
የሥራ አስፈጻሚው ከፍተኛው አካላት የሆኑት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅና ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ህወሃት ቀዩን መስመር ማለፉን አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንጹሀን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት።
“የሰማሁት አሰቃቂ ግድያ ልቤን በእጅጉ ሰብሮታል። ንጹሀን ዜጎች በሌሎች እብደት ውድ ሕይወታቸውን የሚከፍሉበት ንብረታቸው የሚወድምበት መሄጃ አጥተው የሚንከራተቱበት ምንም ምክንያት የለም። የዛሬ ዓመት በ30/10/2019 የጻፍኩትን ትዊት ልድገመው።
“ዘርና ሀይማኖት ለፖለቲካ ጥቅም እንዲውሉ ሲደረግ፤ ንጹሀን ዜጎቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉና ሲንከራተቱ ስናይ ስሜትን ለመግለጽ ቃላት ያጥራል። ለቅሶ፣ ድንጋጤና ሥጋት የብዙዎችን በር አንኳኩቷል ሃዘናቸው ሃዘኔ/ሃዘናችን ነው። “ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባን ቀይ መስመር ተጥሷል፤ አገራችንን ካንዣበበባት ክፉ አዳጋ ለማዳን ሁላችንም ሚና አለን። የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው፡ቀይ መስመር መጣስ የለበትም እንበል”።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው ይህንን መልዕክት በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው አስፍረዋል፤
“ሕወሐት በትግራይ በሚገኘው የመከላከ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል። ይህ ሠራዊት ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ ሠራዊት ነው። በቦታው የሚገኘውም የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ነው። ሕወሐት ግን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ ሀገር ሠራዊት ቆጥሮ። የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነሥቷል። በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት ከፍቷል።
“መንግሥት የትግራይ ሕዝብ እንዳይጎዳ በማሰብ፣ ጦርነት እንዳይፈጠር የትእግሥቱ ጫፍ ድረስ ታግሷል። ጦርነት የሚቀረው ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ አይደለም።
“የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል። ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል። ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል።
“የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ እንዲከታተል፣ በየአካባቢው ሊከሠቱ የሚችሉ ትንኮሳዎች በንቃት እንዲቃኝና ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን እንዲቆም ጥሪ አቀርባለሁ”።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply