
ከሱዳን ወደ ሀገር ውስጥ ሊገባ ለነበረው የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን የተዘጋጀ ገጀራ እና የሐሰት መታወቂያ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሽንፋ ንዑስ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ከሱዳን በቲሀ በኩል ወደ ሀገር ውስጥ ሊገባ ለነበረው እና በጀግናው የፀጥታ ኀይል ለተደመሰሰው የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ሊሰጥ የነበረ 260 ገጀራ እና 1 ሺህ 149 ሕገ ወጥ መታወቂያ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሽንፋ ንዑስ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ጉባይ ቀበሌ በቀድሞው የሰሜን ጎንደር ዞን ጉባይ ጀጀቢት ቀበሌ በሚል ስያሜ ተዘጋጅቶ ከሱዳን ሊገቡ ለነበሩ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት ሊሰጥ የነበረ 1 ሺህ 149 ሕገ ወጥ መታወቂያ የቅማንት ጽንፈኛ ቡድን መሪ በሆነው አቶ ሻንቆ አየልኝ ቤት መገኘቱን የሽንፋ ንዑስ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ተወካይ መርማሪ ፖሊስ ምክትል ሳጅን ወርቅዬ ዋለልኝ አሰታውቀዋል።
መታወቂያው ለሳምሪና በቲሃ በኩል ሊገባ ለነበረው የሽብር ቡድን በመስጠት የአማራ ተወላጅ መስለው በአካባቢው የሽብር ተልኮን ለመፈጸም ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን መርማሪ ፖሊሱ ጠቅሰዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ ባደረገው አሰሳና ፍተሻ በጽንፈኛው ቅማንት ቡድን አባል አቶ መከተ ብርቄ የንግድ መካዝን ስሪቱ የእንግሊዝ የሆነ 260 ገጀራ መገኘቱንም የሽንፋ ከተማ ቀበሌ አስተዳደሪ አቶ በለጠ ዳምጤ ተናግረዋል።
በቅማንት ጽንፈኛ ቡድን መሪነት ከሱዳን በቲሀ በኩል ወደ ሀገር ውስጥ ሊገባ የነበረው የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ሽንፋን ለመቆጣጠር ጦርነት ቢከፍትም በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖና በአካባቢው ማኅበረሰብ መደምሰሱን መዘገባችን ይታወሳል።
ሽንፋን ዳግማዊ ማይካድራ ለማድረግ የሞከረው የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ዳግም ላይመለስ ቀብረነዋል ያሉት በመተማ ወረዳ የሽንፋ ንዑስ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ተሾመ በሪሁን ናቸው፡፡ ሽንፋ በሽብር ቡድኑና በተላላኪዎች ላትደፈር ወጣቱን ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በማቀናጀት አካባቢያቸውን እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል። (አሚኮ: ቴዎድሮስ ደሴ – ከሽንፋ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply