ይህ ለውጥ እውን ከሆነ በኋላ ሕዝብን ስሜታዊ የሚያደረጉ ተግባራት ናቸው በቅስቀሳ መልኩ የሚሰራጩት። ሰው ይገደልና ይሰቀላል። ተሰቅሎ ሲወገር ፊልም ይቀረጻል። ወዲያው ለሕዝብ ላይቭ ይለቀቃል።
“እኔ ከእገሌ ብሔር አልተወለድኩም በል” እየተባለ ሰው በማንነቱ ሲገደል የሚያሳይ ፊልም በቅጽበት አየር ላይ እንዲውልና በብርሃን ፍጥነት እንዲሰራጭ ይደረጋል።
ንጹሐን እንዲታገቱ ይደረግና እገታው በሚፈለገው መንገድ ተቀነባብሮ በማኅበራዊ ሚዲያ እንዲጎን ይደረጋል።
ነፍሰጡር ስትሞት፣ ሕጻን እያየ አባት ሲገደል፣ ንብረት ሲቃጠልና ሌሎች በሟችና በሚወድመው ንብረት ሲዛበቱ የሚያሳይ ምስል በተቀናበረ ሁኔታ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ይጦዛል። ይህ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በማራ፣ አፋር … ሆኗል። አሁን ደግሞ መልኩን ቀይሮ እየሆነ ነው። ሲሆን ንጹሐን ላይ የደረሰን ጉዳት ለፖለቲካ ገበያ ለማዋል ታስቦ ሲሆን፣ አንድም ሆነ ተብሎ ጉዳቱ እንዲደርስ ሤራ ይጠነሰሳል፤ ሤራውን ፈጻሚና አስፈጻሚ ይቀጠራሉ። በጀት መዳቢዎቹ ሚዲያዎችንም ያካትታሉ። በግብስብስ በተከፈቱ የቁጭ በሉ ስሞች ድራማው ይረጫል። ሕዝብ በሚያየው ተቃጥሎ ስሜት ውስጥ ይገባል። ስሜት ውስጥ የሚገቡ ማሰብ ያቆማሉ። ማሰብ ባቆሙት አማካይነት የሚፈለገው የወቅቱ አጀንዳ ይፈጸማል።
ዛሬ ቃላት ሳይመረጥ “ቤተመንግሥት ክበብ፣ ቤተመንግሥት ውረር፣ ቤተመንግሥት ገብተህ ንቀል” የሚባለው እምነት ላይ የተንጠለጠለ “የቅዱስ ሲኖዶስ የሰማዕትነት ጥሪ” አዝማቾቹ አባቶቹ ላይ “እንዳትወያዩ፣ እንዳትነጋገሩ” በሚል ጫና እያደረጉ እየቆሰቆሱት ነው።
በስመ ነጻ ሚዲያ የሚደረገው ይህ የዓመጽ ጥሪ ሁሉንም ዓይነት አማራጭ ተከትሎ በኪሣራ ሲቋጭ አስቀድሞ የሞከረው ሙስሊሞችን ነበር። የሙስሊሞች በር ሲዘጋ፣ መቶ ሃያ አምስት ሚሊዮን ሕዝብና በርካታ ዕምነት ባለበት አገር “አንድ እምነት፣ አንድ ቤተክርስቲያን፣ አንድ ጳጳስ፣…” በሚለው ለስምምነት የማይበጅ፣ ለዘመኑ የማይመጥን፣ ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ዘመቻ በታሪካዊቷ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስም ተከፈተ። ይህ ዘመቻ የመጨረሻው ካርድ ባለው ከፍተኛ በጀት እየታገዘ ያገኝውን ሁሉ አዝማች፣ አጋፋሪ፣ አውራጅና ጫኝ፣ ተቆርቋሪና አልቃሽ … አድርጎ “ለጠቅላይ” እንጫወት እያለ ነው።
በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ ካሉት አባቶች አንዳንዶቹ ለቅሰቀሳ በሚጋበዙባቸው ሚዲያዎች “አንወያይም አላልንም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያወያዩን እንፈልጋለን፤ ጥላቻ ኃጢአት ነው። መስዋዕት ፍቅር ከሌለበት ዋጋ የለውም” ሲሉ የሰሙ፣ ሲኖዶሱ በተወሰኑ ክፍሎች ጫና ሥር ስለመውደቁ ማሳያ እንደሆነና አድሮ ሌላ ጣጣ እንደሚያመጣ ይገልጻሉ።
ሌሎች ደግሞ “እጅግ ያከረሩና የመንፈሳዊነት ጠረን የሌላቸው” መኖራቸውን ጠቅሰው ልዩነት መኖሩን ያመልክታሉ። እነዚህ ክፍሎች “አፈንጋጭ” ከሚባሉት ወገን ሆነው ያልተገባ ድርጊት እንዲፈጠር የሚሠሩ መኖራቸውን ያክላሉ። በፖለቲካው አመራር ውስጥም አብረዋቸው ያሉ መስለው ባለተገባ መንገድ ልዩነቱን የሚያከሩ ካድሬዎች ስለመኖራቸው አይጠራጠሩም።
የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ከፍተኛ ግፍ ይፈጸምበት እንደነበረ “ሰው ይሸጥበታል” በሚል ሰሞኑንን የገለጹ፣ ጸቡ የሃብት ቅርምትና የሌብነትም እንደሆነ ሰሞኑን ቃለ ምልልስ ሰጥተው የተናገሩ አሁንም በሥራ ላይ ያሉ ምስክሮች ተሰምተዋል።
አዲስ አበባ አገር ስብከት ገቢው ከፍተኛ በመሆኑ፣ ውዝግብ፣ ሽኩቻ የሚበዛበት ሆኖ መቆየቱን የመሰከሩት እንደሚሉት ከሆነ በሲኖዶስ ውስጥ ከበድ ያለ ገቢ ባለበት አቅጣጫ ለመሰለፍ እጅ መንሻው ለጉድ ነው።
በዚህ ሁሉ የቅድስና ትብትብ ውስጥ ያለችውና የአምልኮ አጸዷ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተቸርችሮ ጸዳሏን በሚገፏት የተከበበችው ቤተክርስቲያን ለዚህ ሁሉ የተዳረገችው በሯን ለመዝጋት የሚያስችል ጽዳት ያላቸው መሪዎች ስለሌሏት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል።
ከውስን ደጋግ አባቶች በስተቀር ጥቅም ላይ የተንጠለጠሉት ወገኖች ራሳቸውን ሳይሆን ቤተክርስቲያንንም ባልተገባ ስፍራ እንድትሆን አድርገዋታል። ነብሳቸውን ይማረውና አለቃ አያሌው “እንኳንም አይኔ አሳወርከኝ። አመስግንሃለሁ” ሲሉ በሕይወት ዘመናቸው ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቤተክርስቲያን ንግሥ ላይ ሲያስተምሩ እያለቀሱ” እኔ በምሰማው ልፈነዳ ደርሻለሁ። እናንተ ከመስማትም አልፎ እያያችሁ እንዴት ቻላችሁት” ሲሉ ስለ መቆሸሽ አስተምረው እንደነበር የሚያስታውሱ፣ ሲኖዶስ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ “ቤተመንግሥት ውረሩ፣ የሰማዕት ሞት ሙቱ” በሚል የስልጣን ጥማት ያሰከራቸው ክፍሎች ለሚያራግቡት እልቂት ጋባዥ ፉከራ ተላቀው ራሳቸው እንዲመለከቱ ይመክራሉ።
መንግሥትም ዕልህ መጋባቱን ትቶ በሆደ ሰፊነት ልቅ የሆኑትን በማረቅ ቤተክርስቲያኒቱ ባላት ደንብና መተዳደሪያ መሠረት ችግሯን እንድትፈታ ሚናውን እንዲጫወት በርካቶች እየጠየቁ ነው። የዓመጽ ጥሪውን ንቆ፣ ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ ባስቸኳይ በመፈለግ ዕልባት እንዲገኝ ሊፈጥን እንደሚገባው የሚያሳስቡ ወገኖች መንግሥት ውስጥ ያለው መዥጎርጎር ሊታረም እንደሚገባው አመልክተዋል።
ይህንን ልዩነትና ወይም አለመግባባት ተንተርሶ “አርቲስት ነን፣ ኮባ ለፍላፊ ነን፣ ማስታወቂያ ሠራተኛ ነን፣ የባንክ ካሸር ነን፣ የዩትዩብ ተከፋይ ነን …” እያሉ ከየሥርቻው እየተጠራሩ “ግፋ በለው” የሚሉ በማያተርፉበት ጨዋታ ዝም ብለው ነገር ማንቀርቀባቸው ጊዜው የመረጃ ዘመን ነውና የከፋ ነገር ቢከሰት አብረው ሲጠቀሱ ከመኖር የዘለለ ጥቅም አያስገኝላቸውምና ቢተውት የሚሉ አሉ።
“ተጸዕኖ ፈጣሪ ነን” ብለው ራሳቸውን የቆለሉ ጥቁር ለብሰው “ሐዋሪያዊ የፖለቲካ መመሪያ” ሲሰጡ “አብዛኛው” የሚባሉ አድፋጮች ለፈገግታ እንደሚጠቀሙባቸው፣ በተለይ ውጭ ያሉትን “ሻሸመኔ ናና ተሰዋ” ሲልም በማኅበራዊ ሚዲያ የተሳለቁባቸው ጥቂት አይደሉም። አንዳችም የማኅበረሰብ ሥራና ጥቅም ላይ ፈጠራቸውን ያላኖሩ፣ የማኖር ብቃትም የሌላቸው፣ አገር በተወረችበት ወቅት ቤት ዘግተው ሃድራ ሲያሞቁ የነበሩ፣ ዛሬ ወጥተው ምስኪን መእመናን ወደ እሳት ለመንዳት ሲነደፋደፉ ማየት እጅግ አሳዛኝ እንደሆነ የሚገልጹ “ኢትዮጵያ የተሠራችበትን ውቅሯን ለሚረዳና የክልሎችን ሕገ መንግሥታዊ አቅም የሚያውቁ በዚህ መልኩ መንግሥትን ለመናድ ማሰባቸው መጨረሻው ሃዘን እንደሚሆን ይወቁት” እያሉ ነው። (ፎቶ፤ በስሪ ላንካ የተደረገው የቤተ መንግሥት ወረራ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
afuye says
As always your are biased and partial, I think the government has plenty platforms and I don’t think needs your help.