
አርሶ አደር ፈንታዬ አበረ ተወልደው ያደጉት በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ ቀበሌ 32 ነው። እንደአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ሁሉ እሳቸውም በደግነታቸው፣ በታታሪነታቸውና በጀግንነታቸው ይታወቃሉ። በግብርና ሥራም ቢሆን የተዋጣላቸው አርሶ አደር ናቸው። በእንግድነት ለመጣባቸውም አልጋቸውን ይለቃሉ፣ የሚበላ የሚጠጣ ቤት ያፈራውን ሁሉ ያቀርባሉ።
ዛሬ ግን ወደ አርሶ አደሩ ቀዬ ብቅ ያለው ተናፋቂ እንግዳ አይደለም፣ ወይም አረምን በማረም አርሶ አደሩን ለመርዳት የመጣ አይደለም፣ ቀማኛ፣ ወራሪ፣ አሸባሪ እና ዘራፊ ቡድን እንጂ። አርሶ አደሩ ለዚህ ወራሪ እንደ እንግዳ ተቀባይነታቸው አላስተናገዱትም ከልጃቸው ጋር በመሆን የጀግንነት ክንዳቸውን አቀመሱት እንጅ። እሳቸውም ሆነ ልጃቸው የመተኮስ ልምዱ ቢኖራቸውም የጦር መሳሪያ ግን የላቸውም። የነበራቸው ጀግንነትና ልበ ሙሉነት ነበር። ከልጃቸው ጌጡ ፈንታዬ ጋር በመሆን ጠላት ወደ እነሱ ሲመጣ ተመለከቱ።
እንደለመደው ጠላት ሊዘርፍና ሊያጠፋቸው መሆኑን ቀድመው የተረዱት ጀግናው አባት፣ ልጃቸው በያዘው ዱላ የጠላትን አንገት እንዲመታው በአይናቸው ጥቅሻ ትዕዛዝ ይሰጡታል። ወጣት ጌጡ “የአባቴን የዓይን ጥቅሻ ትዕዛዝ ተቀብዬ በያዝኩት ዱላ ብርቱ ክንዴን የጠላት ጭንቅላት ላይ አሳረፍኩበት” ብሏል። አንገቱ ላይ የተመታው ጠላትም የወረደበትን ውርጂብኝ መቋቋም ስለተሳነው እስከወዲያኛው አሸለበ።
ወጣት ጌጡም አሁን የጠላትን ክላሽ ታጠቀ። የያዘውን ዱላ አመስግኖ በማስቀመጥ በማረከው ክላሽ ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በመሆን አካባቢውን ከጠላት እየጠበቀ መሆኑን ተናግሯል።

የልጃቸው የቁጣ ክንድ ስኬታማ መሆኑን የተመለከቱት አባቱ እሳቸውም ሊያጠፋቸው የመጣውን ሌላ ጠላት ተናንቁት፣ ልክ እንደ ጀግናው ልጃቸው በያዙት ዱላ ቀጠቀጡት፣ ጠላትም የወረደበትን ምት መቋቋም ስለተሳነው የያዘውን ክላሽ ጥሎ ፈረጠጠ። “ሮጠ ብዬ አልማርኩትም አነጣጥሬ በራሱ ክላሽ ማጅራቱን ብዬ ገደልኩት” ብለዋል። በፈጸሙት ታላቅ ጀብድ ኩራትና የላቀ ሞራል የተሰማቸው አባትና ልጅ የጠላትን ትጥቅ መረከብ ችለዋል። ጠላት አጥፊነቱ እና ቀማኛነቱ ቢከፋም በሚደርስበት ዱላ በተለያየ አካባቢ የያዘውን ትጥቅ ለነዋሪዎቹ እያስታጠቀ እየፈረጠጠ እንደሆነ ነው ጀግኖቹ የተናገሩት።
ተደራጅተው የቆዩ የቀበሌዋ ነዋሪዎች ከአረመኔው ቡድን ራሳቸውን ለመከላከል በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል። “ጠላትን መሸሽ ለእሱ ጉልበት መስጠት ነው” ያሉት አርሶ አደር ፈንታዬ ጠላትን ለመቅበር ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
“ሽሮ፣ በርበሬና ሊጥ ፍለጋ እንደውሻ ሲዞሩ እዚያው ተቀብረው እንዲቀሩ እናደርጋለን” ብለዋል። በዚሁ ጀብድ በተፈጸመበት ቀን ተደራጅተው የነበሩ የአካባቢው አርሶ አደሮችም 11 ሰርገው የገቡ የአሸባሪውን ቡድን አባላት እንደደመሰሷቸው አርሶ አደር ፈንታዬ ተናግረዋል። ሰረገው የገቡ ጠላቶች ሁሉ ማለቃቸውን ነው የተናገሩት።
“የእኔና የልጄን ጀብዱ ያዩ የቀበሌያችን ወጣቶች ሁሉ እናንተ የሄዳችሁበትን መንገድ በመከተል የጠላትን አንገት እናስደፋለን በማለት ከጎናችን ተሰልፈዋል” ብለዋል። በሁሉም አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ራሳቸውን ከጠላት ወረራ በመመከት የጀግንነት ታሪካቸውን ሊደግሙ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
የጀግኖቹ ጎረቤት የሆኑት አርሶ አደር አዳነ አራጌ የቀበሌያቸው ጀግኖች በዱላ መትተው ጠላት የያዘውን መሳሪያ መረከባቸውን መስክረዋል። የ32 ቀበሌ ነዋሪዎች ተደራጅተው በጠላት ላይ በከፈቱት ጥቃት ጠላት የያዘውን ቁሳቁስ ባለበት ትቶ እንዲሸሽ እንዳደረጉ ተናግረዋል። “ጠላት አርሶ አደሮችን ለማታለል ሽማግሌ ቢልክም ሥራው የማታለል መሆኑን ስለምናውቅ ጠንክረን እየታገልነው ነው” ብለዋል።
አሸባሪው ቡድን በቀበሌያችን ከቆየ የበለጠ ውድመትና ግድያ ስለሚፈጽም ከወዲሁ ጠንክረን እየታገልነው ነው ብለዋል። (አሚኮ: ቡሩክ ተሾመ – ከፍላቂት)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply