ከለውጥ ወዲህ መላው የኢትዮጵያ ክፍል ሲታመስ ሰላሙ ተጠብቆ የነበረው በትግራይ ነበር። በአገሪቷ ውስጥ እየተከሰተ ያለው የሰላም መታጣት ያሳሰባቸው እናቶች ወደ ተለያዩ ክልሎች ሄደው ስለ ሰላም ሲማጸኑ ቆይተው ትግራይ ሲደርሱ የተነገራቸው እነርሱንም ያስደመመ ነበር። በወቅቱ ከታቦት እኩል ለአምልኮ የደረሰው ደብረጽዮን የመለሰላቸው በትግራይ ሰላም ነው፤ ሰው ወጥቶ ይገባል፤ ሰላም የታጣው በሌላ ክልል ነው፤ እዚያ ሄዳችሁ ብታለቅሱ ይሻላል ነበር ያላቸው። ሌላው የአገሪቱ ክልል ቀውስ ውስጥ መግባት ዋናው መሪ እና ግጭት ቀማሚ ህወሓት መሆኑን የካደ ግብዝነት የተሞላበት ምላሽ ነበር።
እጅግ ከፍተኛ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ያለችው ትግራይ እስካሁን ድምጽ ሳይሰማባት ቆይቶ ዛሬ በተቃውሞ ስትናወጥ ውላለች። በጦርነቱ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በመለስ ዜናዊ አነጋገር “ቁሻሻ” የሚባሉት ዛሬ የምንበላው አጣን ብለው መቀሌ ሰልፍ ወጥተዋል።
የትግራይ ፖለቲካ አንጻራዊ መረጋጋት ያሳያል ተብሎ በተገመተበት ወቅት የዛሬው ትዕይንት ተጠባቂ አይደለም። ሰሞኑን ትህነግ ምርጫ አካሂዶ ጌታቸው ረዳ በድምጽ ብልጫ ማለፉ ይታወቃል። በቀጣይም የክልሉ የሽግግር ጊዜ ርዕሰ መስተዳድር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ለዘመናት በዓድዋ ያውም በአንድ ቤተሰብ ተይዞ የነበረው በዚህ መልኩ ማፈትለኩ የራያውን ጌታቸው ሹመት “በአማራ አንመራም” እንዲሉት አድርጓቸዋል። የዛሬውም ሰልፍ ይህንኑ ተከትሎ የጌታቸውን ሥልጣን ቀውስ ውስጥ ለመክተት የታሰበ ነው ተብሎ ይነገራል።
ዛሬ ከመቀሌ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው መለስ ካምፓስ የጦር ጉዳተኞች ማዕከል ተሰባስበው በመነሳት እስከ የትግራይ ክልል አስተዳደር መሥርያ ቤት የተለያዩ መፈክሮች እያሰሙ የተጓዙት እነዚህ የጦር ጉዳተኞች፥ ደረሰብን ያሉዋቸውን የአስተዳደር ችግሮች «ሕዝብ ይስማልን፣ ይወቅልን» ብለዋል ። «በኛ ስም ከሕዝብ የሚሰበሰብ መዋጮ እኛጋ እየደረሰ አይደለም»፣ «በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አጥተናል» የሚሉት እነዚህ በአብዛኛው ወጣት የጦር ጉዳተኞች፥ «በቂ ምግብና ውኃ እንኳን አጥተን የከፋ ሁኔታ ላይ ነን» ሲሉ ገልፀዋል።
«የታጋዮች ድምፅ ይሰማ»፣ «ትኩረት ለጦር ጉዳተኞች»፣ «ተክደናል» የሚሉና ሌሎች ብልሹ አሠራሮች የሚያወግዙ መፈክሮች የጦር ጉዳተኞቹ ያሰሙ ነበር።
ሰልፈኞቹ «ድምፃችንን ለማሰማት ወደ ከተማ እንዳንገባ መቐለ ዩኒቨርስቲ አሪድ ካምፓስ አካባቢ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ጭምር እንድንበተን ሙከራ ተደርጓል» ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።
ከፍተኛ የቁጣ ስሜት ይታይበት የነበረው የጦር ጉዳተኞቹ ሰልፍ በሃይማኖት አባቶች ሸምጋይነት እንዲረጋጋ ተደርጓል። ሰልፈኞቹ የክልሉ አስተዳደር መሥርያ ቤት በሆነው ደጀን ቢሮ በር በነበራቸው ቆይታ የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ከሌሎች ወታደራዊ መሪዎች ጋር በችግሮቻቸው ዙሪያ ተወያይተዋል።
ሰልፈኞቹ ወራት ካለፈ በኋላ ዛሬ ጉዳታቸው ለምን እንደተሰማቸው ግልጽ ባይሆን የተቀናጀ የፖለቲካ ሤራ ይኖርበታል የሚል አስተያየት ይሰጣል። ከፌደራል መንግሥት የሚፈለጉት ነገሮ እየቀረቡና አንጻራዊ የኑሮ መረጋጋት በሚይታይበት ወቅት አካል ጉዳተኞቹ «ተክደናል» ብለው መውጣታቸው እስካሁን መከዳታቸውን እንዴት አላወቁም የሚል ጥያቄ ያስነሳ ሆኗል። ምክንያቱም አንድ ሚሊዮን የትግራይ ሰው በጦርነቱ መሞቱ በተለያዩ መንገዶች ሲገለጽ የሰነበተ ጉዳይ ነውና።
ከዚህ የአካል ጉዳየኞቹ ሰልፍ ሌላ በተናበበ መልኩ በሚመስል እስካሁን ሥልጣን በቁጥጥሩ ሥር ያደረገው የዓድዋው ቡድን ትናንት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ሕዝብ ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎች ይቆሙ ዘንድ የአፍሪካ ኅብረትና የዓለም ማኅበረሰብ ትርጉም ያለው እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቋል። አሁንም ድረስ የኤርትራ ጦርና ሌሎች ታጣቂዎች በትግራይ ሕዝብ ላይ ወንጀል እየፈጸሙ ነው ያለው ድርጅቱ፣ ይህንን ለማስተካከል የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል ብሏል።
ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያን የጎበኙት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን በሰብዓዊ መብቶች ስብሰባ ላይ ይህንኑ የህወሓት/ትህነግን ዓይነት ንግግር አድርገዋል። “ምንም ዓይነት የውጪ ሠራዊት በኢትዮጵያ የለም” ብለው የተናገሩ ብሊንከን ከትህነግ መግለጫ የተወሰደ የሚመስል ንግግር ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢቃወምም ሰውየውን ለዚህ መሰል የፖለቲካ አክሮባት ያበቃቸው ጉዳይ ሰሞኑን በአላማጣ ከተደረገውና የራያንና የወልቃይትን ጉዳይ ዕልባት ከተጠየቀው ትዕይንተ ሕዝብ ጋር ቁርኝት እንዳለው ይነገራል።
ብሊንከን በትዊተር መልዕክታቸው የጦር ወንጀል ተፈጽሟል ብለው ዛሬ የጻፉት መልዕክት በአብዛኛው ኢትዮጵያን በጎበኙብት ወቅት ከተናገሩት የተለየ ባይሆንም የቆየውን ነገር አሁን የተከሰተ አስመስለው የጻፉበት ሥልት ግን ማንን ለማስደሰት ያለመ እንደሆነ ከጽሁፋቸው መረዳት ይቻላል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን (ህወሓት) ከአሸባሪነት ለመሰረዝ ነገ ረቡዕ መጋቢት 13፤ 2015 “ልዩ ጉባኤ” ሊያካሄድ መሆኑን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገለጹ። ሰባት የፓርላማ አባላት፤ ለነገው ልዩ ጉባኤ “ማንም አባል እንዳይቀር” ከሚል ማሳሰቢያ ጋር ጥሪ እንደተደረገላቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
እነዚሁ የምክር ቤት አባላት በነገው ዕለት “ልዩ ጉባኤ” እንደሚካሄድ ቢያረጋግጡም፤ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር እንደሚደረገው የስብሰባው አጀንዳ አስቀድሞ እንዳልተላከላቸው አስታውቀዋል። የፓርላማ አባላቱ ይህን ቢሉም፣ የተወካዮች ምክር ቤት የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ግን በነገው ስብሰባ ህወሓትን ከሽብርተኝነት የሚሰረዝ የውሳኔ ሃሳብ ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
የጌታቸው መመረጥ ይፋ ከሆነ ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያ ኢትዮጵያን የሚያናውጥ እና ዕረፍት የሚነሳ ሰበር ዜና በእጅጉ የቀነሰ ሲሆን ምንም የማይሰማባት ትግራይ ግን የማኅበራዊ ሚዲያ ትኩዳት እየሆነች መጥታለች። ከዚህ በፊት በትግራይ ፖለቲካ ብዙ ሲሉ የነበሩና በቅርቡ ግን ከሚዲያው ጠፍተዋል ወይም ሞተዋል ሲባሉ ከነበሩትም የዓድዋው ቡድን ደጋፊዎች ጥቂቶቹ ብቅ ማለት ጀምረዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply