የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 100 ቀናት የሥልጣን ጊዜ አስመልክቶ ጽህፈት ቤታቸው በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑትን ጉዳዮች በሚከተለው መልኩ ማብራሪያ ሰጥቶበታል።
- ውስጣዊ መረጋጋትን ከመፍጠር አኳያ
ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡበት ወቅት በሁሉም ረገድ እጅግ ፈታኝ የሆኑ ጉዳዮች ባረበቡበት ወቅት ነው። መንግስት ውስጣዊ መረጋጋት ማስፈን ተስኖት ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የተገደደበት፣ እዚህም እዚያም ግጭቶችና ትርምሶች የሚፈሉበት፣ በማንኛውም ቅፅበት አዲስ አበባ በኹከት ልትናጥ እንደምትችል የምታስፈራበት፣ ተረጋግቶ መስራትና መኖር አዳጋች የሆነበት፣ ኢኮኖሚው ተንገጫግጮ የነበረውን ፍጥነት ለማስቀጠል የተቸገረበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ጫፍ የደረሰበት፣ ኢህአዴግ በየጊዜው መግለጫ ቢያወጣም ተሰሚነቱ/ተዓማኒነቱ እጅግ የቀነሰበት፣ … ነበር። ይህንን ነባራዊ እውነታ ከመቀየር አንጻር ባለፉት 100 ቀናት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው።
1.1. ተስፋን የሚያጭሩ ንግግሮች
ገና ወደ ስልጣን ከመምጣታቸውም በፊት “ቃል ይገድላል፥ ቃል ያድናል” ይሉ የነበሩት ጠ/ሚ/ር ዶ/ር ዐብይ፣ ባለፉት 100 ቀናትም ይህን እምነታቸውን በተግባር አሳይተዋል። በበዓለ ሲመታቸው ያደረጉት ንግግር ከላይ የነበረውን የጭንቀት መንፈስ ከመግፈፍ አንጻር ከፍተኛ ሚና ተወጥቷል። በዚህ ንግግራቸው ስለአንድነት፣ ስለኢትዮጵያዊነት፣ ስለዴሞክራሲና የሃሳብ ብዝሃነት ያነሷቸው ሃሳቦች እና ባልተለመደ ሁኔታ እናታቸውንና ባለቤታቸውን ለማመስገን የሄዱበት ርቀት ሰዎች ለውጡን ከምር (seriously) እንዲያዩት ያስቻለ የመጀመሪያው እርምጃ ነበር። እስካሁንም ድረስ እንደ ጥቅስ የሚነሱ ዓ/ነገሮች (ስንኖር ኢትዮጵያ ስንሞት ኢትዮጵያዊ)፣ ለቀጣይ ስራዎቻቸው መነሻ የሆኑ አቅጣጫ አመላካቾች (የኤርትራ ግንኙነት)፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን የምር የማስፋት እርምጃዎች፣ … የተንፀባረቁበት ንግግር ነበር። ከዚህም በኋላ በየክልሉ ባደረጓቸው ንግግሮች የየአካባቢውን ቋንቋ በመቀላቀል፣ የአካባቢውን ባህል በማንጸባረቅ፣ የምር የሚያማቸውን ጉዳይ ከልብ በመስማትና የሚያረካ ምላሽ በመስጠት ሁሉም ተስፋ እንዲያድርበትና ለለውጡ ድጋፉን እንዲሰጥ አድርገዋል።
1.2. ጉብኝቶች
ባለፉት ሶስት ዓመታት ችግር ፀንቶባቸው የነበሩ አካባቢዎችን ቅድሚያ በመስጠት በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች በመገኘት ንግግር ለማድረግና ህዝቡን ለማወያየት ባለፉት ሶስት ወራት እረፍት የለሽ ጉዞዎችን አድርገዋል። በዚህም በደረሱበት ሁሉ የአካባቢውን ቋንቋና ባህል በማንጸባረቅ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሪ መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል።
1.3. የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት
የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። ከእነዚህም መካከል በዋነኝነት የፖለቲካ አመራር እስረኞችን መፍታት፣ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ የአገር ውስጥ ድርጅቶችን መሰረዝ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ‘ተፎካካሪ’ እያሉ መጥራትና አብረው እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረብ (በቤተመንግስት ተገናኝቶ መወያየት)፣ ለማፈን በርካታ ገንዘብ ይወጣባቸው የነበሩ ሚዲያዎችን መተውና ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረብ፣ ታግተው የነበሩ በርካታ ድረገፆችንና ጦማሮችን ነጻ መልቀቅ፣ …. ይጠቀሳሉ። እነዚህ ውሳኔዎች ለውጡ የምር መሆኑን በማሳየት መንግስትን በመቃወም ለበርካታ ዘመናት የኖሩ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ሳይቀር ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከለውጡ ጎን እንዲቆሙ አድርጓቸዋል። ይህ የይቅርታ ምህረት አሰጣጥ ሂደቱ ወጥ እንዲሆን የምህረት አዋጅ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።
ከዚህም በተጨማሪ በመንግስት ቤት ውስጥ ያሉ ችግሮችንና ክፍተቶችን በፓርላማ ሳይቀር በግልፅ በማንሳት ‘እኛም አሸባሪ ነበርን’ እስከማለት መድረሳቸውና ይህን ችግር ለመቅረፍም መሰረታዊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመራቸው ተጠቃሽ ክስተት ነው። ሚዲያዎች በአጠቃላይ (የመንግስት ሚዲያዎችም ጭምር) በነጻነት እንዲዘግቡና በመንግስትም ጭምር ያሉ ክፍተቶችን ያለገደብ እነዲዘግቡ በመደረጉ በተለይ በእስረኞች አያያዝ ላይ የተፈጸሙ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን ማጋለጣቸው የሚጠቀስ ነው።
ከዴሞክራሲ ምህዳር መስፋት ጋር ተያይዞ ሊጠቀስ የሚችለው ባለፉት ሶስት ወራት በበርካታ አካባቢዎች የተደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች ናቸው። እነዚህ ሰላማዊ ሰልፎች የተለያዩ አርማዎችና ሰንደቅ ዓላማዎች የታዩባቸውና የተለያዩ መልዕክቶች የተላለፉባቸው ናቸው። ዴሞክራሲ ማለት ትክክል የሆነው ብቻ ሳይሆን የተሳሳተ ሃሳብም ቢሆን ሰላማዊ እስከሆነ ድረስ የሚንጸባረቅበተን እድል መፍጠር በመሆኑ፥ እነዚህ መድረኮች መፈጠራቸውና በህዝቡ ልብ ውስጥ ያለው ነገር መንጸባረቁ መልካም ጅምር ነው።
1.4. የደህንነት ተቋማት ሪፎርምና የአመራሮች መቀያየር
ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ ብዙ ትችት እና የእምነት ማጣት ስሜት ያስተናግዱ ከነበሩ ተቋማት ዋነኞቹ የደህንነት ተቋማት ናቸው። እነዚህን ተቋማት ሪፎርም ማድረግና አስፈላጊ በሆነባቸው ቦታዎች የአመራር ለውጦችን ማድረግም አንዱ የለውጡ አካል ነበር። የአመራር ለውጡ በደህንነት ተቋማትም ሳይገደብ በሁሉም ተቋማት ላይ በእውቀት፣ ክህሎት እና የአመራር ብቃት ላይ የተመሰረተ ድልድል ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ፥ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርን እና ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምን በክብር የመሸኘት ተግባራት ተከናውነዋል። ሌሎች ነባር አመራሮችም በጡረታ እንዲሰናበቱ ተደርገዋል።
- በዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ረገድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከፍተኛ ልዩነት ከፈጠሩባቸው ጉዳዮች አንዱ የውጭ ግንኙነት ነው። በዚህም ከኤርትራ ጋር ተፈጥሮ የነበረውን ‘ሞት አልባ ጦርነት’ ማፍረስ፣ ከዓለም አቀፍ ሃያላን አገራት ይልቅ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ መስጠት፣ ከዚህ በፊት ይህን ያህል የጎላ ግንኙነት ተፈጥሮባቸው ያልነበሩ አገራት ጋር መልካም ቁርኝት መፍጠር እና ከጎረቤቶች ጋር አዳዲስ ጉዳዮችን ያካተተ የስምምነት ማዕቀፎችን መፍጠር ይጠቀሳሉ። ከዚህ አንጻር ዋና ዋናዎቹ ውጤቶች የሚከተሉት ናቸው።
2.1. ኢትዮ-ኤርትራ
ከኤርትራ ጋር የነበረው ‘ሰላምም ጦርነትም ያልሆነ’ ውጥረት ለመፍታት መልካም ጅምር መፈጠሩ ቀዳሚው ውጤት ነው። በዚህም በሁለቱ አገራት መካከል ተደንቅሮ የነበረው ‘ጥቁር መጋረጃ’ ተቀዷል። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደምም የሰላም ጥሪዋን ለኤርትራ በተደጋጋሚ አስተላልፋ የምታውቅ ቢሆንም፥ በኤርትራ በኩል በግን ‘የኢትዮጵያ ወታደሮች የዓለም አቀፍ ገላጋይ ፍርድ ቤት ከወሰነልኝ ቦታ እስካልወጡ ድረስ አልደራደርም’ በማለት ይመልስ ነበር። ባለፉት ሶስት ወራት በተደረጉ ጥረቶች ግን ይህን ቅድመ ሁኔታ በመተው ልዑካኑን ልኮ ወደ ውይይት ገብቷል። ጠ/ሚ/ር ዐብይም ይህን የሰላም ፍላጎት እውቅና ለመስጠት በሚመስል መልኩ ልዑካን ቡድን በመላክ ፈንታ ራሳቸው ወደ አስመራ በመጓዝ የሰላም ምክክር ሂደቱን በከፍተኛ ሁኔታ አጉነውታል። በአስመራ የነበረውን የኤርትራውያንን አቀባበል ያያ ማንኛውም አካል ይህን የሰላም ጥረት ወደ ኋላ ለመመለስ ይዳዳዋል ማለት ይከብዳል።
2.2. የጎረቤት አገራት ቀደምትነት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በሶስት ወራት ውስጥ ወደ ሁሉም የጎረቤት አገራት ጉዞ ያደረጉ ሲሆን የደቡብ ሱዳንን ፕረዝዳንትና ተቃዋሚም በአዲስ አበባ አግኝተው አወያይተዋል። በዚህም ቅድሚያ የሚሰጡት ለጎረቤት አገራት እንደሆነ አሳይተዋል። በፖለቲካ ሳይንስ እንደሚባለው፥ “ማንኛውም አገር ወዳጅ አገር የመምረጥ መብት አለው፤ ጎረቤት አገር ግን አይመርጥም”። ጎረቤት አገር በብዙ ረገድ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው። ጠ/ሚሩም ይህን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ለከባቢያዊ ጉዳዮች ቅድሚያውን ሰጥተዋል።
2.3. በአዳዲስ ጉዳዮች ላይ ስምምነት መድረስ
እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ መንግስት ከጎረቤት አገራት ጋር በነበረው ግንኙነት በሰጥቶ መቀበል መርህ የተመሰረተ የመጠቃቀም አካሄድ እንዲኖር ቢሰራም ባለፉት 100 ቀናት የተደረጉት ድርድሮች ግን ከዚህም ላቅ ያሉ ነበሩ። ከጂቡቲ ጋር በተደረገው ውይይት የወደብ ድርሻ የመግዛትና በኢትዮጵያ ከሚገኙ ውጤታማ ድርጅቶች መሃል የአየር መንገድና የኤሌክትሪክሲቲ ድርጅቶችን ድርሻ ለመሸጥብ ሃሳብ ቀርቦ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ይህም ኢትዮጵያ ውድ ዋጋ ከምታወጣለት የወደብ አገለግሎት ተጠቃሚ እንድትሆን በማድረግ የተረጋጋ የወደብ አገልግሎት ዋጋ እንዲኖር ያደጋል። ቀስ በቀስም ይህ ድርሻ እያደገ ከሄደ በተለይ ከደህንነት አንጻር የሚኖሩ ውስንነቶችን ሊቀርፍ ይችላል።
2.4. በቀይባህር ጉዳይ ላይ ተይዞ የነበረው ቸልተኛ አቋም መለወጥ
በቀይ ባህርና ኤደን ባህረሰላጤ የተለያዩ ዓላማዎችን ያነገቡ በርካታ ሃይሎች ማንዣበብ ከጀመሩ ቆየት ብለዋል። በተለይ የየመን የእርስ በርስን ግጭት ተከትሎ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስትና አማፂያንን በመደገፍ በርካታ የአረቡ ዓለም መንግስታትና ኢራን በሁለት ጎራ ተከፍለዋል። ኢራን፣ ኳታር፣ ቱርክ እና ሱዳን በአንድ በኩል፤ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ባህሬን እና ግብፅ በሌላ በኩል ሆነው የየመንን ምድር የጦር አውድማ አድርገዋታል። ለዚህ ስምሪትም በተለይ ኤርትራ ላይ የተለያዩ የጦር ሰፈሮችንና ቤዞችን አቋቁመዋል። ግብፅም በዚህ አስታካ ኤርትራ ላይ የጦር ቤዝ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ጀምራ ነበር። በዚህ የአገራት አሰላላፍ ውስጥ ኢትዮጵያ የነበራት ሚና ከሁለት አንዱን በመምረጥ ላይ ያልተመሰረተ ነበር። ይህ መሆኑ ከሁለቱም ጥቅም ለማግኘት የማስቻል እድል ቢኖረውም ጉዳቱ ግን ከፍ ያለ ነበር። ይህን እውነታ ከመቀየር አንጻር ባለፉት ሶስት ወራት በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል። በዚህም በተለይ በሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጉብኝት በብዙ ረገድ ፈር ቀዳጆች ሲሆኑ፤ ከግብፅ እና ኤርትራ ጋር ቀጥለው ለተደረጉት ውይይቶችም አስቻይ ሁኔታን የፈጠሩ ነበሩ። (የኤርትራው ልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ የመጣው በዱባይ አየር መንገድ ልዩ በረራ (chartered) እንደሆነ ልብ ይሏል!)
በቀይባህር እና በኤደን ባህረሰላጤ የሚከናወኑ ጉዳዮች በከፍተኛ ሁኔታ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩባቸው አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት። በመርከቦች ጉዞ መታወክ እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ከሚፈጠረው የኢኮኖሚ ጫና በተጨማሪ የአገሪቱ የኢንተርኔት መግቢያ በር (gateway) በቀጥታ ልንከላከለው በማንችለው መልኩ በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኝ በመሆኑ የደህንነት ፋይዳውም የጎላ ነው። ከዚህም ባሻገር ግብፅ እንዳቀደችው ተሳክቶላት ቢሆን ኖሮ ምፅዋ ወይም አሰብ ላይ የጦር ሰፈር አቋቋመች ማለት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚኖረው አንድምታ ከፍተኛ ነበር። እንዲህ አይነት ቀጣይ ስጋቶችን ከመቀነስ አንጻር ባለፉት 100 ቀናት የተደረጉት ዋና ዋና እርምጃዎች፥ ከሁሉም ጎረቤት አገራት ጋር በወደብ ኢንቨስትመንት መተሳሰር እና የባህር ሃይልም የማቋቋም ፍላጎት መንጸባረቅ የሚጠቀሱ ናቸው።
- በኢኮኖሚ ረገድ
የሃገራችን ኢኮኖሚ ላለፉት አስር ዓመታት በከፍተኛ ቁጥር እያደገ የነበረ ቢሆንም፥ ባለፉት ሶስት ዓመታት ግን የውስጥዊ መረጋጋት አለመኖር እና ለረጅም ጊዜ እየተጓተቱ የመጡ የመንግስት ሜጋ ፕሮጀክቶች ምክንያት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ፕሮጀክቶች በሚጠይቁት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ልክ የኤክስፖርት አቅማችን ባለማደጉ፥ የውጭ ምንዛሪ አቅማችን ወራትን እንኳን የማይዘልቅ ሆኖ ነበር። በቁጥጥር መላላትና በባንክ ምንዛሪና በጥቁር ገበያ ምንዛሪ መካከል ሰፊ ልዩነት በመፈጠሩ የውጭ ምንዛሪው ዝውውር በኮንትሮባንድ ነጋዴዎች እጀ ለመውደቅ ጫፍ ደርሶ ነበር። ይህን እጥረት ተከትሎ በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ እና በአጠቃላይም በሌሎች ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ በመፈጠሩ ስራዎች ተቀዛቅዘው፣ የኑሮ ውድነቱም በሁለት አሃዝ ሆኖ ነበር። የውጭ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅማችን በመቀዛቀዙ ምክንያት የስራ አጥ ቁጥር ከፍ ብሎ ነበር። እነዚህን እና ሌሎችም ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለጊዜው ረገብ ለማድረግና በቀጣይ በዘላቂነት ለመፍታት ባለፉት 100 ቀናት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። ከእነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
3.1. ባለሃብቶችን ማወያየት
በሸራተን ሆቴል ውይይት እንዲሁም በቤተመንግስት የራት ግብዣዎች ተከናውነዋል። በተለይ በሸራተን የተካሄደው ውይይት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጥያቄዎቻቸውን ያነሱበትና ሰፊ ውይይት የተደረገበት ነበር። ባለሃብቶች እንደ ግለሰብና እንደ ድርጅት ሊወስዷቸው ስለሚገቡ ተገቢ እርምጃዎችና መርሆች የተወያዩበት ሲሆን፥ በመንግስት በኩልም ወደፊት ሊወሰዱ የሚችል አቅጣጫዎች የተመላከቱበት ነበር።
3.2. የውጭ ምንዛሪን እጥረትን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች
ከላይ እንደተገለፀው ኢትዮጵያ ገጥሟት ከነበሩት ችግሮች አንዱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው። ይህን እጥረት ለመፍታት በርካታ የአጭር ጊዜ እርምጃዎች ተወስደዋል። ከእነዚህም መካከል ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የተገኘው ድጋፍ የሚጠቀስ ሲሀን፥ ከዘላቂ እርምጃዎች ደግሞ የብሄራዊ ባንክ የአሰራርና የአመራር ስርዓት ማሻሻያዎች መደረጋቸው ይጠቀሳል።
3.3. የመንግስት ተቋማት አክስዮን ሽያጭ
የኢህአዴግ መንግስት በሚከተለው የልማታዊ መንግስት አስተሳሰብ በተመረጡ፣ የግሉ ባለሃብት ሊደርስባቸው በማይችላቸው እና ለውጭ ባለሃብቶች ተላልፈው ቢሰጡ ከፍተኛ ተጠቃሚነትን ሊያሳጡ በሚችሉ መስኮች ላይ መንግስት እንደሚሳተፍ ያስቀምጣል። ነገር ግን ልማታዊ መንግስት በባህርዩ የመጨረሻ ዓላማ ሳይሆን፥ መሸጋገሪያ በመሆኑ እነዚህ ተቋማት ላይ የሚኖረው ባለቤትነት በየጊዜው እየታየ እያነሰ እነደሚሄድና ቁልፍ የሆኑ ተቋማት ላይ ብቻ እነደሚወሰንብ ይታወቃል። ይህን መሰረት በማድረግም የመንግስት ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ተቋማትን ወደ ግል ይዞታ ሲያዞር ቆይቷል። ነገር ግን ይን እርምጃው ወደጥ ባለመሆኑ ምክንያት ባለፉት 27 ዓመታት ፕራይቬታይዝ ከተደረጉት ተቋማት ብዛት የማይተናነስ አዳዲስ ተቋማትን መስርቷል። ይህ አካሄድ እንዲጠራና ቀስ በቀስ ለግል ባለሃብቱ የመክፈት ሂደቱ እንዲጀመር ባለፉት ሶስት ወራት አዲስ ጅማሮ ተፈጥሯል። ይህም በአክስዮን መልክ ውስን ድርሻዎችን በመሸጥ የመንግስት እነደሆኑ የግል ባለሃብቱም እንዲሳተፍ ማድረግ ነው። …..
3.4. የእቅድና ቁጥጥር ስርዓት
ለረጅም አመታት በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የእቅድና ክንውን ግምገማ ግልፅነት የጎደለው ሆኖ ቆይቷል። ይሄው ችግር በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም የሚስተዋል ሲሆን ይሄንን ግልፅነት የጎደለውን አሰራር ለመቅረፍ የመስሪያ ቤቶቹ የእቅድ አፈፃፀማቸውን ከሚገመገመው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እቅድ ግምገማ ቋሚ ኮሚቴዎች በተጨማሪ ህዝቡም የሚገመግምበት ስርዓት ተፈጥሮ ከሚቀጥለው በጀት አመት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ ላይ ተደርሷል። መስሪያ ቤቶቹ እቅዶቻቸውን በበጀት አመቱ መጀመሪያ ላይ በዌብሳይቶቻቸው ላይ እንዲያስቀምጡ የሚደረግ ሲሆን ህዝቡ የየመስሪያ ቤቶቹን የክንውን ሁኔታ ጎን ለጎን እየተመለከተ የትኛው ተስርቷል የጥኛው አልተሰራም የሚለውን የሚገመግምበትና ያልተከናወነበት ምክንያትን መስሪያ ቤቶቹ የሚጠየቁበት አሰራር ይፈጠራል።
3.5. ዓመታዊ በጀት
የ2010 በጀት አመት መጠናቀቅን ተከትሎ ለ2011 ዓ.ም የሚሆን በጀት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተዘጋጀ ሲሆን ለአመቱ 346 ቢሊየን 915 ሚሊየን 451 ሺህ 948 ብር ረቂቅ በጀት ሆኖ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የህዝብ እንደራሲዎቹ ተወያይተውበት በጀቱ ፀድቋል። ከተመደበው በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 91 ቢሊየን 67 ሚሊየን 160 ሺህ 588 ብር እንዲሁም 113 ቢሊየን 635 ሚሊየን 559 ሺህ 980 ብር ደግሞ ለካፒታል ወጪ የተመደበ ነው። እንዲሁም ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 135 ቢሊየን 604 ሚሊየን 731 ሺህ 380 ብር እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ደግሞ 6 ቢሊየን ብር ተመድባል። አጠቃላይ በጀቱ ከ2010 ዓ.ም በጀት ጋር ሲነጻጸር የ3 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ አለው። አመታዊ በጀቱ በቀረበበት ወቅት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
- ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸው እንቅስቃሴዎች
4.1. በተለያዩ መድረኮች ላየ በመገኘት (ለምሳሌ ሚሊኒየም አዳራሽ) ያደረጓቸው ንግግሮች እና መልካም ስራ ለሰሩ ሰዎች የሰነዘራቸው የእውቅና ሙገሳዎች ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥረዋል። በተለይ በወጣቱ ዘንድ የፈጠሩት የተነሳሽት ስሜት ከፍ ያለ እንደነበረ የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።
4.2. ይህ መሆኑም የሀገራችን ወጣቶች አስተሳሰብ እና ሀገራዊ አንድነት ወደ አዎንታዊ የመደመር መስመር እንዲመጣ አስችችሏል። ከተለመዱ የፖለቲካ መድረኮች ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሊኒየም አዳራሹን መድረክ መታደማቸው ወጣቱ ለፖለቲካ መደረኮችም ሆነ ለሌሎች ተመሳሳይ ዝግጅቶች ጉጉት እና ክብር እንዲሰጥ የሚያስችል ሌላ እይታ ፈጥሯል።
4.3. በመጅሊስ እና በእስልምና መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ መሀል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት በእርቅ እና በውይይት በመፍታት የሙስሊሙ መህበረሰብ ወደ ፍቅር እና አንድነት እንዲመጣ ማድረግ ተችሏል። ይህም የሰላም እና የይቅርታ አዋጅ እንደ ሀገር ለተጀመረው የሰላም፣ የፍቅር፣ የመደመር እና የአብሮነት ጉዞ ትልቅ ጉልበት እንደሆነ መገንዘብ ተችሏል። ከዚህም ባሻገር አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ባሉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች መሀከል በተፈጠረው አለመግባበት ሳብያ ለሁለት ተከፍሎ የነበረው ሲኖዶስ ወደ አንድ እንዲመጣ እና ምእመናኑም በሰላም አና በፍቀር አxንድነታቸውን እንዲያጸኑ በርካታ ስራዎች ተሰርተው ውጤት አስመዝግበዋል። በቅርቡም የእርቅ እና የይቅርታ ሂደቱ የመጨረሻውን እልባት ያገኛል።
4.4. ትኩረት የሚሹ የግለሰብ ጉዳዮችን ጉዳዬ ብሎ በመከታተል እልባት አንዲያገኝ በማድረግ ትልቅ ድል ማስመዝገብ ተችሏል። ግለሰብ ግለሰብ ብቻ አይደለም በግለሰብ ውስጥ ቤተሰብ- በቤተሰብ ውስጥ ህዝብ እና በህዝብ ውስጥ ደግሞ ሀገር አሉ። ለምሳሌ በሳኡዲ አረቢያ በህክምና ስህተት ስቃይ ውስጥ የነበረው ታዳጊ እና የእናቲቱ ጉዳይ የእነርሱ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያን እንደነበረ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ለችግሩ ትኩረት ሰጥተው ከሳኡዲ መንግስት ጋር በተነጋገሩ ጊዜ ከህዝብ የመጣው ድጋፍ እና ግብረ መልስ በግልጽ ያሳያል።
4.5. በሆስፒታሎች በመገኘት ህሙማንን መጎብኘት እና ማጽናናት የጠቅላይ ሚኒስትር የማህበራዊ እንቅስቃሴ አንድ አካል ነበር። ከዚህም ባሻገር ደም የመለገስ እና እንደ ይስማእከ ወርቁ ያሉ ሰዎችን ደውሎ በመጠየቅ ከህመማቸው እንዲያገግሙ ተስፋ እና መልካም ምኞትን ማጋራት ሌላው የማህበራዊ እንቅስቃሴያቸው መልክ ነው። ይህ መሆኑም በተጠየቁት ህመምተኞች ውስጥ ሌላ ኢትዮጵያውያንን ልብ፤ በይስማእከ ውስጥም ብዙ ከያንያንን በፍቅር የሚያስተሳስር እና በሞራል የሚያንጽ ተግባር ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት
Mesfin says
ስንኖር ኢትዮጵያዊ
ስንሞት ኢትዪጵያ