አምስተርዳም (በቪቫ ምኒልክ)
ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ በኢትዮ 360 በሰሞኑ የኢትዮጵያን መከላከያና ደህንነት ክፍል አስመልክቶ የቀረበው ውይይት እጅግ ስለ አስደነገጠኝ ነው።
ከውይይት ጭብጥ እንደተረዳሁትም ከመከላከያና የደህንነት መስሪያቤት ከፍተኛ አመራሮች በደረሰን መረጃ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አገራችንን ለአረቦች አሳልፎ በመስጠት የእስልምና ሐገራት አባል ለማድረግ እየሰራ ነው የሚልና የምእራብ እዝን ወደ ወለጋ ያዛወረው የኦሮሞን ልዩ ሃይል ለማደራጀት እንዲመቸው ነዉ የሚል በጥላቻ ላይ ብቻ የተመሰረተው ክሳችሁን መሉ ለሙሉ የምቃውምበትን ነጥብ ከዚህ በታች በአጭሩ ዘርዝር አድርጌ ለማስተላለፍ እሞክራለሁ።
የውይይት ሃሳባችሁ መነሻ ያደረጋችሁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከሰይፉ ጋር ያደረጉት ዉይይት ላይ ስለ አረብ አገራት ለኢትዮጵያ በሚሰጡት የገንዘብ ድጋፍ አስከትሎ የሰጡት አስተያየትን ቀደም ብለን መረጃው በእጃችን (በEthio 360) መግባቱን በመረዳታቸው ለመከላከል ያቀዱት መንገድ ነዉ የሚል ነጥብ አንስታችኋል። በዚህ ጉዳይ ለኔ ግልፅ ሆኖ የታየኝ በገና በዓል ምክንያት ረዳት ለሌላቸው አዛውንትና ህፃናት በአደረጉት የምሳ ግብዣ ላይ እነዚህ አዛውንትና ህፃናት በቋሚነት ህብረተሰብ ግንዛቤ አግኝቶ ድጋፍ እንዲያደርግ ሚድያው ከፍተኛውን ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ ብለው ስለገመቱ፤ ከነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነውን ጋዜጠኛ ሰይፉ ፋንታሁንን ጋበዙ። ጋዜጠኛው ካነሳው ጥያቄ ተመርኩዞ የሰጡት መልስ ከሳቸውም በፊት አረቦቹ ከኢህአዲግ ጋር ተቀራርበው ይሰሩ እንደነበር ገልጸዋል። ሌላው ቀርቶ የብሔራዊ ደህንነት ቢሮ (ህንፃ) ግንባታን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውንና በሳቸው አመራር ግዜም ይበልጥ መቀራረብና መግባባት እንዳላቸው ተናግረዋል። ይህንንም ግንኙነት የነሱን ፍላጎት በጠበቀና እኔም የሃገሬን ብሔራዊ መብት በማይነካ ደረጃ እየጠበቁ እንደሚያጠናክሩት በግልፅ አስረድተዋል።
ኢትዮ 360 ግን እነሱ የሚሰማቸውን ብሔራዊ ስሜት ያህል ሀገሪቱን የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማይሰማቸው ናቸው ብሎ በድፍረት መናገራችሁ ለምን ዓላማ ልትጠቀሙበት እንድፈለጋችሁ በግልፅ ሊገባኝ ባይችልም አጀንዳው ወያኔ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ከሚያቀርበው ክስ ጋር ተቀራራቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
ወያኔ ወደ ሥልጣን ለመመለስ ብዙ ቀውስ እየፈጠረ በሚገኝበት ሰዓት ላይ የመጨረሻ አጀንዳው አድርጎ ሊጠቅምበት የሚፈልገው ጉዳይ የመከላከያና የደህንነት ክፍሉን ለመበታተን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ወድቋል በሚል የጀመረውን ቅስቀሳ በሚደግፍ መልኩ እናንተ የምታደርጉት ተደጋጋሚ ዘገባዎችና ውይይቶች ከወያኔ ባልተናነሰ ደረጃ በየቀኑ በጠቅላይ ሚንስትሩ ላይ የምታደርጉት ከመስመር የወጣ ትችትና ዘለፋ ሚዲያችሁ ነፃና ገለልተኛ ነው ብዬ ለማመን እቸገራለሁ።
ከሃገሬ በብዙ ሺህ ማይል የራኩና ከሃገሬም ከወጣሁ ሩብ ክፍለ ዘመን ያስቆጠርኩ እንደ መሆኔ አፌን ሞልቼ በትውልድ እናት ሃገሬ ውስጥ በየቀኑ ስለሚካሄደው ሁኔታ በቂ መረጃ አለኝ ብዬ ባላምንም አሁን በሃገራችን የሚካሄደውን ለማወቅ ግን ዘመኑ የደረሰበት የመረጃ ፍሰት መረጃን ለማግኝትም ሆነ እውነተኛውን አጣርቶ ለማወቅ ብዙ አስቸጋሪ ሆኖ አላገኘሁትም ስለዚህ ነው ኢትዮ 360 የተሳሳተ መረጃ ከማስተላለፍ ልትቆጠቡ ይገባል የምለው።
ከውይይታችሁ ዉስጥ እንደተደመጠው የምዕራብ እዝን ወደ ወለጋ የወሰደው የኦሮሚያ ልዩ ሃይልን ለማጠናከርና የኢትዮጵያ መከላከያ ለማዳከም ነዉ የሚል ክስ አቅርባችኋል። የኢትዮጵያ መከላከያ የምድር ጦር እደረጃጀት በእዝ የተከፋፈልና አስፋፈሩም በግልፅ የሚታወቅ መሆኑም ለማንም ማወቅ ለሚፈልግ አስቸጋሪ ያለመሆኑ እየታወቀና የምእራብ እዝ ወደ ወለጋ ለግዳጅ መንቀሳቀስ በየቀኑ በየሚዲያው በግልፅ እየተነገረ፣ እናንተ ለምን ትርጉም ልትሰጡት እንደፈለጋችሁ ለኔ አልገባኝም?
ወያኔ ላለፉት ሃያ ሰባት አመት ኢትዮጵያ አገራችንን ምን አይነት አዘቅት ዉስጥ ከቷት እንደሄደና የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ሰጥቻችዃለሁ ብሎ እየተመፃደቀ በሚገኝበት በአሁኑ ሰአት፣ ወያኔ በአደራጀው የአፓርታይድ የዘር አከላለልና አንዱ በእንዱ ላይ እንዲነሳሳ በረጨው የጥላቻ ፖለቲካ በተለያየ የሃገራችን ቦታዎች ዜጎች የመኖርና ወጥቶ የመግባት ዋስትና አጥተው ህይወት እንደ ቅጠል እየረገፈ በየቦታው እየተፈናቀሉ በምንሰማበት ሁኔታ ይህን ችግር ለማስወገድ የሚቻለውን ሁሉ በማደረግ ላይ የሚገኘውን መንግሥት ብዙ ማጣጣልና እንዲዳከም ብሎም እንዲወድቅ ከወያኔና ዘረኛ ከሆኑ ሃይሎች ጋር በግልም ሆነ በተዘዋዋሪ መተባበር ኢትዮጵያን እንደማፍረስ ይቆጠራል።
ካቀረባችሁት ከፍተኛ ክስ ዋናው ሊሰመርበት የሚገባው ተወዳጁ የኢትዮጵያ መከላከያ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃገሪቱን ደህንነትና መከላከያ ተቋም በውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት አስደፍረዋል በሚል በመቃወሙ ከቦታው ሊነሳ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበረ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊያነሱት ነበር በመሀል ተገደለ። ከግድያው ጀርባም የሳቸው እጅ አለበት የሚል ጥርጣሬ እንዳላችሁ፤ አሁንም ይህንን ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙት ከፍተኛ ጀኔራል መኮንንኖች ይህው ግድያ እንዳይደርስባችው ስጋት እንዳላችሁ የገለፃችሁበት መንገድ ምንም አይነት የማጣራትና የመመርመር በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተመረኮዘ የጋዜጠኝነት ሥራ ሳትሰሩ በነፍሰ ገዳይነት መፈረጅ እናንተን በግልፅ የወያኔ መንገድ ተባባሪ ናችሁ ለማለት ያስችላል ።
እውነታው ግን እኔ እንደተረዳሁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከሚደነቁበት ዋንኛው ነጥብ በአብላጫው በወያኔ ትግራይ የበላይነት የተያዘውን የመከላከያና የደህንነት ተቋም በፍጥነት ማሻሻያ (Reform) ማድረጋቸው ነው። ለዚህም ተግባር ተባባሪ ከነበሩት ውስጥ በግንባር የሚጠቀሱት ጀነራል ሰአረ መኮንን ሲሆኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የለውጥ እንቅስቃሴ አጋርና ለኢትዮጵያ ህዝብ ታማኝ በመሆን ህይወታቸው እስካለፈ ድረስ በሃቅ አግልግለዋል። እኝህን የመሰለ ታማኝ ጀነራላቸውን ነው ዓብይ እውን አስገደለው የምትሉን?
በኔ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሃገሬቱን ላለፉት ሁለት አመታት መምራት ከጀመሩበት ግዜ እስካሁን ብዙ ሊመስገኑም ሊወቀሱበት የሚችል ብዙ ዝርዝር ሁኔታዎች ቢኖሩም አሁን ምርጫ ሊቃረብ ጥቂት ወራት ሲቀረው ይህን ሁሉ አፍራሽና ሚዛናዊነት የጎደለው ፕሮፓጋንዳ ማድረግ ለሐገራችንና ለህዝባችን ምን ጥቅም እንድ ሚሰጥ ፍርዱን ለአንባቤና አድማጭ እየተውኩ፣ ሃገሬ መቼ ይሆን በሙያው የተካነ አድሎአዊ ያልሆን ለአንድ በድን ወይም ብሔር ያልወገነ በጋዜጠኝነት ሙያና ስነ ምግባር ያለው ጀግና ጋዜጠኛ የሚወጣላት እያልኩ ላለፉት ፪ ዓመታት ከመቼውም ግዜ በበለጠ ዝምታ የመረጥኩበት ሁኔታ ላለፉት ሩብ ክፍለ ዘመን በስደት የትግል ሕይወቴ ብዙ ነገር ያሳየኝና ያስተማርኝ ቢሆንም እንዳለፉት ፪ ዓመታት እጅግ የሚገርምና አይን ያወጣ እናውቅልሃለን ባይ የበዛብት ግዜ ላይ በመድረሴ ዝም ብሎ ማዳመጥ የተሻለ መሆኑን በማመኔን ነበር።
እጅግ የምወዳትና ከፍተኛ የአካል መስዋእትነት የከፈልኩባት እናት ሐገሬ ዛሬ ባለችበት ከፍተኛ ስጋትና ተስፋ ውስጥ ከእግዚአብሔር በታች የሐገሬን ህዝብ ብቸኛ ዋስትና በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጠቅላይ አዛዥነት የሚመራው የሃገር መከላከያና የድህንነት ሃይል ብቻ ነው ብዬ እኔ አምናለሁ። ቢያንስ ትክክለኛ ምርጫ ተካሂዶ በህዝብ ድምፅ የሚመረጥ መንግሥት ሃላፊነትን እስኪረከብ ድረስ ትእግስት ይኑረን እያልኩ ለዛሬው ሃሳቤን በዚሁ አጠቃልላለሁ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply