
ከአዘጋጆቹ፤ባለፈው ሳምንት “እኚህ ሰው ማናቸው? – ፬” በሚል ለቀረበው ምላሽ በድረገጻችን በመላክና በፌስቡክ ላይ በመለጠፍ የተሳተፋችሁትን በሙሉ እናመሰግናለን፡፡ በተለይ በግጥም ምላሻችሁን ለሰጣችሁ በሙሉ ከፍያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ የቅንብሩ አዘጋጅ ወለላዬ በቁጥር አራት ለቀረበው ጥያቄ ምላሻቸውን በሚከተለው መልኩ በግጥም አስፍረዋል፡፡
መልስ
ፈረሱን እንደሰው – አስታጠቀው ሱሬ
መተኮሱንማ – ማንም ይተኩሳል
ኃይለማርያም – ማሞ አንጀት ይበጥሳል
በማለት በዜማ – የዘመርንላቸው
ኃይለማርያም – ማሞ ማለት እኚህ ናቸው።
ለዚህ ሳምንት “እኚህ ሰው ማናቸው? –፭” ወለላዬ የሚከተለውን አቅርበዋል፡፡ ምላሻችሁን በግጥም በመመለስ ለዝግጅቱ ውበት እንድትሰጡ ለማደፋፈር እንወዳለን፡፡ የዛሬ ሳምንት መልሱን በግጥም እናቀርባለን፡፡
በሕይወት ዘመኑ – ሳይታክት የሰራ
መልካም ፍሬ – ያለው የሀገር በረከት
በሆነ አጋጣሚ – ብቅ ይላል በድንገት
እንደዚሁ ሁሉ – እኝህ ታላቅ አባት
ሲጠራ ስማቸው – ይሰማናል ኩራት
ማናቸው ንገሩኝ – አንባቢም ይሳተፍ
ፎቶቸውን አይቶ – ስማቸውን ይጻፍ
እኝህ ሰው ማን ናቸው
እኔም አላውቃቸው
ዛሬ ነው ፌስቡክ ላይ
ከልብ ያየሁዋቸው
ባካችሁ ንገሩኝ
እኝህ ሰው ማን ናቸው ?
ላገሩ ያለቀሰ
ብዕሩን ያደማ
ያደረሰ ቁንጮ
ጉዋድ በዓሉ ግርማ
በ አገሩ ጀግና
የሃገሩ ወኔ
የነጻነት ታጋይ
በብዕሩ አማላይ
ከጻፉት የበላይ
ከመጻፉ ኦሮማይ
በአሉ ግርማ
እኝህ መልከ መልካም መልከ ቀና ሰዉ
የአገር ጠበቃ ምሁርም ናቸዉ
በፋሽስት ጦርነት አገር ሲወረር
እኚህ መልካም ጎበዝ ተሟግተዉ ነበር
ተጥቁር ወንድሞች በአንድ በማበር
ጦርም አስተባብረዉ ሊልኩ ነበር
በፓን አፍሪካነት በመተባበር
ታሪካቸዉ ሸጋ ልክ እንደ መልካቸዉ
ስማቸዉም ይኸዉ መላኩ በያን ነዉ
የሃገር ጠበቃ የታወቀው ምሁር
መላኩ በያን ነው ለማያቁት ንገር
ላገሩ ነጻነት ቆሞ ሲከራከር
አሜሪካን አገር ሆኖ የቀረው አፈር
ስሙ ግን ያልሞተ ያልገባ መቃብር
መላኩ በያን በል ወለላዬ አትፈር
እንደው በግርድፉ ፎቶውን ሲያሰሉት
የቆየ ይመሥላል ዘመን ያለፈበት
ደግሞ ሲያስተውሉ ግለስቡን ዘልቆ
አለባበሱንም ካዩ ተጠንቅቆ
ወጣት ከመሆኑም ዘና ከማለቱ
ኮፍያው ከራሱ ከረባት ባንገቱ
ሁሉንም አሥማምቶ የተነሳው ፎቶ
ዘመነኛነቱን ያሳያል አጉልቶ
በውጭ አገር ኖረው ያውቃሉ ለማለት
ነበር ሙከራዬ ይሕ ሁሉ መዋተት
ከዚህ በተረፈ የምስማማው እኔ
የመገምት አቅም ባይኖረኝም ወኔ
ቢሆኑ ደስ ይላል በያን ወመላኩ
እንደተጠቀሰው ከላይ በመድረኩ