው ነገር የለም። ራሺያ ሃገር አቋርጣ ሱዳን ፓርት ላይ የባህር ወደብ ካገኘች፤ ቻይና፤ አሜሪካ፤ ፈረንሳይና ሌሎችም ጅቡቲን እንደ ጉንዳን ከወረሩ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ማቅረቧ ስህተቱ የቱ ላይ ይሆን? ነው ጥቁር ጥቁርን እየናቀው ነው? እናስብ ነገ ተነገ ወዲያ ሊመጣ ያለውን ገመና አሁን ላይ ታይቶት የሚያስጠነቅቀን ምድራዊ ሃይል የለም። ትራምፕ ተመርጦ እንዲህ አለምን ያበራያል ብለው የገመቱ ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። በቅርብ ባየሁት ዘገባ እስራኤልና ግብጽ ሳይቧቀሱ አይቀርም። በሳይናይ ምድረበዳ ጉዳይ የሚታዪ ግርግሮች አሉ። ሃማስና እስራኤል ገና አለየላቸውም። የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ህዝቡላ እንደገና ታጥቆና ፎክሮ ብቅ ማለቱ አይቀሬ ነው። የራሽያና የዪክሬን ጉዳይ አስከፊ ደረጃ እየደረሰ ነው። በተለይ አውሮፓውያን ወታደር ዪክሬን ላይ ለማስፈር ከሞከሩ ውጊያው በእነርሱና በራሺያ ይሆናል። እንግዲህ አያርገውና ከሆነ ለ3ኛው ዓለም ጦርነት ፍልሚያ የበለጠ ያስጠጋናል። 1.4 ቢሊዪንና 200 ሚሊዪን የእስልምና ተከታዪች የሚኖርባት ህንድ ከቻይና ጋር በዚህም በዚያም ይነታረካሉ። ኸረ ስንቱ ቻይና ይገባኛል የማትለው ደሴትና ሥፍራ የለም። ግን የሃገራት መደርጀት የጦርነት ውጤትን መጨረሻ አያሳይም። በቬትናም፤ በኢራቅ፤ በአፍጋኒስታን ሃያላን መንግስታት ተደቁሰውና ደቁሰው ተፈትልከዋል። ጦርነት የገበጣ ጫወታ ነው። የተጨበጠን ነገር በትኖ ባዶ ይዞ መመለስ። ኤርትራም ልብ ከሰጣት የታገቱ መርከቦችን ለቃ ሰላም ከጎረቤቶቿ ጋር በመፍጠር ቢቻል እድሜው የገፋው የሻቢያ ባለስልጣን ሁሉ ፕሬዚደንቱን ጨምሮ ሥልጣን በመልቀቅ አዲስ ትውልድ እንዲመራ ቢፈቅድ የኤርትራ የወደፊት እጣ ብሩህ ያደርጋል። ሌላው ሁሉ ተፍ ተፍ ከንቱና የመተላለቂያ መንገድ ነው። ግጭትና ጦርነት ይብቃ!