አንደ ሻማ ነው ማንባት፣
ቀልጦ ጠብ እንደሚለው፤
የነፍሳችንን ስቃይ፣
ይሉኝታ ሳይጋርደው፤
ማስመሰል ሳያርቀው፡፡
እንደ ሻማ ነው መቅለጥ፣
በነበልባል ነዶ በግኖ፤
ሰብእናን በህይወት ጣር፣
ሰርቶ በማደር ፈትኖ፡፡
እንደ ሻማ ነው መብራት፣
ማለቅም እንደ ሻማ፤
ለሌላም ባይሆን ለነፍስ፣
አብርቶ የእውነትን ፋና፡፡
በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) ፣ /ፍካት ናፋቂዎች፤1999ዓ.ም/
ባለፈው ሁለት ግጥሞችን አቅርበን ነበር፡፡ “ቅኔ” እና “የማይጠፋ ፍቅር” በሚል ርዕሶች ለቀረቡት ግጥሞች ጨዋታውን በማድመቅ የተቀኛችሁትን እና ማብራሪያም የሰጣችሁትን ተሳታፊዎቻችንን በለው፤ YeKanadaw Kebede፤ አሥረዳው፤ እስከመቼ እና ዱባለ ልባዊ ምስጋናችን ይድረሳችሁ፡፡
ለዛሬው ደግሞ በግጥም ልተንፍሥ ከተባለ የፌስቡክ ገጽ ይህንን ግጥም አግኝተን ለጨዋታ አቅርበነዋል፡፡ “እንደ ሻማ”ን እነሆ! ተቀኙበት፤ ቅኔ ዝረፉበት፤ …
በለው ! says
*************************
አይ አንቺ ‘ሻማ’ እራስሽን መስዕዋት ያደረገሽ
መብራት በጠፋ ቀን ሁሉ የሚያበሩሽ
እነሱ ሲደሰቱ አንቺን እየለኮሱሽ
ሀዘንም ሲገጥማቸው አንችው ተቃጥለሽ
ከቶ ማነው አንቺ ቀልጠሽ! አንብተሽ!
ለሌላውን ብርሃን ሁኚ ብሎ የፈረደብሽ ?
***ሻማ !
ምን ነበር ታዲያ ከአንቺ የሰው ልጅ ቢማር
ውጭ ሄዶ ከሚቀልጥ ከሚያነባ ከሚማረር
እንዳይሆን የጋን መብራት እንዳይጠፋ ሳያስተምር
እንደሻማ ተለኩሶ በርቶ እየታየ ለህዝብ ቢናገር
ስንት የጨለመባቸው ፍንትው ብሎ በታያቸው ነበር !!።
*****************
ከምስጋና ጋር፣ ከሀገረ ካናዳ በለው!
ቱሉ ፎርሳ (ከነምሳ) says
“እንደ ሴቴ ሸረሪት ጽንስ
ራሴን በራሴ መዋጤ”
የገዛ ብርሃኔን አስኳል
እኔው በእኔው መሰልቀጤ፡
ፍቅር ቢፈልቅ ብዬ እኮ ነው
ከአለት ልብህ አንዳች ጥጋት
ጀንበር ቢቀድ ብዬ እኮ ነው
በልቦናህ የጎህ ንጋት፡
አንተም ታዲያ ሲደርስ ቀኑ
ሻማ እንድትሆን ለጭቁኑ
ለድምፅ አልባው ለምስኪኑ!
ጧፍ እንድትሆን ልክ እንደኔ
አፍ እንድትሆን ለወገኔ፡፡
( ለእስክንድር ነጋ)
ዱባለ says
እንደ ሻማ ቀልጦ ብርሀን መስጠት
ራስን ሰውቶ መሆን ትሩፋት
ጀግና መሆን በጎ ለሁሉም በረከት
የሰው ልጅ ምሳሌ መሆን በትጋት
ለግለሰብ ኣቅም ይሰጣል ብርታት
ለብዙሀኑ ግን ስንፍና ያወርሳል
የግል ሀላፊነት እኋላ ይቀራል
የራሱን እጅ ኣጥፎ የሌላውን ያያል
ለዚህ የሚበጀን ችቦ መሆንን ነው
እንጨትን ሰብስቦ በልጥ ማያያዝ ነው
ሁሉም የየራሱን መሀል መቆለል ነው
የራስን ለኩሶ ሌላ ማቀጣጠል
ብርሀን ያበዛል
ደስታውም ይደምቃል
ዘላቂም ይሆናል
ችግር ይቀረፋል
ሸክምም ይቀላል::