ብ/ጀኔራል አሳምነው ጽጌ እና ሜ/ጀኔራል አለምሸት ደግፌ ከመከላከያ ሰራዊቱ በተለያየ ጊዜ “የመከላከያ ሪፎርም አደናቃፊ” በሚል ማዕረጋቸው ተገፍፎ የተሰናበቱ ወታደራዊ መኮንኖች ናቸው። ብ/ጀኔራል አሳምነው ጽጌ የቀድሞ የጦር ሠራዊት አባል የነበረና በ1978 ዓ.ም ኢህዴንን የተቀላቀለ ጀግና አዋጊ እንደሆነ የኢህዴን ጓዶቹ ሳይቀር ይመሰክሩለታል። ድህረ-ደርግ በሲቪል አስተዳዳሪነት የላስታ ወረዳ አስተዳደር ቀጥሎም የሰሜን ወሎ ዞን አመራር ሆኖ ሰርቷል።
የባድመ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ ወደ ወታደራዊ አመራርነት የተመለሰው አሳምነው ጽጌ፣ የቀደመ የትግል ልምዱን መነሻ በማድረግ ያለአንዳች ማዕረግ በጦርነቱ ውስጥ በባድመ የጦር ግንባር 22ኛ ክፍለ ጦርን እየመራ ተዋግቷል። ባድመ ላይ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ ከነበሩት ጥቂት አመራሮች አንዱ አሳምነው ጽጌ ይገኝበት ነበር።በጦርነቱ ጊዜ በህወሓት የጦር መኮንኖች ብስለት አልባ የጦር ስትራቴጅና በጦር ግንባሩ ላይ ያደረሱት የጦርነት ኪሳራዎች የከነከነው አሳምነው ጽጌ የህወሃት የበላይነት በሰራዊቱ ውስጥ መኖሩን በመረጃ በመሞገት 1993ዓ.ም ሀረር ሁርሶ ላይ በተካሄደ መድረክ ላይ በመድረኩ ተሳታፊዎች ስምምነት እንዲደረስበት አድርጓል።
ከባድመ ጦርነት በኋላ ወደ ሲቪል አመራርነት በመመለስ መከላከያ ውስጥ ያለውን የህወሓት የበላይነት በአመለካከት ደረጃ እየተዋጋሁ መከላከያ ውስጥ ልቆይ በሚል ሊቆይ እንደቻለ የሚገልጹት የጎልጉል የመረጃ ምንጮች፤ አሳምነው አሜሪካ ሀገር ለአንድ አመት ወታደራዊ ትምህርት ተምሮ መምጣቱን ይገልጻሉ። ከአሜሪካ ወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት መልስ የብርጋዴል ጀኔራልነት ማዕረግ የተሰጠው አሳምነው ጽጌ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲን እንዲያቋቁም የጠሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እንደተወጣ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ነባር መምህራን ይመሰክሩለታል።
የጎልጉል የመረጃ ምንጮች እንደሚሉት “አሳምነው መከላከያ ዩኒቨርሲቲን በብቃት መርቷል። ሆኖም ተቋሙን በሚመራበት ወቅት የህወሓት ሰዎች ‹አሳምነው አሜሪካ ሄዶ ያመጣው ነገር አለ› በሚል ያዋክቡት ነበር” ይላሉ። “አሳምነው ወደ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች (ወታደሮች) በፈተና እንዲገቡ በማድረጉ ጥርስ ውስጥ ገብቷል” የሚሉት ምንጮቻችን በፈተናውም ብዙ የአማራ ልጆች በማለፋቸው የበለጠ አሳምነው ከህወሓት ሰዎች ጋር መቃቃሩን ያስታውሳሉ።
“እንዴት ብዙ አማራዎች ፈተናውን ሊያልፉ ቻሉ” በሚል ሲጠየቅ አሳምነው ለነሳሞራ “ውጤቱን ካላመናችሁ ፈተናውን ራሳችሁ አውጥታችሁ ፈትኗቸው” እንዳላቸው እና ሳሞራ የኑስ በበኩሉ “ይህማ አይሆንም፣ ትምህርት ቤቱ ይፈርሳል እንጂ ይሄን ያህል ቁጥር አማራ አይማርበትም” እስከማለት ደርሶ እንደነበር የወቅቱን ሁኔታ ያስታውሳሉ። ጉዳዩ እስከ መለስ ዜናዊ ደርሶ በመጨረሻ በወታደራዊ ትምህርት ቤቱ የተነሳው መካረር አድጎ ጀኔራል አሳምነው እንዲታገድ መደረጉና ከዚህም አልፎ በሳሞራ የኑስ ነገር ማወሳሰብ የተነሳ “የመከላከያ ሪፎርም አደናቃፊ” በሚል በ1998ዓ.ም ማዕረጉ ተገፍፎ ከሠራዊት አባልነቱ መሰናበቱ የሚታወስ ነው።
ጀኔራሉ በሚያዚያ 2001ዓ.ም “መፈንቅለ መንግስት ሙከራ” ላይ ተሳትፈሃል በሚል ክስ ተመስርቶበት እድሜ ልክ ተፈርዶበት በቅርቡ ከ9 አመታት እስር በኋላ ተፈቷል። ብ/ጀኔራል አሳምነው ጽጌ በሰራዊቱ ውስጥ በቆየባቸው ዓመታት ከሳሞራ የኑስ ጋር ስምምነት እንዳልነበራቸው የሚገልጹት የመረጃ ምንጮቻችን፤ ሳሞራ የኑስ ከኤታማዦር ሹምነቱ በተነሳበት ሰዓት ቤተመንግሥት በክብር እንግድነት ተገኝቶ ወታደራዊ ማዕረጉ በክብር መመለሱና ጡረታ እንዲወጣ መደረጉ ሳሞራን በእጅጉ ያስከፋው ድርጊት መሆኑን የመረጃ ምንጮቻቸን ዘገባ ይጠቁማል።
ዝዋይ አስርቤት ሆኖ ሞቱን ሲጠብቅ የነበረው የኢህዴኑ ታጋይ ብ/ጀኔራል አሳምነው ጽጌ በህዝባዊ ኃይል ጫና ከእስር ተፈትቶ ወታደራዊ ማዕረጉ በጠላቱ ፊት እንዲመለስለት የተደረገበት አጋጣሚ ለብአዴን ሰዎች የሰርግና ምላሽ ያህል ሲያስፈነድቃቸው የህወሓት ሰዎችን ደግሞ ጸጉር እንዳስነጫቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው።
በተመሳሳይ መልኩ የኦህዴድ ሰዎችን ያስፈነጨ ድርጊትም ታይቷል። የኦህዴዱ ሜ/ጄኔራል አለምሸት ደግፌ የኢህዴን መስራቹን ሜ/ጀኔራል ኃይሌ ጥላሁንን ተክቶ የአየር ኃይል አዛዥ እንደነበር ይታወሳል። የቀድሞው ጦር ሠራዊት አባል የነበረውና ሩሲያ ድረስ ተልኮ ከፍተኛ የወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት እንደተማረ የሚነገርለት ይሄው ጀኔራል ብዙም ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ “የመከላከያ ሪፎርም አደናቃፊ” በሚል ማዕረጉን ተገፎ ከሠራዊቱ እንደተሰናበተ ይታወቃል።
ጄኔራሉ የአየር ኃይል አዛዥ በነበረበት ወቅት ከጦር አውሮፕላኖች እና የመለዋወጫ ግዥዎች ጋር ተያይዞ በሙስና ንክኪ እንዳለበት እና “የድርሻህን ይዘህ ጥፋ” የተባለው ጄኔራል፤ ሲ.ኤም.ሲ ላይ “አይማ ኢንተርናሽናል” የተባለ ታዋቂ ሆቴል በስሙ ከፍቶ ንግዱን በማጧጧፍ ላይ ይገኛል። “ኢህዴን/ብአዴን ብቻውን ከሚደሰት አጫፋሪ ያግኝ” በሚል የሜ/ጀኔራል አለምሸት ደግፌ ማዕረግ ሊመለስለት እንደቻለ የመረጃ ምንጮቻችን ይገልጻሉ። ጀኔራሉም “የኦሮሞ ዘመን አሁን ነው” በሚል መኩራራት በቤተመንግሥቱ ውስጥ ሲናገር እንዳመሸ የሚገልጹት የመረጃ ምንጮቻችን ጄኔራሉ የሆቴል ንግዱ የተስማማው በመሆኑ ወታደራዊ ማዕረጉ መመለሱ ለህይወት ታሪኩ ማሟያ እንጂ ለኑሮ መደገፊያ እንደማይጠቀምበት ለህወሓትም ሆነ ለኦህዴድ አመራሮች ግልጽ መሆኑን ያስረዳሉ ነው።
ከአራተኛ ክፍል ዕውቀት ያላለፈ የትምህርት ደረጃ ላይ ከሚገኙት የህወሓት ጄኔራሎች አንጻር በተለይ (ሜ/ጄ አለምሸት ወደ ንግዱ በመመለሱ ካልፈለገው) የብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ወደ ሠራዊቱ በከፍተኛ አማካሪነት ወይም በሌላ ጠቃሚ መስክ መመለስ ለአገርም ለሠራዊቱም ጠቃሚ እንደሆነ በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየት የሚሰጡ ይናገራሉ።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Leave a Reply