![](https://www.goolgule.com/wp-content/uploads/2024/01/wolkayit-welkayit-.jpg)
ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) ጋር አብሮ “የጠብ መንጃ ትግሉን ማጧጧፍ” በሚል ከውሳኔ የደረሱ ክፋይ የ”አማራ ነጻ አውጪ” ኃይሎች መኖራቸው ተሰማ። ለስምምነቱ ትሕነግ ምዕራብ ትግራይ የሚለውንና አሁን “ነጻ ወጥቷል” የሚባለውን ወልቃይት ተላልፎ እንዲሰጥ ፈቃደኝነት ያለበት እንደሆነ ተመልክቷል።
ራሳቸውን በተለያዩ አካባቢያዊና አደረጃጀት ከሰየሙት መካከል አሁን አንድ ለመሆን እየሠሩ እንደሆነ የሚነገርላቸው በዝናቡ የሚመራው የጎጃም ዕዝና የዘመነ ካሴ ኃይል ነው ይህን ስምምነት ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ የተሰማው።
“ጊዜው አሁን ነው፤ ይህንን ጊዜ ልንጠቀምበት ይገባል” በሚል በገሃድ ወልቃይትን ዳግም በኃይል ለመያዝ ደብረጽዮን በቅርቡ መናገሩ ይታወሳል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከሕዝብ ጋር በተለያዩ ከተሞች ውይይት ያደረገው ጌታቸው ረዳም “እኛ ሥራችንን መሥራት ባለመቻላችን ነው እናንተ ተፈናቅላችሁ የምትሰቃዩት” ብሎ በትግራይ መናገሩ አይዘነጋም።
ዜናውን ለአዲስ አበባ የጎልጉል ዘጋቢ ያቀበሉ “ፋኖና ትሕነግ ልዩነታቸውን አስወግደው በአንድነት ብልጽግናን ማስወገድ አለባቸው” በሚል በውጭ አገር ባሉ አመራሮች አማካይነት ንግግር እንደነበር ያስታውሳሉ። ሙከራው ተግባራዊ ሊሆን ያልቻበትን መሠረታዊ ጉዳዮች ያስረዳሉ።
በአማራ ክልል ውስጥ ያለው የጠብመንጃ እንቅስቃሴ በኤርትራ የሚደገፍ መሆኑ ሻዕቢያ ከትሕነግ ጋር የሚፈጠር ማንኛውንም ጥምረት አለመፍቀዱና ወልቃይትን ከትሕነግ በላይ ሻዕቢያ ስለሚፈልገው፣ ከፋኖ ውስጥም ሆነ ከአማራ ልዩ ኃይል ከወጡት ውስጥ የወልቃይትን ጉዳይ ለድርድር የሚያቀርቡ ስላሉ ንግግሩ ከምኞት አለመዝለሉን በዋናነት ይገልጻሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው አዲሱ የማበር ዜና ሾልኮ የወጣው። ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ያገገመው ትሕነግ መንግሥትን በድርቅ፣ በተለያዩ ወንጀሎች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰልፎች ጫና በማሳደር፣ ከአሜሪካ የምስራቅ አፍሪቃ አምባሳደር ሃመር ጋር ተከታታይ ግንኙነት እያደረገ ባለበት ወቅት ነው።
ዩኤስ ኤይድ (USAID) “የዕርዳታ ስንዴ ተሰርቋል” በሚል ያቋረጠውን እርዳታ ሲጀመር “ብቻዬን ልሥራ፣ አጠገቤ ድርሽ አትበሉ” ማለቱንና መንግሥት ይህ ዓለም ላይ በየትኛውም አገር የማይሠራበት አሠራር ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑንን በሁለት ከፍል ባሰራጩት የሥልጠና ቪዲዮ ላይ ማስታወቃቸውንም የዜናው ምንጭ ጉዳዩን እንደሚያጠነክረው ገልጸዋል።
በአማራ ስም በተለያዩ የአካባቢና የአደረጃጀት ስም የሚጠሩት ነፍጥ አንጋቢዎች መከፋፈላቸው በኢትዮ360 ሳይቀር በይፋ እየተገለጸ ባለበት፣ እስከንድር ነጋ ከጎጃም ወደ ሸዋ እንዲሸሽ መደረጉ ከተሰማና በጎንደርና አካባቢው አሉ የሚባሉ አደረጃጀቶች አቋም ጠርቶ ባልወጣበት፣ በሸዋ ያለው ትግል በዕርስ በርስ ግጭት ላይ መሆኑንን ከስፍራው ታዛቢዎች ይፋ እያደረጉ፣ በደሳለኝ ሲያስብ ሸዋ እና የእርሱ አለቃ የነበረው መከታው ማሞ ኃይሎች መካከል የነበረው አለመግባባት እያየለ ሄዶ በሰላ ድንጋይ አካባቢ ደም መፋሰሳቸው በተሰማበት ሰሞን፣ በወሎ ማዶ ደግሞ የመሪነት ማዕረግ ያስነሳው አለመግባባትና ከመንግሥት ጋር ስምምነት እያካሄዱ ያሉ ወገኖች መኖራቸውን ተከትሎ ነው የጎጃሙ ቡድን ከትሕነግ ጋር መነጋገር እንደጀመረ የተሰማው።
ዜናውን ያሳበቁ እንደሚሉት ትሕነግ ዋና አጀንዳው ወልቃይት ነው። ወልቃይትን የማስመለስ አጀንዳው በየትኛውም ዘመን የሚታጠፍም አይደለም። ይህ ከሆነ ደግሞ ከትሕነግ ጋር ለማበር ወልቃይት ላይ ያለውን የትሕነግ አቋም መቀበል ወይም በተግባር “እንካችሁ” ማለት ግድ ነው።
ይህ ከትሕነግ ውልደት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ጸንቶ የቆመው የወልቃይት ጉዳይ፣ “እንደፍጥርጥሩ” በሚል አብሮ ለመታገል ውሳኔ መነሻቸውን ጎጃም ያደረጉት ኃይሎች እየሠሩ ቢሆንም፣ ጉዳይ አማራውን ስለሚያስቆጣ እጅግ ሚስጢር ተደርጎ ተይዟል።
ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ አሁን ከጀርመን የሚሰራጨው ኢትዮ ሚዲያ ፎረም የሚባለው የትሕነግ ልሳን ሰሞኑንን ባሰራጨው ዘገባ አውቆም ይሁን ሳያውቅ የአማራና የትህንግን ትግል የማቀናጀት ዕቅድ ቢኖርም፣ ሻዕቢያ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ወደተግባር የመሸጋገሩ ጉዳይ ለጊዜው እንደማይሆን በወፍ በረር ጠቆም አድርጎ ነበር።
አሁን የድርድርና የሽምግልና ወሬ በሚናፈስበት ወቅት የሻለቃ ዳዊት የሚመራው ኃይልና ሀብታሙ አያሌው የሚመራው 360፣ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚመራውና መሳይ መኮንን የከፈተው አንከር ሚዲያ በጋራ ለመሥራት ደፋ ቀና እያሉ እንደሆነ ነው።
ጉዳዩን የሚከታተሉ “ብዙ ጊዜ ተገዳድላችኋል፤ ለዜና ፍጆታ አይሆንም ብለን ይዘነው ነው” ሲል ሃብታሙ አያሌው ሰሞኑንን ዝናቡና ዘመነ ካሴ የሚመሩትን ኃይሎች መክሰሱ ራሱን ከነሱ የተለየ አዲስ ህብረት ጎጃምን ማዕከል አድርጎ መቋቋሙን ያረጋገጠ ሆኗል። ይህ ኃይል እስክንድርን ወደ ሸዋ ማባረሩ ይታወሳል።
ከኤርትራ አጀንዳና ፍላጎት አንጻር የሚቀኘው አንዳርጋቸው ጽጌ የሚመራው ኃይል፣ የጎጃሙን ኃይል ለመጠቅለል በርካታ ሙከራዎች አድርጎ እንደነበር የሚገልጹ እንዳሉት፣ በዝናቡ የሚመራዉ የጎጃም ዕዝ ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚህ ሁሉ ፍትጊያ በኋላ አሁን እንደተሰማው ይህ የጎጃም ኃይል አዲስ ለጀመረው እንቅስቃሴ ይጠቅመው ዘንድ ምናላቸው ስማቸውን ከ360 በማስወጣት የሚዲያ ዘመቻ ለመጀመር ዝግጅቱን ጨርሷል።
ቀደም ሲል ጀምሮ የተወለደበት መንደሩን፣ የጎጃምና አካባቢውን መረጃ በማጠናከር የሚታወቀው ምናላቸው፣ “የጎጃም ፋኖ ዜና ለአንተ ብቻ ይሰጥሃል፣ መቋቋሚያ ገንዘብ ይለገስሃል፣ ጎፈንድሚ በስምህ ትከፍትና እዚያ በቂ ገንዘብ በመዋጮ ስም እንዲገባልህ ይደረጋል” በሚል አሜሪካ የሚኖሩ ባለአቅሞች ቃል እንደገቡለት ጎልጉል ጉዳዩን በቅርብ ከሚያውቁ ሰምቷል።
ከዚህ ቀደም ምናላቸው ኢሣትን ለቅቆ ከወጣ በኋላ በዘይት ነጋዴው ወርቁ አይተነው በኩል በየወሩ በኢትዮጵያ ብር ቋሚ ደመወዝ እየተከፈለው፣ በውጭ አገርም ድጋፍ እየተደረገለት የራሱን ግዮን ቲዩብ የተባለ ሚዲያ ከፍቶ እንደነበር አይዘነጋም። ኤርሚያ ለገሰ ከ360 በብሄር ምክንያት መባረሩን ጠቅሶ ሲለቅ ምናላቸው ወደ 360 መመለሱ አይዘነጋም።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply