
በቤተ ሙስና፣ የ”ጥልቅ ተሃድሶ”ው ድራማ ተጀምሯል! የእርስ በርስ እና ራስን በራስ መተካካት ቧልት እና ፌዝ።
ከመጋረጃው ጀርባ ስብሃት ነጋ፣ አቦይ ጸሃይ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ደብረጽዮን እና በረከት ስምኦን የሚቆምሩትን ካርታ ሃይለማርያም ደሳለኝ እንደቬጋስ አጫዋች ፊት እያመጣ ይዘረጋዋል። በዲዮጋን ያደረጉት አብዮታዊ እና ልማታዊ “ምሁራን” ፍለጋ ውጤት ነበረው። “የዶክተር ያለህ” ፍለጋ ጥቂት ታማኝ አገልጋዮችና፣ በርካታ ሮቦቶችን አስገኝቷል። “በዲሞክራሲ” በተመረጠው “የህዝብ ምክር ቤት” የሚኒስትሮቹ ስም ይፋ በሆነ ግዜ፤ ለይስሙላ እንኳን ተቃውሞ፣ አልያም ድምጸ-ተአቅቦ ቢያደርግበት ድራማውን ያሳምረው ነበር። በሙሉ ድምጽ ጸደቀ ተባለ። የነዚህ ሮቦቶች ምርጫ የፍልፍሉን ቀልድ ያስታውሷል።
የድሃው ልጅ ለሃብታሙ ልጅ፣ “ምን ያንጠባርርሃል? አንተም የምትበላው አንድ እንጀራ፣ እኔም የምበላው አንድ እንጀራ…” ይለዋል።
የሃብታሙ ልጅ መለሰለት፣ “እንጀራውን ተወውና ስለ ወጡ እንነጋገር?”
ነገሩ ወዲህ ነው። ተጫዋቾች እና አጫዋቾች። መቼም ሹመኛው ሚኒስቴር ነኝ ብሎ ደፍሮ ቢያወራም፣ ሚኒስቴር ነኝ ብሎ ግን ደፍሮ ውሳኔ አይሰጥም። ውስጡን ያውቀዋል። ስለዚህ ስለ ተጫዋቾቹ ሳይሆን ሰለ አጫዋቾች እንነጋገር። ስለ ሚንስትሮቹ ሳይሆን ስለ ምክትሎቹ እናውራ። በቀላል አማርኛ “ዶክተሩ” ከላይ ይቀመጣል። ከስር ያለው ካድሬ እንደ እንዝርት ያዞረዋል። ላለፉት 25 አመታት ከዚህ የተለየ ነገር አልነበረም። ወደፊትም ከዚህ የተለየ አይሆንም። ጨዋታው እንደነበረ ይቀጥላል። የሳሞራ የኑስ የግል ንብረት የሆነው የመከላከያ ሚኒስቴርን ሲራጅ ፈጌሳ ይመራዋል ብሎ የሚያምን ካለ ልጅ ወይንም ጅል መሆን አለበት። ለውጥ የሚመጣው ጌታቸው አሰፋ የደህነንቱን ስፍራ ለተቀናቃኝ አስረክቦ ቢሄድ ነበር። ወርቅነህ ገበየሁ ወ/ኪዳን የተሰጠውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነገር ወደ ኋላ ልመለስበት። ድራማውን ስንቃኘው አሁንም በጥልቅ ተሃድሶ ስም ቀልድ ነው የተያዘው። ይህቺ ሃገር ገና ከአሁኑ የባሰ አምባገነን፣ ሙስና፣ ስቃይ እና አፈና ይጠብቃታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንስ እያሳዘኑን መጡ። በእርግጠኝነት ለመናገር ማን እንደተሾመ እንኳን ለፓርላማው ከማንበባቸው በፊት አያውቁትም። በሙስና እና በወንጀል እጃቸው የተጨማለቁ ሰዎችን ጭምር ሹመት አደባባይ ወጥተው ሲናገሩ በኩራት ሳይሆን በፍራት ነበር መሆን የነበረበት። እሳቸው ግን ትልቅ እና ግዙፍ ለውጥ ነው ብለው ተናገሩ። በዚህ “ጥልቅ ተሃድሶ” ሕዝባዊ አመጹ ይቆማል ብለውም ያምናሉ። በጥይት እና በጭስ ከ700 ሕዝብ በላይ ሲያልቅ የቶክስ ድምጽ አልነበረም ብሎ በአለም አቀፍ ሜዲያ ለሚናገር ምስኪን ጠቅላይ ሚኒስትር ማዘን እንጂ ማውገዝ አይገባም።
የሚኒስትሮቹን ምክር ቤት የእግር ኳስ ቲም አስመሰሉትኮ። የመብት ጥያቄ በመጣ ቁጥር የሚፐወዝ ቲም። ጥያቄው የስርዓት ለውጥ እንጂ የሰዎች መገለባበጥ አይደለም። ካቢኔውን ሺህ ግዜ ቢፐውዙት፤ ለሃገሪቱ ችግር መፍትሄ አይሆንም። የእግር ኳስ ቲምም ቢሆን እኮ ሲገነባ የእያንዳንዱ ተጫዋች ብቃት እና ስነ ምግባር በባለ ሞያዎች ተገምግሞ ነው። እጃቸው በደም እና በሙስና የተጨማለቁ ሰዎችን እያመጡ፤ የሕጻን አይነት ድብብቆሽ መጫወት ግዜ ለመግዛት ይረዳቸው ይሆን እንጂ ሕዝባዊ ቁጣውን ሊያቆመው አይችልም። በዚያ ሰሞን በቴሌቭዥን ቀርበው መንግስታችን ጥልቅ በሆነ ሙስና ተዘፍቋል ያሉን እነሱው ናቸው። ሙስኞቹ አሁንም አሉ። በጥልቅ ሙስና የተዘፈቁ ሰዎች የችግር እንጂ የመፍትሄ አካል እንደማይሆኑ እያወቁ በህዝብ ላይ ማፌዙ ለምን አስፈለገ? የሚደረገው ድራማ ለመግለጽ የአናንያ ሶሪን ቃል ልዋስ፣ “በዚህ ሁኔታ የሚመጣው በጥልቅ መታደስ ሳይሆን በጥልቅ መበስበስ ነው።”
“ጥልቅ ተሃድሶ” ሲሉን ቢያንስ አዲስ ምርጫ ያደርጋሉ ብለን ጠብቀን ነበር። እውነት ይቀየራሉ ብለን አምነን ተሳስተናል።እነሱ ግን ሕዝብን ሳይሆን ራሳቸውን ነው እያታለሉ ያሉት።
ከተሾሙት ሚንስትሮች ውስጥ ሁለት ፕሮፌሰሮች፣ ሁለት ኢንጅነሮች እና አስራ አራት ዶክተሮች ይገኙበታል። ያልተገነዘቡት ከለውጥ ይልቅ የዶክተር መደርደር ሾተልን ወደ ሰገባ ቁጣን ወደ ትእግስት እንደማይመልሰው ነው። የዶክትሬቱ ዲግሪም እኮ ከየት እንደመጣ ለሕዝብ የተደበቀ ነገር አይደለም። ግን የዶክተር ያለህ እየተባለ ከየስፍራው ሲለቀም ጀነራል ባጫ ደበሌ ለምን ተረሳ? ምሁር የሚያሰኘው የዲግሪ ወረቀቱን ከሁሉም በፊት እሱ ገዝቷል። ጀነራል የሚለውን የፉገራ ማእረግም ከፕሮፋይሉ ላይ አንስቶት ነበር። አባ ዱላ ገመዳስ ቢሆን ለአዲሱ ከቢኔ ምን ያንሰዋል? ሳይማር ዶ/ር አባ ዱላ እየተባለ አይደል የሚጠራው? ፕ/ር ቆስጠንጢኖስም ከሴንቸሪ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ገዝቷል። እሱስ ቢሾም ምን ይለዋል?
ከሆነ አይቀር ለምን ሁሉንም ሚኒስተሮች በባለ ዶክተር ማዕረጎች አልተኩትም ነበር? ለወረቀቱም ቢሆን ችግር የለም። የሲቪል ሰርቪስ ወፍጮ ዶክተሩን እና ፕሮፌሰሩን በገፍ እያመረተ ነው። ዘንድሮ ከአንዳንድ የርቀት ትምህርት ቤቶች በሳምንት ግዜ ፕሮፌሰር መሆን ይቻላል።
በሸገር የሚነገር አንድ ቀልድ አለ። ወያኔ ስልጣን ሲይዝ መጀመርያ የወረረው ወታደራዊ ካምፖችን ነበር። መኮንኖችን ለመያዝ። ወያኔ ሲወድቅ ደግሞ ተቃዋሚው ሃይል መጀመርያ የሚወርረው ሲቪል ሰርቪስ “ኮሌጅ”ን ነው። እንደ ድንጋይ የሚያስቡትን እያመረተ ሕዝብን የሚፈጅ ተቋም!
መቼም ተቀለደ። ተቀልዶ ግን አይቀርም። መዳኛ ያልተገኘለት የህወሃት የፖለቲካ መፍትሄው የህዝብ ድምጽ ነው። የህዝብ ድምጽ ደግሞ በሶስት ቃላት ተገልጿል። ለውጥ!
“መተካካት” እያሉ ጆሮ ሲያደነቁሩ የነበረው ይኽንን ነበር እንዴ? ወርቅነህ ገበየሁ ወ/ኪዳን ከትራንስፖርት ሚኒስትር አንስቶ በወርቅነህ ገበየሁ ነገዮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መተካት? እርግጥ ነው ፈረንጆቹ በጥቂቱም ቢሆን ተሸውደዋል። አሶሴትድ ፕሬስ ዜናውን ሲዘግብ፣ “The new ministers of foreign affairs — Workneh Gebeyehu, a former transport minister is Oromo, replacing the Tigrayans who previously held the posts.” ኦሮሞው ወርቅነህ ገበየሁ ትግሬ ይዞት የነበረውን የውጭ ጉዳይ ሚንስተር ተክቶታል ብሎናል።
ምነው እነ ደብረጽዮን በወርቅነህ ኦሮሞነት አመረሩ? እኔ ያልገባኝ ወርቅነህ የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት በሚፈቅደው “ጉዲፈቻ” እና “ሞጋሳ” ባህል መሰረት ወደ ኦሮሞነት ቀይረውታል እንዴ? ይህ ነገር ግልጽ ይሁን። ካልሆነ የሱን ማንነት የሚገልጸውን ዶክመንት እንልቀዋለን። ጥያቄው ሹመቱ ላይ አይደለም። ሲፈልጉ ጠ/ሚኒስቴርም ያድርጉት። ግን በኦሮሞ ካርድ አስይዘው ማጫወታቸው ነው የሚደብረው። የሕወሃት አባል ሆኖ ጨዋታውን በዚያው ካርድ ቢያደርገው ችግር የለውም። ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል ይሚለውን የሂትለሩን ጎብልስ ብሂል የሙጥኝ ያሉም ይመስላል።
የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት መወገድ ያልተጠበቀ አልነበረም። ከፍተኛ የህወሃት አመራሮች የድል አጥቢያውን ታጋይ፣ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን እንደማይወደዱት በስፋት ይነገር ነበር። ዶ/ሩ ፌስቡክ በብዛት ይጠቀማል። ስራውን ብርሃነ ገብረክርስቶስ ስለሚያከናውንለት ለፌስቡክ በቂ ግዜ ነበረው። እታች ወርዶ ከተራው ዜጋ ጋር በማህበራዊ ሜድያ መነጋገሩ ግን በህወሃት ዘንድ “ፖፑሊስት” የሚል ስያሜ አሰጥቶታል – ልክ እንደ አርከበ እቁባይ። በዘር መስፈርት ብቻ ከመንገድ ተወስዶ የተቀመጠ ምኒስቴር ነበር። “ይሰረዝ !” ብለው ከፈረዱበት ቆይቷል። ከዚያ በፊት ግን ሁነኛ ሰው መፈለግ ነበረባቸው። እነሆ አሮምኛ ተናጋሪ ትግሬ ተገኘ። የማኬያቬሊ ሊቅ!
በአሮጌ ጠርሙስ አዲስ ወይን ቢያቀርቡ አንድ ነገር ነው። በአዲስ ጠርሙስ አሮጌ ወይን ቢጨምሩ ደግሞ ሌላ የተለየ ነገር ሊመስል ይችላል። የነሱ ሙከራ ሁለቱም አይደለም። በአሮጌ ጠርሙስ አሮጌ ወይን ይዘው የተሃድሶ ዘፈን ይዘፍናሉ። በአስተሳሰብም በመልክም አንድ የሆኑ የድሮ አሻንጉሊቶችን እንደ እላቂ እቃ እያሽከረከሩ ያመጧዋቸውና ተሃደሶ ይሉናል። ችግሮችን መፍታት ሲሳናቸው ስህተትን እንደመፍትሄ ይወስዱታል። ሁለት ስህተት ደግሞ አንድ እውነት አይሆንም። አሸዋወዱንም አላወቁበትም። ዳሩ ሕዝብ ቀድሟቸው ሄዶ እንዴትስ ያታልሉታል?
አካሄዳቸው የሚነግረን ነገር አለ። እነዚህ ሰዎች አሁንም ለለውጥ ዝግጁ አይደሉም። ሕወሃት ፈጽሞ አይታደስም!
ህወሃት በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ግድያ፣ ሙስና እና አፈና ከሃገሪቱ አይጠፋም። “አደገኛ ፎርስ ናቸው … ይጥፉ ወይንስ እንጥፋ!” ያለው ማን ነበር?
ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር የምትወጣው ይህ ፋሽታዊ አገዛዝ ሲጠፋ ብቻ ነው!
ክንፉ አሰፋ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
>>> የ”ጥልቅ ተሃድሶ” ድራማ ተጀምሯል! …
_____ አንዳንዶች “የጥልቅ ብስባሶ” ብለው ያሽሟጥጣሉ… ሌሎችም ደበላን በጨመዳ ደህንነት: መከላከያውንና ኢኮኖሚውን ጭምደዳ ! ይላሉ ሌሎች የሽግግር መንግስት ! የሞግዚት ግዜያዊ መንግስት ይቋቋም ! ሕዝባዊ አስቸኳይ ምርጫ ይካሄድ ! ይላሉ ሌሎች ህወአት/ኢህአዴግ ይውረድ የመንግስት ሙሰኛና ነፍሰ ገዳዮች ተጠያቂ ሳይሆኑ ሰፈሩንም ክልልና ቤተመንግስቱ አንደርስም ብለው ይጥፉ? ወይንስ እናጥፋቸው? ይላሉ “ኢህአዴግ የኦሮሚያ ክልላዊ ሕዝቦች ያቀረቡት ሕገመንግስታዊ ጥያቄን ትክክል ነው ሲል የዘጠኝ ወር ተጋድሎ በአንድ ሺህ የድሃ ልጅ ደም: በሕገመንግስታቸው (ማኒፌስቶ) ጥቅማጥቅም ሙሉ መብት በብሔር ተዋጽዎ በዶ/ር.. ኢንጂነር..ፕሮፌሰር ፓርላማውን ቀወጠው!! “ከዛሬ ጀምሮ ኦሮሞው ለኦሮሞ ብቻ አይሰራም! ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነው” አለ ኅይለመልስ ደስአለኝ ዜናው:: ለመሆኑ ላልፉት 25ዓመት የተሠራው ሁሉም ለጎጡ ብሔርና ክልልሉ በሙስና መር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ በመሆኑ በአድርባይነት የጥቅምና ሥልጣን ሽኩቻ እንጂ ኢትዮጵያዊነት አልነበረም ሲሉ አስረግጠው መሰከሩ።አራት ነጥብ::
>>”የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ታውጇል!…
___ አዋጁ ለምን? ለማን? ከሚሉት ውጭ አዋጁን መስመር በመስመር ሲተነትኑ የነበሩ ምሑራን ተብዬዎች ከማሳቅም አልፈው አሳቀዋል:: ግን ያ.. የፈረደበት ድሃና የዋህ ሕዝብ የማንነት መገለጫ በአነጣጥሮ መምቻ (ሳይዳበል) ብሄር: ቋንቋው: አመጋገብ አለባበሱ: የቅንድቡ ላይ ጭረት: የግንባሩ ላይ ብጥ: ሳይመተር ሰው በመሆኑ ብቻ በሕገመንግስቱ ዕውቀና የሌለው ሁሉ በወንጀለኛ መቅጫ: በሽብርተኛ አዋጅ ከተጠረነፈው በላይ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ቆለመመው ብሔር ብሔረሰቦችን(ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኞች) ደፍጥጦ ለሕዝቦቹ ግን 25 ኪሎ ሜ. በላይ የመንቀሳቀስ መብታቸው ይከበራል:: ያለ እነሱ’ ልማታዊ ዴሞክራሲ’ አይቀጥልማ !?
>>> “ገበሬያዊ የ25 ዓመት ዴሞክራሲዊ ብሔርተኝነት !” መግለጫ ወጥቷል!:
____ የኢህአዴግ ረጅም ጉዞና የወደፊት የ25ዓመት ዕራይ ከተቃዋሚ ፓርቲ አለመኖር የአጋር ፓርቲ በረከት ስሞዖን (በመድብለ ፓርቲ) ተተክቷል” ይላሉ ይህ 83 ተቃዋሚ ፓርቲ ቁጥርን ለመቀነስ ብቻ ሳይሆን ለማጥፋት የተነሳው የሶስተኛ አማራጭ( በመደናነቅና መሞካከሽ ላይ የተመሠረተፓርቲ) ወደ አጋር ፓርቲ ማስጠጋት ኢህአዴግ የውስጥ ዶሞክራሲ: የአባላት መናበብና መደጋገፍ: የዓላማ ጽናት: የለውጥ ሀዋሪያ የዕድገት ቀንዲል: የልማት መሪ ከሆነ 80 ከመቶ ፓርላማ በሕዝብ የተመረጠ ከሆነ መድረክ: ሰማያዊ: ኤዴፓ: ለምን ያስፈልጋል!? የቀድሞ የፓርላማ አባል(የተከበሩ) ለመባል ነውን? ” ከዛሬ ጀምሮ ይቺ ሀገር የኢህአዴግ ብቻ አደለችም የወቅቱ ሁኔታ ይህንን አሳይቷል” አቶ ልደቱ ተስካር ላይ …? ” 80 ከመቶው ገበሬ በሆነባት ሀገር ጥቂቶች አመጽ ቢያነሱ:ንብረት ቢያወድሙ:ፓሊስ ቢገድሉ አንደነቃቀፍም እንተኩሳለን ይላሉ ይሳቃል: ይጨበጫባል:: ጉድ!!
>>> “አስቸኳይ የኦሮሞ የምሥራቅ አፍሪካ ክልላዊ መንግስት ቻርተር ሰነድ በሕግ ባለሙያዎች ፀድቋል !”
_____ ማን ከማን ያንሳል! “500ሺህ ጠመንጃ የያዘ የኦሮሞ ልጅ ወታደር አለን” ሻለቆች ሻምበሎች አውጡን እያሉ ለሜ/ጀዋሪ ሜኒሶታ/አሜሪካ እንዲሰፍሩ ዝውውር መጠየቂያ ፎረም አቅርበዋል” ቡናና ውሃ ከእኛ ቤት ነው: እንጀራ ዶሮ ወጥ የአማራና ትግሬ ማንነት ነው ነጠላና ጋቢ ኢትዮጵያዊነት ኦሮሞ ላይ በግድ የተጫነበት ነው” ይልና ከእኛ ጋር በጉርብትና የሚኖሩና ዜግነትም ለሚጠይቁ መብታቸው ይጠበቅላቸዋል ይሉናል:: አሜሪካ 11ሚሊየን የመኖሪያ ፍቃድ አልባ ሕገወጦች እንዳሉ ሁሉ …ኦሮሚያ ክልላዊ ራስ ገዝ ዞን 11 ሚሊየን ሕጋዊ ብሔር ብሔረሰቦች ሲኖሩ መሬቱ ግን የማንና መቼ ባለቤት እንደሆኑ ህወአት እና ኦነግ ደደቢት ያጠኑትና ቃለመሐላ የፈረሙበት እከክልኝ ልከክልህ ማኒፌስቶ የአሁኑ ሕገመንግስት ሕዝብን ጠርንፎ ሳይሰፋና ሳይስፋፋ ለመንቀሳቀስ አስፈቅዶና አሳውቆ እንዲጠብ አድርገው ጠባብ ብለው ይሰድቡታል!? :: ይህ ቃለ ጫካ ውሎ አድሮ ጉበት አጥንት እንደሚሆነው “የኢትዮጵያ ማንነትን በህወአት/ ኢህአዴግ ጥላ ሥር ላለፉት 43 ዓመት በሐሰተ የፈጠራ ታሪክ: የአማርኛ የተራራና የሠፈር ሥም ወደ ኦሮሚኛ በመቀየር የተካኑ ወያኔን ከድተው ትግሬ ወደ መቀሌ ሊሉ የኢትዮጵያ ማንነት የለም ሲሉ ህወአት/ ኢህአዴግ በቆፈረው ራዕይ ተቀበቀበበት ሲሉ አይፈረድባቸውም የትግራይም ሕዝብ ሳይቸግረው በገዛ ልጆቹ ደምና አጥንት አመድ አፋሽ ሆነ አሁንም ተጠያቂው ያው ያለዕዳው ዘማች አማራ ነውን… ታዋቂው የፖለቲካ ሳይንቲሰት አብርሃ ደስታ በጣም የሚያደንቀው የፖለቲካ ተንታኝ(በታኝ) ኢትዮጵያን አፈራርሶ ኦሮሚያን እገነባለሁ ለሚለው ጃዋር መሐመድ የሜንጫ አብዮት! የምስጋናና የአጋር አስቸኳይ የአቋም መግለጫ አለመላኩ ዘ-ይገርም ብለናል!?
>>> “የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ” (እውነተኛ የአማራጭ ኅይል?” ) ተመሥርቷል!..
” የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ራዕይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚጠበቅበት፤ የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች መብት ሳይሸራረፍ የሚከበርበት፤ ባህላቸዉ፣ ታሪካቸዉና ማህበራዊ እሴቶቻቸዉ የሚንፀባረቁበት፤ ሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦች በዜግነታቸዉ ተከብረዉ በህግ ፊት በእኩልነት የሚስተናገዱበት እና ዕድገትና ብልፅግና የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ የሆነ የፌዴራል ሥርዓት መመሥረት ነዉ፡፡”
_____ ቼ በለው! እሺ ይህ ሥልጣን ለመጋራት ነው? ግንቦት ሰባት ከጦር ሰራዊት (ሁለገብ )ታክቲክ ወደ ወዶ ገብ ሊቀየር ነው? ይህ የትብብርም ይሁን የአጋርነት ጉዳይ ግንቦት ሰባት በሰበታ ቦንብ ሲጥል… ዳውድ ኢብሳ ሠራዊታችን ሀገር ወስጥ ገብቶ ትግሉን ጫፍ አድርሶት ሚኒሊክ ቤተመንግስትን ልንቆጣጠር ትንሽ ቀንና ኪሎ ሜትር ቀረኝ ሲሉ: የድሃው ልጅ ሀገሬ! መብቴ! ወገኔ! የሌላው ብሔር ድም ደሜ ነው! ..ሐዘንና ጉስቁልናው ይሰማኛል!ህመሙ ያማል!የበይ ተመልካችነት ይብቃ! የጋራ በደል በአንድነት! የዜግነት ነጻነት! የሚለውን ሀገራዊ አጀንዳ በክልል ለማጥበብ ዓላማውን ለማሳትና ለመበከል ከሰላማዊ ተቃውሞ ወደ ጎጥና የራስን ንብረት እስከማውደም ማበረታታት ያልተጣደፈ የምሁር ደንባራ የለም!! ያ..የዋህ ሕዝብ” የተማረ ይግደለኝ “ብሏላ!! ኋላ ቀር! ምቀኛ!ጠባብ! ዘረኛ! ከመባል አላዳነውም ጭራሽ ከግራም ከቀኝም ከውስጥም ከውጭም በምሁር(ዶ/ር:ፕሮፍ:እንጂነር) መጎንተሉ ቀጥሏል:: ይህ የሽግሽግ ይሁን የጦር ቀጠና ሀገራዊ ንቅናቄ ሁለት ሀገሮች ኢትዮጵያና ኦሮሚያ ባንዲራቸውን አስደግፈው ሲፈራረሙ” የንቅናቄዉ ተልዕኮ ደግሞ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አስተባብሮ በአንድ አገራዊ ዓላማ ሥር በማሰባሰብ ከሕዝቦች ፍላጎት ዉጭ በጠመንጃ ኃይል የያዘዉን ሥልጣን በመጠቀም የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ተቋማት በበላይነትና በብቸኝነት የተቆጣጠረዉን አምባገነን ሥርዓት በተባበረ ሕዝባዊና ነፍጥ-አልባ ትግል አስወግዶ ዕዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ የፌዴራል ሥርዓት መመሥረት የሚለዉን የአገራዊ ንቅናቄዉን ራዕይ ከግብ ማድረስ ይሆናል፡፡
“የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) -የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ -የአፋር ሕዝባዊ ፓርቲ -የሲዳማ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ናቸው:: ሰሞኑን አማራ ለምን በጎጥ ተደራጀ በዘረኝነት ህወአት ቦይ ፈሰሰ ከሚሉት አማራ መሳዮች አዛኝ ቅቤ አንጓቾች ‘የራስን በራስ እስከመላጨት’ ከሚሉት አማራ አማሳይ የህወአት: ኦነግና ኦብነግ ተቀፂላዎች ውጭ “የአማራውን ወገን ከጥቃት ለመከላከልና በደሉን ለማጋለጥ ከተነሱት” እንኳ በዚህ የሽግግር መንግስት አለማስገባት ዳግማዊ ህወአት የቆረጣ ሥልት ከአንድነት ይልቅ በትብብርና አጋርነት የጎፈሩ በኢትዮጵያዊ ማንነት ጥላ ሥር ያሉ ከጎረቤት ክልላዊ ሀገር ጋር የተፈጠረው ውል ከውስጥ ሲፈርስ ከላይ ለመጫን ነው::የጥሪ ማስታወቂያቸው ግን የአማራው መፈክር ነው:: አዳሜ ግራ ገብቶህ: ግራ አታጋባ: እርስበእርስ ትመራረጣለህ ፈርመህ ትቀዳልህ ማጣፊያው ሲያጥር ወያኔ ትላለህ የአዞ እንባ የቁራ ጩኽት..!!በወያኔ ጠፋ ወኔ ያለው ማን ነበር! ቢጠፋ ነው ዳውን ዳውን ያለው ባትሉኝ….መሪ ነኝ ባይ ጩኽቱን ባይሻማው ነበር በለው!!!::