
የገፊና ጎታች ሴራ፣ የአማራ ሕዝብ መከራ
ክልሉ የፖለቲካ ቧልት እየበላው ነው
የአማራ ክልል የራሱን መሪዎች በመብላት ሤራ ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በተለየ መታወቂያው ነው። የአማራ ክልል አሁን ላይ በፖለቲካ አመለካከት ሳቢያ ሰዎች የሚገደሉበት ክልል ሆኗል። አማራ ክልል ላይ በተደጋጋሚ የሚስተዋለው መጠፋፋትና ይህንኑ በማወደስ የሚያራግቡት ክልሉን “ለፖለቲካ ቧልት” ዳርገውታል እየተባለ ነው።
“የገፊና ጎታች ፖለቲካ መሃል ሜዳ” የሚባለው የአማራ ክልል መሪዎቹ እንዲገደሉ የሚያቅዱ፣ ግድያውን የሚያቀነባብሩ፣ ግድያውን የሚፈጽሙ፣ ግድያው ሲፈጸም ወደ ሌላ በመጠቆም ሕዝብ እንዲቆጣ የሚያደርጉ ተዋንያኖች የሚተራመሱበት እንደሆነ በርካታ መረጃ በማንሳት የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። ከሁሉም በላይ በፍረጃና ማጠልሸት ላይ አተኩረው የሚሠሩት ሚዲያዎች “የገፊና ጎታች” ፖለቲካው ፊት አውራሪዎች መሆናቸው ቀና ልቡና ባላቸው ዘንድ ፍርሃቻን ፈጥሯል።
ክልሉ እንደ ሌሎች ክልሎች ከለውጡ በኋላ ራሱን ማጽዳት ያልቻለ፣ በትህነግ ብብት ውስጥ የተወሸቁ የሤራ ቋቶችን ያላራገፈ፣ ግብስብሱን ይዞ ለመጓዝ የመረጠ መሆኑ ለበርካታ አሁናዊ ችግሮች ዳርገውታል። በዚህ አሳብ ዙሪያ “አሁን ድረስ ትህነግ ያሰፋለትን ባንዲራ ተብዬ ጥብቆ እንኳን መቀየር ያልቻለ” ሲሉ ክልሉን የሚመራውን ፓርቲ ይወቅሱታል። ይህ ያለመጥራቱ ማሳያ አንዱ በሽታ እንደሆነም ያሳያሉ።
የዶ/ር አምባቸው መኮነን፣ አቶ ምግባሩ ከበደ እና አቶ እዘዝ ዋሴና የአቶ ተስፋዬ ጌታቸው ግድያ እንዴት እንደተቀነባበረ፣ ማን እንዳቀነባበረው፣ ግድያው ለምን እንደተፈለገ፣ ወዘተ ገና ከጅምሩ ጀምሮ በገፊና ጎታች ፖለቲካ እንዴት ይነዳ እንደነበር የሚገልጹ “አማራ ክልል በሤራ መሪዎቹን እየበላ እዚህ ደረሰ” ሲሉ ክልሉ እንዴት ከድጡ ወደ ማጡ እንደተሽቀነጠረ ይገልጻሉ። መሪዎቹ እንዲበሉ የሚያደርጉትም ባንዳዎችና እንደሆኑ ይገልጻሉ።
መሪዎቹን የበላቸውን ወገን በማጀገን የሚዘመርበት የአማራ ክልል፣ ይህ ባንዳዎችን የማጀገን ስካሩ አልበርድ ብሎ ዛሬ ላይ አማራ ማንም የሚነዳው፣ ማንም የሚያንቦጫርቀው ፖለቲካ ሰላባ ለመሆን በቅቷል። እንደ ሕዝብ ተፈርጆ የሚደርስበት መከራና ሞት ሳያንሰው በሰላም በሚኖርበት ቀበሌው ማረስ እንዳይችል ሆኖ ሽፍታ ቀላቢ ሆኗል።
አማራ የሚመራው ብቁ ሰው ያጣ ይመስል የግድያው ተሳታፊና አራጋቢ በነበሩት የመሸታ ቤት ፖለቲከኞች እንዲመራ እየታዘዘ ነው። ይህን ግምገማ የሚሰጡ ወገኖች እንደሚሉት አማራ በየመድረኩ በሚያንዛርጡ ጨዋ መሳዮች፣ ራሳቸውን የአማራ መሪና ተቆርቋሪ ባደረጉ ባንዳዎች፣ የቀድሞ የትህነግ ተላላኪዎችና፣ ወልቃይትንና ጠገዴን ጨምሮ ፈርመው ለትህነግ እየገለፈጡ ባስረከቡ ከርሳሞች ያለ አንዳች ኃፍረት እንዲመራ የነዚሁ ወገኖች ተከፋይ በሆኑ ሚዲያዎች በሰበር ዜና እየደነቆረ ነው።
በተለይም በአሜሪካን ሜሪላንድ በሚኖሩ ባለቤትነት እንደተቋቋመ የሚነገርለትና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሻዕቢያ በጀት በሚደገፈው የመረጃ ቲቪ ተሳታፊ በሆኑ ዩቱበኞች የሚረጨው የከፋ ሤራ ክልሉን መንጋ እየተነሳ እንዲያወድመው ምክንያት እንደሆነ በስፋት መረጃዎች እየወጡ ነው።
“ያሳፍራል” ሲሉ የሚናገሩ “አማራን ክልል እንደ ዘመድኩን በቀለ ዓይነት አእምሮው ትክክል እንዳልሆነ የመሰከረ ቃልቻ በዚህ መልኩ አዛዥና ናዛዥ ሆኖ ሲመራና የትግል አቅጣጫ ሲያዘጋጅለት ማየት የቁም ሞት ነው” ይላሉ። “ሻለቃ ዳዊትን ያክል በደም የተጨማለቀ ከሃጂ ባንዳ፣ እንደ ገዱ ዓይነት የአማራን ክልል ለትህነግ እየገለፈጠ ያስረከበ አለቅላቂ እና ሌሎችም አማራን ሊመሩ ሲደለቅላቸው መስማት ከቁም ሞትም በላይ ነው” ሲሉ ሃዘናቸውን ይገልጻሉ።
ሲቀጥሉም “እስክስታ ወራጁና ተወዛዋዡ የፖለቲካ ተንታኝና መሪ ሆኖ የተዋጊው ቡድን ቀለብ አልሰፍርም፣ ጥይት አልገዛም፣ ዘርፈህ ብላ” በሚል በገሃድ መዘባበቻ ያደረጉ ባዶዎች ሕዝቡን እንዴት ባለ ሞራል ሊመሩት እንዳሰቡ መገመት በራሱ ሕመም እንደሆነ ያስታውቃሉ።
እነዚህ ወገኖች በዚህ አያበቁም፣ ሻዕቢያ የሚሰፍርላቸው ጋጋኖዎች በየወሩ እየተገላበጡ በሚረጩት የቀጣሪዎቻቸው ሤራ የአማራ ሕዝብ ችግሩን፣ በደሉን፣ የደረሰበትን ግፍ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ሆኖ በአንድ ላይ እንዳይጋፈጥ ጠንቅ ሆነውበታል። ልክ ትህነግ የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች ወገኖቹ ለይቶ ብቻቸውን እንዳስቀራቸው አማራም ልዩ ፍላጎት ያለው ሕዝብ አድርገው እየሳሉት ነው። በዚህም በመላው ኢትዮጵያ በሰላም የሚኖሩትን የአማራ ተወላጆች ሥጋት ላይ እየጣሉ ነው።
የአማራን ለም መሬቶችና ርስት ተማምለው ያስረከቡ ባንዳዎች፣ ሕዝብን አስተባብረው ባንዶቹ የሰጡትን ርስት ያስመለሱትን ለመንቀፍ ሞራል የሌላቸው ከላይ በተዘረዘሩት ሚዲያዎች እየተሞካሹ ነው። እስኪ ዶ/ር ይልቃልን ወይም አቶ አገኘሁን ለመውቀስ አቶ ገዱ ምን ዓይነት የሞራል መሠረት አላቸው?” እርግጥ አሁን ባለው የክልሉ አመራር ውስጥ የገፊና ጎታች ሤራ አራማጆች ቢኖሩም በግርድፉ የቀደመው ብአዴን አብዛኛው አመራሮች ፍትህ ቢኖር ለፍርድ የሚቀርቡ በሆኑ ነበር።
ሁሉም ሆኖ አሁን ላይ አማራ ክልል በማጅራት መቺ፣ ባንዳና የመሸታ ቤት አለቅላቂዎች እንዲመራ የሚደረገው ትርምስ አካሄዱ ለገባቸው ሥጋት ሆኗል። የተለየ አሳብ ያላቸውን፣ በሰከነ ፖለቲካ ክልሉን ለማራመድ የሚፈለጉ፣ ችግርን ሳያሰፉ አማራ እንደ ሕዝብ ከደረሰበት ጉዳት አገግሞ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር መብቱና ጥቅሙ ተጠብቆለት እንዲኖር የሚመኙ አዳዲስም ሆኑ ነባር ቀና አሳቢዎችን የሚያሸማቀቀው፣ በግድያ ስንጠርዥ ውስጥ የሚያስከትተው የአማራ ፖለቲካ መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል በርካቶችን አስጭንቋል።
“አስወግደው” የሚል መመሪያ የሚያስተላልፉ ሚዲያዎች ጥቆማ እየሰጡ ባለበት ባልተለመደ ሁኔታ ከአማራና ኦሮሞ መወለድ ወይም መቀላቀል “ሃፍ ካስት ነው” በሚያሰኝበት ሁኔታ፣ ይህም የሚያስገድል መሆኑ፣ የባለሃብቶች ስም እየጠተራ ሳይቀር በቀድሞ የኢህአዴግ አዲስ አበባ ወጣቶች ሊግ መሪ ሃብታሙ አያሌውና የስኳር አክሲዮን ተዋናይ ምናላቸው ስማቸው አማካይነት ማስፈራሪያ በሚቀርብበት በዚህ ወቅት አማራን ማን ይምራ? ቁልፍ ጥያቄ ነው።
ምስክሮች እንደሚሉት ዶ/ር ይልቃል “በቃኝ” ካሉ ቆይቷል። ከእርሳቸው ቀደም ሲል አቶ አገኝሁ ክልሉን ለመምራት የተስማሙት በአጭር ጊዜ ውል ነበር። አሁን ላይ በርካታ ብቃት ያላቸው ጥያቄው ቀርቦላቸው አልፈለጉም። በሌሎች ክልሎች የሚፈለገውና እርስ በርስ የሚያቧጭቀው የክልል መስተዳድር መሪነት ቦታ በአማራ ክልል ግን ፈላጊ የለውም። በሌሎች ክልሎች እኔ ልምራ ባዩ ለቁጥር በሚያታክትበትና ሥልጣን ላይ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሮች ስዩመ እግዚአብሔር የሆኑ ይመስል ማንም እንዳይነቀንቃቸውና ቦታቸው እንዳይነጠቅ አጥብቀው ሲከላከሉ የአማራ መስተዳድር ግን የተሾመው “መቼ በተገላገልሁ” የሚልበትና “ተሹመሃል” ተብሎ የሚነገረውም “አልፈልግም” የሚልበት ወቅት ላይ ነው ያለው። በመሆኑም አሁን ላይ ክልሉን ዳግም ለማደራጀት እየተሠራ ባለው ሥራ ፈላጊ ያጣው የአመራር ቦታ ጉዳይ ፈታኝ እንደሆነ ይነገራል።
ተሹዋሚዎችን የሚያሳቅቀውና ብሎም የሚገድለው፤ በሌላ ጽንፍ ደግሞ “የአማራ ክልል መሪ እንዳይወጣበት ተደርጓል” እያለ በተመሳሳይ የሚደሰኩረው በአማራ ክልል የተጎነጎነው የገፊና ጎታ ሤራ የክልሉን መሪዎች እየበላ ክልሉን መሪ ዓልባ እያደረገ ያለው አካሄድ ካልቆመ የአማራ ክልል የከሸፈ ክልል (failed regional administration) እንደሚሆን ብዙ አመላካቾች አሉ።
በትግራይ ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በተለይ ወጣት ያስጨፈጨፉት በምዕራቡ ዓለም ለጉብኝት ሲመጡ አዳራሽ ተለቅቆላቸው፣ ፈንዲሻ ፈንድቶላቸው፣ ቄጤማ ተጎዝጉዞላቸው፣ በእልልታ አቀባበል ሲደረግላቸው የአማራ ክልል አመራሮች በተገኘው ሚዲያ ሁሉ ያለማቋረጥ ይሸማቀቃሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ እንደ ሚዳቋ በጥይት ይታደናሉ። ይህንን መረን የለቀቀ ፖለቲካ የሚመራው ኃይል በተመሳሳይ መልኩ በየሚዲያው እየወጣ “ክልሉ ሆን ተብሎ መሪ ዓልባ እንዲሆን ተደረገ” እያለ የአፍዝ አደንግዝ ድቤውን ይመታል። ድንቁርና በረከት የሆነላቸውም ይህንን እየሰሙ እንደ ገደል ማሚቶ “ሼርና ላይክ” እያደረጉ ያስተጋቡታል።
ነገ አርብ በሚደረገው ስብሰባ አዳዲስ አመራር እንደሚመረጡ እየተነገረ ይገኛል። ገና ማን ምን ቦታ እንደተመረጠ ይፋ ሳይሆን የስም ማጠልሸቱና ማሸማቀቁ ተግባር ተጠናክሯል። ገና ወንበሩ ላይ ሳይቀመጡ “አስወግዷቸው” ባዩም ቁጥሩ ቀላል አይደለም። ይህ በስካር ላይ የሚገኘውና በገፊና ጎታች ሤራ የተተበተውና የማንም አልፎ ሂያጅ የአረቄ ማኅበርተኛ መደዴ እመራዋለሁ የሚለው የአማራ ክልል ፖለቲካ በዚሁ ከቀጠለ የክልሉን ነዋሪ እጅግ ከፍተኛ የኅልውና አደጋ ውስጥ ይጥለዋል። በተለይ በእርሻ ወቅት ሆን ተብሎ የሚደረገው የክፋት ሤራ መቋጫ ካልተደረገለት የክልሉን ነዋሪ ቅስም በሚሰብር ሁኔታ የሌሎች ክልሎች ተመጽዋች እና ወደ ሌሎች ክልሎች ተሳዳጅ እንደሚያደርገው ለመገመት የፖለቲካ ልሒቅ መሆን አይጠይቅም። ይህም “የአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላታችን ነው” ብሎ የተነሳውን አማራን በጠላትነት የመፈረጅና ቀጣይ ሕይወቱ የመሸማቀቅና የውርደት እንዲሆን ታስቦ የተዋቀረው የትህነግ የፖለቲካ ርዕዮት ፍጻሜ የሚያገኝበት ይሆናል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
የሃበሻ የፓለቲካ ጋጋታ እንደ ቀጥር ጥላ ነው። ትንሽ ቆይቶ የማይታይ። ከዘመን ዘመን የማይሻለው የሃበሻ ፓለቲካ ትሻልን ትቶ ክፉን የሚላበስ በህዝብ ስም የሚነግድ የዘር፤ የቋንቋና የክልል ሰካራሞች የተሰለፉበት ነው። ዛሬ ዓለም እየጠበበች ሰው በተገኘው ስፍራ ተሽጉጦ ኑሮውን በሚመራበት ዘመን የእኛ ፓለቲከኞች ሰው እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ፤ ከላይ በዚህ ጽሁፍ እንደተመላከተው አማራ ራሱን እየበላ ለአማራ ቆሜአለሁ የሚሉ የሃሳብ ጉንድሾች የሚርመሰመሱበት የሃበሻ ምድር ግፍ ሰማይ ደርሶ ፈራጅ ጠፍቶ ወደ ምድር ተመልሶ ሰውን አሳብዶት እናያለን።
ሲጀመር ሰውን በመግደል ሃገርን ማጽናት አይቻልም። የገዳይ ገዳይ ሁልጊዜም ይኖራልና ከሽክርክሪቱ ለመውጣት ይህም ያን ያም ይህን እየገደለ ዝም ብሎ ዝንተ ዓለም በጨለማ መኖር ነው። የአለማችን የአሁን ችግር እውነተኛ ወሬ ማግኘት ነው። ይህም ያም ያቺም የፈጠራና ቅይጥ ወሬ እያናፈሱ ሽርፍራፊ ሳንቲም የሚለቀምበት በመሆኑ እውነቱን እንዳለ ለህዝብ ጀሮ ማድረስ የማይታሰብ ነው። በዚህም የተነሳ በዓለም የተበተኑት ሃበሾች (ሁሉም አይደሉም) በቋንቋ ሰክረው፤ በክልላቸው ኮርተው ሃገርን ረስተው ሰው መሆናቸው ቀርቶ በሩቅ ሆነው እሳት እያቀበሉ እያጫረሱን ይገኛሉ። እውነት አፍጣ ፊቱ ላይ ቆማ እያለ ተጨቁኛለሁ፤ ተርቤአለሁ፤ ታስሬአለሁ፤ ተገርፌአለሁ፤ ተገድያለሁ አሁን ደግሞ ወረፋው የእኔ ነው ፍርድ ለመስጠት በበማለት እልፎችን አሁንም የሚያሰቃዪ የዘር የፓለቲካ ድውያኖች በሚተራመሱበት ምድር እውነትን ለማየትም ሆነ ሚዛናዊ ፍርድ ለማግኘት ጭራሽ አይቻልም።
ሰው ግን ደንዝዟል። አማራ በለው ሌላ ድኑዛዜው በዝቶ ሞት በሩን አንኳኩቶ አንድ ወይም ይበልጡን ቤተሰቡን ከወሰደ በህዋላ ነው የሚነቃው። የሌላው ሞት ሞት አይመስለውም። ማን ሞተ፤ ማን ታሰረ፤ የማን ዘር ነው፤ ማን ተፈናቀለ በማለት መርጦ በሚለቀስበት ምድር ላይ ምንም ቢሆን ምንም ፍትህ አይኖርም። የአማራ መሪዎችን በመግደልና በማስገደል አንድም በጎ ነገር ለአማራ ህዝብ አያስገኝም። መግደል መሸነፍ ነው ያለን መሪ ዛሬ ራሱ ገዳይ ነው። ድሮም ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም ያሉን ምን ያህል ሰቆቃ በህዝባችን ላይ እንደፈጸሙ ታሪክ ይነግረናል። ፋኖ የብልጽግና ባለስልጣኖች ናቸው እያለ በዚህም በዚያም የሚገድላቸው ሁሉ ደማቸውን በከንቱ ነው የሚያፈሰው። የእነርሱ ሞት ምንም ነገር አይለውጥም። በተለያዪ የሃገሪቱ ክፍል ያለ ልክ ጠበንጃ ያነገቱ ሁሉ መራወጣቸው የምድሪቱን ህግ አልባነት ያሳያል እንጂ አንድም አይነት የነጻነት ትግል ብሎ ነገር የለም። ግብርና ውሎ የሚመለስ ገበሬን አንበርክኮ አይደለ ወያኔ የረሸነው? እንሳሳት ሳይቀሩ አይደል የገደለው? ዛሬ ላይ ለትግራይ ህዝብ በዚያ ሁሉ እልቂት ያተረፈው ረሃብና የእልፍ የትግራይ ልጆችን ሞት ብቻ ነው። በአማራ ያለውም ግርግር ትርፉ መተላለቅ ብቻ ነው! የሚያሳዝነው የወያኔ መሪዎች ከቀን ወደ ቀን እየወፈሩ ሰው በትግራይ ሞተ ሲባል መስማት መፈጠርን ያስጠላል። በአማራ ህዝብ ላይ በፋኖም ሆነ በፌዴራል መንግስቱ የሚወርደው እሳት የአማራን ህዝብ ወደ ድህነትና መከራ የሚያወርድ እንጂ ሰላምና ብልጽግናን አያመጣም። መነጋገር መመካከር አስፈላጊ ነው። ሁሌ አካኪ ዘራፍ ማለቱ ኋላ ቀርነት እንጂ የጀግንነት ምልክት አይደለም። የፌዴራል መንግስቱ ሁሉን በጉልበት የሚለው አካሄድ ገልቱነቱን ያሳያል። በስመ አማራ እያፈሱ እስር ቤት መክተቱና ማፈናቀሉ መቆም አለበት። ሰውን እንዲጨክን፤ መሳሪያ ይዞ እንዲታገል የሚያደርገው ግፍና መከራ ማባሪያ ሳይኖረው ሲቀር ነው። መንግስት የሚወቀስበት እልፍ ነገር አለ፤ ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ ነን የሚሉ ከፍርስራሽና ከመከፋፈል የተረፉትም ራሳቸውን መፈተሽ አለባቸው።
በማጠቃለያው ፓለቲካ ውሸትን የተቃመሰ ሁሌም ለራሱ ሲቆርስ የማያሳንስ፤ በአለም የፓለቲካ አሰላለፍና ንፋስ የሚነዳ ለመሆኑ ዛሬን ከታሪክ ጋር አገናዝቦ መረዳት ይረዳል። ያኔ በዳርፉር የሰላም አስከባሪ ከነበሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች መካከል በብልጽግናና በወያኔ ፍልሚያ የተነሣ ወደ ሃገራችን አንመለስም በማለት መሬት ላይ ወድቀው በመንከባለል የቀሩት የሰራዊቱ አባላት ዛሬ የት ናቸው? ሱዳን እንዲህ ስትፈራርስ ወድ 30 ሺህ የትግራይ ተወላጅ ግማሹ በማይካድራ ግፍ ሰርቶ ሱዳን የተሻገረው ዛሬ በሱዳን ያለውን መከራ ያኔ ማየት ይችሉ ነበር? አሁን ሲኦል ውስጥ ወርደን ቢሆን ኢትዮጵያን እናፈርሳለን ያለው ጌታቸው ረዳ የወያኔ ቁንጮ ይሆናል ብሎ ያሰበ ነበር? የሃበሻው ፓለቲካ የተሳከረ ነው የምለው ለዚህ ነው። የአማራ የመጀመሪያ ጠላቱ አማራው ራሱ ነው። የራሱን ልጆች እየበላና እያስበላ ለአማራ ህዝብ ሰላምንና ብልጽግናን የሚያመጣ አንድም የፓለቲካ ሃይል አይኖርም። ማንም ይሁን ምንም ይመከር/ትመከር እንጂ መግደል የውሻ ፓለቲካ መለያ ነው። ይቁም እላለሁ። ታጥቆ የመጣው ጋር ተፋለሙ፤ ግን በመንግስት መ/ቤት በስልጣን ላይ ናቸው በማለት መገደሉ ግን ከአውራ ጣት አመልካች እጣት ይበልጣል እንደማለት ነው። አይመችም። በቃኝ!