ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን እንደ ጎልያድ በማስመሰል በአንድ ምሳሌያዊ ዳዊት እንዲግደሉ የሃይማኖታዊ ግድያ ጥሪ ያስተላለፉት አቡን ሉቃስ የወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው። አቡነ ሉቃስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 247 እና 251 ድንጋጌ ተላልፈዋል በሚል ክስ ተመሰረተባቸው፡፡
ክሱ የቀረበባቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ሕገመንግስታዊና በሕገመንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ነው። በአቡነ ሉቃስ ላይ ሁለት ክሶችን ያቀረበው የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ነው፡፡
ይህም ተከሳሽ አቡነ ሉቃስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 247 (ሐ) እና አንቀጽ 258(ሀ) ስር የተደነገገውን ድንጋጌ እንዲሁም የወንጀል ህግ አንቀጽ 251 (ሐ) እና አንቀጽ 258 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚሉ ሁለት ክሶች ናቸው የተመሰረቱባቸው።
በተጨማሪም ተከሳሹ በፀረ ሰላም ሃይሎች የሚፈፀሙ የወንጀል ተግባሮችን ተከትሎ መንግስት ፈፃሚዎቻቸውን ለሕግ ለማቅረብ እና ሕግ ለማስከበር የሚያደርግባቸው ጥረቶችን ለማደናቀፍ እና ህዝብ መንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ ማነሳሳታቸው በክሱ ተመላክቷል።
የክስ ዝርዝሩ የደረሰው ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ፋና)
አቡን ሉቃስ ይህንን የግድያ ጥሪ ካስተላለፉ በኋላ የኦርቶዶክስ ቤተክስቲያን ጳጳሱን እንድታወግዝ ከተለያዩ አካላት ጥያቄ ቢቅርብላትም ሳትፈጽመው ቀርታለች። ይህም በርካታ በሚባሉ ምዕምናኖቿ ዘንድ ቅሬታን የፈጠረ መሆኑ በስፋት ይነገራል።
በወቅቱ ካለው የፖለቲካ ትኩሳት አኳያ በአደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን ባያሰሙም ጥቂት የማይባሉ የእምነቱ ተከታዮች “ጠቅላይ ሚኒስትሩን የምንቃወም ብንሆንም በዚህ ልክ ግን ግድያ እንዲፈጸምባቸው በተለይ ከሃይማኖት አባት መስማታችን አሳፍሮናል” በማለት በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ተስተውለዋል።
“ጠላትህን ውደድ” የሚለውን የወንጌል ቃል ፍጹም በመጻረር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ግድያ እንዲፈጸም ሃይማኖታዊ ጥሪ ያስተላለፉትን አቡን ሉቃስ ጉዳይ በተመለከተ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቡነ አብርሃም ከጥምቀት በዓል በፊት መልስ ሰጥተው ነበር። በአንድ በኩል ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶስ መታየት ነው ያለበት ያሉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ልናወግዝና መግለጫ ልንሰጥ አስበን ነበር ግን የሚያስከትለውን መጠላለፍ ተመልክተን ትተነዋል ማለታቸው ይታወሳል።
ይህንን የአቡነ አብርሃም ንግግር የሰሙ “እንደ ቅዱሱ ቃል የአቡነ ሉቃስን ንግግር ማውገዝ ተገቢ ነው፤ ግን ካወገዝን ደግሞ ከፋኖ እና ከደጋፊዎቻቸው ጋር ያጣላናል” በሚል የተረዱት እንዳሉ ብዙዎች ይስማማሉ።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
በታሪክ አዱኛ
Tesfa says
የእኛ ችግር ስለ ፍትህና የህዝቦች ሰላም በአደባባይ ከመሟገት ይልቅ ምላጭ መሳብና ማሳብ ይቀለናል። ለነገሩ ሁሉ በሚባል ደረጃ እምነቱ ሁሉ የማታለያና የመኖሪያ ብልሃት ምንጭ በመሆኑ እንዲህ አይነቱ ገድለህ ሙት የሚለው አስተሳሰብ እንደ ባህል ተወስዷል። ሲጀመር የጠ/ሚሩ መገደል በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ለውጥ አያስገኝም። ግን ያው በሃሳብም ሆነ በጦር ሜዳው የሚፋለሟቸው ሁሉ በሞታቸው ዳንኪራ ሊመቱ ይችላሉ። ያ ቢሆን ጊዜአዊ ጭፈራ ነው። ለገባው የጠ/ሚሩ ህልፈት የኢትዮጵያን ችግር አይፈታም። የምድሪቱ ችግር በሞትና በደም የሚፈታ ቢሆን ኑሮ እልፎች እረግፈዋል በመርገፍም ላይ ናቸው። ለውጥ ግን የለም። ከነብር የሸሽው እዘንዶ አፍ ገባ እንጂ!
የሃገሪቷ ችግር የአፓርታይድ የቋንቋና የክልል ፓለቲካ ነው። ሰው በቋንቋው ያስብ የሚሉ እብዶች ያሉበት ሃገር ነው። ሰው በቋንቋው ሳይሆን የሚያስበው በጭንቅላቱ ነው። የአንድ ሃሳብ ጥንስስም በቋንቋ ብቻ ሳይሆን በልዪ ልዪ መንገድ ሊገለጥ ይችላል። ለምሳሌው ሰአሊዎች ምስልን ሲነድፉ በኦሮምኛ ወይም በአማርኛ እያሰቡ አይደለም። ወደ ጭንቅላታቸው የመጣውን ምናባዊ ነገር አለዚያም ከሚታየውና ከሚዳሰሰው ቆንጥረው ነው ስዕላቸውን ነፍስ የሚዘሩበት። ስለዚህ የቋንቋ አምልኮና የእኔ ብቻ እይታ ውሃ አይቋጥርም። ቋንቋ መግባቢያ እንጂ ሌላ ተግባር የለውምና!
እነዚህ የዘመኑ የዘር ሰካራሞች ናቸው አሁን ምድሪቱን እያመሱ ያሉት። እድሜ ለሻቢያና ለወያኔ ኦነግን ጥሩ አርገው ከክፋት ጽዋቸው ስለ ጋቷቸው አሁን እውነት ፊታቸው ላይ ቆማ ተው ብትል ሰሚ ጀሮ የላቸውም። ስብዕና ያላቸውን ኦሮሞዎች እየገደሉና እያሰሩ ትግላችን ለህዝብ ነው ይሉናል። ተግባራቸው ሁሉ ሻቢያና ወያኔን ይሸታል። ሙት ይዞ ይሞታልና! የብሄር ፓለቲከኞች መከራ አዝናቢዎችን እንጂ ነጻነት አፍላቂዎች ሆነው አያውቁም። ታሪክን ማየት ነው።
በእኔ እይታ የእምነት ሰዎች ስለ ፍትህ በአደባባይ ከማንባትና ከመከራከር አልፎ እከሌን ግደል ያን ያዝ የሚሉ ከሆነ እምነታቸው ብላሽ ነው። እይታቸው ከስሜት የጠራ፤ ብሄር ብሄረሰብ የሚባሉትን በእኩል አይን የሚያይ፤ ለሚበደሉ ሰዎች ያለ ምንም አድሎ ጥብቅና የሚቆም፤ የበደሉ ሰዎችን በመረጃ የሚሞግት መሆን ይገባዋል። ከዚህ በተረፈ በለውና በይውን መስቀል ሳይዙ ከባህር ማዶም ከሃገር ቤትም እሳቱ እንዳይበርድ ያላሰለሰ ጥረት የሚያደርጉ ስላሉ የመንፈሳዊ አባቶች ሚና ከላይ እንደጠቀስኩት ቢሆን ለሃገርም፤ ለምዕመናንም ለቤ/ክርስቲያንም መልካም ይመስለኛልና። መገዳደሉን ለሚፈላለጉት ቢተውት ይሻላል ባይ ነኝ።