በኢትዮጵያ ካሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ “ከፍተኛ” የሚባለውን ደረጃ ያሟሉ፤ አራት ብቻ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ካሉ 47 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተፈላጊውን “ከፍተኛ ደረጃ” የሚያሟሉት አራቱ ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ወላጆች፣ የቀድሞ ተማሪዎች እና መምህራንን የሚያሳትፍ፤ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ያለመ ሀገር አቀፍ የትምህርት ዘመቻ በአንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ያስታወቀው ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 15፤ 2015 በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት ነው። ሪፖርቱን ለፓርላማ አባላት ያቀረቡት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአጽንኦት ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ፤ የትምህርት ቤቶችን ጥራት የሚመለከት ነው።
እርሳቸው የሚመሩት መስሪያ ቤት በሀገሪቱ አጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ባሉ 47 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ግምገማ ማድረጉን የተናገሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በተገኘው ውጤት ላይ ተመስርቶ ትምህርት ቤቶቹ በአራት ደረጃዎች እንደተመደቡ ገልጸዋል። ግምገማው የተደረገው፤ ትምህርት ቤቶች በሚጠቀሟቸው ግብዓቶች፣ በመማር ማስተማር ሂደቶቻቸው እንዲሁም ተማሪዎቻቸው በሚያስመዘግቧቸው ውጤቶች ላይ እንደነበር አመልክተዋል።
በሌላ ዜና ዘንድሮ የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች የመውጫ ፈተና እንደሚወስዱ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቋል።
በ2015 በመንግስትና በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተሰበሰበው መረጀ መሠረት 240 ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎች በበይነ-መረብ የመውጫ ፈተና ለመስጠት መዘጋጀቱን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቋል። ሚኒስቴሩ ይህ ያስታወቀው የ9 ወራት የአፈፃፀም ሪፖርቱን ለህ/ተ/ም/ቤት እያቀረበ በሚገኝበት በአሁን ሰዓት ነው።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ፤ በ2015 በመጀመሪያ ዲግሪ ኘሮግራም ለሚመረቁ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ብሉ -ኘሪንት የተዘጋጀ መሆኑና የመውጫ ፈተና የክፍያ ተመን ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱን ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት አብራርተዋል።
የመውጫ ፈተናን ለመተግበር የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱንም የገለፁት ሚኒስትሩ፤ የመውጫ ፈተና ስትራቴጂ ማስፈፀሚያ መመሪያ እና የድርጊት መርሃ-ግብር ዝግጅት መጠናቀቁንም አብራርተዋል። በመውጫ ፈተና የሚካተቱ የትምህርት ዓይነቶች (ኮርሶች) ተለይተው፤ በቅድመ-ምረቃ በሚሰጡ በሁሉም የትምህርት መስኮት የፈተና ንድፍ ማሳያ መዘጋጀቱንም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply