ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የተባሉ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተር የሆኑት ተስፋዬ ደሜን ጨምሮ በአራት የአገልግሎቱ ሰራተኞች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ።
በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ስም 29 ሺሕ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ከኹለት ፋብሪካዎች ገዝተው ለግለሰቦች በመሸጥ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ የአገልግሎቱ የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተርን ጨምሮ በአራት ሰራተኞች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው፤ ተከሳሾች በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ውስጥ 1ኛ ተስፋዬ ደሜ በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተር፣ 2ኛ አሸናፊ ተስፋዬ የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ግዢ ዋና ክፍል ሃላፊ፣ 3ኛ ቱጅባ ቀልቤሳ እና 4ኛ ተከሳሽ ሙስጠፋ ሙሳ የግዢ ባለሙያ ናቸው፡፡
ግለሰቦቹ በተቆሙ ውስጥ ሲሰሩ ተገቢ ያልሆ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በ2013 እና 2014 በተለያዩ ወራት በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምንም አይንት ሲሚንቶ ግዢ ባልተፈፀመበት ሁኔታ በሥሙ ሲሚንቶ ከፋብሪካዎች በአነስተኛ ዋጋ በመግዛትና ገበያ ላይ በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ ህገ-ወጥ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ፤ 1ኛ ተከሳሽ አገልግሎቱ የሲሚንቶ ግዢ ፍላጎት ሳይኖረው እንዳለው በማስመሰል ለአገልግሎቱ አስቸኳይ የግንባታ ሥራ የሚውል በድምሩ 29 ሺሕ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ሽያጭ ከደርባና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲፈፀም በ3ኛ እና በ4ኛ ተከሳሽ ሥም ደብዳቤዎችን በመፃፍ፣ በተከሳሾች የግል አካውንት ገቢ በማድረግ፣ ወደ ፋብሪካችሁ ገቢ በሆነው ገንዘብ ለመስሪያ ቤታችን የሲሚንቶ ሽያጭ እንድትፈፀሙ በማለት ደብዳቤ በመፃፍ በመስሪያ ቤቱ ስም ግዢ እንዲፈፀም እና ሲሚንቶው ወደ መስሪያ ቤቱ ገቢ ሳይደረግ አየር ላይ ተሸጦ ለግል ጥቅሙ እንዲውል ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በተመሳሳይ 2ኛ ተከሳሽም 1ኛ ተከሳሽ ያለምንም ግዢ ፍላጎት በተቋሙ ሥም ግዢ እንዲፈፀም የፃፋቸውን ደብዳቤዎች 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ለደርባ እና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲያደርሱ እና ተከሳሾች በግል አካውንታቸው ገቢ በሚያደርግላቸው ገንዘብ ከየፋብሪካዎቹ የሲሚንቶ ግዢ እንዲፈፅሙ በመንገርና ደብዳቤዎቹን በመስጠት በተቋሙ ስም የተገዛውን 29 ሺሕ 200 ኩንታል ሲሚንቶ በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው እንዲውል ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ደግሞ፤ ለደርባ እና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በተቋሙ የሲሚንቶ ግዢ ፍላጎት ሳይኖር ለደርባ እና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በ3ኛ ተከሳሽ ሥም 7 ሺሕ 200 ኩንታል፣ በ4ኛ ተከሳሽስም 22 ሺሕ ኩንታል ሲሚንቶ፣ በድምሩ 29 ሺሕ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ግዢ እንዲፈፀም በተፃፈ የተቋሙ ደብዳቤ አማካኝነት በግል አካውንታቸው በሚገባ ከፍተኛ ገንዘብ ግዢ በመፈፀም ሲሚንቶው ወደ ተቋሙ ገቢ ሳይሆን አየር በአየር በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው እንዲውል ያደረጉ መሆኑ በክሱ ተዘርዝሯል።
በአጠቃላይ ተከሳሾች በጥቅም በመመሳጠር ምንም አይነት የግዢ ፍላጎት ሳይኖር በአገልግሎቱ ሥም በፃፏቸው ደብዳቤዎች ከዳንጎቴ እና ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በድምሩ 29 ሺሕ 200 ኩንታል ሲሚንቶ በመግዛት ወደ ተቋሙ ገቢ ሳያደርጉ ገበያ ላይ በመሸጥ 30 ሚሊዮን 99 ሺሕ 360 ብር ጥቅም ያገኙ በመሆኑ፤ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ተከሳሾች የተከሰሱበት ክስ በችሎት ደርሷቸው ክሱ የተነበበላቸው ሲሆን ተከሳሾችም የክስ መቃወሚያ ካላቸው በጽሁፍ እንዲያቀርቡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ወንጀል ችሎትም ለታሕሳስ 7 ቀን 2015 ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ይህ ዘገባ ተከሳሾች ላይ ክስ ስለመመስረቱ ለማሳወቅ የቀረበ ሲሆን፤ የተከሳሾችን ከፍርድ በፊት እንደ ንፁህ የመገመት ህገ-መንግስታዊ መብትን እንደሚያከብር ፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል። (አዲስ ማለዳ)
Leave a Reply