በአዲሱ መንግሥት ምስረታ ውስጥ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ከ7 እስከ 13 ሆኖ የሚደራጅ ሲሆን አባላቱም እንደየ ሙያቸው ዘርፎችን እንዲከታተሉ የሚደረግ መሆኑን አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ለመንግሥት ምስረታው እየተደረገ ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ የመንግሥት ምስረታ የሚካሄድ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ገልጸዋል።
አፈ-ጉባዔው በሕገ መንግስቱ መሰረት መስከረም መጨረሻ ባለው ሰኞ የመንግስት ምስረታው ይካሄዳል ብለዋል።
የሕግ አወጣጥ ሂደቱን አስመልክቶ የተካሄደውን ጥናት መነሻ በማድረግ የሕግ አወጣጡን የሚያዘምን መመርያ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ምክር ቤቱ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓቱን ማዘመን የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ተዘርግቷል ያሉት አፈ-ጉባዔው የመንግስት ትኩረትን የለየ ጠንካራ የቁጥጥርና ክትትል ስርዓት እንደሚተገበርም ነው ያስረዱት።
የምክር ቤቱ አባላትም የሕዝብ ውከልናቸውን ለማረጋገጥ ወደ መረጣቸው ሕዝብ ቀርበው ተከታታይ ውይይት የሚያደርጉበትም ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል።
የምክር ቤቱ ስብሰባን በተመለከተም በየወሩ አንድ ሙሉ ሳምንት የምክር ቤቱ አባላት ተሰብስበው የአስፈጻሚ አካላት ሪፖርት የሚያዳምጡበትና የሕግ ማውጣት ስራቸውን የሚያከናውኑበት አሰራር እንደሚጀመር ገለጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply