እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
“በሚኖሩባት ሰዎች ክፋት የተነሳ ፍሬያማዋን ምድር ጨው አደረጋት” የሚል ቃል በቅዱሱ መጽሀፍ ውስጥ ሰፍሯል።ሕዝብ መቼም ቢሆን ክፉ ሆኖ አያውቅም፤ አይሆንምም። ነገር ግን ከሕዝብ የወጡ ጥቂቶች በዕኩይ ዓላማና ምግባራቸው ምድሪቱን ለጥፋት፣ ሕዝቡንም ለስቃይ ይዳርጋሉ።
ይህንን ለማረጋገጥ ባህር ተሻግረን ማሳያ መፈለግ ሳይጠበቅብን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ነኝ ባይ የነበረውን ትህነግን ማየት ይበቃል።
ትህነግ ግማሽ ምዕት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በሕዝብ ትከሻ ላይ ተንጠላጥሎ፤ በሕዝብ ገላ ላይ እንደመዥገር ተጣብቆ የኢትዮጵያ ሾተላይ ሆኖ ኖሮ ሞቷል።ነጻነት ሳያውቅ ህዝብን ነጻ አወጣለሁ ብሎ ደደቢት ላይ የተፈለፈለው እፉኝት በሞቱ ለኢትዮጵያ ነጻነት ታውጇል።
“ቀን ያስጎነበሰውን ቀን ቀና ያረገዋል” እንዲሉ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ያስጎነበሳት ጥቁር ቀን ነው።ሕዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ደግሞ ያዘመመችዋን አገር ቀና አድርጓታል።
ይህ ጽሁፍ በትህነግ የሸፍጥና የዘረኝነት ስንክሳር የመጨረሻ ገጽ ላይ የሰፈረውን ጥቁር አሻራ – የማይካድራን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ከዓለምአቀፍና ከአገራችን የወንጀል ሕግ ማዕቀፍ አንጻር ይቃኛል።
ዓለም አቀፍ ወንጀሎች
ዓለም አቀፍ ወንጀሎች የሚባሉት በሰብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ ዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀል፣ የባህር ላይ ውንብድና፣ የባሪያ ንግድ እና የመሳሰሉት ናቸው።ዓለም አቀፍ ወንጀሎች የሆኑበት ምክንያት ደግሞ አገራት ተስማምተው የፈረሟቸውን ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጣስ የሚፈጸሙ በመሆናቸው ነው።
በሌላ በኩል ሰው በሚባለው ፍጡር ላይ የሚፈጸሙና የሰውን ዘር ስሜት የሚጎዱ የወንጀሎች ሁሉ የመጨረሻዎቹ ከባዶች በመሆናቸው ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ተሰኝተዋል።በመላው ዓለም የሚወገዙም ናቸው።በአይሁዶች ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ እና የርዋንዳው እልቂት ጎልተው የሚጠቀሱ ምሳሌዎች ናቸው።
በሰብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን፣ የዘር ማጥፋትንም ሆነ ሌሎቹን ወንጀሎች ዓለም አቀፍ ያሰኛቸው ሌላው ጉዳይ የወንጀሎቹ ፈጻሚዎች ድርጊቶቹን በፈጸሙባቸው አገራት ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የዓለማችን ጥግ በሚገኝ ፍርድ ቤት ለፍትህ የሚቀርቡበት ዓለም አቀፍ ሥርዓት መኖሩ ነው።
በመሆኑም ወንጀል ፈጻሚዎቹ ሸሽተው የተጠለሉባቸው አገራት በእነዚህ ወንጀሎች ላይ ዓለም አቀፍ የዳኝነት ሥልጣን ስላላቸው በራሳቸው ፍርድ ቤቶች ጥፋት ሰሪዎቹን ይቀጣሉ።አልያም ወንጀሉን ለፈጸሙበት አገር አሳልፈው እንዲሰጡ ዓለም አቀፍ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
የዘር ማጥፋት እና የጦር ወንጀሎች
የዘር ማጥፋት ወንጀል እኤአ በ1948 ዓ.ም. በጄኔቫ በወጣ ዓለም አቀፍ ሥምምነት ተደንግጓል።ኢትዮጵያም ይህንን ሥምምነት ፈርማ በመቀበል የሕጓ አካል አድርጋዋለች።ይህ ወንጀል በሰላማዊም ሆነ በጦርነት ጊዜ ይፈጸማል።ወንጀሉን የሚፈጽሙት ደግሞ ጦር የሰበቁ ወይም ሲቪሎች ሊሆኑ ይችላሉ።
ይህ ወንጀል በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 269 ሥር ተደንግጓል።ማንም ሰው በሰላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በጎሳ፣ በዘር፣ በዜግነት፣ በቀለም፣ በሐይማኖት ወይም በፖለቲካ አንድ የሆነን ቡድን በመላ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ የጥፋቱን ድርጊት በማደራጀት፣ ትዕዛዝ በመስጠት ወይም ድርጊቱን በመፈጸም በማናቸውም ሁኔታ የማህበረሰቡን አባሎች የገደለ፣ አካላዊ ወይም ኅሊናዊ ጤንነት የጎዳ ወይም የአካል ጉዳት ያደረሰ ወይም ያጠፋ እንደሆነ ዘርን በማጥፋት ወንጀል ይጠየቃል።
ይህ ብቻም ሳይሆን የማህበረሰቡ አባላት በዘር እንዳይራቡ ወይም በሕይወት እንዳይኖሩ ለማድረግ ማናቸውንም ዘዴ በሥራ ላይ ማዋልም ዘርን የማጥፋት ወንጀል ነው።
ከዚህም ሌላ የማህበረሰቡን አባላት ወይም ሕጻናትን በግዴታ ከሥፍራ ወደ ሥፍራ ያዛወረ ወይም የበተነ ወይም ሊሞቱ ወይም ሊጠፉ በሚችሉበት የኑሮ ሁኔታ እንዲኖሩ ማድረግም እንዲሁ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሆኖ ተደንግጓል።
በሌላ በኩል የጦር ወንጀል የሚባለው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግን በመጣስ በሰው ዘር ላይ የሚፈጸም ከባድ ዓለም ዓቀፍ ወንጀል ነው።
ከሥሙ ለመረዳት እንደሚቻለው የጦር ወንጀል በጦርነት ወቅት የሚፈጸም ነው።የወንጀሉ ፈጻሚዎች ጦር የሰበቁት ተፋላማዎች ወይም ሌሎች ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።ለጦርነቱ ማስፈጸሚያ ከሚውሉት ውጭ ያሉ እንደ ሆስፒታል፣ የሐይማኖት ተቋማትና ሌሎችም ተጎጂዎች ይሆናሉ።
የወንጀሉ ሰለባዎች ደግሞ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ውስጥ ጥበቃ የተደረገላቸው ተዋጊዎች ወይም ንጹሃን ሰዎች ናቸው።
በሰብዓዊነት ሕግ ጥበቃ የተደረገላቸው ተዋጊዎች የሚባሉት የተማረኩ፣ የቆሰሉ፣ የታመሙ፣ የጦር እስረኛ የሆኑ ወይም እንዲህ በመሳሰለው ሁኔታ ውስጥ በሌላኛው ተዋጊ እጅ የወደቁ ናቸው።
ንጹሃን ሰዎች የሚባሉት ደግሞ ሰላማዊ ኑሯቸውን የሚመሩ ወይም ስደተኞች ሊሆኑ ይችላሉ።እናም በእነዚህ ሰዎችና ተቋማት ላይ የሚፈጸም ወንጀል የጦር ወንጀል ነው።
የዘር ማጥፋትን እና የጦር ወንጀልን የሚለያቸው ዓይነተኛ ምክንያት የዘር ማጥፋት ወንጀል አንድ የሆነን የብሔር፣ የዘር ወይም የሐይማኖት ቡድን በመላ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ የሚፈጸም መሆኑ ነው።
የጦር ወንጀል ደግሞ ብሔርን፣ ዘርን፣ ሐይማኖትን አልያም የፖለቲካ ቡድንን በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት ዒላማ የማያደርግ፤ ይልቁንም በዓለማቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ጥበቃ የተደረገላቸውን ተዋጊዎችን ወይም ሲቪሎችን ዒላማ ያደረገ ወንጀል ነው።
በዘመናችን ለዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ መሰረት የተጣለው እኤአ በ1949 ዓ.ም. በተፈረሙት የጄኔቫ ስምምነቶች ነው።እነሱንም ተከትለው የተለያዩ ፕሮቶኮሎች ወጥተዋል።ኢትዮጵያም የእነዚሁ ዓለም አቀፍ ሥምምነቶች ቀደምት አባል ናት።
የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግም የጦር ወንጀሎችን በዝርዝር አስቀምጧል።ከእነዚህም ውስጥ ሰፊውን ሥፍራ የሚይዙት በጦርነት ወቅት በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች (ከ15 በላይ የወንጀል ዓይነቶች) ናቸው።
ከሕጉ እንደምናነበው ማንም ሰው በጦርነት፣ በጦርነት ግጭት፣ ወይም በጠላት ወረራ ጊዜ የዓለም አቀፍ ሕግ ድንጋጌዎችንና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግጋትን በመጣስ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ በማደራጀት፣ በማዘዝ ወይም ድርጊቱን በመፈጸም ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ሰውን የገደለ፣ ያሰቃየ፣ ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መንገድ ያጉላላ፣ ሥነ-ሕይወታዊ ሙከራዎችን ያደረገ፣ በሰው አካል፣ አዕምሮ ወይም ጤንነት ላይ ከባድ ስቃይ ወይም ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ሌሎች ድርጊቶችን ያደረገ እንደሆነ በጦር ወንጀል ይጠየቃል።
ከዚህም ሌላ ሕዝብን በኃይል ከሥፍራው እንዲፈናቀል ወይም እንዲበተን ያደረገ፣ በተደራጀ ዕቅድ ከአገር ያስወጣ ወይም ወደ አንድ የግዞት ሥፍራ ወይም የግዴታ ሥራ ማከናወኛ ሥፍራ በመላክ እንዲታሰር ማድረግም የጦር ወንጀል ነው።
የማስፈራራት ወይም የማሸበር ድርጊት መፈጸም፤ በመያዣነት ማገት ወይም የጅምላ ቅጣት መጣል ወይም የበቀል ድርጊት መፈጸምም እንዲሁ የጦር ወንጀል ነው።
ማይካድራ – የዘር ማጥፋትና የጦር ወንጀል
በዚያች የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ዳር ሃገር የተፈጸመውን ዘግናኝ ድርጊት ለመግለጽ ቃላት አቅም ያላቸው አይመስልም።የመገናኛ ብዙሃን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በተለያዩ ቀናት ስለጉዳዩ መረጃዎችን ለሕዝብ አድርሰዋል።
በዚያች ምድር የተፈጸመውን ድርጊት ከላይ ካብራራኋቸው ዓለም አቀፍ ወንጀሎች አንጻር ለማየት ድርጊቱን በዝርዝር ማስቀመጥ የግድ ነው።
በቀደሙት የ27 ዓመታት ጭቆናና መገለል ማግስት የማይካድራ አማሮች በትህነግ ቅጥረኞች ጥቃት ይደርስብናል የሚል ሥጋት ነበራቸው።(የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንደመሆኑ መጠን አማሮችና ወልቃይቴ በሚል የገለጸውን በተመለከተ “ወልቃይቴ” የሚለው አነጋገር ጥንቱንም በአካባቢው እትብታቸው ተቀብሮ እዛው የኖሩት አማሮች የሚጠሩበት ሲሆን፤ አማሮች የሚባሉት ደግሞ በተለያየ ምክንያት ወደስፍራው አቅንተው የሚኖሩት ስለመሆናቸው በአግባቡ ግልጽ አድርጎ ጭፍጨፋው የተፈጸመው በአማራ ላይ መሆኑን በግልጽ እንዲያስቀምጥ ይጠበቃል)
የሆነው ሆኖ በጥቃት ኢላማ ውስጥ ያሉት አማሮች በሚሊሻ በፖሊስና ሳምሪ በተባሉት የሳምራ አካባቢ የትህነግ ወጣቶች በአይነ-ቁራኛ ይታዩ ጀመር፤ እንቅስቃሴያቸውም ተገደበ።
በዚያች ጥቁር ቀን ደግሞ ፈርተው ከከተማዋ ሊወጡ ሲሉ ኬላዎች ላይ በትህነግ ቅጥረኞች ታገዱ።ቅጥረኞቹ እጅግ በፍጥነት መታወቂያ ማየትና የመለየት ሥራ ጀመሩ።
አማሮች የሚኖሩባቸውን ቦሌና ግንብ የሚባሉትን አካባቢዎች በተለየ ጭንቀት ውስጥ በማስገባት በየቤታቸው እየሄዱ የሱዳን ሲም ካርድ ያላቸውን ሰዎች እየለዩ ስልኮቻቸውን ቀምተው ሰባበሩ።ይህን ያደረጉትም በቀጣይ ያሰቡት ጭፍጨፋ መረጃው እንዳይወጣና ርዳታም እንዳይደርስ ነበር።
ቅጥረኞቹ አጥፊዎች ወገኖቻቸው የሆኑትን የትግራይ ተወላጆችን ከከተማዋ አስወጡ።“የእኛን ልዩ ኃይሎች የእናንተ ወገኖች በጦርነት እየጨረሱ ስለሆነ እኛም እናንተን እናጠፋለን” በማለት ቅጥረኞቹ ሳምሪዎች ወደ አማሮቹ መኖሪያ ሄደው በገመድ እያነቁ፣ በገጀራ እየቆራረጡ፣ በስለት እየወጉ ሰይጣናዊ ድርጊታቸውን ፈጸሙ።
ነፍሳቸውን ለማትረፍ የሚሮጡትን ደግሞ ሚሊሻዎችና ፖሊሶቹ በጥይት ለቀሟው።በዚህ ድርጊት ተሸናፊ ሆነው በሽሽት ላይ የነበሩት የትህነግ ልዩ ኃይል አባላትም ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በዚያች ቀን በውስን ሰዓታት በትንሹ ከ600 በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፋቸውን በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ አሳውቋል።ከዚህ ሪፖርት በኋላ ከአንድ ሺ በላይ ንጹሃን ሰዎች ዘራቸው ተለይቶ እንደተገደሉ መረጃዎች ወጥተዋል።
የቁጥሩ ነገር እስኪጠራ እንተወውና ጨፍጫፊዎቹ ንጹሃን ሴቶችን “ነገ ወደ እናንተ እንመለሳለን” ብለው ምድሪቱን የባሰ በደም ሊያጨቀዩ ሲሰናዱ የመከላከያ ሰራዊትና የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ደረሱ።አፍነው የወሰዷቸውን ከምን እንዳደረሷቸው ሳይታወቅ በበረሃው ወደ ሱዳን ገብተዋል።
የተፈጸመው ድርጊት በአጭሩ ይህ ነው።በደደቢቱ ማኒፌስቶ አማራንና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን በግልጽ በጠላትነት ፈርጆ ነፍጥ ያነገበው ትህነግ ይህንን ያደረገበት ሁለት መሰረታዊ ምክንያት ስለመኖሩ ነው ነገሩን የሚተነትኑ መረጃዎች የሚያሳዩት።
በአንድ በኩል መከላከያና የአማራ ልዩ ኃይል በቁጣ ተነሳስቶ በትግራይ ወገኖቹ ላይ የበቀል ርምጃ እንዲወስድ ለማነሳሳትና ቀውሱንም የእርስ በእርስ ጦርነት አድርጎ በማቅረብ ዓለም ዓቀፍ ጣልቃ ገብነትን ለመማጸን ስለመሆኑ ይገለጻል።ዓላማው ባይሰምርለትም።
ከዚህ አንጻር ካየነው ምናልባትም ይህ የኋላ ኋላ በማስረጃ የሚረጋገጥ ከሆነ ትህነግ የፈጸመው የጦር ወንጀል ሆኖ እንደሚፈረጅ ግልጽ ነው።
በማይካድራ የተፈጸመውን ድርጊት እያንዳንዱን ሰበዝ በዝርዝር ከተመለከትነው ግን ድርጊቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል ስለመሆኑ ጥርጥር የለም።መታወቂያ እየታየ፣ በአማሮች ላይ ተለይቶ የተፈጸመ መሆኑና በነጋታውም ሴቶችና ሕጻናትን ለመፍጀት በማስፈራራት በይደር ተይዞ የነበረ ዕቅድ መኖሩ ሲመዘን ድርጊቶቹ በዓለም ዓቀፍ ድንጋጌዎችና በወንጀል ሕጉ የተቀመጡትን የዘር ማጥፋት ማቋቋሚያ ፍሬ ነገሮችን ሙሉ በሙሉ ያሟላሉ።
እርግጥ ነው “አንድ የሆነን ቡድን በመላ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ” ከሚለው የህጉ አገላለጽ በመነሳት 600 ወይም አንድ ሺ ሰዎችን በመግደል አማራን ማጥፋት ይቻላል ወይ የሚል መከራከሪያ በብዙዎች ዘንድ የሚነሳ ቢሆንም ቅሉ፤ በበርካታ የዓለም ዓቀፍ ልምዶች እንደታየው ዋናው ጉዳይ የወንጀል ሰሪዎቹ ዓላማ ሊሆን ይገባዋል የሚለው ውሃ የሚያነሳ ነጥብ ነው።
በመሆኑም የተጎጂዎቹ ቁጥር ሳይሆን መታየት ያለበት የእኩያኑ ዓላማ በተግባር በተገለጸበት ወቅት ያደረሰው የሞት፣ የአካል እንዲሁም በሌላው የማህበረሱ አባላት ዘንድ ያስከተለው የሞራል ስብራት ሲለካ ሚዛን የሚደፋ በመሆኑ ድርጊቱ ዘርን የማጥፋት ወንጀል ስለመሆኑ እርግጥ ነው።
የማይካድራ ፍትህ – በየትኛውም አገር ፍርድ ቤት ይታያል፤ ይርጋ፣ ምህረትና ይቅርታም የለም
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 28 ሥር እንደተመለከተው የዘር ማጥፋትም ሆነ የጦርነት ወንጀል በፈጸመ ሰው ላይ የሚቀርብ ክስ በይርጋ አይታገድም።ይህም ብቻ ሳይሆን ወንጀሎቹ በምህረትም ሆነ በይቅርታ አይታለፉም።
ከሁሉም በላይ የዘር ማጥፋትም ሆነ የጦር ወንጀሎች ዓለም አቀፍ ወንጀሎች በመሆናቸው የወንጀሎቹ ፈጻሚዎች ድርጊቶቹን በፈጸሙባቸው አገራት ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የዓለማችን ጥግ በሚገኝ ፍርድ ቤት ለፍትህ የሚቀርቡበት ዓለም አቀፍ ሥርዓት አለ።
ስለዚህ ወንጀል ፈጻሚዎቹ ሸሽተው የተጠለሉባቸው አገራት በእነዚህ ወንጀሎች ላይ ዓለም አቀፍ የዳኝነት ሥልጣን ስላላቸው በራሳቸው ፍርድ ቤቶች ጥፋት ሰሪዎቹን ይቀጣሉ።አልያም ወንጀሉን ለፈጸሙበት አገር አሳልፈው እንዲሰጡ ዓለም አቀፍ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
የትህነግ ቁንጮ ጅጁ ሽማግሌዎችና ጀሌዎቻቸው ካልተገደሉ ወይም ራሳቸውን ካላጠፉ አልያም በክፋታቸው የተነሳ ጨው ካደረጓት ለምለሚቱ ምድር ኢትዮጵያ ለቀው ወጥተው ካልሆነ በስተቀር በቁጥጥር ሥር ውለው እዚችው አገር ለፍርድ ይቀርባሉ።ሸሽተውም ከሆነ የደረሱበት አገር በራሱ ፍርድ ቤት ለፍትህ እንዲያቆማቸው ዓለም አቀፍ ግዴታ አለበት።
ማይካድራ ላይ ድርጊቱን የፈጸሙት እነዚያ የሰው አምሳያ ያላቸው ሰይጣኖች አብዛኞቹ ከስደተኞች ጋር ተደባልቀው ወደ ሱዳን ለመውጣታቸው የተጠናከሩ መረጃዎች በስፋት እየተሰራጩ ነው።
በዓለም የስደተኞች ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በስደተኛ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ወጣቶች መሆናቸው እና በየጣቢያዎቹም የአማራ ብሔር ስደተኞችን የማግለልና የማስፈራራት ድርጊቶች መፈጸማቸው የእነዚህን መረጃዎች እውነትነት ማሳያ ይሆናል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳን መንግስት ይህንን መረጃ በመያዝ ጉዳዩን እንዲያጣራውና የዓለም ዓቀፍ ረጂዎችም ለዚህ ትብብር እንዲያደርጉ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል።
በደህና እንሰንብት!
ከገብረክርስቶስ፤ አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም