የተከበራችሁ የጎልጉል አንባቢያን፤ ለወራት ጠፍተን በመቆየታችን ታላቅ ይቅርታ እንጠይቃለን። አንዱና ዋንኛው ምክንያት ድረገጻችን በማደስና የምናትማቸውን ጽሁፎች ባዲስ መልክ ለማድረስ እየሠራን ስለነበር ነው። ሥራው በፈቃደኝነት የሚሠራ በመሆኑ ካሰብነው ጊዜ በላይ ቢወስድብንም ባሁኑ ጊዜ በመጠናቀቅ ይገኛል። በቅርቡ አዲሱን ድረገጻችንን እናስተዋውቃለን። እስከዚያው ግን እዚሁ ላይ እንደተለመደው መረጃዎችን ማተማችንን እንቀጥላለን። በተደጋጋሚ ለጠየቃችሁንና መልዕክቶች ለላካችሁልን ምስጋናችን የላቀ ነው። ከልብ እናመሰግናለን። ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ።
በኢትዮጵያ ከፖለቲካው ቀውስ በማያንስ መጠን የኢኮኖሚው መላሸቅ፣ የሥራአጥነትና ድህነት የሚያስከትሉት አደጋ አሳሳቢና አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ተጠቆመ። የለውጡ ኃይሎች ለውጡን በሚያደናቅፉ ላይ ፈጥነው እርምጃ አለመውሰዳቸው ስህተት መሆኑ ተነገረ።
የጎልጉል ታማኝ የአሜሪካ ዲፕሎማቲክ ምንጭ እንዳሉት ኢትዮጵያን ከለውጡ በኋላ አላላውስ ያላት ችግር የኢኮኖሚው ጣጣ ነው። ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ሲቀነቀን የነበረው የኢኮኖሚ መርህ የተነሳ ዜጎች ለሥራአጥነት ተዳርገዋል፤ የሥራአጡ ቁጥርም ከሚገመተውና በይፋ ከሚነገረው እጅግ የበለጠ ነው። በአሁን ወቅት የመንጋ፣ ቡድን፣ ጥርቅም የሚባሉት አካሎች ይኸው ድህነቱ የፈጠራቸው ክፍሎች እንጂ ሌላ እንዳልሆኑ የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉት ዲፕሎማት አመልክተዋል። የመንደርና የጎጥ ፖለቲካውም የራሱን ጫና ማሳደሩን ዲፕሎማቱ አይክዱም።
ችግሩን ይባስ ያወሳሰበው ደግሞ ይህንን ኃይል ገንዘብ ያላቸው ክፍሎች እንዳሻቸው መጠቀም መቻላቸው ነው። የለውጡ ኃይሎች ወደ ሥልጣን እንደመጡ ወዲያውኑ ሊወስዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች ባለመውሰዳቸው “ፌዴራል መንግሥት አይነካንም፤ አያዘንም” የሚሉ ጡንቸኛ አካላት እንዲፈጠሩ አድርጓል።
ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት አገሪቱን ሲመሩ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ሥር ወዲያውኑ አለመዋላቸው በሽሽት ከተደበቁበት ሆነው የቀድሞውን ሰንሰለታቸውን በተዋረድ እንዲጠቀሙበትና ተመልሰው ጡንቻቸውን እንዲያፈረጥሙ እንዳደረጋቸው ዲፕሎማቱ አስረድተዋል። የሚገርመው ይህንን አካሄድ የሚረዱ ዜጎች አገራቸውን ለመታደግ አሁን ድረስ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በውል ያወቁ አይመስሉም። ከዚያ ይልቅ የለውጡ ነቃፊዎችና ተቃዋሚዎች በስልትና በረቀቀ ጥበብ የሚነዛውን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ እንደ እውነተኛ መረጃ በመቁጠር በመንግሥት ላይ የማያቋርጥ ነቀፋ በየሚዲያው ሲሰጡ መታየታቸው ሕዝቡን ክፉኛ እያደናገረው ይገኛል።
ከለውጡ በፊት በተደጋጋሚ በእነ ዲ.ኤል.ኤ. ፓይፐር ዓይነት በሎቢ አድራጊዎቻቸው (ወትዋቾቻቸው) አማካይነት ዕድሜ ለማራዘም በተደጋጋሚ አሜሪካንን ሲወተውቱ የነበሩት የህወሓት ሰዎች አሁንም እስከ ሶስት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ክፍያ በመመደብ ዘመቻ ላይ መሠማራታቸውን ዲፕሎማቱን የጠቀሰው የመረጃው ባለቤት አስታውቋል። በተቃራኒው “ሌሎች እርስ በርስ ይተራመሳሉ፤ አገር በማተራመስም የጥፋት ተልዕኳቸውን ይወጣሉ፤ ብዙዎችም መንግሥትንና የለውጡን ኃይል በጭፍን በመተቸት አገር ያፈርሳሉ” ሲልም የዲፕሎማቱን ንግግር ቃል በቃል በመጥቀስ ያክላል።
የፌደራሉ መንግሥት ትርምሱንና በየቀኑ በረቀቀ ስልት የሚነዙትን የሃሰትና የጥላቻ መረጃዎችን ተከትሎ በሚፈጠሩ አደጋዎች ተወጥሮ ሌሎች ሥራዎችን እንዳይሰራ ጤና መንሳትን ዋናው ዓላማው ያደረገ በበጀት የተደገፈ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ ለጎልጉል የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።
ለውጡ እየመሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አገሪቱን አንድ አድርጎ መምራት እንደተሳናቸው ተደርጎ በረቀቀ ስልት ከሚፈጠሩ ቀውሶች ጋር በማቀነባበርና ኢትዮጵያ በቀውስ ውስጥ ነች በማለት የምዕራቡን ዓለም በተለይም አሜሪካንን ለማሳመን መጣር የውትወታው (የሎቢው ሥራ) ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን ዲፕሎማቱ ይናገራሉ። ይህንንም በማሳየት ዳግም ወደቀድሞው የአገሪቱ አመራር ለመመለስ ህወሓት እየሠራ መሆኑንን ያመለከቱት እኚሁ ከፍተኛ ዲፕሎማት “ሌሎች ወገኖች እንዲህ ያለውን አካሄድ ተረድተው እርምጃቸውን አለማስተካከላቸው በግል ያስገርመኛል” ሲሉ ተችተዋል።
በኤርትራ መፈንቅለ መንግሥት እንዲሆን ወይም በማንኛውም መልኩ በኤርትራ ለውጥ እንዲደረግ ሌት ተቀን የሚሰራው ህወሓት፣ የቅርብ ጊዜ ሙከራው ቢከሽፍም አሁንም በኢትዮጵያ የተከሰተው ዓይነት አፋጣኝ የፖለቲካ ለውጥ በኤርትራ ካልታየ ህወሓት ወደ ቀድሞ ስፍራው ለመለስ ያሉትን አማራጮች ሁሉ እየተጠቀመ መሆኑን ያመከቱት እኚሁ አንጋፋ ዲፕሎማት፣ “ጆሮ ያለው ይስማ” ሲሉ ምክር መሰንዘራቸውን ምንጩ አስረድቷል።
የዋጋ ንረት፣ ሥራአጥነትና ድህነቱ ከሚደረጉት ሽረባዎች ጋር ተዳምሮ ከቁጥጥር ሥር ሊወጣ ይችላል በሚል ስጋት መኖሩን ዲፕሎማቱ አልሸሸጉም። በዚህ መልኩ የሚፈጠረው ቀውስ ደግሞ መያዣና መጨበጫ ስለማይኖረው አሁን አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚሰሙት የወሮበላነት አዝማሚያ ያላቸው እንቅስቃሴዎች ይስፋፋሉ። እናም ዜጎች አገራቸውን ለማዳን ለውጡን እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው መረዳትና ለውጡ መደገፍ ይኖርባቸዋል። ይህን ማድረግ ካልቻሉ የችግሩ ፈጣሪዎች አጋዥና ረዳት ከመሆን እንደማያልፉም አመልክተዋል።
ለጎልጉል መረጃ የሰጡት ክፍሎች እንዳሉት አንጋፋው ዲፕሎማት ባላቸው መስመር አማካይነት ምን መደረግ እንዳለበትና ለውጡ አሁን የተጋረጡበትን ችግሮች በአሸናፊነት እንዲወታ በምን መልኩ መደገፍ እንዳለበት ለሚመለከታቸው ሃላፊዎች ምክር እንደሰጡና ወደፊትም እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
ነጻነት የሚመኙ ዜጎች ነጻነታቸውን በሰላም ማጣጣም ካልቻሉ፣ ሥጋት ላይ ይወድቃሉ። ሥጋት ሲበዛ ዜጎች ከነጻነት ይቅል ቅድሚያ ሰላማቸው እንዲጠበቅ ይመኛሉ። ይህንን ሃቅ አምባገነኖች ስለሚረዱ ሕዝብ ሰላም እንዳይሰማው ሁሉንም ዓይነት ጉድጓድ ይቆፍራሉ። ዜጎች ሥጋት እንዲሰማቸው ሃብታቸውን ያፈሳሉ። እናም ሰላም ከሌለው ነጻነት ይልቅ፣ ሰላም ያለውን አፈና እንዲመርጡ ይገደዳሉ። በዚህ ስሌት ለውጡ ከመጣ ጀምሮ ሰፊ ዘመቻ ሲካሄድ እንደነበር፣ ከለውጡ እውን ሊሆን ባለበት ጊዜም ቢሆን ለውጡ ከተካሄደና “እነርሱ” ከሥልጣን ከተነሱ አገሪቱ እንደምትፈርስ በማስጠንቀቅ በተደጋጋሚ የህወሓት ቁንጮዎች ዘመቻ ሲያካሂዱ እንደንነበር ጎልጉል መዘገቡ አይዘነጋም።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Leave a Reply