
የወገን ጦር በወሰደው የማጥቃት ርምጃ ፍላቂትን ከአሸባሪው ትህነግ ቡድን አስለቀቀ
የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ላይ በጥመረት በወሰዱት እርምጃ ፍላቂትን አስለቅቀዋል።
የወገን ጦር የማጥቃት እርምጃውን አጠናክሮ በመቀጠል ወደፊት እየገሰገሰ መሆኑ ተገልጿል።
በአሁኑ ሰዓትም በደብረዘቢጥ እና አካባቢው የቀረው የአሸባሪ ርዝራዥ ቡድን ሙሉ በመሉ ተለቅሞ የአካባቢው ነዋሪዎች መደበኛ ሥራቸውን ቀጥለዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል።
በደባርቅ አካባቢ በብና ሜዳ ሾልኮ ለመግባት የሞከረው የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂ ቡድን ተደመሰሰ
በደባርቅ አካባቢ በብና ሜዳ ሾልኮ ለመግባት የሞከረው የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂ ቡድን በዛሬው ዕለት ተደምስሷል።
ታጣቂ ቡድኑ በዝንጀሮ አፋፍ፣ ወርቅ አዝላ እና በቅሎ ማነቂያ ሾልኮ ለመግባት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም በርካታ አባላቱ መደምሰሳቸውን አውደ ውጊያውን የመሩት የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ገልጸዋል።
የሽብር ቡድኑ በመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያ፣ በኦሮሚያ ሚሊሺያ እንዲሁም በፋኖ አከርካሪው መመታቱ ነው የተገለጸው።
አሸባሪ ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ በመደምሰስ ከወረራቸው የሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ጠራርጎ ለማጥፋት በመከላከያ ሠራዊቱ እና በሌሎች የፀጥታ ኃይሎች የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑንም አመራሮቹ ተናግረዋል።
በዛሬው ውጊያ በርካቶቹ የአሸባሪ ቡድኑ አባላት ከመደምሰሳቸው ባሻገር በርካታ የጦር መሳሪያ እና የቡድኑ ታጣቂዎችም ተማርከዋል።
ሰቆጣ ከአሸባሪው የህወሓት ታጣቂዎች ነፃ ወጣች
ሰቆጣ በአማራ ልዩ ኃይል ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ነፃ መውጣቷን የክልሉ የሰላምና የሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰማ ጥሩነህ አስታወቁ።
በደቡብ ወሎ ዞን የወጣቶች የክተት መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ኃላፊው ቀጣይ አዲስ ዓመትን የምንቀበለው የሕዝብ እና የሀገር ጠላትን በመቅበር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሐይቅ ከተማ ለመግባት ቋምጦ የመጣው የአሸባሪው ኃይልም ሙት እና ቁስለኛ ሆኖ ተመልሷል ብለዋል።
በሌሎች አካባቢዎችም የወገን ጦር ቁልፍ ወታደራዊ ስትራቴጂክ ቦታዎችን ስለያዘ የሸብር ቡድኑን በገባበት ሁሉ መቀበሪያው እያደረገው እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል።
በቀጣይም ጠንካራ የመከላከያ ኃይል ለመገንባት ወጣቱ መከላከያን እና ልዩ ኃይልን ሊቀላቀሉ ይገባል ብለዋል ዶ/ር ሰማ ጥሩነህ።
የልዩ ኃይሉን አደረጃጀት ለማጠናከር ልዩ ትኩረት በመስጠትም የአማራ ክልል መንግሥት የማሰልጠኛ ካምፖችን በማዘጋጀት የወጣቶችን መግባት እየተጠባበቀ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፣ የሰቆጣ ወጣቶች እና መላው የዋግ ጀግኖች ለከፈሉት መሥዋዕትነት ታላቅ የክብር ምስጋናቸውን አቀርበዋል።
በሰሜን ወሎ የገባው አሸባሪው ህወሓት በመከላከያ ሰራዊት እርምጃ ተወሰደበት
በሰሜን ወሎ በኩል ሰርጎ የገባው ወራሪው የህወሓት አሸባሪ ሃይል በጀግናው መከላከያ ሰራዊት አፀፋዊ እርምጃ ተወሰደበት።
በዚህ ስምሪት 142 የሽብር ቡድኑ ታጣቂ ሃይል ሲደመሰስ 4 ስናይፕር፣ 6 የሞርተር ቅንቡላ፣ 1 ብሬን፣ 18 የእጅ ቦምብ፣ 15 ክላሽ፣ 7 ሺህ የብሬን ጥይት፣ 5 ሺህ የክላሽ ጥይት፣ 1 የመገናኛ ሬዲዬ (1187 አይኮም)፣ 1 የዋይፋይ ሪሲቨር፣ 6 የብሬን ሻንጣና 10 የነፍስ ወከፍ ወታደራዊ የወገብ ሻንጣ ከጠላት ሃይል ተማርኳል።
ከግንባሩ አመራሮች መካከል የክ/ጦር ም/አዛዥ ለኦፕሬሽናል እንደተናገሩት፣ ጠላት አሁን ላይ በሰራዊታችን እየደረሰበት ባለው ኪሳራና ባጋጠመው ሽንፈት የተስፋ መቁረጥ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርግም ከገባበት መግደያ ወረዳ መውጣት እንደማይቻለው ገልፀዋል።
ወራሪውን ሃይል በገባበት አስቀርተን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህዝባችን የድል ዜና እናሰማለንም ብለዋል።
በግዳጅ ቀጣናው የብርጌድ ዋና አዛዥ በበኩላቸው በጭፍን ሃገራዊ ጥላቻ ተነሳስቶ የማይሞከረውን መከላከያ ሰራዊት በመፃረር ህዝብን የተዳፈረው አሸባሪ የህወሓት ቡድን በፈፀመው ስህተት የእጁን እያገኘ ነው ብለዋል።
ሰራዊታችን በተሰለፈበት የወሎ ግንባር በሰርጎ ገቡ ሽብርተኛ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለው አሁናዊ እርምጃና በጠላት በኩል የተመለከትነው መፍረክረክ የፍፃሜውን መቃረብ የሚያመላክት ነው ያሉት ደግሞ በግንባሩ የብርጌድ ም/አዛዥ ለኦፕሬሽናል ናቸው።
ምንጭ፡- መከላከያ ሰራዊት
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply