በሴቶች ጭፈራ ደምቆ በወንዶች የሚታጀበው የአኾላሌ ባሕላዊ ጭፈራን ለማስተዋወቅ የሁለት ቀን ፌስቲቫል በደሴ ከተማ ተካሂዷል።
እራሷን ተሰርታ ወለባ ስጋለች፣ እንሶስላ ሙቃ ሎሚ ጨብጣለች፣ ያች ያገሬ ልጅ እሷዉ ትሆናለች። ሲሉ ጨዋታውን ደመቅ ያደርጉታል የወሎ ወይዛዝርት። ታዲያ በዚህ ጭፈራ ጊዜ ወንዶቹ ሴቶቹን ተቀላቅለው ጭፈራውን ደመቅ ያደርጉታል።
አኾላሌ በሃይማኖታዊና ሃይማኖታዊ ባልሆኑ ክብረ በዓላት የሚከናወን ብዙ ጊዜ ጥር ወር ላይ በአርሶ አደሩ የዕረፍት ወቅት፣ በመተጫጫና ጋብቻ እንዲሁም የመዋቢያ ጊዜ የሚከናወን ባህላዊ ጨዋታ ነው።
በአብዛኛው በወሎ በተለይም በተውለደሬ የሚከወነው ተዉኔት አዘል ባህላዊ የወጣቶች ጭፈራ ሃይማኖት ሳይለይ በክርስትናም በእስልምና ተከታዮችም ይካሄዳል።
አሆላሌ ባህላዊ ጨዋታ የራሱ የኾነ የመከወኛ አጋጣሚዎች እና ወቅቶችም ያሉት ነው። በሁለቱም እምነቶች ዓበይት በዓላትን ተከትሎ ጨዋታው ይከናወናል።
ይህ ጨዋታ ከሚሊዮን በላይ ቱሪስት እንደሚጎበኛቸው እንደ ብራዚል የሪዮ ዴጄኔሮ ካርኒቫል በልዩ ልዩ የባህል ቡድኖች ውድድር አማካኝነት እየተከወነ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ሊያመጣ የሚችል ከመሆኑም በላይ የወሎ፣ የአማራ ክልል፣ የኢትዮጵያ ብሎም የዓለም ህዝብ ህብት ሆኖ በዩኔስኮ ሊመዘገብ የሚችል ነው።
ለዚህ የሚሆን የተቀናጀ ስራ በማከናወን ወሎን ማልማት የነበሩ እሴቶችን ማጠናከር ፈርጀ ብዙ ፋይዳም ያስገኛል።
በዓሉ በተለይም በአረፋ፣ በአሹራ፣ በገና፣ በጥምቀት፣ በአስተርዮ ማርያም እና በጥር ሚካኤል በዓላት በስፋት ይከናወናል።
ይህንን ዕንቁ ባሕል ለማስተዋወቅ ታሳቢ ያደረገ የሁለት ቀን ፌስቲቫል በደሴ ከተማ ተካሂዷል። (አሚኮ፤ ፎቶ ተስፋዬ ይመር)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply