
ወቅቱ ረመዳን ነው፡፡ እነሆ ለረመዳን የሚሆን (አንድ ወግ) ልጋብዛችሁ፡፡
ኸሊፋው ዑመር ኢብን አል-ኸጣብ ዘወትር እንደሚያደርገው የነዋሪዎቹን ሁኔታ ለመታዘብ በምሽት በመዲና ጎዳዎች ላይ ይንጎራደድ ነበር፡፡ ወደ አንድ ሰፈር ሲደርስ በስካር መንፈስ የሚለፈልፍ ሰው ድምጽ ሰማ፡፡ ወደ ቤቱ ተጠግቶ በመስኮት ቢያይ ሰውዬው የወይን ጠጅ እየጠጣ ዓለሙን ሲቀጭ አገኘው፡፡ ዑመር አላስቻለውም፡፡ በመስኮት ዘሎ ገባና ሰውዬውን “አንተ ምን መስራትህ ነው?… ከሰው ብትደበቅ ከአላህ መሰወር የምትችል መሰለህ?… ወይን ጠጅ ለምንድነው የምትጠጣው?” በማለት ተቆጣው፡፡
ሰውዬው እንግዳውን ትክ ብሎ ቢያይ ዑመር ነው፡፡ በጣም ደነገጠ፡፡ ስካሩ በአንድ ጊዜ ለቀቀው፡፡ ከትንሽ ቆይታ በኋላ ተረጋጋና ዑመርን እንዲህ አለው፡፡
“ኸሊፋው ልክ ነዎት! ወይን ጠጅ መጠጣቴ ሐጢአት ነው፡፡ ይሁንና እኔ አንድ ጥፋት ብቻ ነው የሰራሁት፡፡ እርስዎ ግን በዚህች ቅጽበት ሶስት ጥፋቶችን ሰርተዋል”፡፡
ዑመር ሰውዬውን እየተመለከተ “ጥፋቶቼ ምን ምን ናቸው?” አለው፡፡
ሰውዬውም እንዲህ ዘረዘረለት፡፡ “አንደኛ አላህ የሌሎችን ነውር አትከታተሉ ብሏል፡፡ እርስዎ ግን ይህንን ቃል ጥሰው እኔ በድብቅ የምሰራውን አይተዋል፡፡ ሁለተኛ አላህ ወደ ሌሎች ሰዎች ቤት ስትገቡ የባለቤቶቹን ፈቃድ ጠይቁ ብሏል፡፡ እርስዎ ግን ያለኔ ፈቃድ ነው ወደ ቤቴ የገቡት፡፡ ሶስተኛ አላህ ወደቤት ስትገቡ በበር ግቡ ነው ያለው፡፡ እርስዎ ግን በመስኮት ነው የገቡት”፡፡
ዑመር ጥፋቱን አንድ በአንድ አመነ፡፡ እናም “ለጥፋቴ ማበሻ ምን ይሻላል ትላለህ ታዲያ?” በማለት ጠየቀው፡፡
ሰውዬውም “ለሁለታችንም ጥፋቶች ማበሻ የሚሆን መድኒት አላህ ተናግሯል፡፡ ይኸውም የጓዶቻችሁን ነውር ደብቁ የሚለው ነው፡፡ እኔም እርስዎ የሰሩትን ጥፋት ለማንም አልናገርም፡፡ እርስዎም የኔን ስካር ለማንም አይንገሩብኝ፡፡ ከአሁን ወዲያ ላልጠጣ በአላህ ስም ቃሌን እሰጣለሁ” አላቸው፡፡
ዑመር በሰካራሙ ሰውዬ ብልሃት በጣም ተንደቆ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ሰውዬው ሞቶ ይህንን ታሪክ ለተከታዮቹ ከማጫወቱ በፊት ለማንም ተናግሮት አያውቅም፡፡
የሰውን ነውር በመከታተል ሱስ የተለከፋችሁ ሰዎች ሆይ! እባካችሁ ተመከሩ፡፡ የሌላውን ነውር እከታተላሁ ብላችሁ ለራሳችሁ ኩንታል ሙሉ ሐጢአት እንዳትፈጽሙ፡፡
የሰውን ነውር ያያችሁ ሰዎች ሆይ! የጓዶቻችሁን ነውር አታውሩ! የባልንጀራችሁን ነውር ከደበቃችሁለት አላህ እናንተንም ከመጥፎው ሁሉ ይሰውራችኋል፡፡
—–
አፈንዲ ሙተቂ
ሰኔ 21/2005
ሀረር- ምስራቅ ኢትዮጵያ
አፈንዲ ምን አይነት ፍልስፍና ለታስተምር እንደሆነ አልገባኝም ፣ ወሸታሙን ቀጣፊ ባለማለታችን ፣ባንዳውን አገሩን ለጥቅም የሸጠውን
ባለማጋለጣችን ፣ ከጣሊያንና አሁን ደግሞ በእኛ እደሜ ያየነው ከሰማሌ ጋር በመሆን አገሩን የወጋውን ባለማሳወቃችን ህዝብ እንዲያቀው በለማደረጋችን ፣ይህው አሁን አገራችን የባንዶች መጫወቻ ሆናለች ።ማለት ያለብን በውሸት ሥም አለማጥፋት ፣የሰራን ማመስገን፣እህ ምንተባለ ብሎ ጠይቆ ያለተረጋገጠ ወሬ መንዛት፣መጥፎ መሆን መስበክ እንጂ እንዴት ነውር ይደበቅ በለህ ምሳሌ ታቀርባለህ? የህው እነታምራት
ላይኔ የሰሩት ተረስቶ የጨበጨብላቸዋል ፣እነ ሰዬ? ! አንዳርጋቸውም የሄው በኤርትራ እርዳታ ነፃ ያወጣናል ብሎ አዳሜ ቴያትር የሰራል! ይህ ሁሉ ነውረኛን በመደበቃችን ነው ።
“ረጅም እድሜ!
Mesfene I agree the lesson from the story is for people who are close to you or someone you know not to embarrass them in public basically don’t go around and be fault finder .but for the people you mentioned above of course we have to use all our means to fight them dictators and those who support them will never give you your rights .you have to take it. tnx by the way afendy good story I didn’t mean any harm
Mr Afendy if you have another please.
እነደው ለመሆኑ ይሄን ታሪክ ከየት ይሆን ያገኙት ውድ ጸሃፊዬ? ነው ወይስ እስላም እንዲህ የሚራራ ነው ብለው ሊሉን ፈልገው ይሆን? ለመሆኑ በእስልምና መጠጥ፡ መጠጣት ከ8-14 ድረስ የሚሆን ግርፋት እንደሚያመጣ ሃዲቱ የተለያዩ ኡለማዎች እንደሚናገሩ ረስተውት ይሆን? ለማንኛውም እስላም ምን እንደሆነ የኢራቁ እስላማዊ እስቴት (ISIL) በተግባር እያሳየን ስለሆነ የእርሶ እስልምና እንደው የጥጥ ከረሜላውን አይነት መሰለ። ነው ወይንስ ከሰሞኑ በሊባኖስ እና በተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ያሉ አረብ አገራት በሮመዳን ጾም ጊዜ ምግብ ሲበሉ እንዳይታዩ (እስላም ያልሆኑትን) እንደውም ( Saudi warns non-Muslims on Ramadan fasting /http://www.upi.com/Business_News/Security-Industry/2005/10/01/Saudi-warns-non-Muslims-on-Ramadan-fasting/UPI-67841128194966/?rel=78121373377801) እንደው ቀልዶትን ቢያቆሙ ብዬ ነው