“በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት ” በሚል መሪ ቃል ለሚከበረው ለዘንድሮ ለ116ኛው የሠራዊት ቀን እንኳን በሠላም አደረሳችሁ አደረሰን።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የረዥም ዓመታት ሀገርን ከጠላት የመከላከል የተጋድሎ ታሪክ ካላቸው ሀገራት መካከል በጀግኖች ልጆቿ የአይበገሬነት ፊት የምትሠለፍ ታሪካዊት ሀገር ናት።
ከቀደመው ዘመን ጀምረን አሁን ላይ ያለውን እውነታ እንኳ ብንቃኝ ኢትዮጵያ በርካታ የውጪ ወራሪ ሀገራት ያሠፈሠፉባት ጥቂት የማይባሉ የውስጥ እርስ በርስ ግጭቶች የተከሰቱባት በባንዳዎች የተፈተነችበትና በየትኛውም ዘመን ያልተንበረከከች የወራሪዎችን ፈተና አልፋ ዛሬ ላይ የደረሠች ሥለመሆኗ የታሪክ ድርሳናት መዝግቧል።
በሀገራችን የጀግንነት የታሪክ መዝገብ ያልሠፈሩ ግን ደግሞ አለም ያወቃቸው ቱባ ባህሎችና ድንቅ ታሪኮች ያላት ኢትዮጵያ በታሪክ በሠራዊቷ ኮርታ እንጅ አንድም ጊዜ አፍራ እንደማታውቅ ታሪክ ህያው ምስክር ነው ።
ዛሬ ላይም በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ሀገረ ጠል በሆኑ ባንዳዎችና የፀረ ሠላም ሀይሎች ችግሮች ቢከሠቱም ጀግንነት ባህል ልምዱ እና የዘወትር ተግባሩ ባደረገው ሠራዊታችንና ህዝባችን የሠላም እንቅፋቶችን ፈተና ተቋቁማ ሀገራችን በልማት ጎዳና ላይ ትገኛለች።
በመሆኑም በየትኛውም ጊዜ እና በማንኛውም ቦታ ለሠራዊታችን ብርታት ሞራልና የጀርባ አጥንት ከሆነው ህዝባችን ጋር ሆነን ሠላማችንን እያሥቀጠልን እንገኛለን።
116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀንም ይበልጥ ቃላችንን የምናደስበት በየዘመናቱ ለሀገራችን ሉዓላዊነት ሲሉ መስዋዕት የከፈሉ ጀግኖችን የምንዘክርበትና ከመላው ህዝባችን ጋር ሆነን ለሀገራችን ሠላምና ልማት ማበብ በጋራ የምንቆምበት ዕለት ጭምር ነው።
እናም እንደ መሪ ቃላችን በተፈተን ጊዜ ሁሉ ፀንተን የድል ሠራዊት ሆነን ዛሬ ላይ እንደደረሥነው ቀጣይም ከመላው ህዝባችን ጋር ለሀገራችን መክፈል ያለብንን ሁሉ ዋጋ በመክፈል የኢትዮጵያን ሠላም እና ዕድገት አፅንተን እናሥቀጥላለን ።
“በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት”
ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
Tesfa says
በሃበሻ ፓለቲካ በራስ አስቦ የራስን ሃሳብ ለሌሎች ማካፈል ከመ አሪዎስ ተብሎ ከተወገዘ ዘመን አለፈ። ይኸው አሁን እውቁ ጋዘጠኛ ሲሳይ አጌና ላይ የሚለጠፉ ወልጋዳ ሃሳቦችን ለሰማና ላነበበ የሃበሻው ፓለቲካ የጅምላ ህሳቤን የተላበሰ እንጂ በራስ መቆም የማይቻል መሆኑን ያሳያል። በብዙ መከራ ውስጥ ያለፈው ይህ ምጡቅ ጋዜጠኛ የኢትዮጵያን ሰራዊት ጥንካሬና አንድነት ከሃገሪቱ ልዕልና እና ቀጣይነት ጋር አጣምሮ በማየቱ በዚህም በዚያም ይዘለፋል። ይህ በየወንዙ የሚማማለው የሃበሻ ፓለቲካ የአስረሽ ምቺው ስልት ስለሚከተል ከትላንቱ የሚማር ሳይሆን ለዛሬ ብቻ ኑሮ ዛሬ ላይ የሚከስም ነው። ያለፈ ታሪካችንም የሚያሳየው ይህኑ ነው።
የኢትዪጵያ ወታደሮች ያኔም ሆነ አሁን የውስጥና የውጭ ጠላትን የተፋለሙት መጭው ትውልድ በሰላምና በደስታ እንዲኖር ነበረ። ያ ግን ሆኖ አያውቅም። የሰው ተንኮል ከመንግስታት ሸፍጥ ጋር እየተላበደ ህዝባችን እየከፋፈለ ዛሬ ላለንበት እኛ ብቻ እንኑር ፓለቲካ አሽጋግሮናል። እንደ ሃምሌ ዝናብ የማይቆመው ይህ የህዝባችን ሰቆቃ ምንጩ እኛም መንግስትም ነው። ሲጀመር ለሰላም ቆመናል የሚሉ ሃይሎች ሁሉ በተንኮልና በሸር የተነከሩ በመሆናቸው የሚታያቸው የእነርሱ መኖር እንጂ የሰፊው ህዝብ ሰቆቃ አይደለም። የየጊዜው የፓለቲካ እንፋሎትና ሆሆታ በሌላ እልቂትና ለቅሶ እየተተካ ሽምድምድ የሃበሻ ፓለቲካ በሃገርም ሆነ በውጭ የስንቱን ቤት እንዳፈረሰና ሰላም እንዳደፈረሰ አሃዛዊ ስሌት አይገልጠውም። ግን አይናችንና ጆሮአችን ይሰማል። እልፎች እርደዋል፤ ሰላማቸው ተነጥቋል!
ኢትዮጵያዊነት የሚለካው በዘር በተሰፈረ ቁና ሳይሆን እንደ ጣና ሃይቅ በሰፈው ዓለም ውስጥ በሚንሳፈፍ ሚዛን ነው። ነገርን በጭልፋ ይዘው ወራጅ ውሃ አፈለቅን የሚሉን እነዚህ የዘርና የቋንቋ የፓለቲካ ሾተላዪች ቁመንለታል ለሚሉት ህዝብም ቢሆን ያደረጉት ይህ ነው የሚባል አንድም ጠቃሚ ነገር የለም። እንደ ምሳሌ የኤርትራውን ሻቢያን እንዲሁም ሃገር በቀሉን ወያኔን ማየት ብቻ በቂ ይሆናል። ከሰቆቃና ከስደት ሌላ ለምድሪቱና ለሚኖሩባት ምድር ያደረጉት አንድም ነገር የለም። የብልጽግናው መንግስት ከዚህ ተምሮ ራሱን በጊዜ ማሳመርና አፍራሽና አደፍራሽ ነገሮችን ማቆም አለበት። ያ ካልሆነ አፍራሽን አፍራሽ እየተካው ዝንተ ዓለም ከሰቆቃና ከመገዳደል የሚያድነን ምንም ሃይል አይኖርም። እንደሚባለው ሁሉ በእርግጥም በተፈተነ ጊዜ የሚጸና ሰራዊት አንዲት ሃገር ያስፈልጋታል። የአንዲት ሃገር ሰራዊት የህዝብ ልጅ ነው። የመንግስትን ፓሊሲ አለመቀበል በሃገር ሰራዊት ላይ ምንም አይነት ጥላቻና ጥላሸት መቀባት አያስከትልም። የሃገሪቱን ፓሊሲ አስፈጻሚዎችንና መሪዎችን በሃሳብ መሟገት ግን በጎነት ይኖረዋል። መንግስትም ያነጠሰን ሁሉ እያፈሱ ማሰርና መሰወር ነገርን እያከበደ ደርግና ወያኔ በሄድበት የቁልቁለት መንገድ መጓዝ እንጂ ብልህነት ባለመሆኑ ሰው ማሰር፤ ማፈን፤ መግደል እንዲቆም ማድረግ ይኖርበታል። የተካረረ ፓለቲካ ውሉ የጠፋበት በህዋላ ሁሉን የሚጎዳ ዘይቤ ነው። ያም ይሁን ግን አጠፋም፤ አለማም፤ ሞተም፤ ቆመም የሃገሪቱን ሰራዊት አለማድነቅ አይቻልም። ለዪቱቭ የፍራንክ ሽርፍራፊ ተብሎ የሚለጠፈው የውሸትና የፈጠራ ወሬ ሁሉ ሊፈተሽ ይገባዋል እንጂ እንዳለ ሰልቅጦ ማወራራጃ ማጣት ለራስም አይበጅም። የሲሳይ አጌናና የሌሎችም የሲቪል ወገኖቻችን 116ኛው የሰራዊቱ ቀን እውቅና ማግኘታቸው እሰየው ያሰኛል እንጂ አፋፍ ላይ ቆሞ ኡኡታ የሚያሰሙበት ጉዳይ አይደለም። የኢትዮጵያ ሰራዊትም ከእነ ብርታቱና ድካሙ እንኳን ለ 116ኛ የሰራዊቱ ቀን አደረሳችሁ እላለሁ።