ከ18ሺህ በላይ ሰዎች ጋምቤላ ክልል ላሬ ወረዳ ውስጥ በጎርፍ መፈናቀላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ። የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ የተከሰተበት ወረዳው ኢትዮጵያን ከሱዳን በሚያዋስን አካባቢ ነው።
የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ ቤት ከተፈናቃዮች መካከል ወ/ሮ ኛዳክ ፓችን ጠቅሶ እንደዘገበው ሰሞኑን እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በፈጠረው ጎርፍ ምክናያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከነቤተሰቦቻቸው በትምህርት ቤት አጥር ጊቢ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ። መንግሥት የአልባሳትና የምግብ አቅርቦት ባለማድረጉም ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ወ/ሮ ኛዳክ ተናግረዋል።
በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን የላሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋርዊች ቢየል በስልክ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ሱዳንንና ኢትዮጵያን የሚያዋስነው ጂካዎ ወንዝ ሞልቶ በተፈጠረው ችግር ከ18ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ የሚኖሩትም በትምህርት ቤቶች እንደሆነ አረጋግጠዋል። እንስሳት እንደሞቱና የግጦሽ ሜዳዎችም በጎርፍ በመሸፈናቸው እንስሳቱም ለከፋ ረሀብ መጋለጣቸውን ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል።
አደጋው ከጳጉሜ ጀምሮ የተከሰተ ሲሆን ከክልል ዕርዳታ እንዲቀርብ ሪፖርት ቢደረግም ጉዳቱን መጥቶ ከመመልከት ውጪ እስካሁን ምንም ዕርዳታ እንዳልተገኘ ገልፀዋል።
የጋምቤላ ክልል አደጋ መከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ አቶ ሰይፉ ወልዴ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የአካባቢው ሰዎች አኗኗር ለእንደዚህ ዓይነት አደጋ እንደሚያጋልጥ አመልክተዋል። በመሆኑም ሰሞኑን በአካባቢው የጎርፍ መጥለቅለቅ መድረሱን አመልክተው የተጠቀሰው የርዳታ ፈላጊ ቁጥር ግን የተጋነነ እንደሆነ አመልክተዋል።
ሆኖም ዕርዳታ ወደ አካባቢው ለመላክ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል። በዘንድሮው ክረምት በተለያዩ አካባቢዎች የጣለው ከባድ ዝናብ በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጎርፍና ናዳ በመፍጠሩ በርካቶች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል።
በአፋርና በፎገራም እንዲሁ የደረሰው ከፍተኛ ጎርፍ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል። ከየአካባቢዎቹ የሚወጡት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ነዋሪዎች የድረሱልን ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛሉ።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply