ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ብር ወይም ወደ ሃያ ሚሊዮን ዶላር አካባቢ የተዘረፈባቸው አውቶቡሶች የተገዙት ለዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ መሆኑ ታወቀ።
ኤሊያስ ሳኒ ዑመር እና ያደታ ጁነዲን በክሪ (ብራይተን ትሬዲንግ) የመጨረሻ ተጫራች ሆነው በቀረቡበት ጨረታ ኤሊያስ ሳኒ ዑመር በኢትዮጵያ ውስጥ መኪና አስመጪነት ይቅርና በአጠቃላይ በአስመጪነት ያልተመዘገበ ድርጅት ነው። ሆኖም ለአንድ አውቶቡስ ሃያ ሁለት ሚሊዮን ብር ዋጋ አስገብቷል።
ባልተመዘገበ ድርጅት የተወዳደረው ኤሊያስ ሳኒ ዑመር ከፍተኛ ዋጋ አቀረበ ተብሎ 19 ሚሊዮን ብር ያቀረበው ያደታ ጁነዲን በክሪ (ብራይተን ትሬዲንግ) አሸነፈ ተብሎ ግዢውን ፈጽሟል። ከንቲባዋም የያደታ ጁነዲን በክሪ (ብራይተን ትሬዲንግን) ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል።
ሆኖም ይህንን የመሰለ አደገኛ የሌብነት አሠራር ከመፈጸሙ በፊት የአውቶቡሶቹ ግዥ ይፈጸማል በተባለበት ጊዜ አዲስ ሚዲያ ሰኔ ባወጣው ዜና፤
- በዓለም ባንክ ድጋፍ የአንድ መቶ አውቶቡሶች ግዥ እንደሚፈጸም፤
- አውቶቡሶቹ ሙሉ በሙሉ የአውሮፓ ስታንዳርድ እንደሚኖራቸው፤
- እያንዳንዱ አውቶቡስ ከስድስት እስከ ስምንት ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበት ግዥው የሚፈፀም
መሆኑን በፌስቡክ ገጹ ዘግቦ ነበር።
ከንቲባ አዳነች ወደ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሹመት ወደ ሥልጣን የመጡት ይህ ዜና ከመውጣቱ አስር ወር በፊት ነው። እርሳቸው የተሾሙት በነሐሴ 2012 ሲሆን ዜናው በሰኔ 2013 ነው የወጣው። ስለዚህ ግዢውን በተመለከተ ከዓለም ባንክ ስለተገኘው ድጋፍ አላውቅም ማለት አይችሉም።
አሁንም ያልተመለሱት ጥያቄዎች፤
- ገንዘቡ ከዓለም ባንክ የተገኘ ከሆነ የውጪ ምንዛሪ ፍለጋ ለምን ያንን ያህል ርቀት መሄድ አስፈለገ?
- የዓለም ባንክ በቀጥታ ለቻይናው ኩባንያ እንዲከፍል አልተደረገም?
- የመጀመሪያውና ሁለተኛው ተጫራች ወረታ ትሬዲንግ በምንዛሪ ችግር ምክንያት ተብሎ ለምን ከጨረታው እንዲሰናበት ተደረገ?
- ገንዘቡ ከዓለም ባንክ የሚመጣ መሆኑ እየታወቀ ሦስት ጊዜስ ጫረታ ለማውጣት ለምን አስፈለገ?
- ይህ ሁሉ ግልጽ ሌብነት ሲካሄድ የከተማው መስተዳድር፣ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ከሁሉ በላይ ሕዝብ የመረጠው የከተማው ምክር ቤት የት ነው ያለው?
- ለምንስ ዝምታ ተመረጠ?
ሌብነትን በትክክለኛ ስሙ እንጥራው፤ አግዙን እንተባበርና ሌብነትን እንዋጋ የሚሉት ዐቢይ በፊታቸው የቀረበውን ጉዳይ በፓርቲና በታማኝነት መነጽር ነው የሚያዩት ወይስ የሕግ ሚዛን በእጇ ይዛ ዓይኗ ታሥሮ እንደምትፈርደው የፍትሕ ተምሳሌት የፍትሕ አርበኛ መሆናቸውን ያሳያሉ?
በርካታ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉ ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ይጣራ፤ ይህንን ያከለ ምዝበራ እንደ ኮንዶሚኒየሙ ጫረታ በቴክኒክ ምክንያት ማሳበብ ሳያስፈልግ ከንቲባዋ ባስቸኳይ ከሥራ ይልቀቁ። እርሳቸው በሥልጣን እያሉ የሚደረግ ማጣራት የጥቅም ግጭት (conflict of interest) የሚያስከትልና ወደ እውነቱ ለመድረስ የማያስችል ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ©
Leave a Reply