
ማስታወሻ እንደ መጠቆሚያ – የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትህነግ) በሚል ስያሜ ራሱን ጠርቶ ተመሥርቶ፣ በዚሁ ስም ከበረሃ ተነስቶ አገር የመራበትና የፈጸማቸው ተግባራት በሙሉ የቅርብ፣ በዚህ ትውልድ ላይ የተፈጸመ ነው። ያለ ነጋሪና መስካሪ ይህ ትውልድ በአይን ብረቱ ያያቸው፣ በጆሮው ያደመጣቸውና በጋራ ሲመክርባቸው የነበሩ ናቸው። አሁንም ጉዱ አላለቀም። እንደውም የአሁኑ “ተያይዘን እንጥፋ ወይም ልሳፈርባችሁና ልዝረፋችሁ” የሚል መፈክር ይዞ ዘጠና አምስት መቶኛ ሕዝብ በአምስት መቶኛ አጣፍቶ ለመንገስ አልሟል።
ይህ ኃይል ዛሬ የሚያወራው፣ የሚሰብከውና የሚጫወተው ከዚህ ግብሩን በደንብ ከሚያውቀውና “በቃኝ” ብሎ ካፈናጠረው ትውልድ ጋር መሆኑን ይዘነጋል። በዚህ ከሥር እንዳለ በቀረበው የትርጉም መረጃ ኤፍሬም ይስሃቅ አምላካዊ ቅባ ቅዱስ የሚቀባው የሉሲፈር ሽል ብርሃነ፣ ከሽግግር በኋላ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚጠይቁና ድራማውን ከጀርባ ሰርተው ሲንፈራገጡ የነበሩት ኢሌኒዎች፣ ህዝብ አፈር ከመሬት ሲደባልቃቸው “ከደሙ ንጹህ ነኝ” እያሉ የሚያሰሙትን ጩኸት በቃላቸው ውስጥና፣ አስረጂ ሆኖ በተተኪ መሪነት በቀረበው ብርሃነ ማብራሪያ ውስጥ መመለከት አግባብ እንደሆነ ለማመላከት እንወዳለን። ድርጅቱ ስሙ ወያኔ ሳይሆን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ነውና ከትግራይ ውጪ ባለ ጉዳይ የማያገባው ድርጅት መሆኑ እየታወቀ ይህ ሁሉ የፖለቲካ ሥሪያ እንዴት ተፈጸመ፣ እንዴትስ ተጠራሩ? የሚለውንም መረዳት ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ይሆናል።
ሲጀመር
“ከአፍ ሲያመልጥና ራስ ሲመለጥ…” ከሚለው የብልሆች ዘዬ የዘለለ የሁለት መድረክ ዳንሰኞችን ጉድ ከነምናምኑ እርቃን ያወጣ፣ አደባባይ ያሰጥ፣ ማስተባበያ ሊቀርበብት የማይችል … አንዳንዶች ከአምላክ ቀና ፍርድ ጋር ያያዙት ድማሚት የፈነዳው ኢትዮጵያዊያን “በቃ” ባሉበት ታሪካዊ ቀን ነው። ድማሚቱም ጄፍሪ ፒርስ ጎልጉሎ አየር ላይ ያሰጣው ፊልም ነው።
በአንድ ቀን ለአገር ክብርና ህልውና የቆሙ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ያሰሙ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ አገርን በክህደት አሳልፎ ለመስጠት የተማማሉ ከሃጂዎች በድብቅ ሲዶልቱ ነበር። የኢትዮጵያ ልጆች በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሰላሳ ከተሞች “በቃ” ባሉበት እሁድ ኅዳር 12፤2014ዓም (ኖቬምበር 21፤2021) ቀን፣ የእፉኚቶቹን ሤራ እንደ መብረቅ ያፈነዳው፣ ካናዳዊው የኢትዮጵያ ወዳጅና የምዕራባውያኑን ሤራ እግር በእግር እየተከታተለ የሚያጋልጠው ጄፍሪ ፒርስ ነበር።
ሁለት ሰዓታትን የወሰደው የሁለት መድረክ ዳንሰኞችን ያካተተው ስብሰባ የተጀመረው በኤፍሬም ይስሐቅ መሪነት ነው፤ አውቆም ይሁን ሳያውቅ እየደጋገመ የስብሰባውን ተሳታፊዎች በስም እየጠራ አስተዋውቋል። ብርሃነ ገብረክርስቶስ፣ ቲም ክላርክ (በቅንጅት የምርጫ ድል ወቅት በኢትዮጵያ የአውሮጳ ኅብረት ተወካይ)፣ ዶናልድ ያማሞቶ (በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበረ)፣ ቪኪ ኸድልስተን (በምርጫ 97 ወቅት ቅንጅቶች የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍና አመጽ ሕዝቡ እንዳይተገብር ያከሸፈች)፣ ክሪስቲ (የፊንላንድ አምባሳደር)፣ እሌኒ ገብረመድኅን (የመለስ አድናቂና የትህነግ ደጋፊ)፣ ጥላሁን በየነ (በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ መምህር)፣ ታደሰ ውሒብ ((የአሜሪካ በሽታ መከላከያ መ/ቤት ሠራተኛ)፣ በቀለ ገለታ (የኢትዮያ ቀይ መስቀል ማኅበር መሪ የነበረ)፣ አቼ (ከኤፍሬም ይስሐቅ ጋር የምትሠራ)፣ ስቴፈን ጎንፐርዝ (አምባሳደር)፣ ቦብ ደዋር (ከሎንዶን አምባሳደር)፣ ኩለኒ ጃለታ (አሜሪካ ምክርቤት ሠራተኛ) ናቸው።
ኤፍሬም ይስሐቅ እንደ ሰም በሚቀልጥ ቃላት እያዘነበ ያሞካሸውን የትህነግ አሸባሪ ደርጅት ወኪል ብርሃነ ገብረክርስቶስን የሥራ ልምዱ ከጠቀሰ በኋላ ብርሃን መግለጫ እንዲሰጥ መድረኩን ወልውሎ አስረከበው። እርሱም የሚከተሉትን ነጥቦች በማንሳት ማብራሪ አወረደ፤ እዚህ ላይ ግልጹ ጉዳይ ይህ መድረክ ብርሃነን እንደ ሽግግር ጊዜ መሪ አድርጎ የሰየመና የሽግግሩ ጊዜ እንዴት እንደተቀመረ ጭምር ለማሳየት የታሰበ መሆኑ ሲሆን ሽማግሌዎቹ ዲፕሎማቶቹን ትተን ሌሎቹን ስናስብ የቁጥር ሁለቱ “ተለጣፊ” ማኅበራት ምልምል ካድሬ ስለ መሆናቸው የጎልጉል አንባቢያን ትረዱ ዘንድ ቃል በቃል አቅርበነዋል።
ጄፍ ምስጋና ይግባውና ይህን ጉድ ይፋ መሆኑን ተከትሎ “ካፈርኩኝ አይመልሰኝ” እንዲሉ በዚህችው በፈረደባት አገር እየማሉ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ለሚገዘቱ “ሁለት ማተብ ላጠለቁ፣ በሁለት ቢላ ለሚውጡ አልጠግብ ባዮች፣ ሁለት ሰፈር ለሚጫወቱ ምንደኞች ምላሽ ይሆን ዘንድና በታሪክ በጽሁፍ ተመዝግቦ ይቀመጥ ዘንድ በመርዝ የተለውሰውን ደባ ብዚህ መልኩ ሰብሰብ አድርገን አቅርበነዋል።
የብርሃነ ማብራሪያ
- ገና ከጅምሩ ዐቢይ ሥልጣን በራሱ ዙሪያ ለማድረግ በመሞከር በፌዴራላዊ መልክ ያዋቀርነውን መንግሥት ወደ ውህዳንና አንድ ዓይነት ሥርዓተ መንግሥት ለመፍጠር ይህም ከአማራ ጋር በመተባበር አሃዳዊ መንግሥት ለመመሥረት እንደፈለገ
- ሕገመንግሥቱን ለማፍረስና ፌዴራላዊ የተባሉትን የክልል መንግሥታትና አወቃቀር ለማፍረስ ይፈልግ እንደነበር
- ይህንንም በቅድሚያ ተግባራዊ ያደረገው የሱማሌን ክልል (ሰው ከአውሬ ጋር በማሰር ግፍ ይፈጽም የነበረውንና መረጃው በሰብዓዊ ድርጅቶች በማስረጃ ይፋ የተደረገበት አብዲ ኢሌ ይመራው የነበረውን ክልል ማለቱ ነው) በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አፈረሰው
- በቀጣይ ወደ ትግራይ ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ በመሞከር ኮማንዶዎቹን ላከ፤ ዓላማው የትግራይ አመራሮችን ለማሰር ነበር፤ የተላኩትን የትግራይ መንግሥት ለሁለት ወር አስሮ ለቀቃቸው
- ዐቢይ የክልል መሪዎችን ለራሱ ታማኝ በሆኑ መሪዎች ለወጠ
- ትግራይ ግን አልቻለም ምክንቱም እኛ ለፌዴራላዊ አስተዳደር ስንታገል ስለነበር አንቀበልም አልን፤ በዚህም ምክንያት
- ትግራይን በአምስት መንግሥታት ከበባት፤ ኤርትራ፣ አረብ ኤምሬትስ፣ የሶማሊያ 3ሺህ ጦር፣ የኢትዮጵያ መከላከያ እና የአማራ ኃይል
- እነዚህ አምስቱ መንግሥታት ትግራይን ወረሯት
- በወረራውና በውድመቱ ምክንያት ትግራይ ወደ ድንጋይ ዘመን ተቀየረች
- የትግራይ መከላከያ ኃይል ገና ሲጀመር የነበረው 9ሺ ፖሊሶች ብቻ ነበር
- ይህም የትግራይን ሰላም ለማስጠበቅ ያለ ፖሊስ ብቻ ነው
- በዚህ በ9ሺህ ኃይል ነው የአምስት መንግሥታትን ወረራ የተቋቋምነው
- በኋላ ግን በዓለም የወታደራዊ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ሕዝባችንን አስተባብረን የራሳችንን ጦር መሠረትን
- የትግራይ መከላከያ የተመሠረተው እነዚህን 5 መንግሥታትን ለመጋፈጥ ነው፤
- ይህንን ያደረግነው ደግሞ በሦስት ወር ውስጥ ነበር
- በውጊያውም የኢትዮጵያን መከላከያ ፍጹም እንዳይኖር አድርገን ደመሰስነው
- አሁን በመከላከያ ስም ያሉት መሃይም ገበሬዎች እና ቆንጨራ የያዙ ወጣቶች ናቸው
- በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ መከላከያ የሚባለው ይህ ነው
- ከውጪ ያስመጡትን የረቀቀ የሚባል የጦር መሣሪያ እንዳይጠቀሙበት በመከላከያው ውስጥ ምንም ብቃት ያለው ሰው የለም
- የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ ለማመን በሚከብድ ሁኔታ የትግራይ መከላከያ ሠራዊትን እየደገፈ ነው
- ለዚህም ነው አሁን ሰሜን ሸዋ የደረስነው
- አሁን በመከላከያ ስም ያሉት መሃይም ገበሬዎች እና ቆንጨራ የያዙ ወጣቶች ናቸው
- ዐቢይ የሰላም ድርድርን የሚቃወመው እና አልቀበልም የሚለው እርሱና ኢሳያስ አሰቃቂ የጦር ወንጀል ስለፈጸሙ ነው
- ይህ ደግሞ የጅምላ ግድያ (ጄኖሳይድ) የፈጸሙ ዓይነተኛ መለያ ነው – ሁሉንም ፈጅተው እስኪጨርሱ ነው የሚቀጥሉት
- እኛ ከሌሎች ጋር በመሆን 9 ቡድኖች ሆነን የተባበረ የኮንፌዴራሊስት ግምባር ፈጥረናል
- ሁላችንም ተመሳሳይ እምነት እንጋራለን
- ዋናው ዓላማችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ጊዜያዊ መንግሥት መመሥረት ሲሆን ከዚያም ሁሉን ያካተተ የሽግግር መንግሥት እንመሠርታለን
- ይህ የሽግግር መንግሥት ግን ብልጽግናን የሚያካትት አይሆንም
- ምክንያቱም ብልጽግና በጦርነት ከተሸነፈ በኋላ በመንግሥት ምሥረታ ውስጥ አይሳተፍም
(ይህ ልክ በ1983 ደርግን አፍርሰው እንዳደረጉት ከ30 ዓመት በኋላ ምንም መልኩን ሳይቀይር የወጣ ዕቅድ ነው)
ብርሃነ ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ ኤፍሬም ይስሐቅ ገለጻውን እጅግ የሚያስደንቅ፣ በጣም በዝርዝር የቀረበ እና የወቅቱን ሁኔታ በግልጽ የሚስረዳ ገለጻ ነው በማለት ሙገሳ ሰጥቷል (በንግግሩ አንዳችም የተግዳሮት ሃሳብ፤ ለምሳል በቅርቡ በወጣው የአምነስቲ ሪፖርት በትግራይ የዘር ማጥፋት አልተፈጸመም ብሏል፤ አንተ (ብርሃነ) ደግሞ በተደጋጋሚ ዘር ማጥፋት ተፈጽሞዋል ነው የምትለው፤ ስለ አምነስቲ ሪፖርት ምን ትላለህ በማለት እንኳ አልጠየቀም ወይም ሞጋች ሃሳብ አላነሳም)። ከዚያም ለጥያቄና መልስ መድረኩ ክፍት ሆነ፤
ስቴፋን መጠየቅ ጀመረ፤ የኔ ጥያቄ ከኤርትራ ጋር ያላችሁን ሁኔታ እና ከወዳጃችሁ ኢሳያስ ጋር እንዴት ነው የምታደርጉት የሚል ነው
ብርሃነ መልስ ሰጠ፤ ኦባሳንጆ ደህና ሰው ነው፤ የትግራይ መንግሥት ግን በአፍሪካ ኅብረት ደስተኛ አይደለም፤ ኅብረቱ የሚያደርገውን አንቃወምም፤ ኦባሳንጆንም ከመጀመሪው ጀምሮ ስንደግፍ ነበር፤ በትግራይ ሁሉን ዓቀፍ የዘር ጭፍጨፋ ተካሂዷል፤ ለምሳሌ እሌኒ ገብረመድህን ትግሬ አይደለችም ግን ስሟ የትግሬም ሊሆን ይችላል በሚል ቤቷ ተበርብሯል፤ ዐቢይ ነገ ከተስማማ እንቀበለዋለን፤ ግን የዘር ጭፍጨፋውን ማቆም አለበት፤ ትግራይን ቆልፎ አንዳች ነገር እንዳታገኝ አድርጎ የቆለፈውን መክፈትና ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርስ መክፈት አለበት፤ ፓርላማው እና ውሳኔዎቹ ተቀባይነት አይኖራቸውም፤ ትግራይ የማዕከላዊውን ሥልጣን የመያዝ ምንም ምኞት የላትም
ቲም ክላርክ ቀጣዩን ጥያቄ ከማቅረቡ በፊት ብርሃን እንዴት አሁን ወጣት እንደሚመስል ሙገሳ ሰጠ፤ የብርሃነን ገለጻ አስመልክቶ ቲም ሲናገር ሚስማሩን አናቱን ነው ያልኸው፤ ይሄ ዐቢይ አሃዳዊ መንግሥት ለመመሥረት ይፈልጋል ያልከውና ፌዴራላዊ አስተዳዳሩን ለማፍረስ ይፈልጋል ያልከው አቀራረብ ወሳኝ ነው፤ እኔ እንደ ሃሳብም ነው የምናገረው፤ ግን ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ወደተጎናጸፈችው አስደናቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ተመልሳ ትመጣ ይሆን፤ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በራሳቸው መፍትሔ ማምጣት ይችላሉ ወይስ እንደ አፍሪካ ኅብረት፣ አውሮፓ ኅብረት ወይም ታዋቂ ግለሰቦች ለመፍትሔው መግባት አለባቸው
ብርሃነ፤ ለተደረገለት የወጣት ነህ ሙገሳ ምስጋና በመስጠት በቅርብ በአካል ተገናኝተን እናወራለን የሚል ተስፋ ሰጥቶ ወደ ምላሹ ሄዷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ መቀሌ የመጣ ጊዜ ትዝ ይለኛል፤ ወደ 3ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ነው በአዳራሽ ንግግር ያደረገው፤ ንግግሩን መጨረስ እንኳን አልቻለም፤ በየዐርፍተ ነገሩ ይጨበጨብለት ነበር፤ በአገሪቷ ውስጥ ያሉት በሙሉ በየክልሉ ድጋፍ አድርገውለታል፤ ከዚህ በፊት በጠቀስኳው ምክንያቶች ግን ያንን ድጋፍ አጣ፤ አገሪቷን መቀመቅ ከተታት፣ ሕዝቡ ተከፋፈለ፣ ምክንያቱም በሚናገራቸው ቋንቋዎች በሙሉ የመከፋፈል ንግግር ነበር የሚደርገው፤ አሁን ዐቢይ የሚደርገውን እንዲያቆም እና ችግሮቹን መመልከት ወደመቻቻል እንዲሄድ ከዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ግፊትና ጫና ሊደረግበት ይገባል፤ ከኢሳያስ በስተቀር ዐቢይ የሚያዳምጠው ማንም ሰው በአቅራቢው የለም፤ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ቢያደርግ ሊሰማ ይችላል፤ ነገርግን በዚሁ እቀጥላለሁ ካለ መወገድ አለበት፤ አሁን ጉዳዩ ይወገድ ይሆን ሳይሆን ሲወገድ ምን እናደርጋለን የሚለው ነው … በእናንተና በሌሎች ወዳጆቻችን መረዳት መደገፍ አለብን፤ ስለዚህ ጦርነቱን ለማቆም በዐቢይም ሆነ በማንኛውም ይህንን ሃሳብ በሚቃወም ሁሉ ላይ ጫና ማድረግ አስፈላጊ ነው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ዘጠኙ ቡድኖች በጣም ለመተባበር ይፈልጋሉ
ክሪስቲ፤ በትግራይ መንግሥትና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል ባሁኑ ጊዜ ግንኙነት አለ
ብርሃነ፤ ኢሳያስና ዐቢይ ወደ ስምምት ሲመጡ የተነጋገሩት ነገር ሌላ ሰይሆን ትግራይንና ትህነግን እንዴት እንደሚያጠፉ ነበር፤ ከዚህ ሌላ ምንም የተነጋገሩት ነገር የለም፤ የመከላከያ ኃይላቸውን ያስተባበሩትም ትህነግንና ትግራይን እንዴት እንደሚያጠፉ ለመተግበር ነው፤ ከዚሁ ጋር ትህነግን አሸባሪ ድርጅት ብለው ስም ከሰጡት በኋላ ምንም ዓይነት ግንኙነት ለማድረግ አይቻልም፤ ትህነግንና የትግራይን ሕዝብ አሸባሪ ማለት የሚያስቅ ነገር ነው፤ ስህተቶች ቢኖሩትም ለፍትሕና ለነጻነት የቆመን ድርጅት አሻባሪ ማለታቸው የመነጋገሪያ መንገዱን እንዲዘጋ አድርገዋል፤ ስለዚህ ከዐቢይ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ማድረግ አይቻልም
በኤፍሬም ይስሐቅ ጎትጓችነት ዶናልድ ያማሞቶ የሚከተለውን ብሏል፤ ዐቢይ ከኢሳያስ ጋር ያለውን ግንኙነት ያቋርጣል ወይስ አያቋርጥም የሚለው ለመመለስ የሚያስቸግር ጥያቄ ነው፤ ያም ሆኖ ግን እናንተ ሌላ አማራጭ ወይም ሥልት ያሰባችሁበት አለ፤ እንዴት ነው ወደ ዐቢይ መድረስ የምትችሉት፤ ኦባሳንጆ እንደሚገባው ለየት ባለ መልኩ ዕርዳታ እያደረገ አይደለም፤
ብርሃነ፤ ዋናው ቁልፍ ያለው ከኢሳያስ ጋር ነው፤ ትንሹ ቁልፍ ያለው ደግሞ ከዐቢይ ጋር ነው፤ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ከመንገዱ ወጥቶ ከዐቢይ ጋር ለመነጋገር ብዙ ጥሯል፤ እርሱ ግን የመረጠው ከኢሳያስ ጋር መለጠፍ ነው፤ የማይነጣጠሉ ሆነዋል፤ ችግሩ ደግሞ በጋራ ሆነው የፈጸሙት ወንጀል ነው፤ እኔ ወዳጆቼን አጥቻለሁ፤ እስከ 25 ሰው ከቤተሰባቸው የሞተባቸው አሉ፤ ያሉት አማራጮች ሁለት ናቸው፤ በሰላማዊ መንገድ መወያየትና መደራደር ወይም ካልሆነ ራሳችንን እስከመጨረሻው መከላከል ነው
ቪኪ፤ የእናንተ ወታደራዊ ስትራቴጂ ምርጥ የሚባለው ነው፤ ወታደራዊ ኃይላችሁ ዐቢይንና ኢሳያስን ለማውረድ የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው፤ ሰብዓዊ ዕርዳታ መስመሩን ማግኘት ሌላ አማራጭ ሊሆን ይችላል፤ እኔ ዐቢይ መውረድ እንዳለበት አምናለሁ ግን ትግሬዎች ተመልሰው በአዲሱ መንግሥት ቦታ ይኖራቸዋል
ብርሃነ፤ የቅድሚያዎቹ ሁሉ ቅድሚያ መሆን ያለበት ለእኛ ትግሬዎችን ከዘር ማጥፋት መታደግ ነው፤ የምዕራብ መውጫ መንገዱ (የወልቃይትን ማለቱ ነው) እንዲከፈትልን በጣም ነው የምንፈልገው፤ ለምሳሌ ትላንት ወደ 100 የሚሆኑ ከምዕራብ ትግራይ ወደ ተከዜ ወንዝ ወስደዋቸዋል፤ የሚሆነው ገድለው ተከዜ ወንዝ ውስጥ ሊጥሏቸው ነው፤ እኛ አዲስ አበባን የመቆጣጠር ምንም ፍላጎት የለንም
ቪኪ፤ በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ በጣም ከባድ ነው፤ በቅርቡ የወታደራዊ ስኬት ትጎናጸፋላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ (እንደ ዲፕሎማት ወታደራዊ ድል ከእነርሱ የራቀ መሆኑን በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ እየተናገረች ነው፤ “ተስፋ አደርጋለሁ” የሚለው አባባል በራሱ ሽንፈት እንደገጠማቸው አመላካች ነው)
ስቴፋን፤ ዐቢይ ጦርነት ወይም ሞት ብሎ ቢያመርር አሁንም ያለው ሁኔታ ያንን ይመስላል፤ በዚሁ ከቀጠለ ግን ዐቢይን ከሥልጣን ሊወርደው የሚችል ወይም እንዲወርድ ሊያደርገው ማስገደድ የሚችል ወይም ያለው ጦርነት እንዲቆም ለማድረግ የሚችል ከመንግሥት የሲቪል አካል ወይም ከሚሊታሪው ይኖር ይሆን፤ እና ወደፊት ይቅርታ ይደረግላችኋል የሚል ማደፋፈሪያ በመስጠት የተወሰኑትን ውጊያ እንዲያቆሙ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ አለ
ብርሃነ፤ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በሁለኛው ዓለም ጦርነት የነበረው ዓይነት ነው፤ ተመሳሳይ ነው ነገሩ ሁሉ፤ (ልክ ያኔ አይሁዶች ተነጥለው ለፖለቲካ መጠቀሚያ እንደዋሉና እንደተጨፈጨፉ ሁሉ ትግሬዎችም እንዲሁ እየሆኑ ነው እያለ ነው ያለው) አሁንም ያለው የቃላት አጠቃቀምና ሁኔታ ፍጹም ተመሳሳይ ነው፤ አብዛኛው ሕዝብ የማገናዘብ ችሎታውን አጥቶዋል፤ ፍጹም መረን የለቀቁና ወገናዊ ሆነዋል፤ ጆኒያው ውስጥ ሆነው የወጡበትን ጆኒያ ማየት የማይችሉ ሆነዋል፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በኢሳያስ ሙሉ ለሙሉ ቁጥጥር ሥር ነው ያለችው፤ ደኅንነቱ፣ ኢሚግሬሽኑ፣ መከላከያው፣ የፋይናንስ ተቋ፣ በሙሉ በኢሳያስ ቁጥጥር ሥር ናቸው፤ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ዘርፏታል፤ ይህ ሰዎችን ምንም ምላሽ እንደዳይሰጡ አድርጓቸዋል፤ እነዚህ በኤርትራ ቁጥጥር ሥር ያሉ ተቋማት ምህረት ዐልባ ናቸው፤ጠቅላይ ሚኒስቱም ምህረት ዐልባ ሆኗል፤ ማንም የማይቆጣጠረው ሆኗል፤ ከሚሊታሪው የሚወጣ ኃይል እኔ አይታየኝም፤ ከጥቂቶቹ በስተቀር ጄኔራሎቹ ብቃት ዐልባ ናቸው፤ ወታደር የሚባል የለም፤ ጥቂት መሃይም ገበሬዎችና ገጀራ የሚይዙ ወጣቶች ናቸው ወታደር የሚባሉት፤ እኛ ፍትሕ መበየን አለበት ብለን እናምናለን፤ እውነት መውጣት አለበት እንላን፤ ምንም ዓይነት ብቀላ የለብንም፤ የትግራይ መከላከያ ኃይል ራሱን የሚጠብቅ ነው ሥርዓት ያለው ነው፤ በምንም ዓይነት ብቀላ ውስጥ የመግባት ፍላጎት የለውም፤ ይህንን ግፍ ማን እንደፈጸመ ያውቃሉ፤ ነገርግን በሌላ ማላከክ አይፈልጉም፤ ለዚህም ነው በአማራና በአፋር ክልል ከሕዝቡ ድጋፍ ያገኙት፤ ካሉት ሁኔታዎች አንጻር እኛ ነገሮችን ኃላፊነት በሚሰማን ሁኔታ ነው የምናከናውነው
እሌኒ፤ ከጦርነቱ በኋላ የታቀደ ማርሻል ፕላን (አውሮጳን ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ መልሶ ለማቋቋም በአሜሪካ የወጣ ዕቅድ ነው፤ ካሁኑ ለዚያ ሹመት ራሷን እያዘጋጀች ይመስላል) አለ፤ ምክንያቱም ቅድም ስትናገር ጦርነቱ ኢትዮጵያን ወደ ድንጋይ ዘመን ወስዷታል ብለህ ነበር፤ ከዚያ የማውጣት ዕቅድ አለ፤ ምን ያህል ነው የሚያስፈልገው፤ ዕቅድና ግምት አለ፤ ከዚህ ሌላ ማኅበራዊ ግንኙነታችን ችግር ላይ ስለወደቀ ወደፊት እንዴት እንደምንኖር የሽግግር መንግሥቱ ምን ያቀደው ነገር አለ፤
ብርሃነ፤ ትግራይ ወደ ድንጋይ ዘመን ተለውጣለች፤ የኩላሊት ዕጥበት ለማድረግ አንዲት ከረጢት እንኳ በትግራይ የለም፤ ምንም ዓይነት መድሃኒት የለም፤ መሰረተ ልማቶች መጀመሪያ ተዘረፉ ከዚያ እንዲወድሙ ተደረጉ፤ እና አሁን ውድመቱን በተመለከተ ስሌቱን እየሠራን ነው፤ ገና ጉዳቱን እየመረመርን ነው፤ መግባት የማይቻልባቸው ቦታዎች አሁንም አሉ፤ እና በቅድሚያ በትግራይ ላይ እየተሠራ ነው፤ ከዚያም በአገሪቱ ይሠራል፤ ጥሩ የሚባለውን ያህል ሠርተዋል፤ ጥሩ ሄደዋል፤ ማርሻል ዕቅድን በተመለከተ ሁላችሁም እዚህ ያላችሁ የምታበረክቱት አስተዋጽዖ አላችሁ፤ ነገርግን አሁን በኢትዮጵያ ያለው መከፋፈል መታመን የማይችል ደረጃ ደርሷል፤ አንድ ሃገር ነበርን ወይ ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርግ ነው፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት የመገንጠልና ነጻ የመሆን ሃሳብ በብዙዎች ዘንድ እየተመላለሰ ነው፤ እኛ ይህ አገር አንድ ሆኖ እንዲቀጥል ባለፉት በርካታ ዓመታት ስንለፋ ስለነበር ብዙዎች የመገንጠልን ሃሳብ ትተውት ነበር፤ አሁን ግን አብሮ መቆየትን በተመለከተ ያላቸው ጥርጣሬ ማመን የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፤ አንቺንና ሌሎቻችሁን የሚጨምር ተሳትፎ አስፈላጊ ነው
ኤፍሬም፤ በኢትዮጵያ ያለው ችግር የሕዝብ ችግር ሳይሆን አንድ በመቶ እንኳን የማይሞሉ ኤሊቶች (ልሒቃን) ችግር ነው፤ እነርሱ ሊነጋገሩ ይገባቸዋል፤ እኔ በበኩሌ ከዚህ ገለጻ በጣም ብዙ የማላውቀውን ነገር ሁሉ ነው የተማርኩት፤ ብርሃነ ድንቅ የሆነ መግለጫ ነው የሰጠኸን፤ ይህንን ደግመን እናደርገዋለን ብዬ አስባለሁ፤ ደግመን እንገናኛለን።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply