
የትላንቱ እንቅፋት፣ ዛሬም ይመታናል
የትላንቱ ገመድ፣ ዛሬም ይጠልፈናል ፤
ሰምተንም – አልሰማን፣ ሳሰማም ሰምተናል
አይተንም – አላየን፣ ሳናይም አይተናል
ላለመማር – መማር እኛ ተምረናል።
አሁን… አሁን ”ከልሂቃኑ እስከ ኢ-ልሂቃኑ” ድረስ፤ ቀድም ብሎ ሙሰላዊያንና ሂተለራዊያን፤ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሻአቢያዊያንና ወያኔያዊያን እንዲሁም ኦነጋዊያን ከባንዳ አያቶቻቸውና አባቶቻቸው የተቀበሉትን የፈጠራና የጥላቻ ታሪክ ስላወሩትና የስልጣን ኮርቻውን ስለተፈናጠጡት፤ የሚንናገሩትና የሚጽፉት ሁሉ እንድ ዕውነት ተቆጥሮ ፤ “በኢትዮጵያ ህዝብ መሃከል ጥላቻ፣ በደልና ቂም-በቀል አለ!” መባሉ ነው።
ሌላውን ሁሉ ትተን ባለፉት 26 ዓመታት ብቻ ሻአቢያዊያን፣ ወያኔያዊያንና ኦነጋዊያን የሰሩትን ግፍና በደል፣ የዘሩትን ጥላቻና በቀል ብናስብ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ‘ርስ-በርሱ ተበላልቶ አይጨራረስም ነበር? የኢትዮጵያ ህዝብ ከአብራኩ በተከፈሉ ዜጎቹ እንዲተላለቅ ያልተቆፈረለት ጉድጉድ፤ ያለተሸረበበት ሴራ፣ ያለተነገረው የፈጠራ ታሪክ፣ ያለተወረወረበት ቦምብ፤ የለተኮሰበት ጥይትስ አለ ወይ? የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳልሰማ ሰምቶና እንዳላየ አይቶ ስንቱን ፈታና አልፉል? አሁንስ ለአንድነቱና ለነጻነቱ እየታገለ ያለው በመሃከሉ ጥላቻና ቂም በቀል ወይም በደል ስላለ ነው? የጥላቻውም ሆነ የፈጠራ ታሪክ ተራኪዎቹ ነጻ አውጭ ነን የሚሉት ራሳቸውን የሾሙ ድኩማኖች አይደሉምን?
በኢትዩጵያዊያን መሃከል ጥላቻም ሆነ በደልና ቂም-በቀል የለም። ወደድንም ጠላንም ሀቁ ይህ ነው። እኛ ኢትዩጵያኖች እንደ ሸማ ድር ተሸምነን፤ ልዩነታችን እንድነታችን፣ አንድነታችን ልዩነታችን፣ ልዩነታችን ውበታችን ፤ ከምንም በላይ ደግሞ በሰውነታችን መከራውንና ደስታውን አብረን ለዘመናት ያሳለፋን መሆናችንና ወደፊትም በአንድነታችን ጸንተን እንደምንቀጠል፤ በዚች ሰዓት እንኳን ለተጠራጣሪዎች አይደልም፤ ለወያኔያዊያን፣ ኦነጋዊያንና ከምድረ-ገጽ መጥፋታችን እንደማለዳ ጸሃይ ለሚናፍቁ ሀሉ እያስተማርናቸው ነው።
ትላንትም ሆነ ዛሬ ያለው እውነታ ፤ ጥላቻ፣ በደልና ቂም በቀል ያለው ፤ …
1ኛ- ከታሪካዊ የሀገሪቱና የህዝቧ ጠላቶች ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ እውን ለማድረግ በተሰለፉ ባንዳዎች መንደርተኞች፤
2ኛ- የስልጣን ኮርቻ ለመፈናጠጥ አቋራጭ መንገድ በሚፈልጉ መሃይማንና ተማርን ባይ ጉልበተኛ ቡድኖችና ግለሰቦች፤
3ኛ- ምንም ዓይነት ሀገራዊ ሆነ ወገናዊ ስሜት ባልተፈጠረባቸው በግል ጥቅም በታወሩ ግለስቦችና ቡድኖች መሃከል ነው።
እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ፤ ለማ መገርሳ ባህርዳር ሂዶ ገዱን ስለጎበኘ፤ ኢትዩጵያዊነትን የሚተርክ በተለቪዚዎን ስለታየ ፤ እርቅ እንደወረድና ወያኔም ችግር ላይ እንደወደቁ ተደርጎ ይሰበካል። የወያኔም ተራ ማታለል፣ እኛም መታለል ችሎታችን ሆኖ የሚቀጥለው እስከመቼ ነው? እድሜ ልካቸውን ውሸት ሲናገሩ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ላይ ለፖለቲካ ፍጆታ በወያኔ ት’ዛዝ፣ የነበረንና ያለን እውነታ ስለተናገሩ እንዴት እንደታ’ምር ሊቆጠር ቻለ? እስከዛሬስ የት ነበሩ? እስቲ ሳምንታት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ወያኔ ዘወር ብሎ ከጎንደር ህዝብ ጋር እርቅ ፈጠርኩ ብሎ “ሲቀረሻብን” ምን ታዘብን? እነ ለማ መገርሳ ባህርዳር ሄዱ ብለን ስንፈነድቅ፤ በጓሮ በር ፕ/ር ህዝቄየል የተባላ ግለሰብ ነጭ “የኢትዮጵያን ወዳጆችን” ሰብስቦ ”አማራ” ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም፣ ጠላታችን ነው እያለ በጀርመኖች የተሰበከለትን ሲደነፋብን ለምንድነው እንደ አዲስ ነገር ያዙኝ! ልቀቁኝ የምንለው?
” …… በስምንተንኛው ሺ፣ በያዝነው ዘመን
ውሸት ገኖ አዘዘው፣ ሰው መስሎ ሰውን።….” አሉ አሉ ወሎየው ።
– በመጀመሪያ ደረጃ ማንና ማን ነው የተጣለውና ያጣለው?
– ለማና ገዱስ ማንን ነው የሚወክሉት? ማንስ ነው የወከላቸው?
– እነዚህ ሰዎች በወያኔ አዝማችነት በሀገርና በህዝብ ላይ ስንት ጉድ ሰርተዋል? አሁንስ ምን እያደረጉ ነው?
– ለመሆኑ ለማና ገዱ እንዲገናኙ ማን ፈቅዶላቸው ነው ? ከወንበሩስ ያስቀመጣቸው ማነው?
– ግድያውም ሆነ የጥላቻ ሰበካውና ሃውልት ማቆሙ የሚካሂደው ”ቦለቲከኛ” ነን በሚሉት እንጅ በየትኛው የህዝብ መሃከል ነው?
– ወያኔ ማጠፊያ ሲያጥረው አቅጣጫ ለማስለውጥና ለማታለል መሆኑ ሩብ ዓመታት አሳልፈንም እንዴት ግንዛቤ እናጣለን?
ተደራጅቶ የሚታገለው ያጣው ወያኔ፣ የህዝብ አመጽ ግን ግራ እያጋባው፣ ትቢያና አቧራ እየላሰ መነሳቱ ከ’ኛ ይልቅ እየገረመው የመጣው ለራሱ ለወያኔ ነው።
ታዲያ ወያኔ ወጥመድ ውስጥ እንዳለች አይጥ ሆኖ በሚሰራው ድራማ፤ እኛ ደግሞ ታዳሚዎች በመሆን አብረን እናጭበጭባለን። ”ወያኔ ተከፋፈለ!… አዜብ ‘ረግጣ ወጣች!… ኦህዴድና ብአዴን እንዲህ አሉ… እንዲህ ሆኖ…. የጡት አባታቼውን ወያኔን ተጋፉ!… ኦነጋዊያንና ጃዋራዊያን እንዲህ አሉ!…” እያልን የወያኔንና የሱን ተከታይ መንደርተኞች እሥስታዊ ባህሪ እናዳምቃለን። ግን ለምን ? ለምንድ ነው ከትላንቱ – ካለፈው የማንማረው? …
በወያኔና በኦነጋዊያን ቦይ መፍሰሳችን አቁመን፤ ስለአንደነት እያወራን አንደነት አተን ‘ርስ-በርስ መቆራቆሳችን ወደ ጎን ትተን የራሳችን የቤት ሥራ መሥራት፤ በወሬ ሳይሆን በተግባር ኢትዮጵያዊ ነኝ ከሚል ዜጋ የሚጠበቅ ነው። ግዜው ደግሞ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ አይደለም ፤ ዛሬ እንጅ። የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ለድል የሚያበቃ መሪና አደራጅ አ’ቶ እንጅ መከፈል ከሚገባው በላይ መሰዋአትነቱን እየከፈለ ነው። እናም…
“እንዳትረግጡት…. የኢትዮጵያን ዐፈር- መሬት! ”
‘ባካችሁ ……… ’ባካችሁ……….
እናንት በምድረ- ኢትዮጵያ ያላችሁ፤
“አትሂዱ …..በ’ግራችሁ…”
ከቻላችሁ ….. “ብረሩ ክንፍ አው’ታችሁ።”
ግን…….. አደራ……….. ……….
አንዳትረገጡት ……. መሬቱን
እንዳታዩት……… አፈሩን፤
ብታርሱት…… አትዘሩበት
ብዘሩበት …….. አይበቅልበት፤……..
ደም ነውና – የትላንና- የዛሬ – የአሁን፣ ትኩስ…. የፈሰሰበት
አጥንት ነውና ያልደረቀ ፣ “አጸደ-ህይወት” የወደቀበት
እናንተም ከእንግዲህ ፣ ”ዐጽም – ‘ርስቴ” የማትሉት፤………..
ያውም ………………………………..
የባቶቻችሁ፣…….. የናቶቻችሁ
ያውም………………………………
የወንድሞቻችሁ፣…….. የህቶቻችሁ
ያውም……………………………………
የእቦቀቅላወቹ፣…… የታዳጊወቹ፣……..የልጆቻችሁ፤
ዓይናችሁ እያየ፣……. እየሰማ ጆሮ’ችሁ
የተመቱ! … የቆሰሉ!….. የተወጉ! …. የተፈነከቱ!…..
የተቀጠቀጡ!…. የተዘለዘሉ!……! ……የተረሸኑ!
….. በገዛ ወገኖቻችሁ………..
ያውም …………”ወገን እኮ ነን “ እያላችሁ።
በደመዋ ልባችሁ……………………………….
“ኤሉሄ …..ላማ ሰበቅተኒ!”……. ብላችሁ
ወሰን – ድንበር ለሌለው ሰቆቃችሁ
ብትነግሩትም “ለሰማይ አባታችሁ”፤
ግን….. ለምንም – ለማንም አይመችም
ሀዘናችሁ መልክ የለውም……….
ያልተነገረ እንጅ፣ ያልተፈጸመባችሁ ግፍ የለም።
ብትጎጉጡ፣ ደም አልቅሳችሁ፣….. እየየ …ብላችሁ –
ቢያዳርስም ዓለም ….. ሲቃ – ዋይታችሁ …
መቼም- መቼም ቢሆን፣ ምንጩ አይደርቅም የ’ምባችሁ::…..
እናማ………………………………………..
ሰላም፣ ፍትህ፣ እኩልነት – ሳታሰፍኑ – በመሀከላችሁ
አንድነትን ሳታነግሱ – በምድራችሁ
ይቅር ሳትባባሉ፣ ‘ርስ – በርሳችሁ
ሳይመለስ ክብራችሁ፣ ጠፈር – ድንበራችሁ
የድል ችቦው – ከፍ ሳይል ፣ ክብር ሰንደቅ ዓላማችሁ፤……
የወገናችሁን ደምና- አጥንት እንዳትረግጡት
“ይወጋችሁልና እሾኽ ሆኖ፣ የኢትዮጵያ ዐፈር – መሬት!”።
ከፊልጶስ/2010
E-mail: philiposmw@gmail.com (ፎቶ ከከቀኝ ወደ ግራ ለማ፣ ግዱ እና አብይ)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply