ጃዋር መሐመድ “የኦሮሞ ፕሮቴስት” ብሎ የጀመረ ሰሞን ብዙ የፌስቡክ ተከታታይ አልነበረውም። ወዲያው አገር ቤት ከኦህዴድ ጋር በነበረው ግንኙነት የተቃውሞ ሰልፎችንና የፖሊስ ግፎችን የሚያሳዩ ፎቶዎችን መለጠፍ ሲጀምር የተከታታዩ መብዛት ጀመረ።ዝግጅቱም፣ ትምህርቱም፣ ሥራውም፣ በሚዲያ ዙሪያ ስለነበር ሚዲያን እንዴት እንደሚቆጣጠርና የሕዝቡን ቀልብ እንዴት እንደሚስብ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። በመሆኑም ከማኅበራዊ ሚዲያ እስከ ዋንኛ (mainstream) ያለውን በቀላሉ ተቆጣጠረው። ለመረጃ፣ ለዘገባ፣ ለዜና፣ … እንደ ምንጭ የሚጠቀስ ሆነ። ትልልቅ የሚባሉት የውጪዎቹ የሚዲያ አውታሮች እሱን ሳያናግሩ ዜና መሥራት አልታያቸው አላቸው። በፍጥነት ወጣ፣ ተመነደገ፣ ከፍ አለ! የዚያኑ ልክ እሱም እያበጠ መጣ።
ዕብጠቱ ገና አፍላ በነበረበት ጊዜ ባደባባይ የዕብሪት ንግግር ለጠፈ። አሁን በማላስታውሰው አንድ ከተማ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ተማሪዎች ወጥተው ነበር። ትህነግ አሰልጥኖ ያሰማራቸው የአጋዚ ፖሊሶች ለደረታቸው ተኩሰው የተወሰኑትን ይገድላሉ። የሞቱትን ልጆች ፎቶ እንደተላከለት ጃዋር ወዲያው በፌስቡክ ገጹ ለጠፈው። ፎቶው መሬት ላይ የተዘረሩ በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች በደማቸው ተነክረው የሚያሳይ እጅግ ዘግናኝ ነበር። ከፎቶዎቹ ጋር እንዲህ በማለት በእንግሊዝኛ ለጠፈ፤ “ጨምራችሁ ግደሉ ሒሳቡ በእኛ ነው”። ይህንን ሲል እርሱ በሞቀ ቤቱ በአሜሪካ ሜነሶታ ጠቅላይ ግዛት ደኅንነቱ ተጠብቆ እየኖረ ነበር።
ዕብሪተኛው በዚሁ ቀጥሎ አገር ቤት ከገባ በኋላ “ሁለት መንግሥት ነው ያለው” ብሎ እስከመናገርና ራሱን እንደ አገር መሪ እስከ መቁጠር ደርሶ ነበር። ሌላም ብዙ መጥቀስ ይቻላል። ወደ አገር ሲገባ ከነበረው ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጋ ጥሬ ብር በተጨማሪ ሌሎች በርካታ የገቢ ምንጮች ነበሩት። ይህም የእብሪት ፊኛውን ለመወጠር አዎንታዊ አስተዋጽዖ ያደረገ ነበር።
የ21ኛው ክፍለ ዘመን አሕመድ ግራኝ ነኝ ሲል የነበረው ጃዋር አሁን የት ነው? ገና በወጣትነቱ የተጠናወተውን በሽታ እያስታመመ፤ አመጋገቡን እየተቆጣጠረ፤ ደግ ደጉን እያወራ ተራራ የሚወጣ (ኪሊማንጃሮን ማለቴ ነው) ኃላፊነቱን የተገነዘበና በትጋት የዜግነት ድርሻውን የሚወጣ “መልካም ወጣት”፣ ጥሩ የሕግ ታራሚ ሆኗል።
ዘመድኩን ይህንን ሁሉ እንደ መግቢያ የጻፍኩት አንተ ራስህን ልክ እንደ ጃዋር ጊዜ “የኦሮሞ ፕሮቴስት” የሰሞኑ “የኦርቶዶክስ ንቅናቄ” ተብሎ በተሰየመልህ አጀንዳ ራስህን መሪ እያደረግህ በመምጣትህን በማየቴ ነው። በነገራችን ላይ ስሜን ያልነገርኩህ ፈርቼ ወይም በሃሰት መረጃ በድብቅ አንተን ለማጥቃት ሳይሆን ያንተን ያህል ባይሆንም የተወሰነ የሚያውቀኝ ሰው ስላለ ነገር ላለማባባስ ነው። እኔና አንተ ግን በደንብ ነው የምንተዋወቀው። አሁንም በአጻጻፌ በደንብ ልታውቀኝ ትችላለህ። በበርካታ ጉዳዮች ላይ ብዙ ተከራክረናል፤ “ተው ተጠንቀቅ፤ እንዳትጠለፍ” እያልኩ መክሬሃለሁ፣ አስመስክሬሃለሁ።
በቤተክርስቲያናችን የደረሰውን አስከፊና አንገት አስደፊ ነገር የእኔን እና የበርካታ ተዋህዶ ልጆችን ቅስም የሰበረ ነው። እንዳንተ እየወጣን አዛኝ ተቆርቋሪ መስለን አጀንዳ ፈጻሚ ባንሆንም መከራና ስቃያችንን ለሚያይ አምላክ በየሰዓቱ እንቃትታለን። አንተ ግን ለተዋህዶ ቤታችን የተጨነቅህ መስለህ የምትጽፋቸው እጅግ ዘግናኝ ልጥፎች እጅግ የዘቀጡ ናቸው።
በቴሌግራም ብዙ ተከታዮች አሉህ። ሰሞኑን በቲክቶክ ደግሞ ዝነኛ ሆነሃል፤ ተከታዮችህ እና የቀጥታ ሥርጭቶችህ ተመልካች ቁጥር በሚያስገርም ሁኔታ በፍጥነት አድጓል። እንዲያውም በቲክቶክ መንደር የአንደኛነትን ደረጃ መጎናጸፍህን ራስህ በቴሌግራምህ ላይ ለጥፈሃል። እንኳን ለዚህ በቃህ። ግን አትርሳ የሚከተልህ ሁሉ ወዳጅህ አይደለም።
የመረጃ ድርቀት ስላለብህና ከስድብ በስተቀር ከዕውቀትም የጸዳህ ስለሆነ አንዲት ነገር ልጥቀስልህ። የዛሬ 11 ዓመት አካባቢ በመጋቢት ወር ውስጥ (እኤአ 2012) አንድ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ የዩጋንዳ አማጺ ቡድን መሪ የሆነው ጆሴፍ ኮኒ እንዴት ሕጻናትን ለውትድርና መልምሎ ግፍ እንደሚሰራባቸው የሚያሳይ ቪዲዮ ለቀቀ። በሁለት ቀናት ውስጥ 30 ሚሊዮን ተመልካች አገኘ። ይህ በዕቅድ የተለቀቀው ቪዲዮ በኋላ ለእንዴት ዓይነት መሰሪ ተግባር ታቅዶ ለዕይታ እንደቀረበና የተሠራውም ለህጻናቱ ታስቦ ሳይሆን ወረራ ለመፈጸም እንደሆነ በኋላ የታወቀ ሆኗል። አትርሳ የሚከተልህ ሁሉ ወዳጅህ አይደለም።
በማኅበራዊ ድረገጾችህ ያለማቋረጥ ትጽፋለህ፤ ስትጀምር በተለመደው ኦርቶዶክሳዊ ቡራኬ ነው፤ ከቡራኬው በኋላ ግን በአማርኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ያሉት ለስድብህ ስለማይበቁህ የራስህን ጨምረህ እጅግ ጸያፍ ስድብ ትሳደባለህ። ተከታዮችህን በመንፈሳዊ ትምህርት እና ክርስቶሳዊ በሆነ ትህትና ከማነጽ ይልቅ ስድብ ስትግታቸው ትውላለህ። አስበኸዋል አንድ ቀን ልጆችህ አድገው ምን ስታደርግ እንደነበር ቢረዱ ምን እንደሚሉህ? ባለቤትህስ? የሚያውቁህ ዘመዶችህስ? በዚህ ላይ ይህንን ስድብህን ለመትፋት “አገልግሎቴን በገንዘብ ደግፉ” እያልህ ሳንቲም ትለቃቅማለህ። ጊዜ ያልፋል፤ ኢንተርኔት የያዘው ግን አያልፍም። ለቤተሰብህ የውርደት ስንቅ በየቀኑ እየቋጠርህላቸው እንደሆነ እወቅ።
የወሊሶው ቡድን አስነዋሪውን ተግባር በፈጸመ ዕለት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተግባሩን ፍጹም ካወገዘ በኋላ ጉዳዩ በውይይት ይታይ፤ እንነጋገር ቢል ተሰምቶ የማያውቅ የስድብ ዶፍ አወረድህበት። ግን የደቡብ ካሊፎርኒያው አባታችን ብጹዕ አቡነ በርናባስ መድሎት ሚዲያ ላይ ባደረጉት ውይይት መፍትሔው ውይይት እና ንግግር እንደሆነ በግልጽ ተናግረዋል። አንተ በመንፈሳዊ ተግባር ስም ቤተክርስቲያናችንን ልታፈርስ የተነሳህ ቅጥረኛ ፖለቲከኛ ካልሆንህ በስተቀር ምን ቤት ሆነህ ነው ውይይት የለም የምትለው? ቀጠልህና አባታችን አቡነ ኤርምያስን ከፍ ዝቅ አድርገህ አጥረገረሃቸው። ወጥተው እንዲናገሩና ሚናቸውን እንዲለዩ የምትመራውን “መንፈሳዊ ቄሮ” መንጋ ላክህባቸውና አዋረድኻቸው። እርሳቸውም በነጋታው በዩትዩብ ቀርበው ቃላቸውን ሰጡ።
በዚህም አላበቃህ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጉዳዩ መንፈሳዊ ነው እንጂ ምንም የፖለቲካ ዓላማ የለውም በማለት በተደጋጋሚ ቢናገርም አንተ ግን ፖለቲካዊ በማድረግ መንግሥትን በኃይል የመናድ ተግባር በገሃድ እንዲፈጸም እየጎተጎትህ ነው። አንተ ጀርመን ተቀምጠህ ነው ይህንን የምትለው፤ ለሚሞቱም “ሰማዕትነት ነው፤ ገነት ትገባላችሁ” እያልህ “ክርስቲያናዊ ጂሃድ” ታውጃለህ። ልክ ጃዋር ተመሳሳይ ተግባር ይፈጽም የነበረው ከሞቀ ኑሮው፤ ደህንነቱ ከተጠበቀበት ሚነሶታ እንደ ነበር ማለት ነው። አንተን ከጃዋር እንዴትና በምን ልለይህ?
አሁን ብዙ ተከታይና ደጋፊ አለህ። አንተ ከዕውቀት የራቅህ ስለሆነ ነው እንጂ ማኅበራዊ ሚዲያ ለትራምፕም አልበጀው። ባንዴ ሁሉንም ሲዘጉበት ያንን ሁሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ተከታዩን በሰከንድ ውስጥ ነው ያጣው። ስለዚህ ትንሽ ቆም ብለህ አስብ! ቀን ያልፋል፤ ገናና መንግሥታትም አልፈዋል፤ ከፈለግን በጥቂት ደቂቃ መንግሥትን መቆጣጠር እንችላለን ያለው ጃዋርም የተነፈሰ ፊኛ ሆኖ ልክፍት እንደያዘው በየተራራው ይሽከረከራል።
ስለዚህ ወዳጄ ልምከርህ፤ የሚከተልህ ሁሉ ወዳጅህ አይደለም። ከወዳጅ ይልቅ ብዙ ጠላቶች ይከተሉሃል፤ ይፈልጉሃል፤ ምክንያቱም አጀንዳቸውን ታስፈጽምላቸዋለህ። ወዳጅ መስለው ያበረታቱሃል፤ “ወጥር ዘመዴ” ይሉሃል፤ ስታወራ ያዳምጡሃል፤ “እግዚአብሔር ይመስገን” በሉ ብለህ ስትጀምር ማኅበራዊ ሚዲያህን ያጧጡፍልሃል፤ ምክንያቱም ሥራቸውን በነጻ እየፈጸምህላቸው ስለሆነ። አጀንዳቸውን አስፈጽመህ ስታበቃ እንደ ሸንኮራ መጥጠው ይወረውሩሃል፤ እንደ ሲጋራ አጭሰው ይረጋግጡሃል። አትርሳ የሚከተልህ ሁሉ ወዳጅህ አይደለም።
ገና ለገና ሽምግልና ውስጥ ገብታለች ብለህ ከፍ ዝቅ አድርገህ የሰደብሃት ኮማንደር ደራርቱ በርግጥም በሒደቱ ውስጥ እንዳለች የሲኖዶሱ የሕዝብ ግንኙነት ሲሳውቅ አንተም “ደርዬን አገኘኋት” ብለህ ብቻ ነው የፖሰትኸው። ቢያንስ እሷንም፣ ተከታዮችህንም ስለፈጸምኸው ነውር ይቅርታ ልትጠይቅና ምሕረት ልትለምን ይገባሃል። ደራርቱን በስልክ ደውዬ አነጋገርኋት፤ እንደለመደቸው መልካም ነገሮችን ነገረችኝ ካልህ በኋላ አንድ ቃል ከሷ ንግግር ጠቀሰህ። እኔም በዚያች የደራርቱ ቃል ልሰናበትህ “አንተም ዘመዴ ተረጋጋ” ነበር ደራርቱ ያለችህ! አትርሳ የሚከተልህ ሁሉ ወዳጅህ አይደለም።
ባለማተቡ ነኝ (trinity123@aol.com)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣበ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Ahoon says
Ishohin be ishoh indemibalew ishoh hono yegebawun gareTa beishoh taweTawaleh inji 5 amet mulu bemeqlesles yameTanew negher alneberem. 2 million yetewahido lijoch inde qiTel siregfu lelaw sew min adereghe?
Qidus qidus bemeChawet ye weyanne inna ye ohded jibim yihun yihuda altemelesem. Lela sint million yileq? Hagheris iske yet dires tiferars? Igna Chewa Chewa siniChawet arba amet hagherachin dirashua Teffa.
Jiraf hono le hagerachin dersolatal. Igziabher YisTew.
Le sidbu atcheneq. Hararghe bitihed, ye Zemede quanqua ijig ye Chewa yihoibihal. Siraw tesertola. Meswa’itnet tekeflobet.
100 million chewa quanqua teTeqami hagherun asdefere inji alaskeberem.
Zemede iskahun beseraw botaw kene Abdisa Agga, kene Zerai Deres, kene Belay Zeleke, kene Abune Petros gar new. Keziyam belay.. ye and teQuam yahil new yeseraw.
Awo. LequrT qen yemiyasfelighew miTmiTTA inji alicha aydelem.
Tebarek Zemede. Ante kifu mesleh lelochachin neTsanetin indinaTaTim adirghehal.
Ye Qurt Qen Lij.
Dedeboch says
ለእነዚህ ተከፋይ ከርሣም ካድሬዎችና ድረ ገፃቸው ይህን ያህል ቦታ መሥጠት አያሥፈልግም። ሢጀመር ማን በድጋሚ ሢጎበኛቸው ነው? ጣዕም ላላቸው ገፆች እንኳን ጊዜው በበቃን። ለሆዳቸው ዓይናቸውን በልጥጠው ከዲያቢሎሡ የተወዳጁ ናቸና: ከእነዚህ ለዘለዓለሙ ያርቀን።
Dedebich says
የምን ኮሜንት ይሆን የምትፈልጉት? መቼም ይህ ሚዲያ የሚሉት መድረክ ሁሉን እኩል በአንድ ቤንች ያሠልፋል። አቤት አቤት አቤት። ለመጀመሪያ ቀን አነበብኳችሁ። እሥከመጨረሻውም ተፀየፍኳችሁ። የነብሠ ገዳዩ የወንበር ጥመኛው ዐብይ ተከፋይይይይይ ድልብ ካድሬዎች። ሁለተኛ ? የእናንተን ገፅ ከማይይይይ: እንቅልፌን በሠላም በደሥታ ብኮመኩም ይጠቅመኛል። ዘመናዊ ከርሣሞች።