ከ27 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትር የስብሰባ አዳራሽ የተገኙት ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፤ ዶ/ር ዐቢይ የዕለቱን የመወያያ አጀንዳ ከገለጹ በኋላ እና የስብሰባው ተሳታፊዎች አሳባቸው እየገለፁ ባሉበት ወቅት ነው፤ የኔታ ወደ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የገቡት። ዶ/ር ዐቢይን ጨምሮ በአዳራሽ ውስጥ የነበሩ ተሰብሳቢዎች የኔታ የመቀመጫ ወንበራቸውን እስኪይዙ ድረስ የተሰብሳቢው ዓይን በፍቅርና በአክብሮት እሳቸው ላይ ነበር ያረፈው።
የተጀመረው ውይይት በተሰብሳቢዎች በሚነሱ ጥያቄዎችና አስተያየት ቀጥሎ ለሻይ ዕረፍት ስብሰባው ተቋረጠ። ሁላችንም ሻይ እና ቡና ወደተዘጋጀበት ቦታ አመራን፤ ዶ/ር ዐቢይ ለሻይ በወጣንበት ወቅት የቱ ጋር እንዳሉ እኔ ልብ አላልኩም፤ ይልቁንም ለየኔታ ትኩስ ነገር ምን ላምጣሎት ብዬ ስጠይቃቸው፤ “አንድ ሲኒ ቡና ትንሽ ስኳር ጨምረ አመጣልኝ፣ ከዚያ በፊት ግን የምቀመጥበት ወንበር አሉኝ” በዚህን ጊዜ አጠገቤ የነበረው አበበ አካሉ ፈጥኖ ቡና ሊያመጣ ሄደ፣ እኔም የመቀመጫ ወንበር አምጥቼ እንዲቀመጡ አደረግን …።
በዚህ መሐል ድንገት ወደኋላ በምዞርበት ወቅት ዶ/ር ዐቢይ ቀይ መለዮ ከለበሱ ጠባቂ ወታደሮች እንዲሁም የጠቅላይ ሚ/ሩ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ ጋር በመሆን አንድ ላይ ሆኖው እኛ ወዳለንበት አቅጣጫ እየመጡ እንደሆነ አየኹኝ፤ ሁኔታው ግልጽ ነበር ዶ/ር ዐቢይ የኔታን ለማግኘት ነው ወደኛ የመጡት፤ ቀይ መለዮ ለባሽ ጠባቂዎች እኛ የነበርንበት ቦታ ክብ ሰርተው በቅርብ እርቀት በተጠንቀቅ ቆሙ…።
ወዲያውኑ አጠገባችን የደረሱት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ እጅግ ትህትናና ፍቅር በተሞላበት ሁኔታ በጣም ዝቅ ብለው እሳቸው (የኔታ) ከተቀመጡበት እጁን ዘርግቶ ሰላምታ ሰጧቸው፤ በዚህን ወቅት የኔታ ቁጭ ብዬ ሰላምታን አልቀበልም በማለት ከወንበራቸው ለመነሳት ሲሞክሩ፤ ዶ/ር ዐቢይ ደግሞ “ፕሮፍ በፍጹም አይገባም” እያሉ ሲከላከሏቸው የነበረው የሰኮንድ ጊዜ ትእይንት፤ የአባትና የልጅ ፍቅርና አክብሮት በአካባቢው ለነበረና ለሚመለከት ሁሉ ልዩ ሰሜት የሚሰጥ ነበር….።
ዶ/ር አብይ “ፕሮፍ እንዴት ኖት?” በማለት በሚገርም ትህትና ሰላምታ እያቀረቡ፤ ድንገት ዞር ብሎ ስሙን አሁን የረሳውት አንድ ሰው በመጥራት “ፕ/ር በየነን ጥራቸው” በማለት ፈገግታ በተሞላበት መልኩ ለመልክተኛው ነገሩት፤ አንደኛው ጠባቂ ሌላ ሁለት ወንበር ይዞ መጣ፣ ዶ/ር ዐቢይ ከየኔታ ጋር አጠገብ ተቀመጠ። ብዙም ሳይቆይ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ አብረው አንድ ላይ ተቀመጡ፤ የሻይ ቡና ሰዓት አጭር ቢሆንም ጠቃሚ ነገር አንስተው አንድ ሁለት አሳብ ተለዋውጠዋል። ንግግራቸው በፈገግታ የታጀበ ነበር።
የጠቅላይ ሚ/ሩ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በአካባቢው የነበረውን ክስተት በምስል ለመያዝ የሞባይል ስልካቸውን በእጃቸዉ ይዘው አካባቢያቸውን በትኩረት ይቃኛሉ፤ ከእኔም ጋር አጭር ቆይታ ነበራቸው። ከንግግራቸውና ከሁኔታቸው እንደተረዳሁት እሳቸውም ከትህትናው በተጨማሪ ሌላውን ለማዳመጥ ያላቸው ፍላጎት ደስ የሚል ነው።
የሻይ ቡና ክፍለ ጊዜ ከተጠናቀ በኋላ ሁላችንም ወደ ስብሰባ አዳራሽ ገባን….፤ ከሻይ ቡና የእረፍት ጊዜ በኋላ የመጀመሪያ ተናጋሪ የነበሩት የኔታ ነበሩ፤ ፕ/ር መስፍን ንግግራቸውን እንዲህ ሲሉ ጀመሩ “የምፈለግ ሰው አይደለሁም በብዙ ቦታ፣ ዛሬ ተፈልጌ መምጣቴ ኢትዮጵያ ምን ያህል እንደተለወጠች የሚያሣይ ነው።” በማለት ለተደረገላችው ጥሪ አስተያየታቸውን ከገለጹ በኋላ ወደ ዋና መልክታቸው ገቡ።
እንዲህ ሲሉ ቀጠሉ “… ዛሬ እዚህ ደርሰናል፣ ኢትዮጵያም እዚህ ደርሣለች፤ ጥያቄው ሁላችን የምንከበርባት፣ በልተን የምናድርባት፣ ኮርተን ኢትዮጵያዊ ነን የምንልባት አገር እንዴት እናድርጋት በማለት ለራሳችን መጠየቅ አለብን፤ ስግብግብነት ከውስጣችን በማውጣት የሚጠቅመን ነገር እሁን የምናደርገው እኛ ነን። …. ስግብግብነት ከመጥፎ ድህነት ወይም ከመጥፎ ጠባይ ይመጣል፤ ጥጋብ ይበልጣል ኩራት?! ጦም ማደርም ወራዳ መሆንም ጥሩ አይደለም፣ ግን የቱ ይሻላል?!” በማለት ጥያቄ ጠይቀዋል።
ዶ/ር ዐቢይን ጨምሮ ሁሉም ተሰብሳቢ በልዩ ትኩረት የየኔታ ንግግር በአጽንዖት መከተተላቸው እንደቀጠለ ነው፤ የኔታም ንግግራቸውን እንዲህ በማለት ቀጠሉ … “88 ዓመቴ ነው፣ ከጣሊያን ጊዜ ጀምሮ በዚህ ዘመን ያላየሁትን አይቻለሁ፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይወዳታል፣ ጥሎ አይጥላትም፣ ዐቢይ አሕመድ እና ለማ መገርሳ ፈጣሪ ከሠማይ የጣለልን ይመሥለኛል…” በማለት የኔታ በሚናገሩበት ወቅት በአዳራሹ የነበረ ተሰብሳቢ በአድናቆት እና በድጋፍ ጭብጨባ ለንግግራቸው ምላሽ ሰጠ፤ ዶ/ር ዐቢይም ፊታቸው በፈገግታ ተሞልቶ ከተቀመጡበት አንገታቸውን ከፍ እና ዝቅ እያደረጉ ለጭብጨባው ምላሽ ሰጡ።
የኔታ እንዲህ በማለት ንግግራቸውን ቀጠሉ “የተጀመረው ለውጥ መቀጠል አለበት፤ እነ ዐቢይ የያዙትን አዲስ ዓላማ ለመትከል ሲፈልጉ እንዴት እንርዳቸው? እንዴት እናግዛቸው ማለት አለብን? ትልቁ ጥያቄ ለእኔ ይሄ ነው፤ መመለስ ያለብን ይህንን ነው። … እኔ በቀረቺኝ ዕድሜ ባለኝ አቅም ሁሉ ለኢትዮጵያ ዜጎች (ብሄሮች አይደለም) በሚያደርጉት ልረዳቸው ቃል እገባለሁ።” ብለው ሲናገሩ ከፊተኛው የበለጠ በስብሰባው አዳራሽ ውስጥ የጭብጨባ ድምጽ ከፍ ብሎ ተሰማ፤ የኔታም ንግግራቸውን አጠቃለው ለመሄድ ፍቃድ ጠይቀው ተነስተው ሄዱ። ዶ/ር ዐቢይን ጨምሮ ሌሎቻችን ግን ስብሰባውን ቀጠልን።
በነገራችን ላይ በወቅቱ በነበረን የግማሽ ቀን ስብሰባ ዶ/ር ዐቢይ አጠቃላይ ቢደመር 30 ደቂቃ ያህል ስለመናገራቸው እርግጠኛ አይደለሁም፤ አብዛኛውን ጊዜ በማዳመጥ እና ማስታወሻ በመፃፍ ነው ያሳለፉት።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Eunetu Yeneger says
ዶ/ር አቢይ ወደዚህ ስልጣን እንደመጡ ወዲያውኑ የከበቧቸው ሰዎች እነማናቸው?የሚለው ጥያቄ አስጨንቆኝ ሳለ ወዲያውኑ በሃገር ፍቅር ተወልደው ካደጉ ሰዎች መካከል የፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም እና የዶ/ር ቶሎሳ ጉዲና ስም ትዝ ብሎኝ ለሁለቱም ስልክ ደውዬ እኒህን ጠ/ሚኒስትር ቀረብ ብለው እንዲያማክሯቸውና አይዞህ በርታ እንዲሏቸው ስጠይቃቸው ዶ/ቶሎሳ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ለዚሁ ሥራ እንደሚሄዱና የፕ/ሩን ስልክ እንደሰጣቸው ጠይቀውኝ ስሰጣቸው ፕ/ር ግን በአሁኑ ጊዜ ጠ/ሚሩን ማግኘት የምችልበት እድል የለኝም ሲሉኝ በአቶ ለማ በኩል እንዲሞክሩ ሳስባቸው ደግሞ እኔን በአሁኑ ጊዜ የሚሰማኝ ሳይሆን ልዩ ትርጉም የሚሰጥ ነው ያለውና ውጤት የሚኖረው አይመስለኝም ማለታቸውን ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ ይህ በራሱ በጠ/ሚንስትሩ መጠራታቸውና ይህን የመሰለ ንግግር ማድረጋቸውን ሳነብ አሁንም የምህረት አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ፈውስ ሥራውን እንደጀመረ ማረጋገጫ ሆነኝ!!!
ክብር ለእግዚአብሔር
ለዘላለም ይሁን