በመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የኤሌክትሮኒክስ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ የራዲዮ መገጣጠሚያ ፋብሪካ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፣ የጦር ሀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ እና የተቋሙ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች በተገኙበት ነው ተመርቆ የተከፈተው።
የመከላከያ ሰራዊታችን አገራችን በየጊዜው የገጠሟትን ፈተናዎች በሌሎች አገራት ቴክኖሎጂዎች ላይ በመመርኮዝ ግዳጅ እየተወጣ እንደዘለቀ አውስተው የተመረቀው የወታደራዊ ራዲዮ ፋብሪካ የሰራዊቱን የተልዕኮ አፈፃፀምና የግዳጅ ስምሪት የሚያቀላጥፍ እንደሆነ ተናግረዋል።
“ወታደራዊ ራዲዮው በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ የመጨረሻው የዲጅታል ስታንዳርድ ራዲዮ ነው።” ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ይህንኑ እውን በማድረግ ረገድ የቻይናው ሀይቴራ ካምፓኒ እና የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን አመራሮች ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ሀይለማርያም በበኩላቸው ፋብሪካው የመካከለኛና የረጅም ርቀት ወታደራዊ ራዲዮኖችን የሚያመርት መሆኑን ጠቅሰው ከወታደራዊ ራዲዮኖች ባለፈ ለሲቪል አገልግሎት የሚውሉ ራዲዮኖችን የሚያመርት ፋብሪካ እንደሆነ ተናግረዋል።
የመከላከያ ተቋም ከዚህ በኋላ ምንም አይነት የግንኙነት ራዲዮ ከውጭ አገር እንደማይገዛና ሙሉ በሙሉ በተመረቀው የራዲዮ ፋብሪካ እንደሚሸፈን ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ጌታቸው ሀይለማርያም ፋብሪካው በዓመት 32 ሺህ ራዲዮኖችን የማምረት አቅም እንዳለውም ገልፀዋል።
የኤሌክትሮኒክስ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ስራ አስኪያጅ ኮሎኔል ዘውዱ አለፈ የፋብሪካውን አጠቃላይ ሁኔታ ለመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ያስቃኙ ሲሆን በፋብሪካው የቴክኖሎጂ ሽግግር የተካሄደበት እና በሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተማሩ የቴክኒክ ሙያተኞች በመገጣጠሙ ተግባር ይሳተፉበታል ብለዋል።
ወታደራዊ ራዲዮው እጅግ ዘመናዊ ፣ በአገራችን ማንኛውም የአየር ፀባይ ያለ እንከን የሚሰራ ፣ ለአያያዝ ቀላል፣ ለየትኛውም ግዳጅ የሚመች እንደሆነና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ መሆኑም በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል። (የመከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply