
በምዕራብ ወለጋ ዞን በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።
ግድያው የተፈጸመው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል እያለ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ “እኛ የፖለቲካ ሰዎች አይደለንም፤ ገበሬዎች ነን ፤ መንግስት ለምን አይደርስልንም?” ብለዋል።
በኦሮሚ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ ቦኔ ቀበሌ፣ ትናንትና
ምሽት 3 ሰዓት ላይ በርካታ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን የአካባቢ ነዋሪዎች
የተናገሩት። ነዋሪዎቹ ፤ አሁን ላይ አስክሬኖች በየቦታው ተጥለው መገኘታቸውን ገልጸው ቁጥሩ ምን ያህል ነው የሚለውን ለመግለጽ አስቸጋሪ እንደሆነ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ሕጻናትና ሴቶች አሁን ላይ ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ጫካዎች መግባታቸውን
የገለጹት አስተያየት ሰጭዎቹ፤ መንግስት የማይደርስላቸው ከሆነ አሁንም ሌላ
ግድያ ሊኖር እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች በቦታው አለመድረሳቸውን የገለጹት
ነዋሪዎቹ፤ አስክሬኖች የተጣሉበት ቦታ ጋሪ የማይገባበት በመሆኑ ለማንሳት
መቸገራቸውን ተናግረዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት እነዚህ ነዋሪዎች “እኛ የፖለቲካ ሰዎች
አይደለንም፤ ገበሬዎች ነን ፤ መንግስት ለምን አይደርስልንም?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
በደረባ (በከብት ማደለቢያና መጠበቂያ ቦታ) ላይ ብቻ 20 አስክሬኖች መገኘታቸውን ያነሱት ነዋሪዎቹ አሁንም ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው
ነው የገለጹት።
አሁን ላይ በአካባቢው በርካታ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት እንዳሉ የገለጹት
ነዋሪዎቹ፤ “መከላከያ ወይም ፌዴራል ፖሊስ ካልገባ ልዩ ኃይሉ ከሞት
ያስጥለናል ብለን አናስብም ” ብለዋል።
በስልካቸው ፎቶና ተንቀሳቃሽ ምስል አንስተው እንዳይልኩ ስልካቸውን
መቀማታቸውን የገለጹት የቦኒ ቀበሌ ነዋሪዎች፤ አሁን የያዙት ስልክ ተለዋጭ እና የቤተሰባቸውን መሆኑን ገልጸዋል።
ግድያ የተፈጸመባቸው ዜጎች አማራ በመሆናቸው ብቻ መሆኑንም ነው አል ዐይን አማርኛ ያስታወቁት። የኦሮሚያ ክልል መንግስት በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ ቦኔ ቀበሌ፣ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጧል። (አል ዐይን አማርኛ)
በምእራብ ወለጋ ንፁሀን ላይ ግድያ መፈጸሙን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ
በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ ቦኔ ቀበሌ፣ ንፁሀን ላይ ግድያ መፈጸሙን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በጥቃቱም የሞቱት 16 ወንዶች እና 12 ሴቶች ህይወት ተቀጥፏል ሲሉ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ መርዳሳ ተናግረዋል።
ከሟቾች በተጨማሪም 12 ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።
የክልሉ ፖሊስ በአካባቢው ደርሶ አካባቢውን ለማረጋጋት በደረገው ጥረት ሶስት የኦነግ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ መርዳሳ ተናግረዋል።
የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ከምሽቱ ሶሰት ሰአት ላይ ከ50 በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎችን ሰብስቦ ጭፍጨፋ ፈፅሟል ሲሉ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ባለፈው አንድ አመት በኦነግ ሸኔ ላይ በተወሰደም እርምጃ 1 ሺህ 947 አባላቱ የተገደሉ ሲሆን 489 አባላቱ ደግሞ መማረካቸውን ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል። (ኢብኮ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply