75% ሆስፒታሎች ሥራ ጀምረዋል
የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ማዕከል ዘርፈ ብዙ ምላሽ ሰጪ ብሔራዊ ኮሚቴ ሳምንታዊ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡
ኮሚቴው በስብሰባው በትግራይ ክልል የአባል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን የአስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲሁም የመልሶ ማቋቋም ስራዎች አፈፃፀምን ገምግሟል፡፡
በክልሉ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ዝግጅት መጠናቀቁ እና ትምህርት ቤቶቹን ስራ ለማስጀመርም ከመምህራን እና ወላጆች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ትምህርት ቤቶቹ በቅርቡ ስራ እንዲጀምሩ የተወሰነ መሆኑ እና ይህን ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁስ መሰራጨታቸውም ተመልክቷል፡፡
በክልሉ ከሚገኙ ሆስፒታሎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ እንዲሁም 10 በመቶ የሚሆኑት በከፊል ስራ መጀመራቸው ተጠቅሷል፡፡
ለአብነትም ባለፉት 2 ሳምንታት 1,583 እናቶች በነዚሁ ተቋማት አገልግሎት ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም 967 ተኝቶ ታካሚዎች እና 44 ሺህ ተመላላሽ ታካሚዎች መስተናገዳቸው ተጠቅሷል፡፡
በክልሉ ከሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በስራ ገበታ ላይ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
30 ተንቀሳቃሽ የሕክምና ቡድኖች በክልሉ እየተዘዋወሩ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ምግብ እየተሰራጨ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን የሴፍቲኔት ተጠቃሚ ላልሆኑ ተረጂዎችም ይኸው እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
በውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎ ት ላይ የተሰማሩ 13 ተቋማት 162 ቦቴ መኪኖችን መድበው በውሃ አቅርቦት ላይ በቅንጅት እየሰሩ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
አብዛኛው የክልሉ መደበኛ ፖሊስ የስራ ኃላፊዎች እና አባላት በስራ ላይ መሆናቸው እና ፖሊስ ጣቢያዎችም አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተገልጿል፡፡
በመቀሌም ፍርድ ቤት ስራ መጀመሩ ተመልክቷል፡፡
በስብሰባው ማጠቃለያ ኮሚቴው ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ (ኢቢሲ)
ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply