ለኢህአዴግ ሊቀመንበርነትና ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የህወሓት እጩ በመሆን የቀረበውና በህወሓት ሙሉ ድምጽ የተሰጠው ሽፈራው ሽጉጤ ከደቡብ ሕዝብ ሊቀመንበርነቱ ለቀቀ።
ሽፈራው ሽጉጤ ራሱ እንደተናገረው ከሆነ “ከሥልጣኔ ለቅቄአለሁ” ቢልም አፍቃሪ ህወሓት የሆኑና እርሱ በኢህአዴግ ሊቀመንበርነት እንዲመረጥ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ሲሠሩ የነበሩ ሰውየው “ተገፍቶ ነው” የወጣው በማለት አቅጣጫ የማስቀየር ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውለዋል።
በቅርቡ በሃዋሳ በደረሰው ግጭት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሚመለከታቸው አመራሮች በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ ቢሆኑም ባይሆኑም ይህ ዓይነቱ ግጭት እየተፈጠረ በኃላፊነት መቀጠል እንደሌለባቸውና ከሥልጣናቸው በፈቃዳቸው መልቀቅ እንዳለባቸው ሃሳብ ሰጥተው ነበር። ይህንንም ተከትሎ ከወላይታ ዞን አራት አመራሮች በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን በደብዳቤ ማሳወቃቸው ይታወሳል።
በዚሁ የሃዋሳ ግጭትና ያንን ተከትሎ በተፈጸመው ግድያ ሽፈራው ሽጉጤ ተጠያቂ እንደሚሆንና ሕዝቡም “አይወክለንም” በማለት ድምጹን ሲያሰማ መቆየቱን በቪኦኤና በሌሎች የሚዲያ ውጤቶች መዘገቡ ይታወቃል።
በበርካታ ወንጀሎች በተለይም በደቡብ ክልል ይኖሩ የነበሩ አማሮችን ከቀያቸው እንዲለቁ በማስገደድ ግፍ እንደፈጸመ በተደጋጋሚ የሚነገርበት ሽፈራው ከፓርቲው ሊቀመንበርነቱ መነሳት ቀጥሎ ከሚኒስትርነቱም እንደሚለቅ በስፋት ይነገራል። በደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በነበረበት ዘመን ፈጽሞታል ከሚባለው ወንጀሎች ጋር በህወሓት አጋርነቱ በሌሎች ሤራዎችም ይጠረጠራል። በዚህ ላይ አስተያየታቸውን የሚሰጡ እንደሚሉት በቀጣይ ወደ ፍርድ ከሚመጡ ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ሽፈራው ሽጉጤ ቀዳሚው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው።
ከኦህዴድንና ብአዴን መክዳት ጋር በተያያዘ ህወሓት አለኝ የሚለው ቀሪው አጋዡ ደኢህዴን እንደሆነ የሚነገር ሲሆን ይህንንም አጠናክሮ የያዘለት ሽፈራው ሽጉጤ ነበር። ከሚመራው የደቡብ ሕዝብ ጥቅም ይልቅ የህወሓት ጉዳይ ይበልጡኑ የሚያሳስበው ሽፈራው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን በህወሓት በኩል ከፍተኛ ጫና ሲደረግ ነበር፤ ህወሓትም ሙሉ ድምጽ ሰጥታው ነበር።
ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ ከሰበሰበው አስተያየት መካከል “አብሬው ሠርቻለሁ” የሚሉ አስተያየት ሰጪ በማኅበራዊ ድረገጽ እንደጻፉት “ሽፈራው ማለት በጣም ደካማ፣ ከዕውቀት የጸዳ፣ ግብረገብነት የሌለው፣ አእምሮው የሞተ ሰው ነው፤ ከዚህ በፊት የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ ለመመረጥ እጩ ሆኖ መቅረቡን ስሰማ ታምሜ ነበር፤ የኢህአዴግ ፖለቲካ ባይሆን ኖሮ፤ ሽፈራው ሚኒስትር መሆን አይደለም የሚኒስቴሩ መሥሪያቤት ጥበቃ የመሆን ብቃት የሌለው ሰው መሆኑን እመሰክራለሁ” ብለዋል።
ሞት እንደ ቡሽ ክዳን ያስፈነጠረው መለስ ዜናዊ፤ የኢህአዴግን ዓላማ እስካስፈጸመ ድረስ መሃይምም ቢሆን በሚኒስትርነት እንሾማለን በማለት ይነዳው ለነበረው ፓርላማ መናገሩ ይታወሳል።
የሽፈራውን ሥልጣን መልቀቅ ተከትሎ በተመሳሳይ የህወሓት ሹመኞች ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይ ቅዳሜ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል ከተሞከረው ጋር በተያያዘ ከ“ቀን ጅቦቹ” መካከል ለፍርድ የሚቀርቡ እንደሚኖሩ ይጠበቃል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Leave a Reply