በየከተማው በየገጠሩ
በየጥሻው በየቆንጥሩ
በለጋ ሕይወታችሁ
ገና ፀሐይ ሳትመታችሁ፤
“ነፃነት ነፃነት የምትሹ
ተዋጉለት አትሸሹ።”
እያላችሁ
ቆማችሁ፤
አባራሪ ግንባር
ሆናችሁ
ቀንዲል ብርሃን
ተነስታችሁ፤
ፀሐይዋ በዕርጋታ
በሀገራችን ወጥታ ገብታ፤
ጨለማው ፈርቶ ሸሽቶ
ብርሃን ባገር ሞልቶ
የማይታሰበውና ደረቁ ሀቅ
በውጥረትና በጭንቅ
ሴትና ወንድ ወጣቶች
ሕፃናትና ሽማግሎች፤
የመኖር ሕይወት ትርጉሙን
ለሌሎች ሕይወት መቆምን
አስተምራችሁን ያለፋችሁ
ቆረቆረኝ መቃብራችሁ።
እሁድ ጥር ፲፪ ቀን ፳፻፭ ዓመተ ምህረት
(ስዕል: የገጣሚው)
በለው ! says
—————————–
የጥቁር ደመና ድሃ ቤት ላይ ከባ
ከደሰሳው ጎጆ ውስጥ እየፈራ እየተባ
የጥቁር ዓይን ዳሩ በነጭ ተከቦ
አይኑን አፍጥጦ ያነባል በደቦ!
እናንት ህልመኞች እራሳችሁን የሰዋችሁ
ከቆሙት በታች ቀና ብላችሁ ባያችሁ
በእርግጥ ይህ ነበርን ራዕያችሁ ?
ቋሚን ይድላው ብላችሁ መሞታችሁ
እናንተንስ መሬት ያዛችሁ ተመቻችሁ
ደግመው አፍርሰው አውጥተው ከጣሏችሁ
ግፍ ነው ሁለተኛ ሞት መች ደላችሁና ቆማችሁ?
ክብር ለዜጋው በለው!
++++++++++++++++
ዱባለ says
ያሰበው ያለመው በጋርዮሽ መኖር
የሰው ጸባይን ነው ያልተረዳው ነገር
መኖር የሚችለው ሌላውን በመቅበር
የሞተው ይሻላል የሰውን ጉድ ሳያይ
በቁም ለሞተ ነው የዘላለም ስቃይ::
YeKanadaw Kebede says
ተው እንጂ ወንድም ዓለም
ለጀግና አይታዘንም
በታሪካችን ተዘክሮ
በወስጣችን ተቀብሮ
ስለ’ሚኖር ዘ’ላለም
የጀግና ሞት፤ ሞት አይደለም
ከትንሽ ውሎ ማነሱን
ከርካሾች ጋር መርከሱን
ስልተጠየፈ ነው
እንደከብት እየተነዳ
ሰበእናው እየተጎዳ
አለመኖርን የመረጠው
እና..ወንድም ዓለሜ..
የሚታዘነው…..ለኛ ነው
ተምረን ለደነቆርነው
እያየን ለታወርነው
ቃላችንን ለበላነው
ዕምነታችንን ለረሳነው
ጓዱና ጓዲትማ…
ጥፍራቸው በጉጥ ሲነቀል
ሥጋቸው በዘይት ሲቀቀል
ወፌ-ይላላ ሲገረፉ
ባፋቸው ደም እየተፉ
ለጠላት ደስ እንዳይለው፤ ወኔያቸው ሳይደፈር
ወደ መቃብር የሄዱት እየዘፈኑ ነበር
እና…ወንድም ዓለሜ…
አገራችን ለተወሰደው
ክብራችን ለተዋረደው
በቁማችን ለሞትነው
የሚታዘነው…ለኛ ነው
Jan.2013
እስከመቼ says
ጎረበጠኝ አልኩኝ እንጂ
ቆረቆረኝ ዕረፍት ነሳኝ፣
አቅሌን ሳበው አልኩኝ እንጂ
ቀን ተሌሊት ሰላም ነፍጎኝ፤
ሰንደቃቸውን አወሳለሁ
እላፊያቸውን አደንቃለሁ፤
አልኩኝ እንጂ በኩራቴ
ግብራቸውን ተሸክሜ በደረቴ፤
ሕይወታቸው በውስጤ አድሮ
ከኔ ሕይወት ተዳምሮ፤
ተነስ ብሎ ቆጠቆጠኝ
አልኩኝ እንጂ ቆረቆረኝ፤
የምን ማዘን በየት አልፎ?
ተደማምሮ በጣም ገዝፎ
ማጣቴነው ተሰልፎ!