
ህወሃት በተለያዩ ጊዚያት አደጋ ሲገጥመው የሚዘይደው የማምለጫ ስልት በአካባቢው ባሉ “አጋሮቹ” ዘንድ “ዘመቻ ራስህን አድን” የሚል ስያሜ አለው። ይኸው ዘመቻ በኦሮሚያ ኦህዴድን እንዳራባው ነው የሚነገረው። የጎልጉል የመረጃ ምንጮች እንደሚሉት ኦህዴድ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ችግር ተዳፈነ እንጂ አልበረደም። ይልቁኑም በድንገት አስተዳደራዊ መዋቅር ሊናጋ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) አንጋቾቹን አሰማርቶ በሺህ የሚቆጠሩ ኦሮሞ ወገኖችን መፍጀቱ፣ በየማጎሪያው ሰብስቦ ማሰቃየቱና በዚሁ ሳብያ የተፈጠረው ማኅበራዊ ቀውስ ከፍተኛ እንደሆነ የሚናገሩት የመረጃው ሰዎች፣ በዚሁ ሳቢያ ኦህዴድ ወደ ሦስት አካልነት መራባቱን፣ ይህ ድርጅታዊ መባዛት የ“ጥልቁ ተሃድሶ” ውጤት እንደሆነ ነው የሚናገሩት።
የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ባሰባሰበው መረጃ መሰረት አሁን ኦህዴድ ሦስት ነው። በውጭ አገር ያሉት “ስውር” ኦህዴዶች ከታከሉ አራት ሊሆንም ይችላል። “መሬቴን አትውሰድብኝ” በሚል ተቃውሞ የተጀመረው ሕዝባዊ አመጽ እያደገ በህወሃት ሥልጣንና ጥቅም ላይ አደጋ ሲሆን “ምንጠራ” መጀመሩን የሚያስታውሱት ክፍሎች የህወሃት “የራስህን አድን ዘመቻ” በሚዲያ የተዘመረለትን ያህል ውጤታማ እንዳልሆነ የሚያመላክት ግምገማ መካሄዱን ያወሳሉ።
“ዘመቻ ራስህን አድን” ህወሃት በችግር ሲዋጥ የሚፈጥረው ማደናበሪያና ስልት ሲሆን፣ በዚሁ ዘዴ በስብሰናል፣ ከእንጥላችን ገምተናል፣ ነቅዘናል … የሚሉ አጀንዳዎች ይቀረጻሉ። ኪራይ ሰብሳቢ፣ አንጃ፣ ሙሰኛ፣ ተላላኪ፣ ጥገኛ ወዘተ የሚሉ የወምጀል “ማዕረጎች” ይሰጡና የማይፈለጉ ክፍሎች ይመታሉ። በዚህ ዓይነቱ ጉዞ ህወሃት ከበረሃ ጀምሮ አፈር እየላሰ የመነሳት እድል አግኝቷል። እንደ እባብ ቆዳውን እየላጠ “ታድሷል” የአሁኑ ተሃድሶ ምንም እንኳን “ጥልቅ” ቢባልም እንደ ቀድሞዎቹ “ተሃድሶዎች” ስጋትን የሚቀርፍ አልሆነም።
የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ምሥጢረኞች እንደሚሉት ድርጅታቸው ኦህዴድ በህወሃት በኩል በተለያዩ እርከኖች ላይ የሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ አመራሮችን “ጠባብ” በሚል ግምገማ አባሯል። ጉዳያቸው በህግ ይታያል በሚል ቀጠሮ የተያዘላቸው አሉ። በምትካቸው አዳዲስ አመራሮች ተሹመዋል፤ እየተሾሙ ነው። ገና ይሾማሉ። ግን ሁሉም ኦሮሞዎች ደማቸው “እኔም ኦሮሞ ነኝ፣ የሁሉም ኦሮሞ ደም የእኔም ነው” የሚል ነው።
“የሁሉም ኦሮሞ ደም የእኔም ደም ነው” የሚለው አስተሳሰብ በጥልቅ ተሃድሶም ሆነ ኃላፊዎችን በመቀያየር ሊቀየር እንደማይችል ሪፖርት መቅረቡን የሚያሳበቁት ክፍሎች፣ አሁን ያለው ኦህዴድ የዕድገት ደረጃው ወደ ሦስት ከፍ ማለቱን ይናገራሉ።
የመጀመሪያው ረድፍ ላይ ያለው ኦህዴድ – ተንሳፈው ደሞዝ የሚከፈላቸውና “የፈለገ ይምጣ” የሚል አቋም የሚያራምዱ የሚካተቱበት ነው። እነዚህ ክፍሎች ለወገናቸው ከመቆርቆር ባለፈ በሙስና የማይታሙ፣ በአካል የህወሃትን፣ በእምነት ግን የህዝብን ስሜት የሚከተሉና በሚገኙበት ስፍራ መልካም ግንኙነት ያላቸው ናቸው። እነዚህን ክፍሎች ህወሃት አብዝቶ ይፈራቸዋል። እርምጃ ለመውሰድም አይቀለውም። ስብሃት ነጋ በቅርቡ አዲስ ዘመን ላይ “የጠባብነትን አመለካከት ለመምታት ሁለት ዓመት ይፈጃል” እንዳለው በጊዜ ሂደት እንዲከስሙ ዕቅድ የተያዘላቸው ናቸው።
በሁለተኛ ረድፍ ላይ ያለው ኦህዴድ – የዘመቻ ራስህን አድን ሲጀመር ከምንጠራው የተረፉና አሁንም በተለያየ አመራር ቦታ እንዲቀጥሉ የተደረጉት ክፍሎች የሚካተቱበት ነው። እነዚህ ከአዳዲስ ተሿሚዎች ጋር ተቀላቅለው የተሃድሶውን ዘመቻ የሚያስፈጽሙ ነባር ካድሬዎች እስከ ቀበሌ ያለውን መዋቅር ዳግም የሚገነቡ ናቸው። በሌላ አነጋገር በሥራቸው አደረጃጀት የሚመሠረቱ ኃላፊነታቸው የበዛ ናቸው። ቀደም ባለው ግምገማ የኦህዴድ የገጠርና የከተማ አስተዳደር መዋቀር መክሸፉ ስለታመነና የበታች አመራሩ ከድቶ ስለነበር ይህንን የማስተካከል ኃላፊነት በእነሱ እጅ ነው።
እነዚህ ክፍሎች በግምገማ ራሳቸው ላይ የተናዘዙ፣ ራሳቸውን የረገሙና “በጥልቁ ተሃድሶ” ማዕቀፍ ግለ ሂስ አድርገው እንዲቀጥሉ የተወሰነላቸው የሚበዙበት ነው። በዚህ ቡድን ውስጥ ህወሃት በሚፈልገው ደረጃ የሚታዘዙ ስለመኖራቸው ጥያቄ አለ። ላለፈው አንድ ዓመት በክልሉ ህዝብ ላይ የተፈጸመው ግፍና ግድያ ትክክል አለመሆኑንን በግልጽ የተቃወሙ ይገኙበታል። ይህ ቡድን የበታች መዋቅርና አደረጃጀትን የመከለስ፣ አምስት ለአንድ ጥርነፋን የሚያደራጅ በመሆኑ ከፖለቲካው አንጻር የዚህ ቡድን ሚና ከፍ ያለ ነው።
ሦስተኛው ረድፍ ላይ ያለው ኦህዴድ – ይህ ቡድን የህወሃት “ተላላኪ” የሚባል፣ የደም መበረዝ ያላቸው፣ በዘር ሳይሆን በቋንቋ ኦሮሞ የሆኑ፣ በደህንነት መዋቅር ውስጥ የተጨማለቁ፣ ወገኖቻቸውን አሳልፈው የሰጡ፣ የካዱ፣ አቅም የሌላቸው፣ ንግድ ውስጥ የገቡ በህወሃት ቋንቋ፣ “የነቀዙ፣ የበሰበሱ፣ የገሙና” ከተሸከሙት ጉድፍ የተነሳ ህወሃት “እንደራሴ” የሚላቸው ናቸው።
ትልልቆቹን ኦህዴዶች /ቅምጦቹን/ የሚያካትተው ይህ ቡድን ለህወሃት በማንኛውም መመዘኛ ስጋት ስለማይሆንና ህወሃት ያሰበበት ቦታ እንዲደርስ አምነው ሁሉን የሚያደርጉ፤ “ስለበሰበሱ” ፍጹም የሚታዘዙ ናቸው። ይህንን የሚያደርጉት ሌላ አማራጭ ማየት ስለማይችሉ፣ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ክፍል የሚጠየፋቸው በመሆናቸው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የፈጸሙት ተግባር ጤና የሚነሳቸው በመሆኑ ነው። እነዚህ ክፍሎች አዳዲስ የተመለመሉትን የፌዴራልና የክልል ኃላፊዎች “ማሰልጠን” ወይም “ማበስበስ” ዋና ሥራቸው ሲሆን፣ በሁለተኛው እርከን ውስጥ ያሉትን ክፍሎች በመቆጣጠርና ከላይ ሆኖ በመከታተል የበታች መዋቅር የማደራጀቱን ሥራ ያከናውናሉ።
የመረጃ ሰዎቹ እንደሚሉት በመጀመሪያውና በሁለተኛው ረድፍ ያሉት ኦህዴዶች አሁንም ህወሃት የሚፈራቸውና ዓይኑን የጣለባቸው ናቸው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲያበቃ በክልሉ አመጽ እንደሚነሳ ይገመታል። ይህ ሲሆን እነዚህ ክፍሎች ህወሃት በሚፈለገው ደረጃ ፋይዳ ያለው ፖለቲካዊ ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ አይታሰብም፤ ምናልባትም ተቃውሞውን በሌላ መልክ የማቀናበር አደገኛ አካሄድ ይሄዳሉ ተብለው የሚጠረጠሩ በብዛት አሉባቸው። በዚህም የተነሳ በሥራ ሰበብ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ አባላትን መመልመል ላይ ትኩረት ተሰጥቷል። ሰፊ ቁጥር ያላቸው ሥራ አጦችን በስራ ስም የድርጅት አባል በማድረግ የተወሰነ ጊዜ ለመጓዝ ታስቧል።
አራተኛ ረድፍ ኦህዴድ ተቀማጭነቱ በውጪ አገር ሲሆን በአብዛኛው የውጪውን የኦሮሞ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ከመሰለልና ሆን ብለው ተቃዋሚ መስለው አፍራሽ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸው የሚታወቅ ነው። በስም የሚታወቁም አሉ። ባስፈለጋቸው ጊዜ የተቃዋሚና የደጋፊ ማሊያ እየለበሱ ተፈላጊውን ጨዋታ በድርብ የሚያቀናብሩ አሉበት፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሰፊው በመሳተፍ ተሳትፎ አላቸው፤ ተደማጮች ናቸው፤ ክርክሮችን በመፍጠር፣ አቅጣጫ በማስቀየር፣ አጀንዳ በማውጣት፣ … የሚጠበቅባቸውን ያከናውናሉ፡፡ ከሦስቱ ክፍልፋዮች እኩል የሚጠቀሱ ባይሆኑም በዳያስፖራ በኩል ያለውን ጉዳይ በትጋት የሚያስፈጽሙ በጥቅም የተደለሉ የህወሃት አገልጋዮች ናቸው፡፡
ከበረሃ ጀምሮ አብረውት የቆሙትን ሁሉ ርኅራኄ አልባ በሆነ መልኩ እየጨፈጨፈ “በእሣት የተፈተንኩ ድርጅት ነኝ” የሚለው ህወሃት ጥይት ከጨረሰ ቆይቷል፡፡ አሁን የተጋረጠበት አደጋ ከዚህ በፊት ከተጋፈጠው በዓይነቱ ለየት ያለ ነው፡፡ በቀለኛና መሰሪውን መለስ ሞት እንደ ቡሽ ክዳን ካስፈነጠረው በኋላ በአገር ውስጥና በውጪ ያለው የተቃዋሚ ደካማነት እንጂ ህወሃት አንድ ዓመት የማያልፍ ነበር የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ አሁን እያካሄድኩት ነው የሚለው “ጥልቅ ተሃድሶ” ከ“ጥልቅ መበስበስ” ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖረው የኦህዴድ ሦስት ገጽታ አመላካች ነው፡፡ በአገር ውስጥ ያለው ብሶት እየከረረ፤ በተላላኪነት ያፈራቸው “ነጭ ወያኔዎች” ከቦታቸው እየለቀቁ ባሉበት ባሁኑ ወቅት ከውስጥና ከውጭ ያለው ተቃውሞ ፈር ይዞ ካልሄደ ህወሃት አሁንም አፈር ልሶ ይነሳል የሚሉ ወገኖች ጥቂት አይደሉም፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ በተለይ በዳያስፖራው የሚታየው በሕዝብ ደም የመቀለድ ዋጋ ቢስ ጉንጭ አልፋ ከንቱ ክርክር ህወሃትን “ዕድለኛ” ድርጅት አድርጎታል፡፡ (ፎቶ: ከኦህዴድ ፌስቡክ ገጽ ለማሳያነት የቀረበ)
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
ይሄንን ሐቅ ሰካራሙ ስብሃት ነጋም አልካደም። እንዲህ ነበር ያለው ሰካራሙ ስብሓት ነጋ “የአሁኑ የህዝብ ቁጣ ከአሁን በፊት ክነበሩት ህዝባዊ ቁጣዎች” የተለዬ እና ከባዱ ነው ሲል ወያኔ ይሄንን ህዝባውዊ አመጽ በኮማንድ ፖስቱም ሆነ በሌላ ቢጠቀም ሊቀልበስው የማይችለው እንደሆነ በቁጭት ተናግሯል። ይሄንን ፍርኃቱንም ነገሮች ሁሉ ከቁጥጥራቸው ዉጭ መሆኑን የገለጸበት “ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች” የሚለው የለመደዉን የልጆች ማሰፈራሪያ አይነቱን ለቅሶዉ አሁንም ደጋግሞ አሰምቷል። ፈረንጅ ብላ እንለዋለን ፈሪውን ስብሃት ነጋን
እርግጥ ነው ሕወኃት እንደ ድርጅት ከበሰበሰ እናከከረፋ ቆይቷል ሕዝብ የለበሰውን ካባ ገልብጦ የውስጡን ገበር ከተመለከተውም ሰነበተ አሁን ለዚህ ገመነኛ የወሮበሎች ጥርቅም የስልጣን ማራዘሚያ ግብአት የሆኑት በተቃውሞ ጎራ ተሰልፈው በታማኝነት የሚያገለግሉ ትግሉንም ወደ አንድ ማእቀፍ ለማምጣት ባልቻሉ ድኩም የመጀመሪያው ረድፍ ተሰላፊወች ላይ የሚታየው መልፈስፈስ ምክንያት ነው ብየ አምናለሁ።
እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ አለመታደል በአለፉት ግማሽ ምእተ ዓመት ውስጥ የራሳችን የሆኑትን ታሪክና ተሞክሮ ጥለን በጥራዝ ነጠቅ ፖለቲካ ራሳችንን አስታጥቀን የባእድ ፖለቲካዊ አስተምህሮን በማቀንቀን ራሷን ለታመመችው ሀገርየሆድ ቁርጠት መድሃኒት በማቃም ጥረታችን ሁሉ ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እየሆነ ይገኛል።
በአጭሩ ለማለት የፈለኩት ቅድሚያ በድርጅት መሪነትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ባርነት ያጎበጠውን ሕዝብ ነፃ ለማውጣት ስንነሳ ቅንነት ታማኝነት ግልፅነት እና ተጠያቂነት ሊኖረን ይገባል መዋቅራዊ አደረጃጀታችን መገምገምን መተቸትን በሚገባ የሚችልበት አቅምንም ቅድሚያ አዳብሮ መነሳት አለበት በተቃራኒወች አንድነትም ማመን የግድ ነው ከሴራ የስልጣን ፍቅር ራስ ወዳድነት የሁሉም ቁልፍ እኔ ነኝ ብሎ ራስን መካብ ሌላው አደጋም እሱ ነውና ጊዜ ሳናጠፋ ወደ መለያየት ሳይሆን ወደ አንድነት የሚያሰባስቡ ወቅቱ የሚፈልጋቸው ጀግኖችን እንፈልጋለን፣ በእየ ጓዳው ሆኖ ማቅማማት ለዛሬ እንጅ ለነገ ምሳ አይሆንም ለሚሰሩ ሰወችም ክብር እንስጥ የፊተኞችን ስናከብር ነው ሌሎች የሚተኩ እላለሁ።