የማጠቃለያው መግቢያ
እስኪ አንድ ጥያቄ እንመልስ፤ እንዴት መሽቶ ይነጋል? እነዚህ ወገኖች እንዴት ቻሉት? እንዲህ ያለው ስቃይ እንዴት ሌሎችን ያስደስታል? በህይወት ያለ ሰው በኤሌክትሪክ ማቃጠል ምን ማለት ነው? ሰውን ማኮላሸት ምን የሚሉት ጭካኔ ነው? ሰውን ሰቅሎ መርሳት፣ ገልብጦ ሲደበድቡ ማደርና ማቃጠል፣ ተነግሮ፣ ተወርቶ፣ የማያልቅ ጉድ! እንዴት ነው እነዚህ ሰዎች የሚያስቡት? ሕዝብ ስሜት ያለው አይመስላቸውም? የወላድንና የህጻናትን እንባና የፈጣሪን ፍርድ ለጊዜው ወደ ጎን ቢሉትም፣ ነገሮች በዋይታ የሚዘልቁ ሆነው ስለመሰራታቸው እርግጠኞች ናቸው? የትግራይ ሕዝብስ ለምን ዝም ትላለህ? የትግራይ ምሁራን ይህ እርካታን ይሰጣችኋል? ከመጠርጠር እስከ መመርመር፣ እስከ ማሰር፣ መክሰስ፣ መፍረድና ይቅርታ ማስጠየቅ በትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) እየተከናወነ፤ የአሳሪው ቋንቋ ትግርኛ፤ የታሳሪው ኦሮምኛና አማርኛ እየሆነ ባለባት አገር ኢትዮጵያዊ ነን የሚሉ የትግራይ ልጆችም ሆነ የቀድሞ የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ዝምታ አልበዛም? ወዴት እየሄድን ነው? ያሳስባል፣ ያስፈራል፣ እጅግ ያስደነግጣል . . .
ለማዕከላዊ “እስር ቤት” ወይም “የምርመራ ቦታ” የሚባለው መጠሪያ አግባብ ባለመሆኑ ያነጋገርናቸው ሁሉ ተመጣጣኝ ስም እንዲሰጠው ያሳስባሉ። ዋይታና የሰው ልጆች በህይወት እያሉ የሚያጣጥሩበት ይህ የግፍና ጭከና ቦታ ተቃጥለው ለዘላለም ከሚጠፉበት ገሃነብም ይብሳል። ምክንያቱም ገሃነብ የፍርደኞች ቦታ ነውና። የሚገቡበትም የተፈረደባቸው ናቸው። ማዕከላዊ የሰው ልጆች ደምና እምባ የሚቀዳበት፣ ህሊና የሚሰለብበት፣ ሞራል የሚኮላሽበት፣ አካል የሚጎልበት፣ የሰው ልጆች ሳይሞቱ ተስፋ እንዲቆርጡ የሚደረግበት መቃብር ነው። በዚህ መቃብር ውስጥ የትግራይ ነጻ አውጪ ኃይሎችና ደጋፊዎቻቸው ብቻ ያሽካካሉ። ይዝናናሉ። አልኮል እየተጋቱ እጅና እግሩ የታሰረ ወንድ ልጅ ላይ ይሸናሉ፤ በከበረው የሴት ልጅ ገላ ዕርቃን ይሴስናሉ፤ ሰው ያመነዥጋሉ።
ጉቦና “ማስተኮስ” የሚባሉት የህወሃት ሰዎች ንጹሃንን እያሸማቀቁ ብር የሚሰበስቡበት ፕሮጀክት ዋና መስሪያ ቤት ይኸው ማዕከላዊ የሚባለው መቃብር ነው። በዚህ ፕሮጀክት ሃብታሞች ተለይተው ይቀመጣሉ። ከዚያም ብሔራቸው ይጠናና ይደገስላቸዋል። አስተኳሾቹ ስምና መረጃ ይሰጡና “አውሬዎቹ” ይላካሉ። የፈረደበት ሃብታም የተዘጋጀለት የፈጠራ ኃጢያት ይነገረውና ጉቦ ከከፈለ ጉዳዩ እንደሚታፈን ይነገረዋል።
በዚሁ መሰረት በትክክል የተያዘም ሆነ ያልተያዘ ጉዳይ በመያዝ በአስተኳሾች አማካይነት ሃብታሞች ይታለባሉ። በቅንጅት ወቅት “ቅንጅትን በገንዘብ ረድተሃል፣ መረጃ ተይዞብሃል” ተብለው በርካታ ነጋዴዎች ለፍተው ያገኙትን ገብረዋል። መርካቶ ምስክር ነው።
ቀደም ሲል የኦሮሞ ሃብታሞች የታለቡ ሲሆን አንዳንዴም ለማስመሰል ማዕከላዊ ድረስ ተጠርተው በህግ በማይታወቅ አግባብ በቁጭበሉ ቃላቸውን እንዲሰጡ የተደረጉ በርካቶች ናቸው። “እያንጓለለ” በሚል ስያሜ የሚታወቀው “አዋቂ ነኝ” ባይ ከመታሰሩ በፊት አስተኳሾቹ የደለበ ብርና ወርቅ እንደተቀበሉት ምስክሮች አሉ። የዛሬው መነሻ ጉዳይ እዚህ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ባለመሆኑ እዚህ ላይ እንገታውና የክፍል ሁለትን ዘገባ …
ጎልጉል የድረገፅ ጋዜጣ በተለምዶ በማዕከላዊ “ወንጀል ምርመራ” በሚባለው፣ ነገር ግን የሰው ልጆች ማሰቃያ ሲኦል፤ በ“ምርመራ ስም” በትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ነባር ታጋዮችና በምልምሎቻቸው አማካኝነት እስረኞች ላይ የሚፈጸሙ የስቃይ ዓይነቶችን ለማጣራት የራሱን ስልት ተጠቅሟል። ተጎጂ ዜጎችን በራሱ መንገድ ከጎረቤት አገር በጥንቃቄ ለማነጋገር ችሏል፡፡ የእያንዳንዱ ተጎጂ ዜጋ ታሪክ ሰፊና ጊዜ ጠብቆ መጽሃፍት ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚታመን ቢሆንም በሪፖርት ደረጃ የሁለት ኢትዮጵያዊ ሰለባዎችን ምስክርነት አጠናክረን አቅርበናል። በሴቶች እህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን በተመለከተ እነርሱ ለመናገር የሚከብዳቸው፤ እኛም ለመተረክ የማንችለው ነው፡፡ “ዓሣውን ለመግደል ኩሬውን ማድረቅ” በሚል የህወሃት ነፍጥ አንጋቢዎች የኦጋዴን ወገኖቻችንን ለመቅጣት ከፈጸሙት ኢሰብዓዊ ድርጊት መካከል ህጻናት ወንዶችን መድፈራቸውን መጥቀሱ በቂ ይመስለናል፡፡
“ብልቴ አካባቢ የበቀለውን ጸጉር በክብሪት እየለበለቡ አሰቃዩኝ፤ ጩኸቴ እነርሱን የሚያዝናና ነበር”
በማዕከላዊ እስር ቤት አሰቃቂ ቶርቸር ከተፈጸመባቸዉ ንጹሐን ዜጎች ውስጥ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ይጠቀሳሉ፡፡ የአንዱን የኮሚቴ አባል በማዕከላዊ የደረሰበትን ስቃይ፣ ቶርቸር፣ ድብደባና ለሰሚው ግራ የሚያጋባውን ሰይጣናዊ ተግባር ከባለ ታሪኩ አንደበት በሰማነው መሰረት ቃል በቃል እንዲህ አቅርበነዋል። ስም ያልጠቀስንበትን ምክንያት አንባቢያን ስለምትረዱት ማብራሪያ ከመስጠት እንቆጠባለን።
“በመጀመሪያው ሳምንት የታሰርንበት ክፍል ጣውላ ቤት የሚባለው ነበር፡፡ በሁለተኛው ሳምንት ሁላችንም የኮሚቴው አባላትን በታትነው ወደ ጨለማ ክፍል ወሰዱን፡፡ የተወሰኑትን ጓደኞቼን ሁለት ካሬ ብቻ ስፋት ባለው መብራት እንኳን የማያገኘው፣ ጠባብ ቀዳዳ በሆነው፣ መንቀሳቀሻ በሌለው ጨለማ ክፍል ለያይተው አስገቧቸዉ፡፡ እኔን ደግሞ ሰፋ ባለ ጨለማ ክፍል ውስጥ ከሌሎች እስረኞች ጋር አብረዉ አሰሩኝ፡፡ ለውጡ ራሱ የፈጠረው ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ነበር፡፡ በህዝቡና በቤተሰብ ናፍቆት ስንቸገር የነበርን ሰዎች ጭራሽ ሰው ወደሚናፈቀን ደረጃ ደረስን፡፡ ጨለማ ክፍል ከእኔ ጋር አብረው የታሰሩ ሰዎች ምንነታቸውን ለመለየት አልቻልኩም፡፡ ከቀናት ብዛት የተረዳሁት ነገር የጋምቤላና የዖጋዴን አካባቢ ተወላጆ የሆኑ እስረኞች መሆናቸውን ተረዳሁ፡፡ ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ውጭም የሚችሉት ተጨማሪ ቋንቋ ባለመኖሩ በጨለማ ውስጥ ሆነን እንኳን ለመረዳዳት አልቻልንም ነበር፡፡ ጨለማ ክፍል ፀድቶ የማያውቅ በመሆኑ የሽንትና የሰገራ ሽታ አለው፡፡ ህመም የሚሰማቸው፣ በድብደባ ብዛት ሽንታቸውን መቆጣጠር የማይችሉ እስረኞች ጨለማ ክፍል ውስጥ እንደሚጽዳዱ በራሴ ላይ ሲደርስ ዘግይቼም ቢሆን ተረዳሁ፡፡
“ጨለማ ክፍል በገባሁ ምሽት ከወትሮው የተለየ ኃይልና ቁጣ የተቀላቀለበት፤ ረፍት የለሽ ድብደባና አሰቃቂ ስቃይ የታከለበት ምርመራ ተጀመረ፡፡ የመጀመሪያዉ ቀን እጆቼን በሰንሰለት አስረዉ የምርመራ ክፍል ውስጥ አስገቡኝ፡፡ አጠገቤ ባለው ወንበር ላይ ጥቁር ቡኒ ስካርፍ ተቀምጧል፡፡ ከትንሽ ቆይታ በኋላ ዘርዓይ የተባለዉ መርማሪዬ (ገራፊዬ) ዓይኔ በስካርፉ እስኪያመኝ ግጥም አድርጎ ሸፍኖ አሰረኝ፡፡ ቀጥሎም እጄን ይዞ የትኛው ክፍል ውስጥ እንደገባሁ እንዳላውቅ በኮሪደሩ አሽከረከረኝ፤ በመጨረሻም አንድ ክፍል ውስጥ አስገብቶ ለቀቀኝ፡፡ ሰው በቀኜ በኩል እንዳለ ተሰማኝ፡፡ ወዴት መሄድ እና ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግን አላወቅሁም፡፡ በስተቀኝ በኩል በትግሪኛ ቋንቋ ሁለት ሠዎች ካወሩ በኋላ ከዚህ በፊት በማላውቀው ድምጽ በአማርኛ ቋንቋ “ቁጭ በል” አለኝ፡፡ አንድ ፈርጣማ ክንድ ትከሻዬን ይዞ ወደ ኋላ ገፋ ሲያድርገኝ ወንበር ላይ ቁጭ አልኩኝ፡፡ ያኔ ከባድ ንዝረት ያለው ኃይል ሰውነቴን ወረረኝ፡፡ ዓይኔን በስካርፍ እንደተሸፈንኩ ወደፊት ተስፈንጥሬ በግንባሬ ተደፋሁ፡፡ መልሰው ሲያስቀምጡኝ፤ ደሜ ተንጠፍጥፎ ያለቀ ያህል እስኪሰማኝ ድረስ የኤሌክትሪክ ንዝረቱ ስቃዬን ጨመረዉ፡፡ ከወንበሩ ላይ ወደ ጎን ስወድቅ ያነሱኛል ብዬ ስጠብቅ ዝምታን መረጡ፡፡ ለካ ወንበሩ ላይ ኤሌትሪክ ንዝረት አስቀምጠውበት ነበር፡፡
“አንደኛው መርማሪ በወደኩበት እግሬን ገልብጦ ያለርህራሄ ገረፈኝ፡፡ ተወራጨሁ፡፡ ሲቃ እያሰማሁ ጨህኩ፡፡ ግርፊያውን አቆመና “ቁም” አለኝ፡፡ ሲቃ እያሰማሁ ጮህኩ፡፡ ግርፊያውን አቆመና አንስቶ እየጮሁ በግራና በቀኝ ጥያቄ ይጠይቁኝ ጀመር፡፡ ለሐጅና ዑመራ ጉዞ ሳውዲ የሄድኩበትን ጉዞ፣ ስለንግድ እንቅስቃሴዬ፣ ኃይማኖታዊ ግዴታ ስለሆነ ነው የዘካ ስጦታዬ፣ … ደግሜ ደጋግሜ የተናገርኩ ቢሆንም፤ የሳውዲ አረቢያ ጉዞዬን “ኃይማኖታዊ መንግሥት ለመመስረት የታቀደ ነበር” እያሉ ያፋጥጡኝ ነበር፡፡
“መልሼ ያው ስሆንባቸዉ፤ በጥቁሩና ወፍራሙ የፖሊስ ፕላስቲክ ዱላ ከወደቅኩበት አጣደፉኝ ፡፡ በተለይም ዘርዓይ የባለዉ “መርማሪ” የአባቱን ገዳይ እንዳገኘ ንዴት በተሞላበት ሁኔታ እየተሳደበ፤ ዱላውን አወረደብኝ፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነውን አላስታውስም ነበር፡፡ ለምን ያህል ሠዓት ራሴን እንደሳትኩ ሳላውቅ ራሴን ጨለማ ክፍል ውስጥ አገኘሁት፡፡ ሱሪዬ በሽንቴ ርሶ ነበር፡፡ በተኛሁበት ሆኜ እንኳ “ቁኑት” እንዳላደርግ ንጹህ አልነበርኩም፡፡ በእስልምና እምነት ለማንኛውም ዓይነት ፀሎት አንድ ሰው ራሱን ሲያዘጋጅ ንጹህ መሆን አለበት፡፡ እኔ ግን አልቻልኩም ነበር፡፡
“ከዚያ አሰቃቂ ምርመራ በኋላ ቁስሌ እንኳን እንዲጠግግ ፋታ ሳይሰጡ በሁለትና ሦስት ቀናት ልዩነት የሌሊት ቶርቸራቸውን አጠናከሩብኝ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሌሎች የኮሚቴው አባላት ጨለማ ክፍል እንዳሉ ብገምትም የትኛዉ ክፍል እንዳሉ አላውቅም ነበር፡፡ ቀንና ሌሊቱን መለየት ባልቻልኩበት በዚህ መሰል አሰቃቂ የምርመራ ቶርቸር ውስጥ ከቆየሁ በኋላ መርማሪዎቹ ለክስ በሚመች መልኩ የሚፈልጉትን ነገር ልናገርላቸው ስላልቻልኩ የመጨረሻውን የጭካኔ ምርመራ (የማዕከላዊ እስረኞች “ስቅለት” ይሉታል) ያለ ርህራሄ ፈፀሙብኝ፡፡
“ውዱ” አድርጌ “ዒሻ” ሰግጄ ከተኛሁ በኋላ እኔ ያለሁበት ጨለማ ክፍል በኃይል ተከፍቶ ስሜ ተጠራ፡፡ ከውጭ በሚታየኝ መብራት እየታገዝኩ ተስቤ መጣሁ፡፡ እንደተለመደው አይኔን በስካርፍ ሸፍነው በኮሪደርሩ እያዘዋወሩ ወደ አንድ የቶርቸር ክፍል ወሰዱኝ፡፡ “ዛሬ የመጨረሻችን ነው” የሚለውን የዘወትር መርማሪዬን ዘርዓይን ድምጽ ስሰማ ንግግሩን የተለመደ ማስፈራሪያ አድርጌ ብወስደውም ቀጥሎ ያጋጠመኝ ግን ዛሬም ድረስ ልረሳው ያልቻልኩት የሥነ-ልቦና ስብራትና ድብደባ ግን የተለየ ነበር፡፡
“የማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ፖሊስ ጣቢያ ዋና ኃላፊ ሆነዉ ኮማንደር ተክላይ “እኛ የማዕከላዊ መርማሪ ፖሊሶች የአገሪቱን የመጨረሻ አሉ የተባልን መርማሪዎች ነን፡፡ የኢትዮጵያ ጓንታናሞ ይሄ ነው፡፡ በአፍህ ካልተናከርክ፤ በቂጥህ ትናገራለህ” ሲለኝ፤ ከኋላዬ በኩል በጆሮዬ አካባቢ ከባድ ጥፊ አረፈብኝ፡፡ ወደ ጎን ተንገዳግጄ ቆምኩ፡፡ ከግራና ቀኝ የሚነሱ እግሮች እንደ ኳስ ተቀባበሉኝ፡፡ ጀርባዬ ላይ ያረፉት ሁለት የእግር ጫማዎች ይበልጥ የህመም ስሜት ፈጠሩብኝ፡፡ የሰውነቴን መዛል አይቶ ኮማንደር ተክላይ “አይኑ ላይ ያለውን ስካርፍ ፍቱት”ሲል ሰማሁ፡፡
“ኮማንደሩ ወደኔ ቀረብ ብሎ፤ ፂሜን እየነጨ “የእኛ እስላም! የእኛ ፆመኛ! ውሸታም እርጉም ስደተኛ!” እያለ ሲሳደብ ቆይቶ “ይሄን እርጉም አንዳይወልድ አኮላሸው” ሲል ወደ ዘርዓይ ተመለከተ፡፡ ዘርዓይም ሱሪዬን እንዳወልቅ አዘዘኝ፡፡ በፍርሃት ዉስጥ ሆኜ እንዳዘዘኝ አደረኩ፡፡ ከኋላዬ የነበረው ፖሊስ የውስጥ ሱሪዬን በኃይል ጎትቶ ዝቅ አደረገው፡፡ ከላይ የለበስኩትን ሸሚዝ በግድ አስወልቀው ራቁቴን አስቀሩኝ፡፡ እጆቼን መልሰው የኋሊት አሰሩኝ አይኔ እያየ ዘወትር በምርመራ ወቅት እኔ ስናገር የምትጽፈው ጽጌ የምትባለው ፖሊስ፤ ክብሪት ይዛ ወደኔ ቀረበች፡፡ ማዕከላዊ ከገባሁ ጀምሮ ምላጭ ባለማግኝቴ ብልቴ አካባቢ ያለው ፀጉር አድጎ ነበር፡፡ ያንን ጽጉር በክብሪት ለበለበችው፡፡ ጩኸቴ ከጣራ በላይ ነበር፡፡ ግን አላዘኑልኝም፡፡ ሁሉም መርማሪዎች በሳቅ እያጀቧት ደጋግማ በክብሪት እንጨት እየለኮሰች የብልቴን ዙሪያ ጸጉር በእሳት ለበለበችው፡፡ ይህ በእኔ ላይ ብቻ የደረሰ ሳይሆን ማዕከላዊ ውስጥ ተመሳሳይ ድርጊት ሌሎች ሙስሊም ወንድሞቼ ላይ ተፈጽሟል፡፡
“ፅኑ ነን! ፅኑ ነን! ለእምነታችን
ይከበር ይከበር መብታችን”
እያልን በመዘመር፤ አካላችን ቢቃጠልም መንፈሳችን እየጎመራ ያሳለፍነዉን የማዕከላዊ እስር ቤት ስቃይ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ አላህ እንባችንን በአደባባይ እንደሚያብስ አምናለሁ!” ሲል ተርኮለታል፡፡ ጉዳዩ ብዙ፣ ለሰሚው ግራ የሆነ በመሆኑ ወደ ሌላው ምስክር እንለፍ!!
“ሽንታም አማራ፤ ብርሃኑ ነጋ ይምጣና ያስጥልህ”
በአሰቃቂው የማዕከላዊ ማጎሪያ ከሚሰቃዩት ዜጎች ውሰጥ ከአማራ ክልል በተለይም ከጎንደርና አካባቢው ታፍነው የሚወስዱ ወጣቶች ይበዛሉ፡፡ በ2008ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ የሰሜን ጎንደር ዞን (ባዕታ) ማረሚያ ቤት ምክንያቱ ዛሬም ድረስ በይፋ ባልተገለፀ የእሳት አደጋ ሙሉ በሙሉ በቃጠሎ ሲወድም፤ በርከት ያሉ እስረኞች አምልጠዋል፡፡ 23 እስረኞች ከወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል፡፡ በእሳት ቃጠሎው የአካል ጉዳት የደረሰባቸው እስረኞች እንደነበሩም ይታወሳል፡፡ በዚህ አሰቃቂ የአደጋ ሰሞን የህወሃት ወታደሮች ጎንደርና አካባቢው ከፍተኛ የእስር ዘመቻ ጀምረው ነበር፡፡ በዚሁ የጅምላ እስር በነፍሰ በሎቹ እጅ ከወደቁት መካከል ስሙን ለጥንቃቄ ስንል የቀየርነው ወጣት የደረሰበትን ግፍና ስቃይ ነግሮናል።
ለጥንቃቄ በሚል ስሙን “አታክልት” ያልነው ወጣት በማያውቀው ጉዳይ የታፈነበትን ቦታና ልዩ ቀበሌ የጠቀሰ ቢሆንም አሁንም ስጋቶችን ከመቀነስና ታሪኩ ላይ የሚፈጥረው እንከን ባለመኖሩ ይፋ ከማድረግ ተቆጥበናል።
አዲስ አበባን በሥም እንጂ በአካል አይቷት የማያውቀው ወጣት አታክልት ወደ አዲስ አበባ ከመምጣቱ በፊት በአንድ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ከድብደባ እና ቶርቸር ብዛት ቀናቱን ለማያስታውሰው ጊዜ ታስሯል፡፡ በመቀጠልም “በአርበኞች ግንቦት ሰባት አባልነትና በሽብር ወንጀል ተጠርጥረሀል” በሚል በከባድ ወታደራዊ አጀብ ወደ አሰቃቂው ማዕከላዊ ሲኦል ተወረወረ፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን የታሪኩን ክፍል ባለታሪኩ አታክልት ቃል በቃል እንደተናገረው እንደሚከተለው ቀርቧል።
“… ድቅድቅ ጨለማ ክፍል ለብቻዬ ተዘግቶብኝ ውዬ አደርኩ፡፡ ምግብ ብለው የሰጡኝ ነገር ፈጽሞ የሚስማማኝ አልነበረም፡፡ በውሃና በዳቦ ነፍሴን ለማቆየት ሞከርኩ፡፡ እስር ቤት በገባሁ በሁለተኛው ቀን ሌሊት ላይ በሩ ተከፍቶ ባትሪ አበሩብኝ፡፡ እየጎተቱ ይዘውኝ ወደ ውጪ ወጡ፡፡ ጨለማ ክፍል ዉስጥ ስላደርኩ ዓይኔ የውጪውን መብራት መቋቋም አልቻለም፡፡ ፊቴን በጨርቅ ሸፍነው እየተጎተቱ ወደ አንድ ክፍል ወሰዱኝ፡፡ በሰው ልጅ ላይ ይፈፀማል ብዬ የማልገምተው ዱላ ወረደብኝ፡፡ ዱላውን መቋቋም ሲያቅተኝ ተዝለፍልፌ ወደቅሁ፡፡ በወደኩበት ይረግጡኝ ጀመር፡፡ በየመሀሉ “ከነ ማን ጋር ነው የምትሰራው? አለቆችህስ እነማን ናቸዉ?” እያሉ ይጠይቁኛል፡፡ “እኔ ከአባቴ ጋር በእርሻ የተሰማራሁ ገበሬ ነኝ” የሚል ቃል ደጋግሜ ብመልስም የሚሰማኝ አጣሁ፡፡
“መርማሪ ፖሊሶች ትንሽ ረፍት ካደረጉ በኋላ ድጋሚ ፊቴን በጨርቅ ሸፍነው እየጎተቱ ወደ ሌላ ክፍል ወሰዱኝ፡፡ ጠባብ መንገድ በመሆኑ ከግድግዳው ጋር ግራ ቀኙን እየተጋጨሁ ተጓዝኩ፡፡ በቀዝቃዛ ውሃ ራሴን ሲዘፍቁኝ ይሰማኛል፡፡ ፊቴንና ራሴ ላይ ቁስለት አጋጥሞኝ ስለነበር ቀዝቃዛ ውሃዉ ህመሜን አባሰው፡፡ ነፈርኩ። የመጀመሪያው ቀን ምርመራዬ እንደዚህ አለፈ፡፡
“ከዚያ በኋላ በነበሩት ቀናት የጊዜ ልዩነቱን ባላስታውስም ሌሊት ሌሊት እየጠሩ የማላውቃቸውን ሰዎች ስም እየጠሩ “አለቃህ ማነው” ይሉኛል፡፡ ብዙ ጊዜ “ብርሃኑ ነጋ፣ ማዕዛው፣ ዘመነ ካሴ” የሚባሉ ስሞችን ደጋግመው እየጠሩ “ከነዚህ አሸባሪዎች ጋር ያለህ ግንኙነት ምንድን ነው” ይሉኛል፡፡ “እባካችሁ እኔ ገበሬ ነኝ የምትሏቸውን ሰዎች አላውቃቸውም” ብላቸውም ዱላው በረታብኝ፡፡ መሬት ላይ ጥለው ቁርጭምጭሚቴን፣ የመርገጫ እግሬን መሀል፣ ባቴን እያፈራረቁ በኤሌትሪክ ገመድ ሲገርፉኝ የወሰደባቸውን ጊዜ አላስታውሰውም፤ …
“አንድ ቀን ረፋድ ላይ ጨለማ ክፍል በጀርባ በኩል ዘወር ያለ ቦታ ላይ አስወጥተው ፀሐይ እንድሞቅ አደረጉኝ፡፡ ከወትሮዉ ለየት ያለ ምግብ ሰጡኝ፡፡ ቆይተው አይኔን ሳይሸፍኑ ወደ ምርመራ ክፍል ቁጥር 27 ወሰዱኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ግራ ቀኜን እያስተዋልኩ ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ የበረሃ ፊት ያላቸው፣ ፀጉራቸው ገባ ገባ ያሉ ሰዎችን ፎቶ ግራፍ እያሳዩኝ “ይህን ታውቀዋለህ ይህኛውንስ” ይሉኝ ጀመር ፡፡ አንዳቸውንም አይቻቸው እንደማላውቅ ብናገርም፤ እየደጋገሙ ይጠይቁኝ ጀመር፡፡ መልሴ “አላውቃቸውም” ሲሆን ጊዜ፤ ለዕለቱ ያሳዩኝ ያልተለመደ ጸባይ ወደ ለመድኩት ቁጣ መቀየር ጀመረ፡፡ ሁለት ሊትሩን የላስቲክ ውሃ አቅርበው እንድጠጣ አዘዙኝ፡፡ የጥማቴን ያህል ጠጣሁ፡፡ “ጨርሰው” አሉኝ፡፡ “ይብቃኝ” ብላቸውም በግድ እየጋቱ አጠጡኝ፡፡ ሁለት ሊትሩ ውሃ ሲያልቅ፤ ሌላ የላስቲክ ውሃ ጨመሩ፡፡ አፌን በግድ ከፍተው ውሃውን እየጋቱ አጠጡኝ፡፡
“ሆዴ በጣም ተነፋ፡፡ በትንታ በአፍንጫዬ ውሃው ይዋጣ ጀመር፡፡ ሁልጊዜ ኃይለኛ ዱላ ሰውነቴ ላይ የሚያሳርፈው በትግሪኛ መሳደብ የሚቀልለው መርማሪ ፖሊስ “ተነስ” ብሎ ጮኸብኝ፡፡ እንደምንም ከወንበሩ ተነሳሁ፡፡ “ልብስህን አውልቅ” አለኝ፡፡ የታቦታት ስም እየጠራሁ ብማፀነውም በእምቢታው ጸና፡፡ ሳልወድ በግዴ ልብሴን አወለቅሁ፡፡ አንደኛው ፖሊስ በጎኔ በኩል ሽንጤን በቦክስ መታኝ፡፡ ፊኛዬ አካባቢ ስለመታኝ በግድ ከተጋትኩት ውሃ ጋር ሽንቴን መቆጣጠር አልቻልኩም ነበር፡፡ ይሄኔ ሁሌ የሚሰድበኝ ፖሊስ “ሽንታም አማራ ብርሃኑ ይምጣና ያድንህ” አለኝ፡፡ ብርሃኑ ነጋ የሚሉትን ሰዉዬ ባላዉቀዉም “ሽንታም አማራ” የሚለዉ ስድብ ሳላስበው አስለቀሰኝ፡፡ ከዚያ በፊት ብዙ ዱላ ሰውነቴ ላይ ሲያርፍ ያልወጣኝ እምባ በስድቡ የተነሳ እምባዬን ማቆም ተሳነኝ፡፡
“በሌላ ቀን ደግሞ እጆቼን የኋሊት አስረው፤ ሱሪዬን በግድ አወለቁት፡፡ ውሃ የሞላ የላስቲክ ጠርሙስ ብልቴ ላይ ላይ በቀጭን ሲባጎ ገመድ አስሩብኝ፡፡ ስቃዬን መቻል አቅቶኝ ስለ ወንድ ልጅ አምላክ ብዬ ብማፀንም ሴቷ ፖሊስ ሳትቀር ጨክና ሳቀችብኝ፡፡
“እንዲህ ባለ መልኩ ለወራት ያህል መልሰው መላልሰው ቢያሰቃዩኝና ቢመረምሩኝም የሚፈልጉትን ነገር አጡብኝ፡፡ በኋላም ሰዎች ወዳሉበት ክፍል አስገቡኝ፡፡ ይህ ሁሉ በደል ሲደርስብኝ ቤተሰቦቼ የት እንዳለሁ አያውቁም ነበር፡፡ በድብደባው ብዛት የቀኝ እጄ አውራ ጣት የተሰበረች በመሆኑ መመገብ ተሳነኝ፡፡ ያም ሆኖ ከጨለማ ክፍል ወጥቼ ከሰዎች ጋር በመቀላቀሌ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ የከተማ ሰዉ ጥሩ ነዉ፡፡ ስቃዬን እንድችለዉ አበረታቱኝ፡፡ ቅያሬ ልብስም ሰጡኝ፡፡ ሰዉነቴን በቫዝሊን እያሹ አስታመሙኝ፡፡ ምንነታቸዉን የማላዉቃቸዉ ሰዎች ሥም እየተጠራ “ግንኙነት አለህ” በሚል ተገረፍኩ፡፡ መልሶ ደግሞ የማላዉቃቸዉ ሰዎች እስር ቤቱ ዉስጥ ልብሳቸዉን አልብሰዉ፤ አስታመሙኝ”፡፡
… እያለ አሰቃቂዉን የማዕከላዊ እስር ቤት ቆይታዉን ከመሪር ሐዘን ጋር የሚተርከዉ ወጣት አትክልት፣ ከ2008 መጀመሪያ ታስሮ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ በኋላ፤ በጅምላ ከታሰሩ የአዲስ አበባና የኦሮሞ ወጣቶች ጋር አዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ዉስጥ “የተሃድሶ ሥልጠና” ወስዶ፤ “አይደገምም” የሚል ቲሸርት ለብሶ ተፈትቷል፡፡ በነፍሰ በላዎቹ ቋንቋ “ተመርቋል”፡፡
የዚህ አሰቃቂ እስር ሰለባ የሆነዉ ወጣት ከ“ተሃድሶ” በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ አዋሽ አርባ ላይ የተዋወቃቸዉ የአዲስ አበባ ልጆች ገንዘብ አዋጥተዉ ወደ ትዉልድ ቦታዉ ሸኝተውታል። አሁን ያ በዱላ የዛለውና የተሰበረው እጁ እርፍ ይዞ እንደወትሮው ህይወቱን ይገፋ ይሆን? ማከሚያ የሌለው ኅሊናውስ?
ወዮ ለማዕከላዊ ገራፊ አስገራፊዎች!
በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሰው ልጅ ላይ ይፈጸማል ተብሎ የማይገመት ኢ-ሰብዓዊና ኢ-ሞራላዊ ቅጣቶች በማዕከላዊ “ወንጀል ምርመራ” ፖሊስ ጣቢያ ይፈፀማል፡፡ በተለይም ህወሓት በከሳሽነት በሚቀርብባቸው ፖለቲካ ነክ እስረኞች ላይ ከማይሸር የሥነ-ልቦና ቅጣት እስከ አካል ማጉደል የሚያደርሱ የስቃይ (ቶርቸር) ዘዴዎች ይፈፀማሉ፡፡
የአንድ ዘውግ ውጤቶች የሆኑት “መርማሪ” ተብለው የሚቀርቡ ፖሊሶች ፖለቲካ ነክ የሆኑ ጉዳዩችን በቡድን በቡድን እየሆኑ በስቃይ የታጀበ “ምርመራ” እስረኛው ላይ ያካሄዳሉ፡፡ አብዛኛው “ምርመራ” በውድቅት ሌሊት የሚካሄድ በመሆኑ “መርማሪ” ፖሊሶች የአልኮል መጠጥ ጠጥተው ወደ “ምርመራ” ይገባሉ፡፡ በዚህም ትዕግስት ማጣት፣ ቁጣ፣ ዘውጋዊና ኃይማኖታዊ ማንነት ላይ ያተኮሩ ጸያፍ ስድቦችና ረፍት የለሽ ድብደባ የ“ምርመራው” አካል ይሆናሉ፡፡
አንድ ታሳሪ በቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ክስ እስኪመሰረትበት ድረስ በህይወቱ ምዕራፍ ውስጥ ገጥመውት የማያውቁ አዳዲስ ክስተቶችን ማስተናገድ ግድ ይሆንበታል፡፡ “መርማሪ” ፖሊሶች አንድን እስረኛ ከመመርመራቸዉ በፊት የሚወስዱት እርምጃ እስረኛዉን ሥነ-ልቦና መስለብ ቀዳሚ ተግባራቸዉ ነዉ፡፡ የእስረኛውን ሥነ-ልቦና ለመግደል ኢ-ሰብአዊና ኢ-ሞራላዊ የሆኑ ጉዳዮችን በእስረኛው ላይ ይፈጽሙበታል፡፡
ማዕከላዊ ዉስጥ፤
የ“መርማሪዎች” (ገራፊዎች!) ዋና ኃላፊ ሆነዉ ኮማንደር ተክላይ (ቶርቸር ክፍል 35)፣
የጣቢያዉ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር ጸጋዬ (ቶርቸር ክፍል 27)፣
ኢንስፔክተር ዘርዓይ (ቶርቸር ክፍል 29)፣
ዋና ሳጅን ኃ/ሚካኤል (ቶርቸር ክፍል 31)፤
እያንዳንዳቸዉ ከሚመሯቸዉ የ“ምርመራ” (የገራፊ) ቡድን አባላት ጋር በመሆን ቃላት የማይጹዋቸዉ የቶርቸር ዘዴዎችን በፖለቲካ አስረኞች ላይ ይፈጽማሉ፡፡ (በርግጥ በወሳኝ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እነዚህ ከፍተኛ የማዕከላዊ ቶርቸር “ኤክስፐርቶች” በጋራ ይሰራሉ)፡፡ ንጹሐን ዜጎች ምንም በማያዉቁት ወንጀል ተጠልፈዉ በሚታሰሩበትና በሚሰቃዩበት ማዕከላዊ እስር ቤት የዜጎች ሰሚ አልባ ዋይታ ለጊዜዉ ታፍኖ ቀርቷል፡፡ ወንድ ልጅ በተመሳሳይ ፆታ ማስደፈር፣ ብልት አካባቢ የበቀለን ጸጉር በክብሪት መለብለብ (ማቃጠል)፣ በኤሌክትሪክ ንዝረት ማሰቃየት፣ ወፌ ላላ ገልብጦ መግረፍ፣ ጥፍር እየነቀሉ ማሰቃየት፣ በቀዝቃዛ ዉሃ መንከር፣ የወንዶች ብልት ላይ በዉሃ የተሞላ ጠርሙስ አስሮ ማንጠልጠል፣… መሰል አሰቃቂ ስቃዮች የማዕከላዊ ገራፊዎች “የምርመራ ዘዴዎች” ናቸዉ፡፡
በትግራይ ተወላጆች የበላይነት በሚመራዉ አሰቃቂ እስር ቤት ዉስጥ በሐሰት ዉንጀላ ተፈርዶባቸዉ በቀል አርግዘዉ ወደ ቃሊቲ የሚወርዱም ሆነ በነፃ የሚለቀቁ ዜጎች የማይሽር የሥነ-ልቦና ጠባሳ ይዘዉ የሚወጡ በመሆኑ የበቀል አጸፋቸዉ ከፋ ይሆናል፡፡ ጊዜና ሁኔታዎች ሲፈቅዱ አሁን እታየ ካለዉ የበቀል ድርጊት በከፋ ሁኔታ ግፉዓን ዜጎች ማዕከላዊ ገራፊና የበላይ አለቆቻቸዉን ምህረት የለሽ በሆነ የቅጣት በትር መቀጥቀጣቸዉ አይቀሬ ነዉ፡፡ ያን ጊዜ ወዮ ለማዕከላዊ ገራፊ አስገራፊዎች!!
ከዝግጅት ክፍሉ፤ የስቃይ ሰለባዎች እንደጠየቁት “ማዕከላዊ” የሚባለውን የስቃይ ዋሻ በትክክል ይገልጸዋል የምትሉት ሥም ካለ የጋራ መግባቢያ ይሆነናልና ላኩልን፤ ሃሳብ መስጫው ላይ አስተያየታችሁን አስፍሩ፡፡ “ማዕከላዊ” እስርቤት አይደለም፤ “የምርመራ ቦታ” ተብሎ በፍጹም ሊጠራ የማይገባው ነው፡፡ “ማዕከላዊ” ከዚህ ያለፈ ገላጭ መጠሪያ ያስፈልገዋል፡፡ ሊፈርስ ይገባዋል ብለን እናምናለን፤ ህንጻው ሳይሆን “ማዕከላዊ” ውስጥ ያለው አስተሳሰብ እንጂ!
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Tesfa says
ባዶ ስድት በወያኔ አለዋ ሳውራ በሻቢያ የበረሃ የማሰቃያና የስለላ ክፍሎች ነበሩ። የበረሃው ኑሮ አክትሞ ከተሜ ከሆኑ በህዋላም የሚገለገሉባቸው የስለላ፤ የአፈና፤ የስቃይና የግድያ ስልቶችም ያው የበረሃውን ተኩላዊ ሥራ የተላበሱ ስለሆነ ከፉት እንጂ ለውጥ አልታየባቸውም። የወያኔው ሰላይ ክንፈ ገ/መድህን እውቁ የሰው ልጆች መብት ታጋይ መስፍን ወልደማሪያም ላቀረቡለት ፓለቲካዊ እይታና የመብት ጥሰት ሲመልስ ” የሚሉት ይገባኛል። ግን እንደዛ ያለ ሃሳብ ባቀርብ ያርድኛል” ነበር ያለው። እንዳለውም አልቀረለትም ወደ አፈር መለሱት። የወያኔ የበረሃ ታጋይ ሃያሎም በኤርትራ ጉዳይ ላይ በነበረው አቋም የተነሳ ወደ እማይመለስበት እንደላኩት ጠንቅቀን እናውቃለን። ሌሎች የወያኔ ወታደራዊና የሲቢል ሰራተኞች በዚህ አጥፊ ድርጅት ተመንጥረዋል። በገሃድ ይህ ነበር ያ ነበር የሚሉን ነገር ሁሉ ከእውነት የራቀ የወያኔ የውሽት ፕሮፓጋንዳ ነው። አብረዋቸው በበረሃ ለተንከራተቱ የትግል አጋሮቻቸው ይህን ያህል ጨካኞች ከሆኑ፤ ነፍጠኛ፡ ኦሮሞ ወዘት እያሉ ለሚያጥላሉት ወገናችን የሚኖራቸውን የጠለቀ ጥላቻ ኢ-ሰብአዊ በሆነ ድርጊታቸው ይፋ ቢሆን አስገራሚ አይሆንም። ሃገራችንና ህዝባችን የአውሬዎች ማላገጫ ከሆነ ዘመን ቆጥረናል። በቅርቡ ጠ/ሚሩ “ምንም የፓለቲካ እስረኛ የለንም” በማለት ሲናገሩ ለሰማ ልብ ያደማል። ለመኖር መዋሸት፤ መግረፍ፤ መዝረፍ፤ ማሰርና መግደል የወያኔና የተቀጥያ ድርጅቶች ሙሉ ሥራ ነው።
በማእከላዊ እሥር ቤቶች የሚደረገው የግፍ ምርመራ የሰው ልጅ በሰው ልጅ ላይ ያደርሰዋል ተብሎ የማይጠበቅ አረመኒያዊ ተግባር ለመሆኑ ከሞት ተርፈው ያለውን ሃበሳ ከተረኩልን ተረድተናል። ሰው በሰው ላይ አይጸዳዳም። ሰው እጅና እግሩ በታሰረ ሰው ላይ ወንድ ወንድን ሴት ሴትን እንድትደፍር በማድረግ ፊልም በማንሳት የፓለቲካ መጠቀሚያ አያደርግም። ወያኔ ግን ይህን ያደርጋል። አንድ የማእከላዊ መርማሪ ለአንድ እሥረኛ ያለውን ልጥቀስ ” ሁለተኛ ልጅ መውለድ እንዳትችል እናረግሃለን። አንተ ሽንታም…. አ… እኛ ማን መሆናችንን አታውቅም? የወለድካቸውንም ልጆች አንድ በአንድ እንመነጥራቸዋለን። ዘርህን ነው የምናመክነው”። ሲቃ የተናነቀው እስረኛም አረመኔ መሆናቹሁን ገና ከተማ ሳትገቡ አውቃለሁ። የፈለጋችሁትን አድርጉ። ጊዜው የእናንተ ነውና በማለት እንደመለሰ በምርመራው ቃል ተቀባይ የነበረና አሁን በህይወት የሌለ ሰው አጫውቶኛል። ማእከላዊ እስርቤት የወያኔ ይፋ እስር ቤት ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ወደ 40 የሚጠጉ ድብቅ የምርመራና የጊዜአዊ ማቆያ ቦታዎች አሉ። በትግራይና በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች ድብቅ የምድር ውስጥ እስርቤቶች ሞልተዋል። ይህ እውን እንጂ ዝም ብሎ የሚወራ ወሬ አይደለም። ወያኔ ለገደላቸው ወታደራዊ ማእረግ መስጠት፤ በስማቸው ስፍራን መሰየም ከሚያዘናጋባቸው አንድ ተግባሩ ነው። በሃገር ውስጥ ያሉትን ገራፊዎችና ህዝባችንን የሚያመሳቅሉትን ስም፤ አድራሻ፤ ቢቻል ፎቶግራፍ በማስደገፍ ህዝቡ እንዲያውቃቸው ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል። ከዛም አልፎ ከሃገር ውጭ የምንኖር በውስጣችን ሆነው ነገር ለወያኔ የሚያቀብሉ፤ በሃገር ህዝባችንን የሚያመሱትን ለይቶ ድርጊታቸውን የሚዘግብ የመረጃ ማእከል ሊኖር ይገባል። በሃገር ሰውን አባልተውና በልተው በውጭም ሆነ በውስጥ ተንደላቀው እንዳይኖሩ ለማረግ በህዝባችን ላይ የሚፈጽሙት ግፍ ለህዝባችን ይፋ መሆን አለበት።