
ኢትዮጵያዊያን በሀገራችው ሰማይ ስር የመጣን ጠላት በማሽመድመድ ካስመዘገቡት ደማቅ ታሪክ ፊት ለፊት ትልቁን ድርሻ ከሚወስዱት አንዱ ናቸው። ለሀገራቸው በዋሉት ውለታ ከሚተረክላቸው ቀዳሚ ባለ ታሪኮች ቀድመው ይጠቀሳሉ። ሙሉ ህይወታቸውን ለሀገራቸው የሰጡ ናቸው። ጀግና ተዋጊ፣ የበቁ የጦር መሪ፣ የተሳካላቸው የጦር አዛዥ ሆነው አገልግለዋል። በበርካታ የጦር ሜዳ ውጊያዎች ተሳትፈው የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የህዝብን ነፃነት ያስከበረ ደማቅ ድል አስመዝግበዋል። ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያም።
ጄኔራል መኮንኑ በ1934 ዓ.ም በጉራጌ ዞን ከቸሀ ወረዳ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሲሰ መንደር ተወለዱ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም እዚያው እምድብር ከተማ ተምረው በ1948 ዓመተ ምህረትም አጠናቀዋል።
ከ1949-1952 ዓ.ም ድረስ አምቦ የእርሻ ልማት ትምህርት ቤት ተምረዋል። በመቀጠልም የምርጥ መኮንኖች ማፍሪያ በነበረው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (ሀረር) የጦር አካዳሚ በመግባት ለ3 ዓመታት ያህል የወታደራዊ ሳይንስና የአካዳሚ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
ጥቅምት 4 ቀን 1956 ዓ.ም ከሀረር የጦር አካዳሚ ከተመረቁ በኋላ የአየር ወለድ ስልጠናም ለ6 ወራት ያህል ወስደው በምስራቅ ዕዝ 3ኛ ክፍለ ጦር 25ኛ ሻለቃ ልዩ ስሙ ኦጋንዳን /ደጋሃብር/ በተባለ ቦታ ላይ በመቶ አዛዥነት ተመድበው ሰርተዋል።
ከ6 ወራት የኦጋደን ደጋሀቡር ቆይታ በኋላ ደሬድዋ ላይ ለ2 ዓመታት ያህልም የስፔሻል ፎርስ አሰልጣኝ በመሆን ሰርተዋል። በ1960 ዓ.ም የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ የትምህርትና ስልጠና ሃላፊ ሆነውም አገልግለዋል።
በ1967 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ ገነት ጦር ትምህርት ቤት በእግረኛ አስተማሪነት ተመድበው ሰርተዋል። በመቀጠልም የኢትጵያን አየር ወለድ ኃይል በሻምበል አዛዥነት መምራት ችለዋል። በወቅቱ የክበር ዘበኛ ክፍለ ጦርና የ3 ብርጌድ አካል የነበረች የ15ኛ ሻለቃ የጦር ከፍል የሳህላ አወራጃ የናቅፋ ከተማን ፀጥታ እስከበረችና ከጠላት ጋር እየተፋለመች ነበር።
ነገሮች እየተካረሩ ሲሄዱም ሻለቃዋን የሚያጠናክር ኃይል መላክ እንዳለበት በመንግስት ታምኖ አየር ወለድም በፓራሹት ወርዶ ድጋፍ እንዲያደርግ ተወሰነ። በወቅቱ ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም የአየር ወለድ አዛዥ ነበሩ። የአየር ወለድ አባላቱም አምነውበት ሀላፊነቱን ተቀበልው ከመንደፈራ ወደ አስመራ ከዚያም ወደ ናቅፋ የግዳጅ ቀጠና በረራ አደረጉ።
በቦታው እንደደረሱም የተቀናጀ ስኬታማ ውጊያ አድርገው የሻለቃዋን ማሽግ ተረክበው ለ6 ወራት ያህልም በምግብ፣ በመጠጥ፣ በልብስ፣ በጥይት በህክምና እጥረት መፈተናችውን ያስታውሳሉ። በመጨረሻም ከነበረው መንግስት ከአቅሜ በላይ ስለሆነ ራስህ ወስን የሚል ትዕዛዝ ደረሳቸው። ይህ ሲባልም ለጠላት እጅ መስጠት፣ ራስን ማጥፋት ወይም ሰብሮ መውጣት ከሚሉ 3 ነገሮች አንዱን መምረጥ ግድ ይላል።
ጀግና ታሪክ ይሰራል እንጂ ታሪክ አያበላሽም። ስለጉዳዩ ውይይት ካደረጉ በኋላም የእጅ በእጅ የጨበጣ ውጊያን ምርጫቸው አድርገው ጠላትን ደምስሰው መውጣታቸውን አስታውሰዋል። ከ3ቀናት የ60 ኪሎ ሜትር ጉዞ በኋላ ከወገን ጦር ጋር ሲገናኙም ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ለፈፀሙት ጀብዱ ማበረታቻ ይሆን ዘንድም ሻለቃ ማዕረግ በለበሱ ከጥቂት ወራት በኋላ የሌተናል ኮሎኔል የማዕረግ ዕድገት ተሰጥቷቸዋል።
ሀዋሳ ላይ ተቋቁሞ የነበረውን የፓራ ኮማንዶ ብርጌድ አደራጅተው አሰልጥነዋል። በወቅቱ የብርጌድ አንድ ክፍል በነበረው ጦርነት ክፍላቸውን ይዘው የተሠጣቸውን ግዳጅ በብቃት ተወጥተዋል። በ1970 ዓ.ም ከምስራቁ የሀገራችን ክፍል ወደ ሰሜን በመመለስ የግብረ ኃይል አዛዥ በመሆን ሰርተዋል። በኤርትራ ምድር ጥይት በጮኸበት ቦታ ሁሉ ያልተሳተፉበት ውጊያ የለም። ለዚህም መስከረም 3 ቀን 1972 ዓ.ም ወደር የሌለው የኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል።
ዘንድሮ በሀገራችን 116ኛው የሠራዊት ቀን ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም ይከበራል። የሠራዊት ቀን ማክበር ደግሞ ለሀገር ብለው ለተሰውም ሆነ በህይወት ላሉት እውቅና መስጠት ነው። ሀገራችንም በዚሁ አግባብ ማክበሯ ተገቢ ነው። ለሀገር መከላከያ ሠራዊታችን አሁንም ቅርበት አላቸው። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ሁኔታ በሠራዊቱ ላይ የደረሰው ጉዳት ጉዳታቸው ሆኖ አሟቸዋል። በጋሸና በአፋርና በጣርማ በር ግንባሮች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። አበረታተዋል።
የውትድርና ህይወት በጣም ከባድ ህይወት ነው። የህይወት መስዋዕትነትን ይጠይቃል። ሰው ሆኖ የማይሞት የለም። መለየት ያለበት የት ሆነህ መሞትን ትመርጣለህ የሚለው ነው። በውትድርና ህይወት ውስጥ መሞት ታሪክ ነው። እንደመኖር ይቆጠራል። ለሀገርና ለህዝብ ደግሞ ህይወትን መስጠት መታደል ነው። ህይወትህን ከፍለህ ህይወት ትሰጥበታለህ። የሀገር ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ፣ ህዝቦች ከቦታ ቦታ በነፃነት ተንቀሳቅሰው መኖር እንዲችሉ ወታደሩ ድንበር ላይ ይቆማል።
ወታደር በወታደራዊ ንድፈ ሀሳብ አእምሮው የጎለበተ መሆን አለበት። ከብረት የጠነከረ የአካል ብቃትና ስነ-ስረዓት ሊኖረው ይገባል። ለችግሮች እጅ የሚሰጥ ሳይሆን ችግርን የሚረታ መሆን አለበት። የዘመናዊነት መነሻው ስህተትን አውቆ ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ስለሆነ አሁን እየተወሰደ ያለው ሠራዊቱን የማዘመን ስራ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ጠንካራ ሠራዊት ለመፍጠር ስልጠና ወሳኝ ነው። በማሰልጠኛዎች ላይ ሊሰራ ይገባል።
የሠራዊት ፈጣሪ ሞተሮች አሰልጣኞች ናቸው። አሰልጣኞችም መስለው ሳይሆን ሆነው ቆመው ሳይሆን ሰርተው የሚያሳዩ ሊሆኑ ይገባል። ያኔ ሠራዊታችን ብቃትና ዲስፕሊንን ከህዝባዊነት ጋር አጣምሮ ይዟል። የተሻለና ዘመናዊም ይሆናል። ስለሆነም ለእናት ሀገሩና ለዓለም ሰላም ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ነው።
ሀገራችን በሰላም ማስከበር ግዳጅ በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ዝናና ክብር አላት። ሠራዊቱም ከፍተኛ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሚናዎችን መጫዎት ችሏል። የጀኔራል መኮንኑ ድንቅ የህይወት ተሞክሮም አሁን ላለው የሠራዊት አመራርና አባላት የሞራል ስንቅ ነውና በዚሁ ልክ ለሀገራችን ልንሰራ ይገባናል። (አደም አሊ የመከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply