የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ቴድሮስ በቀለ እና ባለቤታቸው ሩት አድማሱን ጨምሮ በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ።
ተከሳሶቹ:—
1ኛ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ቴድሮስ በቀለ፣
2ኛ ተከሳሽ የአቶ ቴድሮስ ባለቤት ሩት አድማሱ፣
3ኛ የወ/ሮ ሩት እህት ቤተልሔም አድማሱ እና በግል ሥራ ይተዳደራሉ የተባሉት መርሐዊ መርሃዊ ምክረ ወልደፃዲቅ ፣ ራሄል ብርሃኑ፣ ፀሐይ ደሜ እና ጌታቸው ደምሴ ናቸው።
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ሁለት ክሶችን የመሰረተ ሲሆን፥ አንደኛው በቴድሮስ በቀለ ላይ ብቻ የቀረበ ክስ ነው፡፡
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በተመሰረተው 2ኛ ክስ ከ1ኛ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ተከሳሶች ላይ በዝርዝር ቀርቧል።
በ1ኛው ክስ አቶ ቴድሮስ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ የተቋሙን አሠራር ባልተከተለ መልኩ አስፈላጊው የደኅንነት ይለፍ ያልተደረገለትን የትምህርት ዝግጅቱ ብቁ ያልሆነና በሌላ የሙስና ወንጀል መዝገብ የተከሰሰ አቤል ጌታቸው የተባለ ግለሰብን ከታኅሣሥ 1ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተቋሙ የተደራጁና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀሎች ፍተሻና ትንተና ከፍተኛ ኤክስፐርት ሆኖ እንዲሠራ ወደ ተቋሙ እንዲቀላቀል አድርገዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ ዘርዝሯል።
በዚህም የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1) (ሀ) እና (3) ላይ የተመለከተውን ተላልፈዋል በሚል ነው ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተው፡፡
እንዲሁም ከሰኔ 1ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ አቤል ጌታቸው የተባለን ግለሰብ የፋይናንስ መረጃ ክትትል እና ቅበላ ቡድን መሪ አድርገው ባልተገባ መንገድ መመደባቸው በክሱ ተመልክቷል፡፡
የተቋሙን የቀደመ የመረጃ ምስጢራዊነት የጠበቀ እና ተጠያቂነትን ያማከለ የመረጃ ቅበላ እና ትንተና አሠራርን በመለወጥ፣ በተቋሙ ውስጥ ስልጣንን ተገን በማድረግ፣ የባለሀብቶችንና የድርጅቶችን የባንክ ሂሳብ አስቀድሞ በማጥናትና መረጃ በመውሰድ፣ በተለያየ ጊዜ ለባለሀብቶች ስልክ በመደወል በአካል በማግኘት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲከፍሉ በመጠየቅ፣ የማይከፍሉ ከሆነ ደግሞ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸውን በተመለከተ ምርመራ አድርጎ ለፖሊስ በማስተላለፍ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመርባቸው እንዲደረግ ይገልፅ እንደነበረ በክሱ ተጠቅሷል።
ተከሳሹ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ውስጥ የነበረውን ኃላፊነት በመጠቀም፣ የፋይናንስ ትንተና በመሥራት ውጤቱን ለፍትሕ አካላት የሚተላለፍ ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም፣ ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶችን አስቀድሞ በማጥናት በመምረጥ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም በተለያየ ጊዜ ባለሀብቶች የባንክ ሒሳባቸው እንደሚታገድ እና በፖሊስ እንደሚመረመሩ እንደሚደረጉ በመግለጽ በማስፈራራት ከሦስት ግለሰቦች 3 ሚሊየን 470 ሺህ ብር ገንዘብ በፋፋ ዳባ በተባለ ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢ እንዲደረግ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ስልጣንን አላአግባብ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
በሁሉም ተከሳሾች በቀረበው ሁለተኛ ክስ ደግሞ፥ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አድርጎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 (1) (ሀ) (ለ) እና (ሐ) ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ተከሰዋል፡፡
ተከሳሾቹ በወንጀል የተገኘ 3 ሚሊየን 470 ሺህ ብር የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቁ የገንዘቡን ምንጭ ለመደበቅ በማሰብ ግብረአበር ነው የተባለ ፋፋ ዳባ እየተባለ የሚጠራ ግለሰብ ስም በባንክ በተከፈተ ሒሳብ ገቢ እንዲደረግ በማድረግና ከገንዘቡ በተለያየ መጠን በመጠቀም ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቆረብ ወንጀል ተከሰዋል።
ተከሳሾቹ ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ በችሎት ክሱ በንባብ ተሰምቷል።
ቀደም ሲል ለአንድ ወር ከቴድሮስ በቀለ ጋር በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ ሲደረግባቸው የቆዩት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የመረጃ ኦፕሬሽን ዲቪዢን ኃላፊ ባሕሩ ደምሴን በሚመለከት÷ ዐቃቤ ሕግ ምርመራቸው አለመጠናቀቁን ተከትሎ በዚህ ክስ ላይ አለማካተቱን ረፋድ ላይ የምርመራ መዝገባቸውን ሲመለከት ለነበረው ለጊዜ ቀጠሮ ችሎት አስታውቋል። (ታሪክ አዱኛ Fana)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply