የዓለም ህዝብ ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጭን ድል ያደረገውን የጥቁር ጦር መሪ አጤ ምኒልክን ለማወቅ እጅግ ጓጓ፡፡
ምስላቸውን ለማየት ተቁነጠነጠ፡፡
ሙሉ ታሪካቸውን ለመስማት ተንሰፈሰፈ፡፡
ይህንኑ ተከትሎም፤ “እንኳንም ደስ አለዎት” ለማለት ከቁጥር የበዙ ደብዳቤዎች ይጎርፉላቸው ነበር፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በፖስታ ቤት በኩል የኢትዮጵያ ቴምብር የተለጠፈበት መልስ እንዲላክላቸው ይጠይቁ ነበር፡፡
ለምን… ?
ቴምብሩ ላይ ያለውን የምኒልክን መልክ ለማየት፡፡
ባለ ብዙ ዝናና ክብር ባለቤት የሆኑትን የምኒልክን ጥቁር ፊት ለማየት፡፡
የሰው ሀገር ሰው ሁሉ፤ “ዝናውን እንደሰማሁ መቼ ሄጄ ባየሁት”፣ “በጀግንነቱ እንደ ተማረኩ መች ተጉዤ ባገኘሁት”፣ “ካሁን ካሁን ፈቅዶልኝ ወታደር ሆኜ ባገለገልኩት” ያለላቸው አጤ ምኒልክ የኛ ናቸው፡፡
በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጭን ያንበረከከ የጥቁር ጦርን የመሩት ንጉስ የኛ ናቸው፡፡
መወድስ የማይበዛበት የአድዋ ድልም የኛ ነውና፣
እንኳን ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ለምንኮራበት በዓላችን በጤንነት አደረሰን! (ምንጭ: ነቆራ እና ሌሎችም ወጎች ከሕይወት እምሻው ጋር – Hiwot Emishaw)
በድጋሚ የተለጠፈ
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
ጉልበተኛ ዓለምን እንደሚገዛና እንደሚያስገዛ ቀደም ብለን የምናውቀው ጉዳይ ቢሆንም አሁን የራሽያ ወደ ዪክሬን መግባት በጉዳዪ ላይ ላመነታ ማሳመኛ መድሃኒት ነው። ረጅም በትር ባይመቱበት ያስፈራሩበት ያሉት አበው ሲፈለግ እንደሚመታበትም አውቀው ነው። ይገርማል አሁን በ 140 ሃገሮች የተኮነነችው ሩሲያ ያው ውጊያውን አፋፍማዋለች። የአህያ ባል ከጅብ አያድንም እንዲሉ በፊት ከሩቅና ከቅርብ ሆነው ሲለፈልፉ የነበሩ ሃያላን መንግስታትም ሆነ ተለጣፊ መንግስታት ምንም ማድረግ አልቻሉም። ያው ለዘመናት ሲያረጉ እንደነበሩት በርቀት እሳት ያቀብላሉ።
ወደ አድዋው ድልና አሁን በሃበሻዋ ምድር የሚታየውን የፓለቲካ አተካራና የመገዳደል ዘዬ ተራምደን ከዘመናት በፊት ማንበብና መጻፍ እምብዛም የማይችሉት ለሃገራቸው አንድነት ከጠላት ጋር ተዋድቀው ያቆዪልንን ሃገር እድሜ ለትግራይ ተገንጣይ ቡድን በዘርና በቋንቋ ተሸንሽና አሁን ያለችበት የሰዶ ማሳደድ የዘር ፓለቲካ ላይ ደርሰናል። የአሁኑ ትውልድ ካለፈው የሚልቅበት ኢምንት ነገር የለም። አለ ከተባለም ትቢያ ነው። ያኔ ሰው ሰው ሆኖ ሲያድር ምንም የሃገሪቱ ተወላጅ የትም ሂዶ ሰርቶ የመኖር መብት ነበረው። አሁን ደግሞ ሁሉም በየጓዳህ ስለተባለ ነገሩ ሁሉ ለሚመለከተው አይነ ሸውራራ ያረጋል። እስቲ እንበልና የዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ ድል ሽንፈት ሆኖ ቢሆን ኑሮ ዛሬ በቋንቋ፤ በሃይማኖት፤ ወይም በሌላው ሃበሻው ይዣለጥ ነበርን? ጭራሽ። የጣሊያን ቋንቋ ተናጋሪና ካቶሊክ ነበር የሚሆነው። ይህን ለመረዳት ደቡብ አሜርካን ከብራዚል በስተቀር የስፔን ወራሪዎች እንዴት እንደለወጧቸው ማየት በቂ ነው። ብራዚልም ቢሆን ከአፍሪቃ እልፍ ጥቁሮችን በባርነት ታጓጉዝ የነበረችው ፓርቹጋል የፓርቹጊዝ ተናጋሪ ብራዚልን አርጓታል። ዛሬ በቺሌ፤ በአርጀንቲና በሌሎችም የዚህ ክፍለ ሃጉር የናጠጡ ኗሪዎች መጤዎች ናቸው። ይበልጦቹ ከሁለቱም የዓለም ጦርነቶች በህዋላ የተሰደድ ናቸው። ግን አሁን ሃገራቸው ነው። ይኖሩበታል። ተዋልደውል። የሃበሻው የገማ ፓለቲካ የዛሬ መቶ ዓመት እንዲህ አይነት በደል ደርሶብኛልና ልበቀል የሚል ጥላቻን የተላበሰ የድንበር ገተር ህልፈተ ቢስ የፓለቲካ እይታ እየቆየን እንድንቀጭጭና በረሃብና በቸንፈር እንድንጠቃ አርጎናል። ዛሬ እኔ አማራ ነኝ፤ እኔ ኦሮሞ ነኝ፤ ያ ደግሞ ከደቡብ ነው፤ ይህ ደግሞ ከትግራይ ነው የምንለው ሁሉ የአድዋ ድል በድል ባይጠናቀቅ ኑሮ አይኖርም። ያ ድል የሁለተኛውን የጣሊያን የብቀላ ወረራ ሁሉ ሃገሬው እንዲመክት ያስቻለው የማይነቃነቅ የነጻነት ምሰሶ ነበር፤ ነውም። የሃበሻን አልገዛም ማለት ያዪ የአፍሪቃ ሃገሮችም ነቅተው፤ ታጥቀው በመታገላቸው ዛሬ ግማሾቹ ለህዝባቸው በሚያቀርቧቸው አገልግሎቶች ቀድመውን ሂደዋል። እኛ ግን ከጨካኝ ወደ ሌላ ጨካኝ ስንሸጋገር ባለንበት እንኳን ለመኖር ተስኖን አዲስ ፈሊጥና የመጨቆኛ ዘዴ እያወጣን የቆመን በማፍረስ ላይ እንገኛለን።
ባጭሩ ዛሬ ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚሉን አፍራሽ ሥራ እየሰሩ ነው። ደግሞም በዚህ አያያዝ ኢትዮጵያ የማትፍረከረክበት ምንም ምክንያት የለም። ፈክሮ ከማፋከር ይልቅ በመሬቷ ላይ የሚወርደውን የመከራ ዝናብ ለመግታት በአንድነት መነሳት ተገቢ ነው። ሶሪያ፤ ኢራቅ፤ ሊቢያ፤ የመን ወዘተ የተንኮታኮቱት አንፈርስም እያሉ ነው። አሁን ባለው የፓለቲካ አሰላለፍ (ራሺያና ቀሪው ዓለም) ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ የሚገምት አለ? ጭራሽ። ስለሆነም ከዘመናት በፊት በህብረ ተጋድሎ ያስረከቡንን ሃገር ህልውና ለማስቀጠል የአድዋን ድል በየአመቱ ከማክበር ባሻገር እኔ ለሃገሬ ለወገኔ ዘርና ቋንቋን ወይም ሃይማኖትን መሰረት ስላደርግ ምን ሰራሁ በማለት ራሳችን ጠይቀን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። በቃኝ!