በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ መሰረት መንግሥት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ላገኙ ፖለቲካ ፓርቲዎች በየዓመቱ የበጀት ድጎማ ያደርጋል፡፡ በዚሁ መሠረት የ2015 በጀት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ለማከፋፈል በምርጫ ቦርድ ቀመር መሰረት የገንዘብ ክፍፍሉ መደልደሉን ቦርዱ አስታውቋል፡፡
ቦርዱ ይህንኑ አስመልክቶ ቅዳሜ መጋቢት 2/2015 ከፓርቲዎች ጋር ባካሄደው ውይይት በአገር አቀፍና ክልል አቀፍ ፓርቲዎች 65 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ መደበኛ በጀት የበጀት ሲሆን፣ ፓርቲዎች ለሚያከናውኑት የሲቪል ትምህርት 41 ሚሊዮን ብር መመደቡን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ተናግረዋል፡፡
ፓርቲዎች የሚደርሳቸው ገንዘብ በዋና ዋና መስፈርቶች የሚመዘን ሲሆን፣ በሴት አባል ብዛት፣ በሴት አመራር ብዛት፣ በአካል ጉዳተኛ አባል ብዛትና በአካል ጉዳተኛ አመራር ብዛት ተሰልቶ የሚመደብ መሆኑ ተገልጿል፡፡ እንዲሁም በእኩልነት የሚከፈልባቸው መስፈርቶች በቀድሞ ጠቅላላ ምርጫ ለተወዳደሩና እውቅና ያላቸው ፓርቲዎች ናቸው ተብሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ የገንዘብ ክፍፍል ውስጥ ያልገቡ ፓርቲዎች መኖራቸውን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ጠቁመዋል፡፡ በገንዘብ ክፍሉ ያልተካተቱ ፓርቲዎች ከዚህ በፊት የወሰዱትን ገንዘብ ምንም ጥቅም ላይ ያላዋሉ፣ ቦርዱ ላቀረበው የበጀት ድልድል ጥያቄ ፍላጎት ምላሽ ያልሰጡ እና የፓርቲ ገንዘብ ምዝበራ ተፈጽሞባቸዋል የተባሉ ፓርቲዎች ይገኙበታል፡፡
ፓርቲዎቹ ከዚህ በፊት የተሰጣቸውን ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋላቸውን የሚያረጋግጥ እውቅና ባለው ኦዲተር አረጋግጠው ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ገንዘቡን በአግባቡ ያልተጠቀሙ ፓርቲዎች መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡
ለቦርዱ የኦዲት ሪፖርት ካቀረቡ ፓርቲዎች መካከል፣ እስከ 25 በመቶ ለሚደርሰው ውጪ ማስረጃ ያላቀቡ መገኘታቸው ብርቱካን ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም አሳማኝ የውጪ ምክንያት ያላቀረቡ ፓርቲዎች መኖራቸውም የተጠቆመ ሲሆን፣ ከመንግሥት የተመደበን ገንዘብ በአግባቡ አለመጠቀም ቅጣት እንደሚያስከትልም ተጠቅሷል፡፡
የዘንድሮው ገንዘብ ድልድል የበጀት ዓመቱ ከሰባት ወራት በላይ ካለቀ በኋላ የሚከፋፈል ነው፡፡
በመድረኩም ፓርቲዎቹ በበጀት ድልድሉ ላይ ያላቸውን ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ የገንዘብ ሥርጭቱ ዘግይቶ መምጣቱ ገንዘቡን በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል እንቅፋት እንደሚሆን በማንሳት፣ ከዚህ በኋላ በበጀት ዓመት መጀመሪያ እንዲሰራጭ ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ፓርቲዎቹ ከመንግሥት የተመደበላቸውን ገንዘበ በአግባቡ ለመጠቅም የሚያስችል ነጻ የፓርቲ እንቅስቃሴ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎች አለመኖራቸውን እንደ ችግር አንስተዋል፡፡ በተለይም ገዥው ፓርቲ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ የሚፈጥረው የነጻነት ገደብ ፓርቲዎቹ ገንዘቡን ተጠቅመው ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ እንቅፋት መሆኑም ተነስቷል፡፡(አዲስ ማለዳ)
Leave a Reply