በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ በጸረ ሰላም ኃይሎች ላይ በተወሰደ እርምጃ የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል እየተሠራ መሆኑን የመከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።
መንግሥት በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ሰላም ተመልሶ የግብርና ሥራቸውን እያከናወኑ መሆናቸውን የአካባቢው አርሶ አደሮች መግለጻቸው ይታወሳል።
በመከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ 403ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዘዘው መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት በደብረ ኤሊያስ ወረዳ በስላሴ ገዳም አካባቢ የታጠቀ ፅንፈኛ ኃይል መሽጎ ነበር።
በገዳሙ የመሸገው ኃይል ችግር ለመፍጠር በማለም ተጨማሪ ኃይል በማሰልጠንና በማደራጀት ሲሰራ መቆየቱን በተገኘው መረጃ ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
የአካባቢውን ህዝብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት አንቅስቃሴዎችን ከማስተጓጎሉም በላይ የጸረ ሰላም ኃይሉን አስተሳሰብ የማይቀበል ግለሰቦችን ሲገድሉ እንደነበረም አስታውሰዋል።
መከላከያ ሠራዊት ህግ ለማስከበር ወደ አካባቢው ሲገባም ቀድሞ ባዘጋጀው ምሽግ ውስጥ በመደበቅና ተኩስ በመክፈት ስርአት አልበኝነቱን አሳይቷል ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊት በወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ ጸረ ሰላም ሀይሉ የተመታ ሲሆን ተንጠባጥቦ በመሸሽ ላይ ያለውን የመከታተል ስራ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከአካባቢው መስተዳድርና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበርም የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግም ከጽንፈኛ ኃይሉ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ሰላምና ደህንነት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ላቃቸው አብጠው የተገኘውን ሰላም ለማጽናት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በአካባቢው የጸረ ሰላም ሃይሎች እንቅስቃሴ መስተዋል ከጀመረ የቆየ ቢሆንም ችግሩ እየተባባሰና ስርአት አልበኝነቱ እየተስፋፋ የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በአመለካከት የማይደግፏቸውን ንፁሃን ዜጎች፣ አመራሮችና የሃይማኖት አባቶችን ሲገድሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ ገዳሙ ትክክለኛ የሀይማኖት ስፍራ እንዲሆን ከጠቅላይ ቤተክህነትና ከዞኑ ሀገረ ስብከት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በማህበራዊ ሚዲያው ምስሎችን በመቆራረጥና በማገናኘት ገዳሙ እንደወደመ ተደርጎ የሚነዛው ወሬ የፈጠራ ፕሮፓጋንዳ መሆኑን ሁሉም ህዝብ ሊያውቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አሁን የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድርግም ሕዝቡ ሀይማኖትን ሽፋን በማድርግ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ማጋለጥና መታገል አለበት ሲሉም አሳስበዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
ሲጀመር ከመቼ ወዲህ ነው የታጠቀ ሃይል በገዳማትና በቤተክርስቲያናቶች መካከል የሚመሽገው። መሻጊውም ሆነ አሳዳጅ ሃይል ሁለቱም ወስላቶች ናቸው። እንዲህ አይነቱ ገዳዳ እይታ ነው እምነታችን ባዶ የሚያደርገው። ጠበንጃ አንስተህ ውጊያ መግጠም ካማረህ መጠለያህ የእምነት ቤቶች ሊሆኑ አይገባም። መንግስት ተብዬውም በዚህም በዚያም ሰውን ማንገላታትና መግደሉም ሰላምን አያመጣም። ባጭሩ የሃበሻዋ ሃገር እሳት የማይጠፋባት፤ እፎይ አልን ሲባል ሌላ የሚቀጣጠልባት በዘር ፓለቲካ ጭንቅላታቸው የነጠበ የሚተራመሱባት ምድር ሆናለች። የሃገራችን ጉዳይ ልብ ላለው ከቀን ወደ ቀን አሳዛኝ እየሆነ መጥቷል። ዛሬ ጊዜ ሰጥቷቸው የሚፍነሸነሹት የዘርና የቋንቋ ጥርቅሞች የሌላው ሰው ሞትና መፈናቀል ደንታ የማይሰጣቸው ጭፍን አላሚዎችና ደንቆሮዎች ናቸው። ሰው በስብዕናው መለካቱ ቀርቷል። ጠበንጃ አንጋቾችና ለእነርሱ ያደሩ ህዝቡን ያተራምሱታል። በቅርቡ በአዋሳ ከተማ አፈቀራት በተባለው ታጣቂ ታፍና ለ 10 ቀናት ሃበሳዋን አይታ የተለቀቀችው ጸጋ ለምድሪቱ የሻገተ አስተሳሰብ ማሳያ ናት። ሰው እንዴት በዚህ ዘመን ሴትን ይጠልፋል? ግን በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ማስቆም የሚቻለው የሴቶች ህብረትና አንድነት ሲኖር ነው። ይህና ፓለቲካው ምን አገናኘው የሚል የወሬ ጨላጭ ሊኖር ይችላል። በደንብ ነው የሚገናኘው። ፍትህ ባጣ ምድር ላይ አለቃውም አዛዡም ታጣቂ ሃይል ነውና!
ጄ/አዘዘው መኮነን “ታጣቂ ሃይል መሽጎ ነበር” ይለናል። መቀሌ ላይ የመሸገውንና አሁንም በሰው ህይወት የሚቀልደውን ወያኔን ለምን ሂዳችሁ አትገጥሙትም። ወያኔ የአሜሪካ ጥብቅና ስላለው ፍርሃት ይሆን? ወይስ ከኦሮሞ ጋር ዞሮ ስለተጣመረ? ወታደራዊ ስልት ለገባው ወታደር መሆን ሁሌ ተኳሽ ብቻ እንዳልሆነ መገንዘብ ቀላል ነው። ኢላማን ሳይለዪ እየተኮሱ ሰውን መግደል ለሰማይ አድረናል በማለት በዚያው የተቀመጡትና ታጣቂ ሃይል የሚባለውን መለየት ያልቻለ የጅምላ ፍርድ ነው። ባጭሩ ህይወት በሃበሻዋ ምድር በነሲብ የሚኖርባትና የሚሞትባት ሆናለች። ለአማራ ቤት አታከራዪ የሚሉ ኦሮሞዎች እንደ አሸን በፈሉበት ምድር ላይ ሰው ነኝ ብሎ መቆም ከሰው አውሬ ጋር ያጋጫል። ህጻናትና እናቶች እያለቀሱ እየዘፈነ ቤት የሚያፈርስና የቆመውን እንጨትና ቆርቆሮ ዘርፎ በሚወሰድበት ከተማ ተቀምጦ ለወያኔ ግማሽ ቢሊዪን ብር ለእርዳታ ተሸክሞ መቀሌ ድረስ መሄድ የፓለቲካው ትልቅ ውስልትና ነው። ግን የሃበሻ ፓለቲካ በየተራ የመገዳደልና የማፈራረስ ፓለቲካ ነው። ላስረዳ።
በመጀመሪያው የጣሊያን ወረራ ከየክፍለ ሃገሩ ተሰባስበው በሰሜን ኢትዮጵያ በመገኘት ጣሊያንን ማሳፈራቸው የማይካድ ሃቅ ነው። ግን ከድል በህዋላ የሞቱላት ሳይሆን ለጠላት ያደሩት ነበር ከፍታ ላይ የወጡት። ያ አልፎ ዳግመኛ ጣሊያን ወረራ ሲያደርግ ከመጀመሪያው ጦርነት የተረፉትና በእድሜ የገፉት ጭምር ነበር ዳግም ወደ ሰሜን በመሄድ የተሰውት። ደርግ ሊፈራርስ ሲል ጡረታ የወጡ ወታደሮችን በመጥራት ለወያኔና ለሻቢያ የጥይት ራት አድርጓቸዋል። ወያኔ በባድሜ ሰበብ ከሻቢያ ጋር ሲፋታ ከሁለቱም ወገን ያለቁት ከልዪ ልዪ ጦርነቶች የተረፉት ጭምር ነበር። ይህ የሚያሳየው እረፍ ያላለው የከብት ቆዳ ከበሮ ይሆናል እንዲሉ ነው። ሁሌ መደለቅ። እልፈት የለሽ መገዳደልና መጎሻሸም።
አሁን እንሆ አሜሪካኖች ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር ለማላተም ያለ የሌለ ሴራቸውን ተያይዘውታል። ኤርትራን ራሺያና ቻይና ሊያስታጥቋት ይችላሉ፤ ወያኔ ያው ሶስት ጊዜ ወረራ እንዲያደርግ የገፋፉት አሜሪካኖች እሳት ያቀብሉታል። ሱዳን ላይ እሳቱ ተቀጣጥሏል። ስለሆነም አሳራችን በውጭ ሃይሎችና በዘርና በቋንቋ በሰከሩ የብሄር ድርቡሾች እየታገዘ ይቀጥላል። የዛሬው ገዳይ የነገ ሟች፤ የዛሬው አፈናቃይና ዘራፊ የነገ ነፍሱን ሊያተርፍ ሯጭ፤ የዛሬው ጄኔራልና ወገንተኛ ነገ ቆሞ ለማኝ እንደሚሆን የሃገሪቱ ታሪክ በተደጋጋሚ አሳይቶናል። ለዚህም ነው የጨነቀው እርጉዝ ያገባል የሚሉት አበው። አሁን ማን ይሙት ብልጽግና ከወያኔ ይሻላል? ፍርድን ላንባቢ። ገና ግን ብዙ ጉድ እናያለን። እንሰንብት። በቃኝ!
Selma Atnafu says
ለምን ትዋሻላችሁ፦ ሀገር ያወቀዉን ፀሐይ የሞቀውን እውነት መደበቅ የትም እያደርሰም።
ረቡዕ ሰኔ 14 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ ሥር ባሉ አራት ገዳማት ላይ በደረሰው ከፍተኛ ጉዳት፤ በገዳማቱ አንድ መነኩሴ ብቻ መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስታውቃለች፡፡
በገዳማቱ ከግንቦት 18 እስከ 23/2015 ለተከታታይ አምስት ቀናት “የታጠቁ ኃይሎች በገዳሙ ውስጥ ይገኛሉ” በሚል በተደረገ ኦፕሬሽን እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ መነኮሳት መሞታቸውን፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓበርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አሥተዳደር መምሪያ ኃላፊ መጋቤ ካህናት አባ ሀብተጊዎርጊስ አሥራት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ኃለፊው አክለውም፤ በአራቱም ገዳማት አቢያተ ክርስቲያናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ለአዲስ ተናግረዋል፡፡ በዚህም በገዳሙ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች “ሕግ ማስከበር” ያሉትን ዘመቻ ከማካሄዳቸው በፊት በርካታ መነኮሳት እና አገልጋዮች ይኖሩ እንደነበር ገልጸው፣ የገዳማት አስተዳደር መምሪያው ወደ ሥፍራው ባቀናበት ወቅት የተገኙት አንድ መነኩሴ ብቻ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
“መሞታቸው ከታወቀው መነኮሳቱና አገልጋዮች ውጭ ሌሎቹ የት እንደገቡ አይታወቅም፡፡” ያሉት ኃላፊው፤ በገዳሙ ውስጥ ባለው ሰፊ የአትክልት እርሻ በርካታ ያልተቀበሩ አስከሬኖች መኖራቸውንና በአካባቢው ከፍተኛ የአስከሬን ሽታ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች “በገዳሙ የታጠቁ ኃይሎች መሽገዋል” በሚል ኦፕሬሽን ቢያደርጉም፤ በተለያዩ ጊዜያት ሽፍታዎች የገዳሙን ንብረት ለመዝረፍ ወደ ሥፍራው ይመጡ ስለነበር፣ መነኮሳቱ ምሽግ ቆፍረው ንብረቱን ከዝርፊያ ለማዳን እና ሕይወታቸውንም ለመታደግ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በተደረገው ዘመቻ ጉዳት የደረሰባቸው አቢያተ ክርስቲያናት የሥላሴ፣ ኪዳነምሕረት፣ የኤልያስ እና የጊዎርጊስ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ አቢያተ ክርስቲያናቱ የውጭ ክፍላቸው ጨምሮ ቅኔ ማሕሌቱ፣ ቅድስቱ እና ቤተመቅደሱ ላይ የደረሰው ድብደባ እጅግ ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል።
“በተለይ በኪዳነምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ላይ የደረሰው ጉዳት ከኹሉም የከፋ ነው፡፡” ያሉት ኃላፊው፣ ንዋተ ቅድሳትን ጨምሮ የቤተ መቅደስ መገልገያዎች መውደማቸውን እና ጉልላቱም ተመትቶ መውደቁን ገልጸዋል።