በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)
“እንደቀልድ፣ ሳናውቀው አገራችን ወደ ፍርስራሽነት ተቀየረች” አለ፣ አንድ ታዋቂ የየመን ጋዜጠኛ፤ በአንድ ቃለመጠይቁ ላይ። ነገሮች የረዥም፣ ተከታታይ ሂደት ውጤት ወይም መጨረሻ ናቸው፤ የድንገቴ ክስተት አይደሉም። ጦርነት ያለመግባባትና የቅራኔ ሂደት ውጤት ነው። ሞት ከጤንነት ጀምሮ፣ እየጠነከረ የሚሄድ ህመም ሒደት ውጤት ነው። በሥርዓትና ደንብ የቆመ ሀገር መፍረስም እንዲሁ የረዥም ጊዜ፣ ተከታታይ ከሥርዓትና ደንብ ማፈንገጥ ሒደት ውጤት ነው።
የሀገር መሪዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች . . . ሁላችንም፣ “ኢትዮጵያ አትፈርስም” እያልን እንጮሀለን። ከጩኸቱ ጀርባ የቻሉትን እያደረጉ ያሉት ግን የሀይማኖት አባቶች ብቻ ናቸው፤ ዕንባቸውን ሽቅብ ወደ ፈጣሪ መንበር እየረጩ የመንፈስ ልጆቻቸውን ይለምናሉ፤ ምእመኑን በጸሎትና በጾም ያተጋሉ። ፖለቲከኞች እዚህ ግባ የሚባል አቅም የላቸውም፤ አብዛኞቹ ያላቸውን ትንሽ አቅም ፓርቲያቸውን በምርጫ ቦርድ አስመዝግበው፣ በመጪው ምርጫ መሳተፍ ይችሉ ዘንድ እየተጠቀሙበት ነው። የሀገርንና የዜጎችን ጉልበትና ሀላፊነት ጠቅልሎ የተሸከመው መንግሥት፣ በየአካባቢው ለሚታየው የዜጎችን ህይወትና ንብረት፣ እንዲሁም በሰላም ወጥቶ የመግባት ተግዳሮት ለመቆጣጠርና “አትፈርስም!” የሚላት ሀገር እንዳትፈርስ ለማድረግ የሚያስችል እርምጃ እየወሰደ አይደለም፤ እየተከተለ ያለው አዲስ መንገድ እንደ ሰበካና ልመና እየተወሰደ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰበካና ልመና የሚሰማ ቢሆን ኖሮ፣ በአለም የሚኖሩ ጻድቃኖች ነፍስ ወደ ሰማይ አትሰደድም ነበር፤ ሀገራችን የጻድቃኖች ማረፊያ ምድራዊ ገነት በሆነች ነበር። አይሰማም!
ሁላችንም አንድ ልብ ያላልነው ጉዳይ አለ። ይኸውም፣ በፈረሰ ሀገር ውስጥ የተፈፀመና እኛ ሀገር ያልተፈፀመ የሰብአዊ መብት በደል ምን አለ? ሞት! በየአይነቱ፣ በሚዘገንን መንገድ ተፈፀሟል፤ ዝርፊያ! ባንኮች ጭምር ተዘርፈዋል፤ ሀብታሞች ሰርተው ያፈሩትን፣ ድሆች ጾም አድረው የቋጠሩትን አይናቸው እያየ ተዘርፈዋል። ማፈናቀል! የዚህ ተጠቂዎች በሚሊየን እስከመቆጠር ደርሰው ነበር፤ አሁንም በሺዎች ይቆጠራሉ። የሀይማኖት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ተቃጥለዋል፤ . . . ምን ያልተደረገ ቀረ!?
መፍረስን እየተለማመድነው ነው። ስናስባቸው ያቅለሸልሹንና ያስመልሱን፣ እንቅልፍ ለቀናት ይነሱን የነበሩ አስነዋሪ ተግባራት፣ እንደየልብ ባልንጀራ በየቀኑ የምናገኛቸው ተግባራት እየሆኑ፣ እየተለማመድናቸው ነው። አሁን እንደ ሀገር ከመፍረስ ጋር ያለን ርቀት የቁጥርና የድግግሞሽ ጉዳይ ብቻ ነው። ለመሆኑ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ስንት ሲሆን ነው ሀገር ፈረሰች የሚባለው? ስንት የሀይማኖት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሲቃጠሉ ነው ሀገር ፈረሰች የሚባለው? መንገድ ተዘግቶ ስንት ቀን ሰዎች በወጡበት ሲያድሩ ነው ሀገር ፈረሰች የሚባለው? ስንት ዩኒቨርሲቲዎች የግጭት ማዕከል ሆነው ሲዘጉ ነው ሀገር ፈረሰች የሚባለው? . . . በአጠቃላይ ስንት ክልል፣ ስንት ከተማ፣ ስንት መንደር፣ ስንት ጎጆ ነው የሀገር መፍረስ ማረጋገጫ!? ለዚህ ነው የመናዊው ጋዜጠኛ፣ “እንደቀልድ፣ ሳናውቀው አገራችን ወደ ፍርስራሽነት ተቀየረች” ያለው።
መንግሥት ህግና ሥርዓትን ማስከበር እንዳለበት የሚያምን ከሆነ፣ ጊዜው አሁን ነው። የኢህአዴግ ውህደት በጎ ተስፋ ቢሆንም፣ ትልቅ ችግር ይዞ እንደሚመጣ ምልክቱ እየታየ ነው፤ የኢህአዴግ ውህደት በአዳራሽ ውስጥ፣ በሥራ አስፈጻሚዎች ውይይት ሳይሆን፣ ከአዳራሹ ውጪ ባለው ሰላም፣ የህግና የሥርዓት መከበር ነው እውን ሊሆን የሚችለው።
ህግ፣ መንግሥት መንበረ ሥልጣኑን ሲቀበል የሚረከበው ሀገርና ዜጋን ማስተዳደሪያ መሣሪያ ነው። መንግሥት ከዜጎች ጋር የተቆራኘበት ገመድ ነው – ህግ። ህግን የማያስከብር መንግሥት ዜጎችን ከጥቃት ሊከላከል አይችልም። ህግን ካላስከበረ፣ ዜጎቹ ከመንግስት ይልቅ ህግ በሚጥሰው፣ ግፍ በሚፈጽመው ላይ ለመተማመን ይገደዳሉ (አብዛኛውን ጊዜ እምነት ከፍርሀት እንደሚመነጭ ልብ ይሏል)። . . . መንግሥት ህግን ማስከበር አለበት። ለዚህ ደግሞ ጊዜው አሁን ነው።
(ፎቶ፤ የሰንዓ አሮጌ ከተማ በቦምብ ጥቃት ከፈራረሰ በኋላ)
Leave a Reply