አሜሪካ የአፍሪካ አገራት የተለያዩ ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነፃ ወደ ግዛቷ እንዲያስገቡ ከሚፈቅደው የአጎዋ ዕድል ተጠቃሚነት ኢትዮጵያን ለመሰረዝ መወሰኗ በአሜሪካ አልባሳት እና ጫማ ኢንዱስትሪዎች ላይ ድንጋጤ ፈጥሯል ተባለ።
የአሜሪካ አልባሳት እና ጫማ ማኅበር (AAFA) የቦርድ ሰብሳቢ፣ ፕሬዝዳንት እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ያገለገሉት ሪክ ሄልፌንቤይን ፎርብስ መጽሄት ላይ እንደፃፉት ውሳኔው ትልቅ ስህተት ነው ብለውታዋል።
ውሳኔው ማንም ያለጠበቀውና የአሜሪካ አልባሳት እና ጫማ ኢንዱስትሪዎች በአፍሪካ ያደረጉትን ኢንቨስትመንት ዋጋ የሚያሳጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት አሜሪካ አጎዋን የአገራትን ለመጫን እንደ መሳሪያ እየተጠቀመችበት መሆኗን ነው ሄልፌንቤይን በጽሁፋቸው የገለጹት። ይህ ደግሞ ፍጹም ስህተት ነው ሲሉም አካሄዱን እንደተቃወሙት ነው ኢዜአ የዘገበው።
አሜሪካ የአልባሳት እና የጫማ ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ መዋዕለነዋያቸውን እንዲያፈሱ አሜሪካ ስታበረታታ መቆየቷን አውስተው አሁን ግን ኩባንያዎች ከአገሪቱ ስለመውጣት እንዲያስቡ መፈለጓ ተገቢነት የለውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ቀውስ ተከትሎ አሜሪካ እንዲህ ዓይነቱን ውሳኔ መወሰኗ በርካታ ባለኃብቶችን ለምን ሲሉ ጥያቄ እንዲያነሱ እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ ድንገተኛ ውሳኔ መወሰኑ ሌሎች ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት በኢንቨስትመንት መስክ በተሰማሩ ባለኃብቶች ላይ ሥጋትን ስለመደቀኑ ጠቁመዋል።
ውሳኔው አሜሪካ እኤአ በ2025 አጎዋን እንደማታራዝም ፍንጭ የሰጠ ከመሆኑ ባለፈ በአፍሪካ ለተሰማሩ አሜሪካውያን ባለኃብቶች የመንግሥት ድጋፍ እንደሚያሳጣቸው ነው ስጋታቸውን የገለጹት።
“ሃቁን ለመናገር አጎዋ አሜሪካ ከፈጠረቻቸው የንግድ መርሃ ግብሮች የላቀ ፋይዳ ያለው አይደለም” ያሉት ሄልፌንቤይን፤ ለ21 ዓመታት የአጎዋ አፈፃጸም በተወሰነ ደረጃ ደካማ እንደነበር በማሳያነት አንስተዋል።
እንዲያም ሆኖ በርካታ አገራት የአጎዋ ዕድል ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ነው ያስረዱት።
እናም አሉ ሪክ ሄልፌንቤይን አጎዋ ለአሜሪካውያን ሆነ አፍሪካውያን ያመለጠ ዕድል ሆኖ እንዳይቀር እስከ ጥር ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ አሜሪካ ውሳኔውን ዳግም ልታጤነው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሪክ ሄልፌንቤይን ከአንድ ሺህ በላይ ዓለም አቀፍ ዝና እና ዕውቅና ያተረፉ የምርት ስሞችን የሚወክል ማህበር በሊቀመነበርነት የመሩ ሲሆን ከኢንዱስትሪዎች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በቅርበት ሲሰሩ ቆይተዋል።
በተጨማሪም የበርካታ እውቅ (ብራንድ) ፋሽን ኩባንያዎች ፕሬዝዳንት ሆነው ከማገልገላቸው ባለፈ በ CNBC፣ CNN፣ Bloomberg፣ BBC እና Fox News የኢንዱስትሪ ትንታኔ በማቅረብ ይታወቃሉ። (AMN)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
gi says
የባይደን መንግስትና የቢል ክልንተን የሆባማና የናንሲ ፔሎሲ የግል ስውር ድርጅቶች የኣሜሪካንን አቋም ኣሳዩም በኣሜሪካ መንግስት ጀርባ ላይ ተቀምጠው የግል ጥቅማቸውን ከማሳደድ በቀር ለኣሜሪካ ሕዝብም ሆነ ለዓለም ሰላም ደንታ የላቸውም። በዓለማችን ካደረሱት ግፍ የተነሳ ረጅም ዕድሜ የላቸውም። ቡሽ ተሰናብቶ ይህችን ዓለም ተሰናብቶ ላይመለስ ሄዶኣል። ለጥቁሮች ሰቆቃ ምክንያት የሆነው ሱዛን ራይስና ሆባማ እስካ ኣሉ ድረስ ኢትዮጵያ እረፍት ኣታገኝም። ለአገራችን ሰላም ሲባል ያልጠበቁት፣ ያልስተዋሉት በድንገት የሆነ ለውጥ በኣሜሪካ ይመጣል እነዚህ ሁሉ የመከራችን ምክንያት የሆኑቱ የጥልቁ የስውር መንግስት ለኣንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይጠፋል። ቀኑ ደርሶኣል መለከት ሊነፋና ድሉን ተጠባበቁ።