የኢትዮጵያን ሃብት ከህወሓት ጋር በጥቅም በመመሳጠር ሲበዘብዝ የነበረው መሐመድ አለ አሙዲ (አላሙዲ) እጅግ በርካታ ገንዘብ ከፍሎ በሌብነት ከታሰረበት ሳዑዲ አረቢያ መለቀቁ ተሰምቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሲታሰር 10.9 ቢሊዮን ዶላር የነበረው ሃብቱ ሲፈታ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። በፎርብስ ደረጃ አሠጣጥ መሠረት ከእስር በኋላ የ159ኛ ደረጃ ሰጥቶታል። ሆኖም ፎርብስ የአላሙዲ ሃብት በእርግጥ የእርሱ መሆኑን ማረጋገጥ ስላልቻለ በ2018 ከዓለም ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ አውጥቶታል።
በርካታዎች እየሞቱና መብታቸው ተገፍፎ በእስር እየማቀቁ በነበሩበት ወቅት የንብ ካኔተራ በመልበስ የህወሓት ደጋፊነቱን በገሃድ ያስመሰከረው አላሙዲንን ከህወሓት ለይቶ “የሕዝብ ሰው” አድርጎ ማቅረብ ለህወሓት ያለን “ጥላቻ” ከአላሙዲ “ትግሬ” አለመሆን ጋር የተገናኘ ይመስላል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። ከዚህም አልፎ የዛሬ ሃያ ሰባት ዓመት አካባቢ በኢህአዴግ ሰዎች ሎንዶን ላይ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መጠመቁን የሚናገረውን አላሙዲንን እና ድርጅቶቹን ከኤፈርት ለይቶ ኢትዮጵያዊ አድርጎ ማቅረብ ጭፍንነት ብቻ ሳይሆን ህወሓትን የመቃወሚያው መሠረት አልባነትን የሚያሳይ እንደሆነ ድምጻቸው የታፈነ ጥቂቶች ሲናገሩት የቆዩት ጉዳይ ነው። አላሙዲንና ሚድሮክን የምናሞግስ ከሆነ ስብሃት ነጋንና ኤፈርትን ልንቃወም የምንችልበት መሥፈርት የለንም በማለት እነዚሁ ወገኖች መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ።
ከዚህ አንጻር ግለሰቡ የሳዑዲውን የሌብነት ወንጀል ያደረሰበትን የሞራል ዝቅጠት ተቋቁሞ ወደ ኢትዮጵያ የሚመለስ ከሆነ በበርካታ ወንጀሎች ሊጠየቅ ይገባዋል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። በሸራተን ሆቴል ይሠራል ከሚባለው እጅግ የዘቀጡ ኢሞራላዊ ተግባራት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሃብት እስከ መዝረፍ እንዲሁም ከመሬት ነጠቃ ጋር በማያያዝ በበርካታ ወንጀሎች ክስ ሊመሰረትበት ይገባል የሚሉት ወገኖች አላሙዲ ከህወሓት ጋር በመሆን ከፍተኛ የኢኮኖሚ በደል ያደረሰ ሰው ነው ይላሉ።
ፎርብስ መጽሔትን በመጥቀስ ሪፖርተር ያቀናበረው ዘገባ እንዲህ ይነበባል።
እሑድ ጥር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ከአንድ ዓመት ከሁለት ወራት በላይ ታስረው የተለቀቁት ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲ፣ ከእስር ነፃ ለመውጣት ከፍተኛ ገንዘብ መክፈላቸው ተሰማ። ባለፈው ዓመት 10.9 ቢሊዮን ዶላር ሀብት የነበራቸው ሼክ አል አሙዲ፣ በአሁኑ ወቅት በፎርብስ የቢሊየነሮች ዝርዝር ላይ በ1.2 ቢሊዮን ዶላር ሀብት 159ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ፎርብስ እ.ኤ.አ. በ2018 ሼክ አል አሙዲ ከቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ማስወጣቱ ይታወሳል። በሰጠው ምክንያትም የትኛው ሀብት የእሳቸው እንደሆነ ግልጽነት ባለመኖሩ ነው ብሏል።
የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ባካሄደው የፀረ ሙስና ዘመቻ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ባለሀብቶች አንዱ የሆኑት ሼክ አል አሙዲ፣ ምን ያህል ገንዘብ ለሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ግን እንደከፈሉ ማወቅ አልተቻለም። ለሀብታቸው በከፍተኛ መጠን ማሽቆልቆል ምክንያት ግን ምናልባት ለነፃነታቸው ከፍተኛ ገንዘብ መክፈላቸው ሳይሆን እንዳልቀረ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በፀረ ሙስና ዘመቻው ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሳያገኝ እንዳልቀረ ይገመታል።
ሼክ አል አሙዲ በእስር በነበሩባቸው ጊዜያት ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ባደረጉባት ኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የፖለቲካ አመራር ለውጥ ተካሂዷል። በፖለቲካ ለውጡ ሒደት በነበረው ሕዝባዊ አመፅ የሼክ አሊ አሙዲ የተወሰኑ ንብረቶች ሰለባ ሆነዋል። የፖለቲካ አመራር ለውጥ ከተደረገ በኋላም ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኘው የሚድሮክ ጎልድ የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ በአካባቢና በሰዎች ላይ አድርሷል በተባለ ተፅዕኖ ምክንያት ሲታገድ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለዓመታት ታጥረው የቆዩ 11 ቦታዎች ደግሞ ካርታቸው መክኗል።
የሼክ አል አሙዲ የቅርብ ሰው የሆኑት አቶ አብነት ገብረ መስቀል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት ሼኩ ጂዳ በሚገኘው መኖርያ ቤታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጊዜያቸውን እያሳለፉ ነው።
“ጤናቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፣ ሞራላቸውም እንደዚያው። ፕሮግራማቸውን አሁን መናገር ባይቻልም ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ወደ አገራቸው ይመጣሉ፤” በማለት የገለጹት አቶ አብነት፣ “ሼክ አል አሙዲ አገራቸው ከመጡ በኋላ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትለው ሥራቸውን ማካሄድ ይጀምራሉ፤” ብለዋል። ምንም እንኳን አቶ አብነት ሼክ አል አሙዲ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ ይበሉ እንጂ፣ በሳዑዲ መንግሥት የፀረ ሙስና ዘመቻ ከታሰሩት መካከል አብዛኛዎቹ እስካሁን ከሳዑዲ ዓረቢያ መውጣት አይችሉም። በተመሳሳይም ሼክ አል አሙዲ ከሳዑዲ እንዳይወጡ ዕገዳ ሊደረግባቸው ይችላል የሚሉ ግምቶች አሉ።
“የቆሙ ሥራዎችና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በሙሉ በተካሄደው አገራዊ ለውጥ መሠረት ሥራቸው ይጀመራል፤” በማለት የገለጹት አቶ አብነት፣ “ሼክ አል አሙዲ ባልነበሩባቸው ጊዜያት በኢትዮጵያ የሚገኙት ድርጅቶቻቸው ሥራቸውን በአግባቡ በመሥራት አትራፊ ሆነው ቀጥለዋል፤” ሲሉ አብራርተዋል።
ሼክ አል አሙዲ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ደርግ ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ቢሆንም፣ ሙሉ ለሙሉ ወደ ኢንቨስትመንት ከገቡ 25 ዓመታት ተቆጥረዋል። ባለሀብቱ 105 የሚጠጉ ኩባንያዎችን በአራት ግሩፖች አዋቅረዋል። በእነዚህ ኩባንያዎች ከ50 ሺሕ በላይ ሠራተኞች የሚተዳደሩ ሲሆን፣ ከመንግሥት ቀጥሎ በኢትዮጵያ ትልቁ ቀጣሪ አድርጓቸዋል። (ሪፖርተር)
አብነት ይህንን ቢልም በገሃድ የሚታየው ሁኔታ ግን ይህ አይደለም በማለት የሚሞግቱ ጥቂቶች አይደሉም። ከለገደንቢ ጋር ተያይዞ በወርቅ ላይ ይደረግ ነበር የሚባልለት የወርቅ ዘረፋ አላሙዲንን በከፍተኛ ሁኔታ አክስሮታል። አብረውት በሃብት ዘረፋው ላይ የበላይነትን ተቀዳጅተው የነበሩት የህወሓት ሰዎች ትግራይ ራሳቸውን በፈቃዳቸው አስረው ለራሳቸውም “አዳኝ” እየተመኙ ነው። ሲታመም “አንጠልጥሎ ደቡብ አፍሪካ” ያሳከመው በረከት ስምዖንም “ንጽህናው አልተጠበቀም” ያለውን ምግብ እየበላ በሌብነት የተከሰሰበትን ጉዳይ እየተከታተለ ይገኛል። ከፒያሳ ጀምሮ እስከ ተለያዩ የኢትዮጵያ ቦታዎች ላይሠራ ለዓመታት አጥሮ ያስቀመጣቸው ባዶ ቦታዎች ተወርሰዋል። እንደ ዱሮው በአንድ ቀጭን ስልክ ማስመለስ አለመቻል ብቻ ሳይሆን የማይታሰብ ሃቅ ሆኗል።
በእነዚህና በሌሎች እጅግ በርካታ ምክንቶች የሳዑዲ መንግሥት ከአገር የመውጣት መብቱን ባይከለክለው እንኳን አላሙዲ ወደ ኢትዮጵያ አይመለስም የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። በሌብነት ተከስሶ ከተወነጀለበት ሞራል የሚነካ ክስ ጀምሮ እስከ ህወሓት መክሰም ድረስ በአላሙዲን ላይ የደረሰው ይህ ነው የማይባል ናዳ ማንም ከሚገምተው በላይ ሁኔታውን ውስብስብ አድርጎታል። በመሆኑን ኢትዮጵያ መንግሥት ተገቢውን ክስ በመመሥረት በተወካ እንዲከራከር አድርጎ ሃብቱን ለሕዝብ ጥቅም ቢያውለው ተገቢና መደረግ ያለበት ተግባር ነው በማለት የፖለቲካም የሕግም አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል።
ማስታወሻ፤ አላሙዲንን “አንተ” ብለን መጥራታችን ለሚያሳስባችሁ ይህንን እንድታነቡ ይሁን።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
gi Haile says
ሌባ ሌባ ነው። የተዘረፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሐብት ነው ወርቁን ከወለጋ ወሰዶ የወለጋን ሕዝብ አስርቦና አስገድሎ በለቤት ያልሆነውን እንደከብሩ መድረግ ከወንጀልም የከፋ ወንጀል ነው። ይህ ወንጀል ደግሞ ከአገራችን አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ የተደረገ በመሆኑ ነገሮችን ውስብስብ አድርጓታል። የአገር ሐብት አዘርፎ ሐብታም ከሆኑ በኃላ ገንዘብን አንደ አሸዋ በየቦታው በመበተን ለዝሙትና ታወቂ ሰዎችን ለማሳከም፣ ቆንጆ ሴት ፈልጎ በገንዘብ አጥምዶ መድፈር፣ ለልማት ሳይውል ተዘግቶ ለኣመታት የቆየ መሬቶች ተክስ ገቢ አለመደረጉ። ከዘረፋ ድርጅቶች ሕገሠዊ መስሎ ለመታየት መሞከር የእስልምና እምነት ተከታይ ነኝ የሚልን ሰው በሕሪይ አይወክልም። ኣሳፋሪ ተግባር ነው ከዚህም በላይ የመንጸስና የሞራል ውድቀት በላይ ኪሳራ የለም። አብታችንን ለሰውዲ ኣረቢያ ኣሸፈሳልፎ መስጠቱ ደግሞ ሌላው ኸንጀል ነው። ሰለዚህ 9 ቢሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ ሐብት ሊሆን ይችላል።