• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ደላላው “ባለሃብት” አል-አሙዲ በቁጥጥር ሥር ውሏል!

November 5, 2017 06:00 pm by Editor 1 Comment

  • “ማንንም አንፈራም!” ንጉሥ ሳልማን

የሳዑዲ የዙፋን ተስፈኛ አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን 11 ልዑላንን እና 38 የመንግሥት ባለሥልጣናትን (የቀድሞውን ጨምሮ) እንዲሁም የንግድ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አዋሉ። ደላላ (ተጠሪ ወይም front man) ባለሃብት እንደሆነ የሚነገርለት በግማሽ ኢትዮጵያዊ የሆነው ሞሐመድ አላሙዲ (አል-አሙዲ) በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል መሆኑን ጎልጉል አረጋግጧል። ንጉሥ ሳልማን የሕዝብን ንብረት የመዘበረ ማንም ሰው ተጠያቂ ይሆናል፤ “ማንንም አንፈራም” ብለዋል። ዜናው የተወሳሰበ ትስስር ያላቸውን የአላሙዲ “ወዳጆች” ከፍተኛ ሥጋት ላይ ጥሏል።

ልዑል አልዋሊድ ቢን ጣላልና ባለቤታቸው (የፎቶው ባለቤት Jasper Juinen/Getty Images)

ዜናው በመንግሥታዊው የዜና ወኪል አል-አረቢያ ከተዘገበ በኋላ በተለያዩ ምዕራባዊ የሚዲያ ውጤቶች እንደተነገረው ድርጊቱ “ፈጽሞ ያልተጠበቀ” እና በርካታዎችን “ያስደነገጠ” ሆኗል። በሃብታቸው አይነኬነት የሚታወቁት ልዑል አልዋሊድ ቢን ጣላልን (እንደ ፎርብስ ዘገባ የ17ቢሊዮን ዶላር ባለሃብት ናቸው) ጨምሮ ሌሎች 10 ልዑላን በቁጥጥር ሥር መዋላቸው አዲሱ አልጋ ወራሽ ወደ ዙፋን የሚደርጉትን ጉዞ የተቃና ለማድረግ የተወሰደ ነው ተብሏል። ከተያዙት መካከል የደኅንነቱ ኃላፊ ሚጤብ ቢን አብደላም እንደሚገኙ ታውቋል።

በሳውዲ አረቢያ ለውጥ መካሄድ እንደሚያስፈልግ እና ለዚህም ገጣሚ ናቸው በሚል የሳዑዲው ንጉሥ ሳልማን ቢን አብዱልአዚዝ አል ሳውድ ቁጥራቸው ከማይታወቀው ሚስቶቻቸው ከተወለዷቸው ልጆች መካከል የ32ዓመቱን ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማንን አልጋወራሽ አድርገው ከሾሙ በኋላ በሳውዲ ለውጦች እየተካሄዱ ነው። የሳዑዲ ሃብት ከነዳጅ ወደሌሎች የኢኮኖሚ ውጤቶች ማደግ አለበት በሚል ራዕይ 2030ን አንግበው የተነሱት አልጋ ወራሹ ወደ ዙፋን በሚደርጉት ጉዞ መንገዳቸው ላይ “ዕንቅፋት” የሚሆኑትን ማስወገድ ይዘዋል።

ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን

የለውጡና የተሃድሶው ዋነኛ ደጋፊ የሆኑት ንጉሥ ሳልማን በቅርቡ ባቋቋሙት የጸረሙስና ኮሚቴ አልጋወራሽ ሳልማንን ኃላፊ አድርገው ከሾሙ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ነበር በቁጥጥር የማዋል ዘመቻው ተግባራዊ የተደረገው። እንደ አል-አረቢያ ዘገባ ከሆነ፤ ይህ በንጉሡ የተቋቋመው “የጸረሙስና ኮሚቴ ሞሳኝ ነው ብሎ ያመነበትን የማንንም ንብረት የመመርመር፣ የመያዝ (በቁጥጥር ሥር የማዋል)፣ የጉዞ ዕገዳ የማድረግ፣ ወይም ንብረቱ እንዳይንቀሳቀስ የማድረግ” ሙሉ ሥልጣን ተሰጥቶታል።

ይህ “ኃያላንን” በቁጥጥር ሥር የማዋል ዘመቻ በተወሰነ መልኩ ከአሜሪካ የውስጥ ፖለቲካ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ጎልጉል ያገኘው መረጃ ያስረዳል። ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሆኖ የተዘገበው መረጃ እንደሚያመለክተው በቅርቡ የዶናልድ ትራምፕ ሴት ልጅ ባለቤት ያሬድ ኩሽነር ከዕድሜ አቻው አልጋወራሽ ልዑል ሳልማን ጋር በሳዑዲ ያካሄደው ውይይት እንደ አስረጅነት ይጠቀሳል። ኩሽነር የፕሬዚዳንቱ አማካሪ እንደመሆኑ ጉብኝቱ በምሥጢር መያዙና ከስድስት ቀናት በፊት ይፋ መሆኑ በርካታ መላምት እንዲሰጥበት አድርጓል።

ከዚህ ሌላ ዶናልድ ትራምፕ ለምርጫ በሚወዳደሩበት ወቅት ከይነኬው ባለሃብት ልዑል አልዋሊድ ቢን ጣላል (በሲቲግሩፕ፣ ኧፕል፣ ትዊተር፣ ሊፍት ወዘተ ውስጥ ከፍተኛ የባለቤትነት ድርሻ አላቸው) ጋር የነበራቸውን ቁርሾ የሚያነሱ አሉ። በምርጫው ውድድር ወቅት ልዑሉ ዶናልድ ትራምፕን “ለሪፓብሊካን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ለመላው አሜሪካ ኃፍረት (ውርደት) ነህና በጭራሽ ስለማታሸንፍ ከአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ራስህን አግልል” በማለት የትዊተር መልዕክት አስተላልፈው ነበር።

ትራምፕ ሲመልሱም፤ “ደንቆሮው (በዕጽ የደነዘዘው) ልዑል አልዋሊድ ጣላል በአባቱ ገንዘብ የአሜሪካንን ፖለቲከኞች ለመቆጣጠር ይፈልጋል። እኔ ስመረጥ ይህንን ማድረግ አይችልም” ብለው ነበር። በበቀለኝነታቸውና ጠላቶቻቸውን ጊዜ ጠብቀው በማዋረድ፣ ድባቅ በመምታት የሚታወቁት ትራምፕ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ያለፈውን ቁርሾ አሁን በተግባር ፈጽመውታል የሚሉ አሉ።

ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን አስቀድመው የተመለከቱት ልዑል አልዋሊድ የትራምፕ መመረጥ ይፋ እንደሆነ ወዲያውኑ ለተመራጩ ፕሬዚዳንት እንዲህ የሚል የአጸፋ ምላሽ ሰጥተው ነበር፤ “ያለፈው ልዩነታችን ምንም ይሁን የአሜሪካ ሕዝብ ተናግሯል፤ እንኳን ደስ አለዎት፤ በፕሬዚዳንታዊ ዘመንዎ መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ።”

“በሳዑዲ አረቢያ ታሪክ ተፈጽሞ አያውቅም” በማለት የሚናገሩ፤ ይህ የማጽዳት ዘመቻ ንጉሡ ቅዳሜ ዕለት የጸረሙስና ኮሚቴ መቋቋሙን በተናገሩበት ወቅት ጉዳዩ “የራሳቸውን የግል ጥቅም ከሕዝቡ ጥቅም በማስበለጥ በሚበዘብዙ አንዳንድ ደካማ ሰዎች” ዋንኛው ትኩረቱ እንደሚሆን መናገራቸውን ይጠቅሳሉ። ኮሚቴው እኤአ በ2009ዓም ለመቶ ያህል ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን የመካከለኛው ምስራቅ የመተንፈሻ በሽታ (MERS) አስመልክቶ የመንግሥት ኃላፊነትና በቫይረሱ መከሰት የተፈጸመውን ደካማ እርምጃ ይመረምራል። በኃላፊነት የሚጠየቁትንም በቁጥጥር ሥር ያውላል። ከዚህ ሌላ ከመቶ በላይ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን በ2009 በሳዑዲ (ጂዳ) የደረሰውን የጎርፍ አደጋ በተመለከተ ከመንግሥት የተሰጠውን የአጸፋ እርምጃ ደካማነት በመመርመር ተጠያቂዎችን ለፍርድ ያቀርባል።

ማንኛውንም የማሰር፣ የመያዝ፣ ወዘተ ሥልጣን የተሰጠውን ኮሚቴ አስመልክተው ንጉሥ ሳልማን በሳዑዲ ቲቪ ላይ እንደተናገሩት፤ “የሕዝብን ገንዘብ በነካ፣ በመዘበረ፣ ወይም እንዳይሰረቅ ባልተከላከለ ወይም ሥልጣኑን ተጠቅሞ (ይህንን ዓይነት ተግባር በፈጸመ) በማንኛውም ግለሰብ ላይ ሕጉ በጽናት ተግባራዊ ይደረጋል። ይህ የሚፈጸመው በትልልቆቹም ሆነ በትንንሾቹም ላይ ይሆናል፤ ማንንም አንፈራም” ብለዋል።

የንጉሡን ንግግር ተከትለው አልጋወራሹ ልዑል “ማንም በሙስና ውስጥ የሚገኝ ሚኒስትርም ይሁን ልዑል ማንም ከሕግ በላይ እንደማይሆን ላረጋግጥ እወዳለሁ” በማለት መናገራቸውን አልአረቢያ ዘግቧል።

ተጠርጣሪዎቹ ባለ አምስት ኮከቡ ሪትዝ ካርልተን (Ritz Carlton) ሆቴል በቁጥጥር ሥር እንደሚገኙና ሆቴሉ እስከ ዲሴምበር 1፤ 2017 ድረስ ምንም ዓይነት ክፍት ቦታ እንደሌለው፤ ክፍሎቹ በሙሉ የተያዙ መሆናቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል። እንደ ዜና ዘገባው ከሆነ ይህ የሚያሳየው ይህንን ባከለ ከፍተኛ ደረጃ የሚካሄድ ምርመራ ለሳምንታት ያህል እንደሚወስድ አመላካች ነው ብሏል። ግለሰቦቹ ከሳምንታት ወይም ከቀናት በኋላ የመፈታት ዕድል ቢገጥማቸው እንኳን ባሁኑ የገጠማቸው ኃፍረት ሊሸከሙት የማይችሉት እንደሆነ ይነገራል። የልዑል አልዋሊድ በቁጥጥር ከመዋል ተያይዞ ከሃብታቸው 750 ሚሊዮን ዶላር መጠረጉን ሲኤንኤን ዘግቧል።

እነ ልዑል አልዋሊድ ካላቸው ዓለምአቀፋዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነትና ሃብት ጋር ሲነጻጸር የሽልንግ ያህል እንደሆነ የሚቆጠረው የአላሙዲ ስም በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል “ሞሐመድ አል-አሙዲ፣ ነጋዴ” በሚል የመጨረሻው መስመር ላይ በሮይተርስ ተጠቅሷል። ዜናው ይፋ እንደሆነ በርካታዎችን ያስደነገጠ ከመሆኑ አኳያ ወዳጅና ደጋፊዎቹ እንዲሁም “ከእጃቸው የበላን” ያሉትን ጨምሮ ማስተባበያ ለመስጠት የተሞከረበት ቢሆንም ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የዲፕሎማቲክ ምንጭ በተለምዶ ሼክ መሐመድ አላሙዲን እየተባለ የሚጠራው በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስረድተዋል።

ልዑል አልዋሊድ

እንደ መረጃ አቀባያችን (ጉዳዩ ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ ስማቸው እንዳይገለጽ አሳስበዋል) ከሆነ በቁጥጥር የማዋል ዘመቻው በዕቅድ የተከናወነ ነው የሚሉት። ንጉሡ ኮሚቴውን ማቋቋማቸው ከተሰማ በኋላ ነበር ብዙም ሳይቆይ ሁሉም ሰዎች የተያዙት። ይህም የሆነው የሚፈለጉት ግለሰቦች አገር ውስጥ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው ይላሉ። ይህ ደግሞ እነ ልዑል አልዋሊድን ብቻ ሳይሆን አላሙዲንን የሚጨምር እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህ በሳዑዲ የተወሰደው ተግባር በሙስና ሽፋን ስም የተደረገ ቢሆንም ዋናው አጀንዳ ግን የፖለቲካ እንደሆነ የመረጃው ሰው ይናገራሉ። ምክንያቱም የሙስና ቢሆን ኖሮ እነዚህ ሰዎች ካላቸው ሃብት አኳያ የሚጠየቀውን ገንዘብ ከፍለው በዋስ ይለቀቁ ነበር። ቢለቀቁ እንኳን አገር ውስጥ እስኪገቡ መጠበቁ ኮሚቴው ካለው የጉዞ ዕገዳ የማድረግ ሥልጣን አኳያ ከአገር እንዳወጡ አፍኖ ለመያዝ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነው ይላሉ።

በኢትዮጵያና በዳያስፖራ በተቃዋሚውም ሆነ በወያኔ ደጋፊው ዘንድ ከተራ ግለሰብ ጀምሮ እስከ ራሳቸውን “ጋዜጠኛ፣ ተንታኝ …” ብለው በሚጠሩ ሁሉ አንዳች ልዩነት ሳያደርጉ “የደሃ አባት፣ ሥራ ፈጣሪ፣ የሕዝብ ደራሽ፣ ከእጃቸው በልቻለሁ፣ ወዘተ” እየተባለ በተለያዩ ቁልምጫዎች የሚጠራው የአላሙዲ መያዝ ከተራዎቹ “ፍርፋሪ ለቃሚዎች” በተለየ ህወሓትን በእጅጉ እንደሚጎዳው ጎልጉል ያገኘው መረጃ ይጠቁማል። በተለይ ለዘመናት ግብር ሳይከፍል የኢትዮጵያን ሃብት በመመዝበር ድርጅቶቹን ሲያንቀሳቅስ መኖሩ አሁን እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች በማን ቁጥጥር ሥር እንደሚሆኑና የዕዝ ሠንሠለቱስ እንዴት ተያይዞ እንደሚቀጥል አወዛጋቢ ይሆናል ተብሏል።

ለአስር ሰዎች ሥራ “ለመፍጠር” የሺዎችን የመኖር ኅልውና በመንፈግ ከዓለም የሃብታሞች ተርታ ለመሰለፍ የበቃው አላሙዲን ሥራ ፈጣሪ ተብሎ በተቃዋሚውም ሆነ በህወሓት ደጋፊ መሞካሸቱ የፖለቲካችንን መክሸፍ የሚያመለክት መሆኑን ሲናገሩ የቆዩ ይህ ሥራ መፍጠር ሳይሆን የኔ ከተሳካልኝ ስለሌላው አያገባኝም ዓይነት ሆዳምነት ነው ይላሉ። በድለላ በሚባል ዓይነት የፊትለፊት ሰው በመሆን ሃብት ካካበተው አላሙዲን፤ “ከእጃቸው በልተናል” የሚሉት ህወሓትንና ኤፈርትን ያለመታከት በሚወቅሱበት “ብዕራቸው” አላሙዲንን ዝም ማለታቸው የሚዲያውን መደዴነት፣ አድርባይነትና ጥቅመኝነት የሚያሳይ ነው ይላሉ።

ራሱን “ጋዜጠኛ” ብሎ በመጥራት ከሚዘግብለት ሠንደቅ ጋዜጣ ጎን ለጎን (Honorable Dr Sheik Mohammed Hussien Ali Al-Amoudi) የሚል የፌስቡክ ገጽ የሚያስተዳድረው ፍሬው አበበ በአላሙዲ ስም በከፈተው ገጽ ላይ “የሼህ ሙሐመድ እስር አልተረጋገጠም” በማለት ሲጽፍ በራሱ የፌስቡክ ገጽ ደግሞ “ሼህ አልአሙዲ አልታሠሩም!” በማለት ገልብጦ መጻፉ “ለሆዱ ያደረ ኅሊናቢስነቱን ብቻ ሳይሆን የአላሙዲ በቁጥጥር ሥር መዋል ምን ያህል መደናገጥ መፍጠሩን የሚሳብቅ ነው” በማለት መረጃውን የላኩልን የጎልጉል የፌስቡክ ወዳጅ ተናግረዋል።

ሌላው የአላሙዲ ተጧሪ የEthiopiaFirst.com ቢኒያም ከበደ ዜናውን ለማመን ከከበዳቸው በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሆኗል። ቢኒያም በፌስቡክ ገጹ “… አዲሱ መጤው ልዑል ተፎካካሪ ልዑላልን ሪያድ ወደሚገኘው Ritz Carlton Hotel አሰልፎ በመውሰድ ቃላቸውን እንዲሰጡ ማድረጉ ነው። በዚህ መሀከልም የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆኑት ሼህ ሙሓመድ አል-አሙዲም ቃላቸውን እንዲሰጡ ወደ ግዙፉ ሆቴል መወሰዳቸውን ሰምተናል፤” “… እግዚአብሔር ይጠብቃቸው” በማለት ታማኝነቱን አስመስክሯል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ለቢኒያም መልዕክት በሌሎች የፌስቡክ ገጾች ላይ “የጣናን እምቦጭ እነቅላለሁ ያለው ትልቁ እምቦጭ አላሙዲ እምቦጭ አለ” በማለት አላግጠዋል።

በአላሙዲን ቀኝ የሚታየው አብነት ነው

በርካታዎች እየሞቱና መብታቸው ተገፍፎ በእስር እየማቀቁ በነበሩበት ወቅት የንብ ካኔተራ በመልበስ የህወሓት ደጋፊነቱን በገሃድ ያስመሰከረው አላሙዲንን ከህወሓት ለይቶ “የሕዝብ ሰው” አድርጎ ማቅረብ ለህወሓት ያለን “ጥላቻ” ከአላሙዲ “ትግሬ” አለመሆን ጋር የተገናኘ ይመስላል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። ከዚህም አልፎ የዛሬ ሃያ ስድስት ዓመት አካባቢ በኢህአዴግ ሰዎች ሎንዶን ላይ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መጠመቁን የሚናገረውን አላሙዲንን እና ድርጅቶቹን ከኤፈርት ለይቶ ኢትዮጵያዊ አድርጎ ማቅረብ ጭፍንነት ብቻ ሳይሆን ህወሓትን የመቃወሚያው መሠረት አልባነትን የሚያሳይ እንደሆነ ድምጻቸው የታፈነ ጥቂቶች ሲናገሩት የቆዩት ጉዳይ ነው። አላሙዲንና ሚድሮክን የምናሞግስ ከሆነ ስብሃት ነጋንና ኤፈርትን ልንቃወም የምንችልበት መሥፈርት የለንም በማለት እነዚሁ ወገኖች መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ።

ሳውዲ በወሰደችው በዚህ ያልተጠበቀ እርምጃ አፈ-አላሙዲን በመሆን ሥራውን የሚያስፈጽመው አብነት ገብረመስቀልና ከእርሱ ጋር ያስተሳሰራቸው የህወሓትና ሌሎች የጥቅም ተካፋዮች ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መውደቁ የማይቀር እንደሚሆን ይታመናል። “አላሙዲን ኢትዮጵያ ውስጥ መታሰር አይችልም ነበር፤ ምክንያቱም እርሱ አገሪቷን አስሯታል፤ አትበቃውም። እርሱን በቁጥጥር ሥር ማዋል የሚችለው ሌላ ኃይል ነበር፤ አሁን አይተነዋል፤ ከዚህ በኋላ ድርጅቶቹን እንደ እርሱ ሆኖ መምራት የሚችል ግለሰብ መኖሩ በጣም አጠራጣሪ ነው፤ ይህ ደግሞ ለድርጅቶቹ ብቻ ሳይሆን ለህወሓትም ትልቅ ዱብዕዳ ነው፤ አገር ውስጥ ካለው እንቅስቃሴ አኳያ ሁኔታዎች በዚሁ አይቀጥሉም፤ በቅርብ በርካታ ያልተጠበቁ የሚመስሉ ለውጦችን ማየት እንጀምራለን” በማለት የጎልጉል መረጃ አቀባይ አስረድተዋል።

ማስታወሻ፤ አላሙዲንን “አንተ” ብለን መጥራታችን ለሚያሳስባችሁ ይህንን እንድታነቡ ይሁን።


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: News Tagged With: Full Width Top, Middle Column

Reader Interactions

Comments

  1. Mulugeta Andargie says

    November 7, 2017 03:09 am at 3:09 am

    ጎልጉል? ደላላው!!???
    ምን ማለት ፈልገህ ነው?
    ደላላስ ምንድን ነው??
    ያለቦታ የገባ መጣጥፍ ነው??
    ሳጋ ነው!??
    ድሪቶ ነው?
    መቼም ካንተ በላይ ማወቅ ላሳር ነው!!

    ሼኩ ያይናችን ብሌን: ደም!
    የህዝባችን እንባ አባሽ! ዝናም
    የለውጥ አራማጅ ቅመም
    ሃገር በቀል ደማም! እንዲያም ብሎ ተማም!

    እንጂ አላሙዲን ደላላ?
    ፈረንጅ ብላ!
    ቃላት ያለቦታው ተሸንቅሮ ተጣላና ተባላ!
    ለሼኩ ስም ፈልግና ተጣላ!

    ማን እንደ ሼኩ! ማን ኣለ?
    እጁ ለስጦታ የታደለ!
    በሃብት የተንጣለለ!
    ደላላ ተባለ??
    ወጊድ!!ደርሶ ወሬ ከወሬ ከተዳበለ
    ኣላሙዲን ደላላ ተባለ??
    ወሬ ያለቦታው ኮበለለ!!
    ጭቃ ያለቦታው ተለጠፈ! መሬት ተጣለ!!!

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የ-አብሮነት ማኅበር የመረጠው ሕቡዕ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይፋ ሆነ November 5, 2025 12:06 pm
  • “የኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት አይቀሬ ነው … “ፅምዶ” ራዕይ ዓልባ” ነው – ሼትል ትሮንቮል October 26, 2025 10:15 pm
  • አሜሪካ ስላልተቀበለችው ነው “የሽሽግር መንግሥት” ስብሰባው በአምስተርዳም ተካሄደው October 25, 2025 11:09 pm
  • በዓባይ ግድብ ምረቃ፡ የሕዝብ ደስታ፣ የቴድሮስ ካሳሁን ዝምታ September 14, 2025 04:27 am
  • ኢትዮጵያ የውኃ ኑክሊየር ማብላያዋን ልታስመርቅ ነው  August 29, 2025 11:46 pm
  • መከላከያ በፋኖ አመራሮች ላይ እርምጃ ወሰደ፤ ዘመነ በ“አንድ ማንኪያ ቅንነት” አንድ እንሁን አለ August 23, 2025 12:35 am
  • ፋኖን በፋይናንስና በሎጂስቲክስ የሚደግፉ የጎጃም ባለሃብቶች ከስደት ሊመለሱ ነው August 14, 2025 12:42 am
  • የበቀለ ገርባ የአሜሪካ ጥገኝነት ማመልከቻ ውድቅ ተደረገ August 13, 2025 12:16 pm
  • ሞዐ ተዋሕዶ “ነጻ አውጪ ግምባር” – ሞነግ August 13, 2025 12:58 am
  • የሃይማኖትና የመንግሥት ጥምረት በረከት ወይስ መርገም?  August 5, 2025 09:18 pm
  • የባከነ የስደት ሕይወት ከደባርቅ እስከ ኖርዌይ July 29, 2025 05:44 pm
  • “በዚህ ዓመት መጨረሻ ትግራይን እንቆጣጠራለን”፤ ቲፒኤፍ July 22, 2025 01:28 am
  • Rusted screws, metal spikes and plastic rubbish: the horrific sexual violence used against Tigray’s women July 4, 2025 01:48 am
  • በሞርሞን ቤ/ክ ዕርዳታ የኪዳነምህረት ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ማምለኪያ ሥፍራ አገኘች July 2, 2025 01:28 pm
  • የበረከት ስምዖን “አየር ላይ ትዕይንት” አየር ላይ ተበተነ July 2, 2025 01:24 am
  • “ዐቢይ ይውረድ፣ እኛ እንውጣ፣ በተራችን እንግዛ” ስልቴዎች (ስብሃት፣ ልደቱ፤ ቴዎድሮስ) June 11, 2025 01:56 am
  • ኤሊያስ መሠረት የሚሠራው ለማነው? ለብጽልግና? ወይስ …? June 3, 2025 01:27 am
  • በግንቦት 20 – የሁለት መሪዎች ወግ May 28, 2025 02:01 am
  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am
  • ከትግራይ ሾልኮ የወጣው ምሥጢራዊው ሰነድ ምንድነው? May 20, 2025 09:18 am
  • በደቡብ ጎንደር በጸዳሉ ደሴ የተመሩት 72 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ May 19, 2025 02:24 pm
  • የተመሠረተው የፋኖ አደረጃጀት ዋነኛ ዓላማው ድርድር መሆኑ ተነገረ May 14, 2025 11:07 pm
  • ከፍተኛ የፋኖ አመራሮች መገደላቸው ተነገረ May 6, 2025 10:40 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2025 · Goolgule